በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ የሥራ መስክ መርጫለሁ

ትክክለኛ የሥራ መስክ መርጫለሁ

ትክክለኛ የሥራ መስክ መርጫለሁ

ሶንያ አኩንያ ኬቬቶ እንደተናገረችው

በምሠራበት ባንክ ውስጥ የደረጃ እድገት እንዳገኘሁ ተነግሮኝ ነበር። ቦታው በሌሎች ዘንድ የሚያስከብር ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ደሞዝ ያስገኛል። ይሁን እንጂ፣ በዚያ ወቅት ራቅ ብሎ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ገና መጋበዜ ነበር። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ከ32 ዓመታት በፊት ያደረግሁትን ምርጫ ሳስበው ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንዳደረግሁ ይሰማኛል።

እናቴ ያደገችው በሮማ ካቶሊክ እምነት ውስጥ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተምራቸውን ትምህርቶች አስመልክቶ ጥያቄዎች ነበሯት። ምስሎች የሰው እጅ ሥራ ሆነው ሳለ ለምን የአምልኮ ያህል ክብር ይሰጣቸዋል? ብላ ትጠይቅ ነበር። እውነትን ማግኘት ትፈልግ ስለነበር ለጥያቄዎቿ መልስ ለማግኘት ወደተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን ልፋቷ ውጤት አላስገኘላትም።

ቤታችን የሚገኘው ሜክሲኮ ውስጥ ቱስትላ በምትባለው ከተማ ነበር። አንድ ቀን እናቴ ነፋሻ በሆነው አየር ደጃፍ ላይ ቁጭ ብላ ሳለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን መጣ። ለጥያቄዎቿ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ በማግኘቷ ስለተደነቀች በሌላ ጊዜ ተመልሶ እንዲመጣ ተስማማች። በቀጠሮው ቀን ከአንድ የአድቬንቲስት አገልጋይ፣ የካቶሊክ ቄስና የናዝራውያን ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ጋር ሆና ጠበቀችው። ከዚያም ሰንበትን አስመልክቶ ጥያቄ ያነሳች ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ አጥጋቢ መልስ የሰጣት የይሖዋ ምሥክሩ ነበር፤ ለነገሩ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውም እርሱ ብቻ ነበር! እናቴ ለስድስት ወራት መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናች በኋላ በ1956 ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። በዚያን ጊዜ እኔ የስምንት ዓመት ልጅ ነበርኩ።

አባቴ ስጋት አደረበት

አባቴ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቷ እናቴን አልተቃወማትም። ሆኖም እኔን፣ እህቴንና ሁለቱን ወንድሞቼን ማስጠናትና ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዛን መሄድ ስትጀምር ጽሑፎቿን ከጥቅም ውጭ አደረገባት። እንደተታለልን ሆኖ ስለተሰማው የይሖዋ ምሥክሮች፣ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስገቡት ሰዎችን ለማሳሳት እንደሆነ በመግለጽ ሊያሳምነን ሞክሮ ነበር፤ ይህንን ለማረጋገጥ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ አሳየን። በዚህ ጊዜ እናቴ ይሖዋ የሚለውን ስም ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስታሳየው በጣም ስለተገረመ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለይሖዋ ምሥክሮች ያለው አመለካከት ተቀየረ።—መዝሙር 83:18 NW

በሜክሲኮ ሴቶች ልጆች 15ኛው ዓመት የልደት በዓላቸው በልዩ ሁኔታ ይከበርላቸዋል። ልደትን ማክበር ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ስለሌለው ልደቴን ማክበር አቁሜ ነበር። * አባቴ ግን አንድ የተለየ ነገር ሊያደርግልኝ ፈለገ። ሁኔታውን ካሰብኩበት በኋላ “በቀጣዩ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ አብረኸኝ በመገኘት አንተ ራስህ ስጦታ እንድትሆነኝ እፈልጋለሁ” አልኩት። ግብዣዬን የተቀበለ ሲሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለው ፍላጎት እያደገ ሄደ።

አባቴ አንድ ቀን ምሽት ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስ የጣለውን የኤሌክትሪክ ገመድ ነክቶ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት። ሆስፒታል ተኝቶ እያለ በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለ24 ሰዓት ይንከባከቡት ነበር። አባቴም የክርስቲያናዊ ፍቅር መግለጫ የሆነውን ይህን አጋጣሚ በጭራሽ አይረሳውም። ከጊዜ በኋላ አባቴ በአገልግሎት መካፈል የጀመረ ሲሆን ሕይወቱንም ለይሖዋ ወሰነ። የሚያሳዝነው ግን ሊጠመቅ ከነበረበት ጊዜ አንድ ወር ቀደም ብሎ መስከረም 30, 1975 ሞተ። በትንሣኤ ወቅት አባታችን ከሞት ሲነሳ ለመቀበል በጣም እንናፍቃለን!—የሐዋርያት ሥራ 24:15

