ወጣቶች ፍላጎቶቻቸውን እንዲያሟሉ መርዳት
ወጣቶች ፍላጎቶቻቸውን እንዲያሟሉ መርዳት
ወጣቶች ስለ ግባቸው፣ ስለ ወደፊት ሕይወታቸውና ስላጋጠማቸው ችግር የሚያወያዩት ሰው ይፈልጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ጥሩ ጓደኞች እንዲኖሯቸው ይሻሉ። እንዲሁም በዕድሜ እየበሰሉ ሲሄዱ በራሳቸው ማንነት መታወቅ ይፈልጋሉ። ወላጆች ልጆቻቸው እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት እንዲችሉ የሚረዷቸው ከሆነ በኢንተርኔት አማካኝነት ሊመሠረቱ የሚችሉትን ጨምሮ ከማንኛውም ጎጂ ጓደኝነት እንዲጠበቁ ይረዷቸዋል።
▪ ወጣቶች ከሌሎች ጋር ማውራት ይፈልጋሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ስሜታቸውን አውጥተው ለሌሎች በመናገር ረገድ ቁጥቦች ወይም ድብቅ ይመስሉ ይሆናል። ሆኖም ከባድም ሆነ ቀላል የሚመስሉ ጉዳዮችን ከእናንተ ከወላጆቻቸው ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። ጥያቄው ‘እናንተ ለማዳመጥ ዝግጁዎችና ፈቃደኞች ናችሁ?’ የሚለው ነው።—ያዕቆብ 1:19
የኑሮው ውጣ ውረድ ከልጆቻችሁ ጋር ለመጨዋወት የሚያስችላችሁን ውድ አጋጣሚ እንዲያሳጣችሁ መፍቀድ አይኖርባችሁም። የኑሮው ጫና ጊዜ ካሳጣችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እውቁ’ ሲል የሰጠውን ግሩም ምክር ቆም ብላችሁ ልታስቡበት ይገባል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ታዲያ ከልጆቻችሁ የበለጠ ምን አስፈላጊ ነገር ሊኖር ይችላል?
ወጣቶች ከወላጆቻቸው ይልቅ ከዕድሜ እኩዮቻቸው ምክር መጠየቅ ይቀናቸዋል ብላችሁ ለመደምደም አትቸኩሉ። ከ6ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ ከ17,000 የሚበልጡ ተማሪዎች ላይ አንድ ጥናት ተደርጎ ነበር፤ በዚህ ጥናት ላይ ተማሪዎቹ ወላጆቻቸው፣ ጓደኞቻቸው፣ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች፣ መገናኛ ብዙኃንና አስተማሪዎቻቸው ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩባቸው ለማሳየት ከ0 እስከ 5 ያለውን ነጥብ እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር። ዜሮ የሚል ነጥብ ከሰጡ ምንም ተጽዕኖ አያሳድሩብኝም ማለት ሲሆን 5 ከሰጡ ደግሞ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብኛል ማለት ነው። ከተማሪዎቹ ውስጥ ግማሽ ያህሉ 5 ነጥብ የሰጡት ለወላጆቻቸው ነው።
ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁ በሕይወታቸው ውስጥ ጥሩ አመለካከትና ግብ እንዲኖራቸው በመርዳት ረገድ ቁልፍ ሚና ልትጫወቱ ትችላላችሁ። አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “የምትናገሩት ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ማለት ባይሆንም ከእነርሱ ጋር የሐሳብ ግንኙነት የማታደርጉ ከሆነ ልባቸውን ፈጽሞ ልታገኙት አትችሉም።”
▪ ወጣቶች ጓደኛ ይፈልጋሉ። አንዲት የ15 ዓመት ወጣት “ወላጆች ልጆቻቸው በኢንተርኔት አማካኝነት ከእነማን ጋር እንደሚገናኙ አያውቁም አሊያም ለማወቅ አይፈልጉም” ብላለች። ዛሬ፣ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው የጓደኛ ምርጫ ግዴለሽ የሚሆኑበት ጊዜ አይደለም። ልጆቻችሁ በኢንተርኔት አማካኝነትም ሆነ በአካል ከእነማን ጋር ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ታውቃላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ ) በእርግጥም የልጆቻችሁ ጓደኞች እነማን እንደሆኑ ለመከታተል የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አላችሁ። 15:33
ልጆችን መንከባከብ ሲባል ጎጂ ከሆኑ ተጽዕኖዎች እንዲጠበቁ ማድረግ ማለት ብቻ አይደለም። ልጆች ጥሩ ጓደኞች ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) በመሆኑም ልጆቻችሁ ፈጣሪያቸውን በማሰብ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ወጣቶችን ጨምሮ መልካም ጓደኞች እንዲያፈሩ ልትረዷቸው ይገባል።—መክብብ 12:1
