በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያልተጠበቀ ገጠመኝ

ያልተጠበቀ ገጠመኝ

ያልተጠበቀ ገጠመኝ

እኔና ጓደኞቼ ከሃዋይ ደሴቶች አንዷ የሆነችውን ማዊን ለመጎብኘት ጓጉተን ነበር። በተለይ የጓጓነው 3,055 ሜትር ከፍታ ባለው የሃሌአካላ ተራራ አናት ላይ ሆነን ፀሐይ ስትወጣ ለመመልከት ነው። ይህን ክስተት መመልከት በጣም አስደሳች አጋጣሚ እንደሆነ ተነግሮን ነበር። አስቸጋሪ የሆነብን ካረፍንበት ከካፓሉዋ ጉዟችንን ለመጀመር ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት መነሳታችን ብቻ ነበር። ከዚያም ቀጥ ያለውን አቀበት በመኪና ተያያዝነው። በዚያ ውድቅት ሌሊት ወደዚያ የምንጓዘው እኛ ብቻ እንደሆንን ተሰምቶን የነበረ ቢሆንም ሁኔታው ግን እንደዚያ አልነበረም! ተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ አቀበታማና ጠመዝማዛ በሆነው መንገድ ላይ በዝግታ የሚጓዙ ሌሎች በርካታ መኪናዎች ነበሩ። ተራራው አናት ላይ ስንደርስ አካባቢው በጣም ይቀዘቅዛል። ሆኖም የምንደርበው ብርድ ልብስ ይዘን መጥተን ነበር።

አሥራ ሁለት ሰዓት ገደማ ላይ ወደ መቶ የምንጠጋ ሰዎች የፀሐይዋን መውጣት በትዕግሥት መጠባበቅ ጀመርን። ሰው ሁሉ ይህንን ማራኪ ትዕይንት ፎቶ ለማንሳት በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ ካሜራውን አዘገጃጅቶ ይጠባበቃል። ይሁንና በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ! ጥቅጥቅ ያለ ጉም ወርዶ ይህን ታሪካዊ ትዕይንት ፎቶ ግራፍ እንዳናነሳ ሲጋርደን በጣም አዘንን! ይሁን እንጂ በፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኙ ተራራዎች በጉም መሸፈናቸው የሚጠበቅ ነገር ነው። ስለዚህ የተሰማንን ሐዘን ዋጥ አድርገን የፀሐይዋ ሙቀት ጉሙን እስኪገልጠው ድረስ ጠበቅን። ትንሽ ቆይቶ በተራራው ላይ ያሉት የእግር መንገዶች በግልጽ ይታዩን ጀመር፤ ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ነበር! ስለዚህ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ አይደለም ማለት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ድንገት “ቸካር፣ ቸካር” የሚል ለየት ያለ የማስካካት ድምጽ ሰማን። ከዚያም የምን ድምጽ እንደሆነ መለየት ቻልን። ድምጹ የቆቅ ዝርያ የሆነችውና በአውሮፓም ሆነ በእስያ የምትገኘው ቸካር የተባለች ማራኪ ወፍ ድምጽ ነው። ይህች ወፍ በላቲን አሌክቶሪስ ቸካር የምትባል ሲሆን አብዛኛውን የመራቢያ ወቅቷን መሬት ላይ በምትሠራው ጎጆ ውስጥ ታሳልፋለች። ቸካር ከመብረር ይልቅ መሮጥ ይቀናታል።

እንዲህ ያለችው ወፍ ማዊ ተብላ በምትጠራው በዚህች ውብ ደሴት ላይ እንዴት ልትገኝ ቻለች? ቸካር ከሌላ ቦታ የመጣች ወፍ ሳትሆን አትቀርም። በሰሜን አሜሪካ ውስጥ እነዚህ ወፎች ሰዎች አድነው እንዲይዟቸው ወደ ጫካ ይለቀቃሉ። ቢያንስ ቢያንስ ይህችን ፈሪ ወፍ በቅርበት በማየታችን በጣም ተደስተናል።—ተጽፎ የተላከልን።