ጠቃሚ የሆነ የቤተሰብ ተጽዕኖ

ታላቅ እህቴ ካርመን የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሁልጊዜ በጣም ውድ እንደሆነ መብት አድርጋ ትመለከት ነበር። በ1967 ከተጠመቀች በኋላ ብዙም ሳይቆይ የዘወትር አቅኚ ሆና በእያንዳንዱ ወር በአገልግሎት 100 ሰዓት ማሳለፍ ጀመረች። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በማዕከላዊ ሜክሲኮ ወደምትገኘው ወደ ቶሉካ ተዛወረች። እኔም በባንክ ውስጥ የተቀጠርኩ ሲሆን ሐምሌ 18, 1970 ተጠመቅሁ።

ካርመን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶላት ስለነበር እኔም ወደ ቶሉካ በመሄድ አብሬያት እንዳገለግል ታበረታታኝ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ እያሰብኩ እያለ አንድ ቀን የኢየሱስ ተከታዮች ውድ የሆነ መንፈሳዊ ሀብታቸውን አምላክን ለማክበር መጠቀም እንዳለባቸው የሚያበረታታ ንግግር አዳመጥኩ። (ማቴዎስ 25:14-30) በዚህ ጊዜ ‘በአደራ የተሰጡኝን መንፈሳዊ ስጦታዎች በደንብ እየተጠቀምኩባቸው ነው?’ በማለት ራሴን ጠየቅሁ። እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ ይሖዋን ይበልጥ የማገልገል ፍላጎት አሳደረብኝ።

ከሁለት ግቦች አንዱን መምረጥ

በ1974 በሌላ ክልል ውስጥ በልዩ አቅኚነት ለማገልገል አመለከትኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በሥራ ላይ እያለሁ ቶሉካ የሚገኝ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ስልክ ደወለልኝ። “ስንጠብቅሽ ነበር እኮ፣ ለምን አልመጣሽም?” በማለት ጠየቀኝ። ልዩ አቅኚ ሆኜ መመደቤን የሚገልጸው ደብዳቤ በመሃል ጠፍቶ ነው እንጂ ለካስ ቶሉካ ውስጥ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመድቤ ነበር! (ልዩ አቅኚዎች የይሖዋ ድርጅት በመደባቸው በየትኛውም ቦታ ሙሉ ጊዜያቸውን በአገልግሎት ለማሳለፍ ፈቃደኞች ናቸው።)

ወዲያውኑ ሥራ ለመልቀቅ መወሰኔን ለባንኩ አሳወቅሁ። አለቃዬ አንድ ወረቀት ይዞ “አንዴ ቆዪ ሶንያ! በድርጅታችን ውስጥ በምክትል ሥራ አስኪያጅነት እንዲሠሩ ከተመረጡት ሰባት ሴቶች መካከል አንዷ መሆንሽን የሚገልጽ መልእክት አሁን ደረሰን። ድርጅታችን ከዚህ በፊት በዚህ ቦታ ላይ ሴቶችን ሾሞ አያውቅም። ሥራውን አትቀበይም?” በማለት ጠየቀኝ። መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ይህ የደረጃ እድገት በሌሎች ዘንድ ክብር የሚያሰጥና ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ ቢሆንም አለቃዬን ካመሰገንኩት በኋላ አምላክን ይበልጥ ለማገልገል እንደወሰንኩ ነገርኩት። አለቃዬም “እንደዚያ ከሆነ በርቺ፤ ግን አንድ ነገር ላስታውስሽ፤ በማንኛውም ጊዜ ብትመጪ ባንኩ ለአንቺ ክፍት መሆኑን አትርሺ” አለኝ። ከሁለት ቀን በኋላ በቶሉካ አገልግሎቴን ጀመርኩ።