ይሖዋ አምላክ ወዳጆቹ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች ያወጣቸውን ብቃቶች እንዲያሟሉ ይፈልጋል። እኛም እርሱን መምሰል ይኖርብናል። (መዝሙር 15:1-5፤ ኤፌሶን 5:1) በእርግጥም፣ ልጆቻችሁ እንዲያዳብሩት ልታስተምሯቸው ከሚገባችሁ ችሎታዎች መካከል አንዱ ጥሩ ጓደኛ የመምረጥ ችሎታ ነው። ለዚህ ደግሞ እናንተ ራሳችሁ በቃልም ሆነ በተግባር ጥሩ ምሳሌ መሆን አለባችሁ።—2 ተሰሎንቄ 3:6, 7
▪ ወጣቶች በራሳቸው ማንነት መታወቅ ይፈልጋሉ። የእድገት አንዱና ዋነኛው ገጽታ አንድን ልጅ ከሌሎች ልዩ የሚያደርጉት ባሕርያት እየጎሉ መምጣታቸው ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ‘አንድ ሕፃን ማንነቱ ከአድራጎቱ ይታወቃል’ ይላል። (ምሳሌ 20:11 በዊልያም ቤክ የተዘጋጀው ዘ ሆሊ ባይብል ኢን ዘ ላንግዊጅ ኦቭ ቱዴይ) ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን ልታከናውኗቸው ከሚገቧችሁ ተግባራት መካከል አንዱ ትክክለኛውን መሠረታዊ ሥርዓት በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ መቅረጽ ነው።—ዘዳግም 6:6, 7
በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸው ተገቢ አለባበስ ምን ማለት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ለማድረግ በየዕለቱ ልብስ እየመረጡ ያለብሷቸዋል። ነገር ግን አንድን በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኝ የ30 ዓመት ጎልማሳ ወላጆቹ ያለብሱታል ብለህ ትጠብቃለህ? እንዲህ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ልብስን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ‘አዲሱን ሰው ልበሱ’ በማለት ያሳስበናል። ይህም ማለት የክርስቶስን ዓይነት ባሕርይ ማንጸባረቅ ማለት ነው። (ቈላስይስ 3:10) እናንተም ለልጆቻችሁ ፍቅራዊ ምክርና “ተግሣጽ” በመስጠት አዲሱን ሰው እንዲለብሱ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። (ኤፌሶን 6:4) እነርሱም ሲያድጉና ራሳቸውን ሲችሉ ‘አዲሱ ሰው’ በእርግጥም የሚያምርና ማራኪ “ልብስ” መሆኑን በመገንዘብ እርሱን ለመልበስ መምረጣቸው አይቀርም።—ዘዳግም 30:19, 20
እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ:- ‘ልጆቼ ከአምላክ ቃል ስላገኟቸው ውድ ትምህርቶች በእርግጥ ምን ይሰማቸዋል? “ጤናማ አስተሳሰብ” እንዲኖራቸው እንዴት ልረዳቸው እችላለሁ?’ (ቲቶ 2:12 NW) ግብህ ለይስሙላ ታዛዥ መስለው የሚታዩ ልጆችን ማፍራት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አንዳንድ ልጆች የታዘዙትን ሁሉ በመሥራት ረገድ የተዋጣላቸው ይመስላሉ፤ ጥያቄ አያበዙም፣ አይከራከሩም ወይም ተቃውሞ አያሰሙም። ነገር ግን ዛሬ ያዘዝከውን ሁሉ እሺ ብሎ የሚፈጽም ልጅ ምናልባት ነገ ዓለም እንዲያደርግ የሚፈልግበትን ሁሉ እሺ ብሎ ሊታዘዝ ይችላል። በመሆኑም ልጆቻችሁ ‘አእምሯቸውን’ እንዲጠቀሙበት አሠልጥኗቸው። (ሮሜ 12:1) የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለምን ትክክል እንደሆኑና ለሁላችንም ጠቃሚ የሆኑት እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉም እርዷቸው።—ኢሳይያስ 48:17, 18
እውነት ነው፣ ወጣቶች ፍላጎቶቻቸውን እንዲያሟሉ መርዳት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ይሁንና የሚያስገኘው ውጤት በእጅጉ የሚክስ ነው! ልጆቻችሁ እናንተ ባስተማራችኋቸው ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሲመሩ ስታዩ ከልባችሁ እውነትም “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” ለማለት ትገፋፋላችሁ።—መዝሙር 127:3
[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ልጆቻችሁ ጥሩ ክርስቲያን ጓደኞች እንዲመርጡ እርዷቸው