በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢንተርኔት ተጠቃሚ ወጣቶች!

ኢንተርኔት ተጠቃሚ ወጣቶች!

ኢንተርኔት ተጠቃሚ ወጣቶች!

ልጅህ በውድቅት ሌሊት ብቻውን ጎዳና ላይ ሲዞር ይታይህ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጅህ አንተ ሳታውቅ በገዛ ቤትህ ውስጥ ግብዣ ቢያዘጋጅ ምን እንደሚሰማህ እስቲ አስብ።

ወንድ ወይም ሴት ልጅህ የቤትህን ቁልፍ አባዝተው ፍጹም ለማታውቃቸው ሰዎች ቢያድሉ ምን ይሰማሃል?

ልጅህ ኢንተርኔት የሚጠቀም ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት ለማመን የሚያዳግቱ የሚመስሉ ሁኔታዎች የማይከሰቱበት ምንም ምክንያት የለም። ሳይንስ ኒውስ የተባለ መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ኢንተርኔት አጫጭር መልእክቶችን ለመለዋወጥ ከሚያስችሉ ዘዴዎች አንስቶ ማኅበራዊ ግንኙነት ለማድረግ እስከሚረዱ ድረ ገጾች ድረስ ቁጥራቸውም ሆነ ዓይነታቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ እየበዛ የመጣ የመገናኛ መስመሮች እንዲኖሩ አስችሏል።”

ወጣቶች የኢንተርኔት አጠቃቀምን ለመልመድ ጊዜ አይወስድባቸውም። በ2004፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚኖሩና ከ12 እስከ 17 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 10 ወጣቶች መካከል 9 ያህሉ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኘው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ነበሩ።

ኢንተርኔት ጠቃሚ መሆኑን የማይቀበል ሰው የለም ለማለት ይቻላል። ይሁንና ሁሉም ሰው ኢንተርኔት ጎጂ ጎን እንዳለው መገንዘብ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ወጣቶች ያለምንም ቁጥጥር በኢንተርኔት በመጠቀም በውድቅት ሌሊት ብቻቸውን ጎዳና ላይ ከመንቀዋለል የማይተናነስ ድርጊት ይፈጽማሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ በኢንተርኔት አማካኝነት እናንተም ሆናችሁ ልጃችሁ ቤታችሁ እንዲመጡ ከማትፈልጓቸው ሰዎች ጋር ማኅበራዊ ግንኙነት መሥርተዋል።

ብስለት የጎደላቸው አንዳንድ ወጣቶች ሌላ ሰው ማወቅ የማይገባውን የግል ጉዳዮቻቸውን፣ አመለካከታቸውን ብሎም ፎቶአቸውን በኢንተርኔት ድረ ገጾች ላይ አውጥተዋል። የኒው ዮርክ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጃንግ ያን ወጣቶች “ብዙውን ጊዜ መረጃዎቹ የጾታ ጥቃት ፈጻሚዎችን ጨምሮ ምን ያህል ሰዎች እጅ ሊገቡ እንደሚችሉ አያስተውሉም” በማለት ተናግረዋል።

እስቲ ብዙ ወጣቶች በኢንተርኔት አማካኝነት ምን እንደሚያደርጉ ጠለቅ ብለን እንመርምር። እንዲህ ማድረጋችን በልጆቻችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር እንድናስተውል፣ ልጆቻችን ምን እንደሚፈልጉ እንድናውቅና ይህን ፍላጎታቸውን እንዲያረኩ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያን ወጣቶች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት እንዲያጓድሉ የሚደርስባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5