በሜክሲኮ በልዩ አቅኚነት ማገልገል

ቶሉካ ስደርስ ካርመን በልዩ አቅኚነት ማገልገል ከጀመረች ሁለት ዓመት ሆኗት ነበር። ዳግመኛ በመገናኘታችን በጣም ተደሰትን! ሆኖም አንድ ላይ የቆየነው ለአጭር ጊዜ ነበር። ምክንያቱም ከሦስት ወራት በኋላ እናታችን ድንገተኛ አደጋ ስለደረሰባት ከጎኗ ሆኖ የቅርብ እንክብካቤ የሚያደርግላት ሰው አስፈለጋት። የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ ካማከርን በኋላ ካርመን ወደ ቤት ተመልሳ እናታችንን እንድትንከባከብ ተስማማን። እርሷም ለ17 ዓመታት እናታችንን ተንከባክባለች። በዚህ ወቅትም ቢሆን ካርመን የዘወትር አቅኚ ሆና ታገለግል የነበረ ሲሆን ከእናታችን እንዳትርቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቿ ቤት እየመጡ ታስጠናቸው ነበር።

በ1976 ቴካማቻሎ በምትባል ሁለት ዓይነት ገጽታዎች ባሏት ከተማ ተመደብኩ። በከተማዋ ውስጥ በአንድ በኩል ድሆች ሲኖሩ ሀብታሞቹ ደግሞ በሌላኛው በኩል ይኖሩ ነበር። በዚህች ከተማ ውስጥ፣ ያላገቡና ከሀብታም ወንድማቸው ጋር የሚኖሩ አንዲት አረጋዊት ሴት አግኝቼ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርኩ። እኚህ ሴት የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደሚፈልጉ ለወንድማቸው ሲነግሯቸው ወንድምየው ከቤት እንደሚያባርሯቸው በመንገር አስፈራሯቸው፤ እኚህ ትሑት ሴት ግን አልፈሩም። አረጋዊቷ ሴት ከተጠመቁ በኋላ ወንድምየው ከቤት አባረሯቸው። እኚህ እህት በወቅቱ የ86 ዓመት አረጋዊት የነበሩ ቢሆንም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ታምነዋል። ጉባኤው ባደረገላቸው እንክብካቤ በመታገዝ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በታማኝነት ጸንተዋል።

የጊልያድ ትምህርት ቤት ከዚያም ወደ ቦሊቪያ

በቴካማቻሎ አምስት አስደሳች ዓመታትን አሳልፌአለሁ። ከዚያም በሜክሲኮ በሚካሄደው የመጀመሪያው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ቅርንጫፍ ውስጥ ገብቼ እንድማር ተጋበዝኩ። ስሙ እንደሚያመለክተው ይህ ትምህርት ቤት በኒው ዮርክ የሚገኘው ትምህርት ቤት ቅርንጫፍ ነበር። እናቴም ሆነች ካርመን ግብዣውን እንድቀበል በጣም ስለገፋፉኝ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ውስጥ ጎላ ያለ ቦታ የሚይዘውን የአሥር ሳምንት ኮርስ ለመካፈል በሜክሲኮ ሲቲ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ተጓዝኩ። የካቲት 1, 1981 ከተመረቅን በኋላ ከኤንሪኬታ አያላ ጋር (አሁን ኤንሪኬታ ፈርናንዴስ ሆናለች) ቦሊቪያ ውስጥ በምትገኘው ላ ፓዝ የምትባል ከተማ እንዳገለግል ተመደብኩ።

ላ ፓዝ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ስንደርስ የሚቀበሉን ወንድሞች ገና አልመጡም ነበር። እርስ በርሳችን “ለምን ጊዜ እናባክናለን?” ተባባልንና አውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መመሥከር ጀመርን። ለሦስት ሰዓታት ያህል ደስ በሚል ሁኔታ ካገለገልን በኋላ ከቅርንጫፍ ቢሮ ከመጡት ወንድሞች ጋር ተገናኘን። ይቅርታ ከጠየቁን በኋላ በበዓል ምክንያት መንገድ በመዘጋቱ እንደዘገዩ ነገሩን።

ከደመና በላይ መመሥከር

ላ ፓዝ ከባሕር ወለል በላይ 3,625 ሜትር ከፍታ ላይ ስለምትገኝ አብዛኛውን ጊዜ ከደመና በላይ እንሆን ነበር። አየሩ ስስ በመሆኑ ምክንያት ለመተንፈስ በጣም ስለሚያስቸግር ትንሽ ካገለገልኩ በኋላ ይደክመኛል። ከአየሩ ሁኔታ ጋር ለመላመድ አንድ ዓመት ቢወስድብኝም ከይሖዋ ያገኘኋቸው በረከቶች የሚያጋጥሙኝን ችግሮች የሚያስረሱ ነበሩ። ለምሳሌ፣ በ1984 አንድ ቀን ጠዋት አለታማ የሆነ አቀበት ጫፍ ላይ ወደሚገኝ ቤት ወጣሁ። እዚያ በደረስኩ ጊዜ በጣም ደክሞኝ ነበር፤ በሩን ሳንኳኳ አንዲት ሴት ወጣች። አስደሳች ውይይት ካደረግን በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደምመለስ ነገርኳት።

