በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትሕትና የድክመት ምልክት ነው ወይስ የጥንካሬ?

ትሕትና የድክመት ምልክት ነው ወይስ የጥንካሬ?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ትሕትና የድክመት ምልክት ነው ወይስ የጥንካሬ?

በዓለም ላይ ኩሩ የሆኑና ከልክ በላይ በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ምሳሌዎች እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። ትሑትና የዋህ የሆኑ ሰዎች ደግሞ እንደ አቅመ ቢስ፣ ፈሪ ወይም አድር ባይ ይቆጠራሉ። ይሁንና እውነተኛ ትሕትና በእርግጥ የድክመት ምልክት ነው? ኩራትስ የጥንካሬ መግለጫ ይሆን? ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ የሆነ ኩራት እንዳለ በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያኖች አምላካቸው ይሖዋ በመሆኑና በእርሱ ዘንድ በመታወቃቸው ሊኮሩ ይገባል። (መዝሙር 47:4፤ ኤርምያስ 9:24፤ 2 ተሰሎንቄ 1:3, 4) ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ክርስቲያናዊ ጠባይ ሲያሳዩና ከእውነተኛው አምልኮ ጎን በድፍረት ጸንተው ሲቆሙ ሲመለከቱ ኩራት ይሰማቸዋል። (ምሳሌ 27:11) ይሁን እንጂ ኩራት መጥፎ ጎንም አለው።

ኩራትና ትሕትናን በጥልቀት መመርመር

ኩራት ለሚለው ቃል ከተሰጡት ፍቺዎች መካከል አንዱ ለራስ ከልክ ያለፈ ግምት መስጠት የሚል ነው። ይህ ዓይነቱ ኩራት ምናልባት አንድ ሰው ባለው መልክ፣ በዘሩ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ቦታ፣ በችሎታው ወይም በሀብቱ ከሌሎች የተሻለና ይበልጥ ተፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርገው ይችላል። (ያዕቆብ 4:13-16) መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች “በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ” ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:4) በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች ያለ ምንም ምክንያት ለራሳቸው እጅግ የተጋነነ አመለካከት ይኖራቸዋል ማለት ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ትሑት የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን በሐቀኝነትና በግልጽ ለመመልከት ከመጣራቸው በተጨማሪ አለፍጽምና እንዳለባቸው አምነው ይቀበላሉ እንዲሁም በአምላክ ፊት ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ። (1 ጴጥሮስ 5:6) ከዚህም በላይ የሌሎችን ግሩም ባሕርያት ለማስተዋል ይጥራሉ፤ እነዚህንም ባሕርያት በሌሎች ላይ መመልከታቸው ያስደስታቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:3) በመሆኑም በሌሎች ላይ አይቀኑም። (ገላትያ 5:26) ስለዚህ እውነተኛ ትሕትና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ከማድረጉም በላይ የተረጋጋ ስሜት እንዲኖረንና ደኅንነት እንዲሰማን ያደርጋል።

እስቲ የኢየሱስን ምሳሌ ተመልከት። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር ነበር። በምድር ላይ በኖረበት ጊዜም ፍጹምና ኃጢአት የሌለበት ነበር። (ዮሐንስ 17:5፤ 1 ጴጥሮስ 2:21, 22) ከሁሉም የላቀ ችሎታ፣ ማስተዋልና እውቀት ነበረው። ሆኖም ይህ እንዲታይለት አልጣረም። ከዚህ ይልቅ በትሕትና ተመላልሷል። (ፊልጵስዩስ 2:6) እንዲያውም የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል፤ በተጨማሪም ትናንሽ ልጆችን ከልብ ይወዳቸው ነበር። (ሉቃስ 18:15, 16፤ ዮሐንስ 13:4, 5) በአንድ ወቅት አንድን ሕፃን በደቀ መዛሙርቱ መካከል አቁሞ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 18:2-4) አዎን፣ በኢየሱስም ሆነ በአባቱ ዘንድ ታላቅ የሚያሰኘው ትሕትና እንጂ ኩራት አይደለም።—ያዕቆብ 4:10

ትሕትና የጥንካሬ መግለጫ ነው

ኢየሱስ ትሕትናን በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ቢሆንም ፈሪ ግን አልነበረም። እውነትን በድፍረት ይናገር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ፈጽሞ የሰው ፍርሃት አላደረበትም። (ማቴዎስ 23:1-33፤ ዮሐንስ 8:13, 44-47፤19:10, 11) በዚህም ምክንያት ከተቃዋሚዎቹም ሳይቀር አክብሮት አትርፏል። (ማርቆስ 12:13, 17፤ 15:5) ሆኖም ኢየሱስ ፈጽሞ አምባገነን አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሌሎችን በትሕትና፣ በደግነትና በፍቅር ይይዛቸው ስለነበር ኩሩ ከሆኑ ሰዎች በተለየ የብዙዎችን ልብ መማረክ ችሏል። (ማቴዎስ 11:28-30፤ ዮሐንስ 13:1፤ 2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) በዛሬው ጊዜም ቢሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለኢየሱስ ባላቸው እውነተኛ ፍቅርና ጥልቅ አክብሮት ተገፋፍተው በታማኝነት እየተገዙለት ነው።—ራእይ 7:9, 10

