“በተፈጥሮ ላይ የሚንጸባረቀው ጥበብ”
“በተፈጥሮ ላይ የሚንጸባረቀው ጥበብ”
ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በ2005፣ በጃፓን አቼ ግዛት ውስጥ ይህን ጭብጥ ያስተጋባ አንድ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር። በኤግዚቢሽኑ ላይ 121 አገሮች የተካፈሉ ሲሆን በዚያ የተገኙ ጎብኚዎች ከተፈጥሮ እንዲማሩ ብሎም “የአካባቢን ሥነ ምሕዳር ሳያዛቡ በኢኮኖሚ ማደግ የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመፈለግ ብርቱ ጥረት እንዲያደርጉ” ተበረታተዋል። በማዕከላዊ ጃፓን በናጎያ ከተማ የቀረበው ይህ ኤግዚቢሽን ደኖችን፣ ኩሬዎችንና አበቦችን ለሕዝብ አሳይቷል። የጎብኚዎችን ትኩረት በእጅጉ የሳበው 2.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ከፍ ብሎ የተሠራው ግሎባል ሉፕ የሚባለው የእግረኞች መንገድ ነበር። ይህ 21 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ አካባቢውን ቁልቁል ለማየት አልፎ ተርፎም የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ውበት ለመጠበቅ ያስችላል።
ጉብኝቱ የፈጠረው ስሜት
ከላይ ሲታይ ግዙፍ እጭ የሚመስለው የጃፓኑ የኤግዚቢሽን አዳራሽ የፀሐይን ቃጠሎ ለመከላከል ተብሎ በቁመታቸው የተሰነጣጠቁ 23,000 ረዣዥም ቀርከሃዎችን በማጠላለፍ የተገነባ ነው። የቀርከሃው አማካይ ርዝመት 7 ሜትር ሲሆን ሕንጻው 19 ሜትር ከፍታ፣ 90 ሜትር ወርድና 70 ሜትር ጥልቀት ያለው መሆኑ በዓለም ላይ በቀርከሃ ከተሠሩት ነገሮች ሁሉ ትልቁ እንዲሆን አድርጎታል። አዳራሹ ባለ 360 ዲግሪ ክብ የፊልም ማሳያ ክፍል አለው። ጎብኚዎች 12.8 ሜትር ዲያሜትር ባለውና ዙሪያውን በተንቀሳቃሽ ምስሎች በተሞላው ክብ ክፍል ውስጥ ሲገቡ ከምድርና በውስጧ ካሉ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሕይወት ያላቸው ነገሮች ጋር አብረው እንዳሉ ሆኖ ይሰማቸዋል።
የማሌዥያው ኤግዚቢሽን አዳራሽ በምስል ማሳያዎች አማካኝነት የአገሪቱን ዝናባማ ደኖችና ኮራል ሪፍን አሳይቷል። የታይላንዱ ኤግዚቢሽን አዳራሽ ደግሞ በታኅሣሥ 26, 2004 በሱናሚ ምክንያት የደረሰውን አሳዛኝ እልቂት ያሳየ ሲሆን ይህም ጎብኚዎቹን “ሰው ተፈጥሮን መቆጣጠር እንደማይችል” አስታውሷቸዋል። የደቡብ አፍሪካው አዳራሽ በእንስሳት ዝርያዎች ላይ ያጠላውን የመጥፋት አደጋ ለማመልከት በ19ኛው መቶ ዘመን በአደን እስከጠፋበት ጊዜ ድረስ በደቡባዊ አፍሪካ ሜዳዎች ሲፈነጭ የነበረውን ክዋጋ የሚባል የሜዳ አህያ የሚመስል አጥቢ እንስሳ ምስል ለዕይታ አቅርቧል።
የኤግዚቢሽኑ ጭብጥ ካለበት አዳራሽ ቀጥሎ ባለው ባለ ማቀዝቀዣ ማሳያ ውስጥ በ2002 ከሩሲያ፣ የሳይቤሪያ ፐርማፍሮስት ምድር ውስጥ ተቆፍረው የወጡ የዝሆን ዝርያ የሆነ ግዙፍ እንስሳ ቅሪተ አካላት ይታያሉ። በተገኘባት አካባቢ ስም ዩካጊር ማሞዝ ተብሎ የተሰየመው ይህ የጠፋ የዝሆን ዝርያ ሁለት ትላልቅ ቆልማማ ጥርሶች የነበሩት ሲሆን ዓይኖቹ በትንሹ ከፈት ብለው ይታያሉ። ራሱ አሁንም በቆዳና በፀጉር እንደተሸፈነ ነው። የዚህ አስገራሚ ፍጡር ቅሪተ አካል ብዙ ፍጥረታት በሚያሳዝን ሁኔታ ከምድረ ገጽ መጥፋታቸውን የሚጠቁም ሌላው ማስረጃ ነው።
ወደፊት የተሻለ ጊዜ ይመጣ ይሆን?