“መምጣትሽን እጠራጠራለሁ” በማለት መለሰችልኝ። ሆኖም በሌላ ቀን ተመልሼ ሄድኩ፤ በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ልጇን መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስተምርላት ጠየቀችኝ። “ይህ የወላጆች ኃላፊነት ነው፤ እንዳስተምርልሽ ከፈለግሽ ግን ልረዳሽ እችላለሁ” አልኳት። በሐሳቡ የተስማማች ሲሆን እሷም መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ያቀረብኩላትን ግብዣ ተቀበለች። ይህቺ ሴት ማንበብና መጻፍ ስለማትችል እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ለመርዳት ታስቦ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ማንበብና መጻፍ መማር (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት ማጥናት ጀመርን።

ከጊዜ በኋላ የዚህ ቤተሰብ ልጆች ቁጥር ስምንት ደረሰ። ወደ ቤታቸው ስሄድ ልጆቹ እጅ ለእጅ ተያይዘው ያንን ዳገት እንድወጣ ይረዱኝ ነበር። ውሎ አድሮ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ማለትም አባት፣ እናትና ስምንቱም ልጆች ይሖዋን ማገልገል ጀመሩ። ሦስቱ ሴቶች ልጆች አቅኚዎች ሲሆኑ አንዱ ወንድ ልጅ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ነው። አባትየው በ2000 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የጉባኤ አገልጋይ ነበር። ይህን አስገራሚ ቤተሰብና ታማኝነታቸውን ሳስብ ልቤ ምንኛ በደስታ ይሞላል! ይሖዋ ይህን ቤተሰብ እንድረዳ ስለፈቀደልኝ አመሰግነዋለሁ።

ከካርመን ጋር እንደገና ተገናኘን

እናታችን በ1997 ስትሞት ካርመን በልዩ አቅኚነት እንድታገለግል እንደገና ተጋበዘች። በ1998 ቦሊቪያ ውስጥ እኔ በማገለግልበት ኮቻባምባ በሚባል ከተማ እንድታገለግል ተመደበች። አዎን፣ ከ18 ዓመት በኋላ እንደገና አብረን እንድናገለግል ተመደብን። ካርመን ወደዚያ የመጣችው የሚስዮናዊነት መብት ተሰጥቷት ነበር። እኔና ካርመን አንዴ ከገቡበት በማይለቀውና አስደሳች የአየር ጠባይ ባለው በኮቻባምባ ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሸለቆ ውስጥ በተመሠረተችውና 220,000 ሕዝብ በሚኖርባት ሱክሬ በተባለች ውብ የቦሊቪያ ከተማ ውስጥ እንገኛለን። በአንድ ወቅት ይህቺ ከተማ በርካታ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙባት ስለነበር ትንሿ ቫቲካን ተብላ ትጠራ ነበር። አሁን በዚህች ከተማ አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ።

እኔና ካርመን በድምሩ ከ60 ዓመት በላይ በአቅኚነት ያገለገልን ሲሆን በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲጠመቁ የመርዳት ተወዳዳሪ የሌለው መብት በማግኘታችን ተደስተናል። አዎን፣ ይሖዋን በፍጹም ነፍስ ማገልገል ከፍተኛ እርካታ የሚያስገኝ የሕይወት መንገድ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም!—ማርቆስ 12:30

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አረማውያን ያከበሯቸው ሁለት የልደት በዓላት የተጠቀሱ ሲሆን የተመዘገቡትም በመጥፎ ጎናቸው ነው። (ዘፍጥረት 40:20-22፤ ማርቆስ 6:21-28) የአምላክ ቃል በኅብረተሰቡ ወይም በእኩዮች ተጽዕኖ ተገፋፍተን ሳይሆን ከልብ ተነሳስተን ስጦታ እንድንሰጥ ያበረታታናል።—ምሳሌ 11:25፤ ሉቃስ 6:38፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከዚህ ቤተሰብ ጋር ለማጥናት አለታማ የሆነ አቀበት እወጣ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእህቴ ከካርመን (በስተ ቀኝ) ጋር በአገልግሎት ላይ ሳለን