የአምላክ ቃል ትሑት እንድንሆን ያበረታታናል። ምክንያቱም ትሑት የሆኑ ሰዎች ምክርን ለመቀበል ዝግጁ ከመሆናቸውም ሌላ እነርሱን ማስተማርም አስደሳች ነው። (ሉቃስ 10:21፤ ቈላስይስ 3:10, 12) የተማረ ሰው እንደነበረው እንደ ጥንቱ ክርስቲያን አስተማሪ እንደ አጵሎስ ትክክለኛ የሆነ አዲስ መረጃ ሲቀርብላቸው አመለካከታቸውን ለማስተካከል ፈቃደኞች ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 18:24-26) ትሑት የሆኑ ሰዎች ጥያቄ ለመጠየቅ አይፈሩም፤ ኩሩ የሆኑ ሰዎች ግን አለማወቃችን ይጋለጣል ብለው ስለሚሰጉ እንዲህ ከማድረግ ይቆጠባሉ።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ የተወውን ምሳሌ ልብ በል። ይህ ሰው እያነበበው ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መረዳት አልቻለም ነበር። በዚህ ጊዜ ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ፊልጶስ ጃንደረባውን “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢትዮጵያዊውም “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” በማለት መለሰለት። በአገሩ እጅግ የተከበረ የነበረው ይህ ሰው ያሳየው ትሕትና እንዴት የሚደነቅ ነው! ትሑት መሆኑ ጥልቅ የሆነ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት አስገኝቶለታል።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-38

ይህ ኢትዮጵያዊ የሃይማኖት ሊቅ ነን ከሚሉት ከአይሁዳውያን ጸሐፍትና ከፈሪሳውያን በጣም የተለየ ነበር። (ማቴዎስ 23:5-7) እነዚህ ሰዎች ኢየሱስንም ሆነ የእርሱን ተከታዮች በትሕትና ከማዳመጥ ይልቅ ያሾፉባቸውና ስህተት ይፈላልጉባቸው ነበር። ስለዚህም ኩራታቸው በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንዲዳክሩ አድርጓቸዋል።—ዮሐንስ 7:32, 47-49፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29-33

ለመቀረጽ ፈቃደኛ ነህ?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋን ከሸክላ ሠሪ፣ ሰዎችን ደግሞ ከሸክላ ጋር ያመሳስላቸዋል። (ኢሳይያስ 64:8) ትሕትና አንድን ሰው በአምላክ እጅ እንዳለ ለስላሳ የሸክላ አፈር እንዲሆን የሚረዳው ሲሆን አምላክም ጥራት ያለው የክብር ዕቃ እንዲሆን አድርጎ ይቀርጸዋል። ኩሩ ሰው ግን በቀላሉ ሊፈረካከስ እንደሚችል ለሸክላ ሥራ አመቺ እንዳልሆነ ደረቅ አፈር ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ይሖዋን በመገዳደሩ ምክንያት ሕይወቱን ያጣው የጥንቷ ግብጽ ንጉሥ የነበረው ኩሩው ፈርዖን ነው። (ዘፀአት 5:2፤ 9:17፤ መዝሙር 136:15) የፈርዖን አስከፊ ውድቀት “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” የሚለው አባባል እውነት መሆኑን ያሳያል።—ምሳሌ 16:18

ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች የአምላክ ሕዝቦችም ቢሆኑ የኩራት ስሜት እንዳያሸንፋቸው ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁሙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የኢየሱስ ሐዋርያት በተደጋጋሚ ጊዜያት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ይከራከሩ ነበር። (ሉቃስ 22:24-27) ያም ሆኖ በኩራት የተዋጡ አልነበሩም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን በመስማት ቀስ በቀስ ያን ዓይነቱን ዝንባሌ ማስወገድ ችለዋል።

ሰሎሞን “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 22:4) ትሕትናን እንድናዳብር የሚያነሳሳ እንዴት ያለ ግሩም ምክር ነው! ትሕትና ግሩምና ተወዳጅ ባሕርይ ብቻ ሳይሆን የአምላክን ሞገስ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የሚረዳን ባሕርይ ነው።—2 ሳሙኤል 22:28፤ ያዕቆብ 4:10

ይህን አስተውለኸዋል?

ሁሉም ዓይነት ኩራት ጎጂ ነው?—2 ተሰሎንቄ 1:3, 4

ትሕትና እውቀት ለመቅሰም ፈቃደኞች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው? —የሐዋርያት ሥራ 8:26-38

የአምላክ አገልጋዮች ትሕትናን ለማዳበር መጣር ይገባቸዋል?—ሉቃስ 22:24-27

ትሑቶች ምን በረከት ያገኛሉ?—ምሳሌ 22:4

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ትሑት ስለነበር ልጆች ይቀርቡት ነበር