ታዲያ ሰዎች እንደ ብክለትና የምድር ሙቀት መጨመር ያሉትን በፕላኔታችን ላይ አደጋ እንዲጋረጥ ያደረጉ ነገሮችን
ማሸነፍ የሚችሉት እንዴት ነው? “የ2005 ኤግዚቢሽን አርማ” እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው ባዮ ላንግ ተብሎ የተጠራው ግዙፍ “አረንጓዴ” ግድግዳ 150 ሜትር ርዝመትና 15 ሜትር ከፍታ አለው። ይህ ግድግዳ አበቦችን ጨምሮ ከ200 ዓይነት የዕፅዋት ዝርያዎች በተሰባሰቡ 200,000 ተክሎች የተሠራ ነው። እንደየወቅቱ የተለያዩ ተክሎችና አበቦች የሚተከሉባቸው እንዲህ ያሉት “ላንጎች” ወይም “ሳንባዎች” ለከተማዋ እንደመተንፈሻ አካል ሆነው በማገልገል ካርቦን ዳይኦክሳይድ የተባለውን የተቃጠለ አየር ተጠቅመው ኦክስጅንን በማስወጣት አየሩን እንደሚያጣሩ ተነግሯል።በተጨማሪም በኤግዚቢሽኑ ላይ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ አውቶቡሶችን ጨምሮ የተለያዩ መጓጓዣዎችም ቀርበው ነበር። እነዚህ ተሽከርካሪዎች ሰዎችን ሲያጓጉዙ እንደ ጪስ ሆኖ የሚወጣው ውኃ ብቻ ነው። ለቴክኖሎጂ አፍቃሪዎች ዕይታ የቀረበው ሌላው ነገር ደግሞ ጃፓን ለመጀመሪያ ጊዜ ለንግድ የሠራችው በማግኔት ኃይል አማካኝነት ሐዲዱን ሳይነካ የሚጓዘው ባቡር ነው። ሊኒሞ ተብሎ የሚጠራው ይህ ባቡር ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ማግኔቶች በመጠቀም ከሐዲድ መስመሮቹ በላይ 8 ሚሊ ሜትር ያህል ከፍ ብሎ ምንም ድምፅ ሳያሰማና ሳይንገጫገጭ ይጓዛል። በተጨማሪም በባትሪ የሚሠሩ ባቡሮች፣ የብስክሌት ታክሲዎችና በሹፌር ወይም ያለ ሹፌር ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ አውቶቡስ የሚመስሉ ተሽከርካሪዎች ለሕዝብ ዕይታ ቀርበዋል። ሁለት ወይም ሦስት ሆነው የሚከንፉት እነዚህ የመጪው ዘመን ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት የተፈጥሮ ጋዝ ሲሆን ይህም በአሁኑ ጊዜ እንደምንጠቀምበት ነዳጅ ብክለት የሚያስከትል አይደለም።
እንደ ምግብ ትርፍራፊ ካሉ የካርቦን ይዘት ካላቸው ቆሻሻዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና ማዳበሪያ ማምረት እንደሚቻል ብታውቅ ምን ይሰማሃል? በሥፍራው የሚገኝ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሚቴን የተባለውን ንጥረ ነገር በማብላላት ይህን ማድረግ ችሏል። የኃይል ማመንጫው ከተለያየ አካባቢ የሚሰበሰበውን ቆሻሻ በማስወገድ ወይም በማቃጠል ፋንታ እንዲቦካ በማድረግ ሚቴን ወደሚባለው ሃይድሮጅን የሚገኝበት ጋዝ ይለውጠዋል። ፊውል ሴል ተብሎ የሚጠራው ኬሚካሎችን የሚጠቀም የኃይል ማመንጫ ኤሌክትሪክ የሚፈጥረው ኦክስጅንን ከሃይድሮጅን ጋር በማዋሃድ ነው። የዚህ ኃይል ማመንጫ ተረፈ ምርቶች ደግሞ ውኃና ማዳበሪያ ናቸው። እንዲያውም በኤግዚብሽን ማዕከሉ ካሉት አዳራሾች ውስጥ አንዳንዶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኙት ይህ የኃይል ማመንጫ በአካባቢው የሚሰበሰበውን ቆሻሻ በሙሉ በዚህ መንገድ አብላልቶ ካመነጨው ኃይል ነበር።
ሮቦቶችን በማምረት ረገድም እንዲሁ ሰዎችን የሚያግዙ ቀላል ክብደት ያላቸውን ሮቦቶች ለመሥራት ከፍተኛ ምርምር በመካሄድ ላይ ነው። በአንደኛው የኤግዚቢሽን ማሳያ አዳራሽ ውስጥ የሮቦቶች ቴክኖሎጂ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚጠቁም ሁኔታ ታይቷል። ሰባት ሮቦቶች ወደ መድረኩ መሃል ተራምደው መጥተው ሙዚቃ በመጫወት በዚያ የተሰበሰበውን ሕዝብ አዝናንተዋል። አንዳንዶቹ ሮቦቶች “ጣቶቻቸውን” ያለአንዳች ችግር በማንቀሳቀስ የትንፋሽ መሣሪያዎችን ሲጫወቱ ሌሎቹ ደግሞ ከበሮ ይመቱ ነበር። “እንቅስቃሴያቸው ሁሉ ምንም ችግር የሌለበትና በቅልጥፍና የተሞላ ከመሆኑ
