በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ሰው “አብሬው እንድወጣ” ቢጠይቀኝስ?

አንድ ሰው “አብሬው እንድወጣ” ቢጠይቀኝስ?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

አንድ ሰው “አብሬው እንድወጣ” ቢጠይቀኝስ?

“አንዳንድ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት እስከ መፈጸም ድረስ ሊቀራረቡ ይችሉ እንደሆነ ለማየትና ከምን ያህል ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም እንደሚችሉ ለማወቅ ሲሉ ብቻ ካገኙት ሰው ጋር አብረው ይወጣሉ።”—ፔኒ *

“ወንዶች ልጆች ስለ ጉዳዩ ያለ አንዳች እፍረት ይናገራሉ። የሴት ጓደኛ ብትኖራቸውም እንኳ ከብዙ ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት እንደፈጸሙ በጉራ ያወራሉ።” —ኤድዋርድ

“የጾታ ግንኙነት እንድንፈጽም ግብዣ ያቀረቡልኝ ሰዎች ጥያቄያቸው ቀጥተኛ ነበር፤ ጥያቄውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኔን መናገሬም ድጋሚ ከመጠየቅ ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም!”—አይዳ

በአገራችን “አብሮ መውጣት” በመባል ይታወቃል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሌላ ስያሜ ይሰጠዋል። በጃፓን የምትኖር አኪኮ የተባለች ወጣት በምትኖርበት አካባቢ ይህ ድርጊት ‘መውጣት’ የሚል ስያሜ እንዳለው ተናግራለች። አክላም “ሴፍሬ ተብሎም የሚጠራ ሲሆን ይህ ቃል ‘ሴክስ ፍሬንድ’ የሚለው ሐረግ አጭር አጠራር ነው። ጓደኝነቱ የሚመሠረተው የጾታ ግንኙት ለመፈጸም ብቻ ተብሎ ነው” ብላለች።

መጠሪያው ምንም ይሁን ምን ትርጉሙ ግን ተመሳሳይ ነው፤ ቃሉ ምንም ዓይነት ስሜታዊ ቅርርብ ሳይኖር የጾታ ግንኙነት መፈጸምን ያመለክታል። * እንዲያውም አንዳንድ ወጣቶች ረዘም ላለ ጊዜ የፍቅር ግንኙነት መሥርቶ መቆየት ከሚያስከትለው “የተወሳሰበ” ሁኔታ ነጻ ሆነው የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም የሚያስችሏቸውን ጓደኞች ማግኘታቸውን በኩራት ይናገራሉ። አንዲት ወጣት “ይህን መሰሉ የጾታ ግንኙነት ጊዜያዊ እርካታን ለማግኘት ተብሎ የሚደረግ ሲሆን የፈለጋችሁትን ካገኛችሁ በኋላ መሄድ ትችላላችሁ” ብላለች።

ክርስቲያኖች እንደመሆናችሁ መጠን ‘ከዝሙት መሸሽ’ ይኖርባችኋል። * (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህን ማወቃችሁ ወደ ችግር ከሚመሩ ሁኔታዎች ለመራቅ ጥረት እንድታደርጉ እንደሚገፋፋችሁ እሙን ነው። ያም ሆኖ አንዳንዴ ፈተናዎች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። ሲንዲ የተባለች ወጣት “አብሬያቸው የምማራቸው በርካታ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት እንድንፈጽም ይጠይቁኛል” ብላለች። በሥራ ቦታም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ማርጋሬት እንዲህ ትላለች:- “አለቃዬ የጾታ ግንኙነት እንድንፈጽም ጠይቆኝ ነበር፤ አላስቆም አላስቀምጥ ስላለኝ ሥራዬን መልቀቅ ግድ ሆኖብኛል!”

