በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?

የክርስትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?

የክርስትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?

መላው ዓለም ወደ ክርስትና ይለወጥ ይሆን? ወይስ ክርስትና ይጠፋ ይሆን? ክርስትና በጨለማ በተዋጠው ዓለም ውስጥ እንደ ደማቅ መብራት ማብራቱን ቀጥሏል ወይስ ብርሃኑ ደብዝዟል? እነዚህ ጥያቄዎች አሁንም ቢሆን ያሳስቡናል።

ኢየሱስ አንድ ቀላል ምሳሌ በመጠቀም እርሱ የክርስትናን ዘር ከዘራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጠላት የሆነው ሰይጣን ተጻራሪ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 13:24, 25) ስለዚህ ኢየሱስ አገልግሎቱን አጠናቆ ከሄደ በኋላ በነበሩት ጥቂት መቶ ዘመናት ውስጥ ክርስትና መለወጡ እንዲሁ ማኅበራዊ ክስተት ብቻ አልነበረም ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ ጠላት የሆነው የዲያብሎስ ሥራ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እንደቀድሞው ዘመን ተመሳሳይ ስህተት መሥራታቸውን ስለቀጠሉ የእጃቸውን እያገኙ ነው። —2 ቆሮንቶስ 11:14, 15፤ ያዕቆብ 4:4

በክርስትና ላይ የተሰነዘረ መሰሪ ጥቃት

ኢየሱስ እርሱ ያስተማረው ትምህርት እንደሚበረዝ ትንቢት ተናግሯል። እንዲህ ብሎ ነበር:- “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ።” የሚገርመው ነገር አገልጋዮቹ የተደረገውን ነገር ለባለቤቱ ነግረው እንክርዳዱን ለመንቀል ፈቃድ ሲጠይቁ ሰውየው “አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ። በዚያን ጊዜ አጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ” አላቸው።—ማቴዎስ 13:24-30

ኢየሱስ ራሱ እንደገለጸው በምሳሌው ውስጥ በማሳው ላይ ስንዴ እንደዘራ የተገለጸው ሰው ኢየሱስን የሚያመለክት ሲሆን የዘራቸው ዘሮች ደግሞ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ይወክላሉ። በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ በሄደው ጠላት የተመሰለው “ዲያብሎስ” ነው። እንክርዳዶቹ የሚያመለክቱት በውሸት የአምላክ አገልጋዮች ነን የሚሉ ዓመጸኛና ከሃዲ ሰዎችን ነው። (ማቴዎስ 13:36-42) ሐዋርያው ጳውሎስም ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስመልክቶ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ሰጥቷል። “እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ። ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ” ብሎ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30

ክርስትና ተበረዘ

ኢየሱስ በምሳሌ የገለጸውና ጳውሎስ የተነበየው ነገር ፍጻሜውን አግኝቷል? አዎን፣ በትክክል ተፈጽሟል። ትልቅ የመሆን ምኞት የተጠናወታቸው ሰዎች ኢየሱስ ያቋቋመውን ጉባኤ በመቆጣጠር የራሳቸውን ዓላማ ለማስፈጸም ተጠቅመውበታል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “የዓለም አይደላችሁም” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:19) ይሁን እንጂ የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ ሰዎች ከገዢዎች ጋር ኅብረት በመፍጠር የመንግሥት ሃይማኖት መሠረቱ፤ ይህም ከፍተኛ ሥልጣንና ሀብትን በእጃቸው እንዲያስገቡ አስችሏቸዋል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት “ጠማማ ነገር” አስተምረዋል። ለምሳሌ ያህል ሰዎች መንግሥትን እንዲያመልኩና በጦርነት ወቅትም ሕይወታቸውን እንዲሠዉለት እስከ ማስተማር ደርሰዋል። በመሆኑም እነዚህ ስመ ክርስቲያኖች በመስቀል ጦርነቶች በመካፈል አረመኔ እንደሆኑ የቆጠሯቸውን ሰዎች ጨፍጭፈዋል። በተጨማሪም ወደ ጦርነት በመሄድ የእምነት አጋሮቻቸው የሆኑትን የራሳቸውን “ወንድሞች” ገድለዋል። ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትና ጎረቤትን መውደድ በእነርሱ ሕይወት ውስጥ ቦታ እንደሌላቸው የተረጋገጠ ነው።—ማቴዎስ 22:37-39፤ ዮሐንስ 15:19፤ 2 ቆሮንቶስ 10:3-5፤ 1 ዮሐንስ 4:8, 11