የተነሳ ሙሉ በሙሉ ሰዎች ይመስላሉ” በማለት አንድ ተመልካች ተናግሯል።በማዕከሉ ከታዩት ሁለት ተጨማሪ የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንደኛው ከበቆሎ ዱቄትና ከመሳሰሉት ምርቶች የሚሠራው በቀላሉ የሚበሰብስ ፕላስቲክ ነው። ሌሎቹ ደግሞ በማይክሮስኮፕ ካልሆነ በስተቀር በዓይን የማይታዩ ዲያሜትራቸው ከ200 ናኖሜትር በታች የሆኑ የጋዝ አረፋዎች (nanobubbles) ናቸው። የሰው ፀጉር ዲያሜትር 50,000 ናኖሜትር ገደማ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ጥቃቅን አረፋዎች በተፈጥሯቸው በፍጥነት በንነው የሚጠፉ ናቸው። ይሁን እንጂ የጃፓን ተመራማሪዎች “ቅርፊት ያላቸውና የሌላቸው ዓሦች በአካባቢያቸው ከሚከሰቱ ለውጦች ጋር እንዲላመዱ” የሚረዱ በቀላሉ በንነው የማይጠፉ የኦክስጅን አረፋዎችን ለመሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂም አዳብረዋል። እንዲያውም የኦክስጅን አረፋዎች በተጨመሩበት ሰው ሠራሽ ኩሬ ውስጥ ከጨው አልባም ሆነ ከጨዋማ ውኃ ውስጥ የተወሰዱ አንዳንድ የዓሣ ዝርያዎችን ማኖር ተችሏል! ተመራማሪዎቹ ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ ለዓሣ እርባታ፣ ለእርሻና ለሌሎችም መስኮች የሚውልበትን መንገድ የማግኘት ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ።
ዓለም ትኩረት ሰጥቶት ይሆን?
ኤግዚቢሽኑ ‘በተፈጥሮ ላይ ለሚንጸባረቀው ጥበብ’ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ቢገልጽም በአጠቃላይ ሲታይ ዓለም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። ተፈጥሮ የሚያሰማው ይህ ድምፅ በድንቁርና፣ በስግብግብነትና በሙስና ተውጧል። በዚህም ምክንያት ምድር በአንድ ኤግዚቢሽን ላይ እንደተገለጸው “የቆሰለች ፕላኔት” ሆናለች። ይሁን እንጂ በጥሩ ዓላማ የተነሳሱ ሰዎችም እንኳ ለሰው ልጅና ለምድር ሥነ ምሕዳራዊ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሔ የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው መፍትሔው ከሰው እውቀትና ጥበብ በላይ ነው። (ኤርምያስ 10:23) ይህ ሲባል ግን ችግሩ መፍትሔ የለውም ማለት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ከፍተኛው የጥበብ ምንጭ የሆነው ፈጣሪያችን ሰዎች የእጅ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ከማጥፋታቸው በፊት በምድር ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ራእይ 4:11፤ 11:18) መዝሙር 37:10, 11 “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ይላል። እውነት ነው፣ ተፈጥሮን መስማት ብልህነት ነው፤ ሆኖም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ሥራ ላይ በማዋል ፈጣሪን መስማት ደግሞ ከዚያ የበለጠ አስተዋይነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ የቆሰለችው ፕላኔታችን ሙሉ በሙሉ ተፈውሳ ወደ ገነትነት ስትለወጥ ያያሉ።—ሉቃስ 23:43
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኦክስጅን አረፋዎች ማሳያ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያለ ሹፌር የሚሄዱ አውቶቡሶች
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባለ 360 ዲግሪ ክብ ፊልም ማሳያ ክፍል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከ200 ዓይነት የተክል ዝርያዎች በተወሰዱ 200,000 ተክሎች የተሠራው ባዮ ላንግ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮቦቶች ተመልካቾችን በሙዚቃ ሲያዝናኑ