በሌላ በኩል ግን የሚቀርብላችሁን ጥያቄ ለመቀበል ብትፈተኑ ያን ያህል ሊያስደንቃችሁ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም” በማለት ይናገራል። (ኤርምያስ 17:9) ሉርደስ የተባለች አንዲት ወጣት ይህን አባባል እውነት ሆኖ አግኝታዋለች። “የጾታ ግንኙነት እንድንፈጽም የጠየቀኝን ሰው ወድጄው ነበር” በማለት በግልጽ ተናግራለች። ጄንም ብትሆን ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟት እንደነበር ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “ለጠየቀኝ ወጣት ልዩ ስሜት ስለነበረኝ እምቢ ማለት ከምንም ነገር በላይ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኤድዋርድም ንጽሕናን ጠብቆ መኖር ቀላል አለመሆኑን ተናግሯል። ኤድዋርድ፣ “ብዙ ወጣት ሴቶች የጾታ ግንኙነት እንድንፈጽም ይጠይቁኛል። በክርስትና ሕይወቴ ውስጥ እጅግ ከባድ ሆኖ ያገኘሁት ይህን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም ነበር፤ አልፈልግም ማለት ቀላል አይደለም!” ብሏል።

እናንተም እንደ ሉርደስ፣ ጄንና ኤድዋርድ የሚሰማችሁ ቢሆንም፣ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን እያደረጋችሁ ከሆነ ልትመሰገኑ ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይታገለው የነበረውን መጥፎ ዝንባሌ ለመዋጋት ያልተቋረጠ ትግል ማድረግ አስፈልጎት እንደነበር ማወቃችሁ ሊያጽናናችሁ ይችላል።—ሮሜ 7:21-24

ሆኖም አንድ ሰው የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ቢጠይቃችሁ ልታስቡባቸው የሚገቡት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

ልቅ የጾታ ግንኙነት ስህተት የሆነበትን ምክንያት መረዳት

መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ የጾታ ግንኙነትን ያወግዛል። እንዲያውም ዝሙት እጅግ ከባድ ኃጢአት ከመሆኑ የተነሳ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች “የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ድርጊቱን በይሖዋ ዓይን መመልከታችሁ በአጋጣሚ ካገኛችሁት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ የሚቀርብላችሁን ፈተና ለመቋቋም ይረዳችኋል። ምርጫችሁ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ መኖር ሊሆን ይገባል።

“የይሖዋ መንገድ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን ከልብ አምናለሁ።”—ካረን፣ ካናዳ

“አንድ ሰው ለጥቂት ደቂቃዎች እርካታ ብሎ ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች ችላ ካለ ብዙ ነገሮች ያጣል።”—ቪቪያን፣ ሜክሲኮ

“ወላጆችና በርካታ ጓደኞች እንዳሏችሁ እንዲሁም የአንድ ጉባኤ አባል እንደሆናችሁ አትዘንጉ። በፈተናው ብትሸነፉ እነዚህን ሁሉ ሰዎች ታሳዝናላችሁ!”—ፒተር፣ ብሪታንያ

ሐዋርያው ጳውሎስ “ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 5:10) ፍጹም ባለመሆናችሁ ድርጊቱ ማራኪ እንደሆነ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ይሁንና ዝሙትን በተመለከተ ይሖዋ ያለው ዓይነት አመለካከት በማዳበር ‘ክፋትን መጥላት’ ትችላላችሁ።—መዝሙር 97:10

በተጨማሪም:- ዘፍጥረት 39:7-9ን አንብቡ። ዮሴፍ የቀረበለትን ከጾታ ብልግና ጋር የተያያዘ ፈተና በድፍረት እንደተቋቋመና ይህን ለማድረግ ያስቻለው ምን እንደሆነ አስተውሉ።

በእምነታችሁ ልትኮሩ ይገባችኋል

ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ላመኑበት ነገር በኩራት ጸንተው መቆማቸውና ያመኑበትን ነገር ለማስረዳት መጣራቸው የተለመደ ነው። ክርስቲያን እንደመሆናችሁ መጠን ምሳሌ የሚሆን ሥነ ምግባር በማሳየት የአምላክ ስም እንዳይነቀፍ የማድረግ ጥሩ አጋጣሚ አላችሁ። ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መደረግ የለበትም በሚለው ጥብቅ አቋማችሁ ልታፍሩ አይገባም።