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ራሳቸውን ክርስቲያን እያሉ ሲጠሩ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት የሚወክሉት አስመሳዩን ክርስትና ነው። ባለፈው ርዕሰ ትምህርት ላይ ለማየት እንደሞከርነው አብያተ ክርስቲያናት በየጊዜው የሚከፋፈሉት፣ በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ የሚገቡትና ለአምላክ ሕግ ደንታ ቢስ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው። እንዲህ ዓይነቱን መጥፎ ፍሬ ያፈራው እውነተኛው ክርስትና ሳይሆን ዲያብሎስ የዘራው አስመሳዩ ክርስትና ነው። ታዲያ ይህ የሐሰት ሃይማኖት መጨረሻው ምን ይሆን? ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እንደገለጸው የሐሰት ሃይማኖት የሕዝብ ድጋፍ በማጣት ብቻ አይጠፋም። የሚጠፋው የጥፋት ፍርድ ተበይኖበት ነው።

እውነተኛ ክርስቲያኖች በጨለማ ውስጥ ያበራሉ

ይሁን እንጂ በእንክርዳድ የተመሰለው የሐሰት ክርስትና ተሰብስቦ ከመጥፋቱ በፊት መፈጸም ያለበት አንድ ነገር እንዳለ የኢየሱስ ምሳሌ ይጠቁማል። በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሐሰት ክርስትና “እንክርዳድ” በሰፊው ተዛምቶ ስለነበር “ስንዴ” መሰሉን እውነተኛ ክርስትና ውጦት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስንዴው ከእንክርዳዱ የሚለየው ‘የዓለም መጨረሻን’ በሚያመለክተው ‘በመከር’ ወቅት መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም “በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:39-43) ከ90 ዓመታት በፊት ከተካሄደው አንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ዘመን ውስጥ እንደምንኖር ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። (ማቴዎስ 24:3, 7-12) ኢየሱስ በትንቢታዊው ምሳሌ ላይ የገለጸው “ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ” የሚለው አባባልስ ፍጻሜውን አግኝቷል?

እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕዝበ ክርስትና ከምታፈራቸው ‘እንክርዳዶች’ ሲለዩ ቆይተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንዲያውቁት በመርዳት ‘እንደ ፀሐይ እያበሩ’ ነው። ምሥክሮቹ የአምላክን የአቋም ደረጃዎች አቅልለው አይመለከቱም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ምሥክሮች የሚሆኑ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመታዘዝ ሲሉ አብዛኛውን ጊዜ በአኗኗራቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባዎቻቸው ላይ ነፃ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣሉ እንጂ ሕዝቡን በመዝናኛ አይሸነግሉም። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ወቅት የሚማሯቸውን ባሕርያት ማለትም የሞቀ ፍቅርንና ወዳጅነትን ለሌሎች ያሳያሉ። አምላክ በመጀመሪያው ዓላማው መሠረት ምድርን ወደ ገነትነት ለውጦ የምድር ትሑታን እንዲኖሩባት እንደሚያደርግ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ከዚያ በፊት ዓለም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታላቂቱ ባቢሎን በመባል የሚጠራው የሐሰት ሃይማኖት ካሳደረበት ጎጂ ተጽዕኖ መጽዳት አለበት። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት ይሖዋ ይህን ሥር ነቀል ለውጥ በቅርቡ ያመጣል።—ማቴዎስ 5:5፤ ራእይ 18:9, 10, 21

ታዛዥ የሆነው የሰው ዘር ከሐሰት ሃይማኖት የማጭበርበሪያ ድርጊቶች ነጻ ከሆነ በኋላ የእውነተኛው ክርስትና አምልኮ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ በአንድነት ያስተሳስራቸዋል። ይህ ኢየሱስ ለዘራው እውነተኛ ክርስትና እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ብጥብጥ የሚያስከትሉ ከፋፋይ ሃይማኖቶች በማይኖሩባት ሰላማዊት ምድር ላይ ገነት ተመልሳ ትቋቋማለች!

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ።”—ማቴዎስ 13:25

[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ነጻ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሚሰጥበት በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ እንድትገኝ ልባዊ ግብዣ እናቀርብልሃለን

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ።”—ማቴዎስ 13:30