በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አይበገሬው የውኃ ውስጥ ድብ

አይበገሬው የውኃ ውስጥ ድብ

አይበገሬው የውኃ ውስጥ ድብ

ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

▪ በምድር ዙሪያ እርጥበት አዘል በሆኑ ቦታዎች ማለትም በድንጋይ ሽበት ላይ፣ በበረዶ ውስጥ፣ በረግረጋማ ቦታ፣ በፍል ውኃ፣ በሐይቅ ወይም በውቅያኖስ ምናልባትም በጓሮህ ውስጥ ብትፈልገው ችግር ቻይ ከሆኑት ጥቃቅን ፍጥረታት አንዱ የሆነውን ይህን የውኃ ውስጥ ድብ ማግኘትህ አይቀርም። በጣም ደቃቃ ከመሆኑ የተነሳ ለማየት አስቸጋሪ የሆነው ይህ ነፍሳት አካሉ አራት ቦታ የተከፋፈለ ሲሆን ጠንካራ ሽፋን አለው፤ እንዲሁም ጫፎቻቸው ላይ ጥፍር መሰል ነገሮች ያሉባቸው ስምንት እግሮች አሉት። ቅርጹና አረማመዱ ቀርፋፋ ድብ ያስመስለዋል፤ የውኃ ውስጥ ድብ ተብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው።

ይህ ድብ መሰል ፍጥረት ሲሄድ ቀርፋፋ ከመሆኑም ሌላ በመቶ የሚቆጠሩ ዝርያዎች አሉት። እንስቶቹ በአንድ ጊዜ ከ1 እስከ 30 እንቁላሎችን ይጥላሉ። ጥቂት እፍኝ በሚሆን እርጥብ አፈር ወይም አሸዋ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የውኃ ውስጥ ድቦችን ማግኘት ይቻላል። እነዚህ ፍጥረታት በተለይ ጣሪያ ላይ በሚበቅሉ የእንጨት ሽበቶች ላይ አይጠፉም።

የውኃ ውስጥ ድቦች በጣም ቀዝቃዛ ወይም ሞቃት በሆኑ ቦታዎች ላይ መኖር ይችላሉ። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ለናሙና የተወሰዱ አንዳንድ የውኃ ውስጥ ድቦች ምንም አየር በሌለበት ቦታ ለስምንት ቀናት ከቆዩ በኋላ በቤት ውስጥ የሙቀት መጠን ሂልየም የተባለ ጋዝ ባለበት ቦታ ለሦስት ቀናት እንዲቀመጡ ተደረገ። ከዚያም ለበርካታ ሰዓታት ከዜሮ በታች 272 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሆነ ቅዝቃዜ ውስጥ እንዲቆዩ ተደረገ፤ ይህ ሁሉ ሆኖም ወደ ትክክለኛው የቤት ውስጥ የሙቀት መጠን ሲዛወሩ እንደገና ነፍስ ዘሩ።” ሰውን ሊገድል ከሚችለው ብዙ መቶ እጥፍ ለሆነ የኤክስ ሬይ ጨረር ቢጋለጡ እንኳ ምንም ዓይነት ጉዳት አይደርስባቸውም። ከሁኔታዎቹ አንጻር ሲታይ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን በሕዋ ላይ መኖር ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል!

ለዚህ ሁሉ ምስጢሩ እነዚህ ነፍሳት የሞቱ ያህል ሆነው በሕይወት መቆየት መቻላቸው ነው፤ በዚህ ወቅት ላይ በሰውነታቸው ውስጥ ምግብ ተፈጭቶ ወደ ኃይል የሚቀየርበት ሒደት ቀንሶ ከመደበኛው በመውረድ ከ0.01 በመቶ በታች ይሆናል። እነዚህ ፍጥረታት ከሞት በማይተናነስ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለመቆየት እግሮቻቸውን ሰውነታቸው ውስጥ ያስገቡና ከሰውነታቸው የወጣውን ውኃ ልዩ በሆነ የስኳር ዓይነት ይተኩታል፤ ከዚያም ጥቅልል ብለው በሰም ወደተሸፈነ በጣም ትንሽ ኳስነት ይቀየራሉ። ይህ ሁኔታ ታን ተብሎ ይጠራል። ሁኔታው ሲስተካከልና እርጥበት ሲያገኙ ከትንሽ ደቂቃ አንስቶ እስከ ጥቂት ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ወትሮው ሁኔታቸው በመመለስ ዳግም መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። በአንድ ወቅት ለ100 ዓመታት ያህል እንቅስቃሴያቸውን በሙሉ ለጊዜው አቁመው የነበሩ የውኃ ውስጥ ድቦች ያለምንም እክል በድጋሚ ሕይወት ዘርተዋል!

አዎን፣ እነዚህ ጥቃቅን “የሚሳቡ ፍጥረታት” አስደናቂ በሆነ መንገድ ይሖዋን ያወድሳሉ።—መዝሙር 148:10, 13

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Diane Nelson/Visuals Unlimited