“የምትመሩባቸው የሥነ ምግባር ደንቦች እንዳሏችሁ ገና ከጅምሩ በግልጽ ተናገሩ።”—አለን፣ ጀርመን

“በእምነታችሁ የምታፍሩበት ምንም ምክንያት የለም።”—ኤስተር፣ ናይጄሪያ

“‘ወላጆቼ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሬ እንድጫወት አይፈቅዱልኝም’ እንደሚሉት ዓይነት መልሶች የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ የጠየቋችሁ ልጆች አቋማችሁን እንዲያከብሩላችሁ የሚያደርጉ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ከእነርሱ ጋር ተቀጣጥራችሁ ለመጫወት እንደማትፈልጉ በግልጽ ንገሯቸው።”—ጃኔት፣ ደቡብ አፍሪካ

“ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ አብረውኝ የተመደቡት ልጆች ማንነቴን ያውቁ ስለነበር እኔን ለማግባባት መሞከር ከንቱ ድካም መሆኑን ተገንዝበው ነበር።”—ቪኪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ለምታምኑበት ነገር ጠንካራ አቋም መያዛችሁ የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች መሆናችሁን ያመለክታል።—1 ቆሮንቶስ 14:20

በተጨማሪም:- ምሳሌ 27:11ን አንብቡ። የምታደርጓቸው ነገሮች ከይሖዋ ስም መቀደስ ጋር በተያያዘ ለተነሳውና በዘመናት ከነበሩት ሁሉ ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ውዝግብ መልስ ለመስጠት እንዴት እንደሚያስችሏችሁ አስቡ!

ቆራጥ አቋም ይኑራችሁ!

ፈቃደኛ አለመሆናችሁን መናገር አስፈላጊ ነው። ሆኖም አንዳንዶች ተቃውሟችሁን እንደ መግደርደር አድርገው ሊቆጥሩት ይችላሉ።

“ለጾታ ብልግና ጥያቄ ያቀረበላችሁ ሰው እምቢ ስትሉት፣ ችሎታውን ለመፈተን ወይም የበለጠ እንዲጓጓ ለማድረግ እየሞከራችሁ እንዳለ ሊሰማው ይችላል።”—ላውራን፣ ካናዳ

“ሁሉ ነገራችሁ ማለትም አለባበሳችሁ፣ አነጋገራችሁ፣ የምታነጋግሯቸው ሰዎች እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዲህ ያለውን ድርጊት ለመፈጸም አለመፈለጋችሁን የሚያሳይ መሆን አለበት።”—ጆይ፣ ናይጄሪያ

“እምቢታችሁን ቁርጥ እና ጠንከር ባለ መንገድ ልትገልጹ ይገባል።”—ዳኒየል፣ አውስትራሊያ

“ደፋር መሆን ያስፈልጋል! አንድ ወጣት ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ‘እጅህን ከላዬ ላይ አንሳ!’ ካልኩት በኋላ ኮስተር ብዬ ጥዬው ሄድኩ።”—ኤለን፣ ብሪታንያ

“እንዲህ ያለ ድርጊት ለመፈጸም እንደማትፈልጉና መቼም ቢሆን አቋማችሁ እንደማይለወጥ በማያሻማ ሁኔታ መናገር አለባችሁ። ይህ ለስለስ ያለ መልስ የምትሰጡበት ጊዜ አይደለም!”—ጂን፣ ስኮትላንድ

“በአንድ ወቅት አንድ ልጅ ያስቸግረኝና ያፌዝብኝ ነበር። ይሁንና ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ ያደርስብኝ የነበረውን ትንኮሳ አቆመ።”—ዋኒታ፣ ሜክሲኮ

“በምንም ዓይነት ከእነርሱ ጋር የጾታ ግንኙነት እንደማትፈጽሙ ግልጽ ልታደርጉላቸው ይገባል። እንዲሁም የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ጥያቄ የሚያቀርቡላችሁ ወንዶች የሚሰጧችሁን ስጦታ ፈጽሞ አትቀበሉ። ምክንያቱም በምላሹ አንድ ነገር እንድታደርጉላቸው ይፈልጋሉ።”—ላራ፣ ብሪታንያ

በአቋማችሁ የምትጸኑ ከሆነ ይሖዋ ይረዳችኋል። መዝሙራዊው ዳዊት፣ ይሖዋ ‘ከታማኙ ጋር ታማኝ እንደሚሆን’ ከግል ተሞክሮው በመነሳት ተናግሯል።—መዝሙር 18:25

በተጨማሪም:- 2 ዜና መዋዕል 16:9ን አንብቡ። ይሖዋ በፍጹም ልባቸው በእርሱ የሚታመኑ ሰዎችን ለመርዳት ምን ያህል ጉጉት እንዳለው ልብ በሉ።

የማስተዋል ችሎታችሁን ተጠቀሙ

መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ይህን ምክር እንዴት በተግባር ማዋል ትችላላችሁ? የማስተዋል ችሎታችሁን በመጠቀም ነው!

“በተቻላችሁ መጠን ይህን ስለመሰሉ ጉዳዮች ከሚያወሩ ሰዎች ራቁ።”—ናኦሚ፣ ጃፓን

“ወደ አደጋ ሊያስገባችሁ ከሚችል ወዳጅነትም ሆነ ሁኔታ መራቅ ይኖርባችኋል። ለምሳሌ ያህል፣ በመስከራቸው ምክንያት በፈተና የተሸነፉ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ።”—ኢሻ፣ ብራዚል

“አድራሻችሁን ወይም ስልክ ቁጥራችሁን የመሳሰሉ የግል መረጃዎቻችሁን አትስጡ።”—ዳያን፣ ብሪታንያ

“ከክፍል ጓደኞቻችሁ ጋር በመተቃቀፍ ሰላምታ ከመስጠት ተቆጠቡ።”—ኤስተር፣ ናይጄሪያ

“በአለባበሳችሁ ጥንቃቄ አድርጉ። አለባበሳችሁ የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅስ መሆን የለበትም።”—ሃይዲ፣ ጀርመን

“ከወላጆቻችሁ ጋር ጥሩ ቅርርብ መፍጠራችሁና እነዚህን ስለመሰሉት ሁኔታዎች መነጋገራችሁ ከፍተኛ ጥበቃ ይሆንላችኋል።”—አኪኮ፣ ጃፓን

አነጋገራችሁን፣ ምግባራችሁን፣ ጓደኞቻችሁን እንዲሁም አዘውትራችሁ የምትሄዱባቸውን ቦታዎች ገምግሙ። ከዚያም ራሳችሁን ‘ሳይታወቀኝ፣ ሰዎች የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም እንዲጠይቁኝ ሊያደርጉ በሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ እየገባሁ ወይም እንዲህ ዓይነት ጥያቄ እንዲቀርብልኝ የሚያበረታቱ ነገሮች እያደረግሁ ነው?’ ብላችሁ ጠይቁ።

በተጨማሪም:- ዘፍጥረት 34:1, 2ን አንብቡ። ዲና የተባለች አንዲት ወጣት ተገቢ ባልሆነ ቦታ በመገኘቷ ያጋጠማትን ችግር አስተውሉ።

ይሖዋ በአጋጣሚ በተገናኙ ሰዎች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነትን እንደ ቀላል ነገር አይቶ የሚያልፈው ስላልሆነ እናንተም የእርሱ ዓይነት አመለካከት ሊኖራችሁ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ . . . በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም” በማለት ይናገራል። (ኤፌሶን 5:5) ትክክል ለሆነው ነገር አቋም በመውሰድ ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም ለራሳችሁ አክብሮት እንዲኖራችሁ ማድረግ ትችላላችሁ። ካርሊ የተባለች አንዲት ወጣት እንዳለችው “የሌላ ሰው ጊዜያዊ ስሜት ማርኪያ ለምን ትሆናላችሁ? ስትደክሙለት የኖራችሁትን በይሖዋ ፊት ያላችሁን ንጹህ አቋም ጠብቃችሁ ለመኖር ጣሩ!”

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.7 ቃሉ መደባበስን፣ መተሻሸትንና መሳሳምን የመሳሰሉ ድርጊቶችንም ያመለክታል።

^ አን.8 ዝሙት የሚለው ቃል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነትን፣ በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ የጾታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶምን፣ የሌላን ሰው የጾታ ብልት ማሻሸት እንዲሁም የጾታ ብልቶችን በማይገባ መንገድ መጠቀምን የሚጨምሩ ሌሎች ድርጊቶችን ያጠቃልላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ፍጹም ባለመሆናችን የጾታ ብልግና ማራኪ መስሎ ሊታየን ቢችልም ድርጊቱ ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?

▪ አንድ ሰው የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ጥያቄ ቢያቀርብላችሁ ምን ታደርጋላችሁ?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

▪ መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት የሚፈጽም ሰው “በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህ አባባል ትክክል ነው የምንለው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆኑ ነጥቦች ማግኘት ከቻልክ ከዚህ በታች ጻፋቸው:-

․․․․․

ፍንጭ:- ከላይ የተጠቀሰውን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 188⁠ን እንዲሁም ሰኔ 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28 አንቀጽ 14⁠ን እና መጠበቂያ ግንብ ሰኔ 15, 2002 ገጽ 21 አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት። እነዚህ ጽሑፎች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ

“በምማርበት ክፍል ውስጥ የሚገኝ አንድ ልጅ አብረን እንድንወጣ ጠየቀኝ። በእርግጥ ምን እያለኝ እንዳለ ለመረዳት የተወሰነ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር። ያኔ ገና የ11 ዓመት ልጅ ነበርኩ።”—ሊያ

ከላይ ያለው ምሳሌ እንደሚያሳየው ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ስለ ጾታ ግንኙነት ይሰማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ” እና ሰዎች “ራሳቸውን የማይገዙ . . . ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” እንደሚሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3, 4) ከአንድ ሰው ጋር ‘አብሮ መውጣትን’ በተመለከተ በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረበው ሐሳብ የዚህን ትንቢት እውነተኝነት ከሚያረጋግጡት በርካታ ምልክቶች አንዱ ነው።

ዛሬ ያለው ዓለም እናንተ ስታድጉ ከነበረበት ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው። ይሁን እንጂ ችግሮቹ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተመሳሳይነት አላቸው። ስለዚህ በልጆቻችሁ ላይ የሚደርሰውን መጥፎ ተጽዕኖ በማየት ብቻ መሸበር ወይም መደናገጥ አይኖርባችሁም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ ከዛሬ 2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች የሰጠውን “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ” የሚለውን ማሳሰቢያ እንዲከተሉ ልጆቻችሁን ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። (ኤፌሶን 6:11) በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች በዙሪያቸው ጎጂ የሆነ ተጽዕኖ ቢኖርም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚጥሩ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ልጆቻችሁ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

አንዱ መንገድ፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ የሰፈሩትን ሐሳቦች መሠረት በማድረግ ከልጆቻችሁ ጋር መወያየት ነው። “በተጨማሪም . . . አንብቡ” በሚለው ክፍል ውስጥ ትኩረት የሚስቡ ጥቅሶች ቀርበዋል። ከእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ አንዳንዶቹ፣ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ በመቁረጣቸው ምክንያት በረከት ስላገኙ ሰዎች የሚተርኩ ወይም የአምላክን ሕግጋት ቸል በማለታቸው የተነሳ መጥፎ ነገሮች ስለደረሱባቸው ሰዎች የሚናገሩ እውነተኛ ታሪኮችን የያዙ ናቸው። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙት ሌሎቹ ጥቅሶች ደግሞ እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ከአምላክ ሕግጋት ጋር ተስማምታችሁ መኖራችሁ ታላቅ መብት መሆኑን ልጆቻችሁ እንዲገነዘቡ የሚያስችሏቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዘዋል። ታዲያ ይህን ርዕስ አሁኑኑ አብራችሁ ለመከለስ የሚያስችል ዝግጅት ለምን አታደርጉም?

የአምላክን ሕግጋት ተግባራዊ ማድረግ ምንጊዜም ቢሆን ይጠቅመናል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ሕግጋቱን ቸል ማለት ግን ከፍተኛ ሐዘን ማስከተሉ አይቀርም። በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመቅረጽ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንዲባርክላችሁ የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች ምኞታችን ነው።—ዘዳግም 6:6, 7

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምንም ዓይነት ከእነርሱ ጋር የጾታ ግንኙነት እንደማትፈጽሙ ግልጽ ልታደርጉላቸው ይገባል