ሰዎች ሁልጊዜ ከሌሎች ጋር የሚያወዳድሩኝ ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ሰዎች ሁልጊዜ ከሌሎች ጋር የሚያወዳድሩኝ ለምንድን ነው?
“ወላጆቼ ወይም አስተማሪዎቼ ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩኝ በጣም እበሳጫለሁ።”—ሚያ *
“ቀድሞውንም እንደ እገሌ በሆንኩ ብዬ ስለምመኝ ሰዎች ከዚያ ሰው ጋር ሲያወዳድሩኝ ብቃት እንደሌለኝ ሆኖ ይሰማኛል።”—ኤፕርል
በትምህርት ቤት አስተማሪህ፣ አብሮህ እንደሚማረው ልጅ በሒሳብ ትምህርት ጎበዝ ባለመሆንህ ይነቅፍሃል። በቤት ውስጥ ደግሞ ወላጆችህ እንደ እህትህ ንጹሕ ባለመሆንህ ይቆጡሃል። አንድ ሰው “እናትሽ በአንቺ ዕድሜ በጣም ቆንጆ ነበረች!” ቢልሽ፣ ግለሰቡ አስቀያሚ እንደሆንሽ አድርጎ እንደሚያስብ ስለሚሰማሽ ንግግሩ ይጎዳሻል። እንደነዚህ ያሉ ሐሳቦች “ሰዎች እኔን በእኔነቴ መቀበል አይችሉም? ሁልጊዜ ከሌላ ሰው ጋር የሚያወዳድሩኝ ለምንድን ነው?” እንድትሉ ያደርጓችሁ ይሆናል።
ሰዎች ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩን ስሜታችን የሚጎዳው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስገኘው ጥቅም ይኖራል? ሰዎች ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ከሌሎች ጋር ስንወዳደር ስሜታችን የሚጎዳው ለምንድን ነው?
ሰዎች ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩን የምንጎዳበት አንዱ ምክንያት ደስ የማንሰኝበት ጉዳይ ስለሚነሳ ነው። በሌላ አባባል ሰዎች የሚነግሩህ አንተም ስለራስህ ታስበው የነበረውን ነገር ሊሆን ስለሚችል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ቤኪ “በትምህርት ቤት ውስጥ ታዋቂ የሆኑትን ልጆች ስመለከት ‘እንደ እነርሱ ብሆን ኖሮ ብዙ ሰዎች ይወዱኝ ነበር’ ብዬ አስባለሁ” በማለት የሚሰማትን ተናግራለች።
እንዲህ ዓይነቱ በራስ ያለመተማመን ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርገው ምንድን ነው? በአካልህ፣ በስሜትህና በአእምሮህ ላይ ምን ለውጥ እየተከናወነ እንዳለ አስብ። ሰውነትህ በፍጥነት እየተለወጠ ይሆናል። ከወላጆችህ ጋር ያለህ ግንኙነትም ውጥረት የሰፈነበት ሊሆን ይችላል። ከዚህም ሌላ ለተቃራኒ ጾታ ያለህ አመለካከት በጣም ተለውጦ ይሆናል። በመሆኑም ‘እድገቴ ጤናማ ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት የምትችልበት ብቸኛው መንገድ እንደ አንተ ዓይነት ለውጥ እያደረጉ ካሉ ሌሎች ወጣቶች ጋር ራስህን ማወዳደር እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ይህ ግን ትክክል ወዳልሆነ መደምደሚያ ሊያደርስህ ይችላል! ራስህን ከሌሎች ጋር ስታወዳድር እነዚህ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ለውጦች ከአንተ በተሻለ መንገድ እየተወጧቸው እንዳሉ ከተሰማህ በራስ ያለመተማመን ስሜት ያድርብሃል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለህ ደግሞ አንድ ትልቅ ሰው፣ ‘ለምን እንደ እገሌ አትሆንም? ብሎ ሲጠይቅህ የፈራኸው ነገር እንደደረሰና እውነትም ችግር እንዳለብህ ሊሰማህ ይችላል!
ኤፕርል የተባለች ወጣት ከሌሎች ጋር ስንወዳደር
ስሜታችን የሚጎዳበትን ሌላ ምክንያት ስትገልጽ “ሰዎች ከሌላ ሰው፣ በተለይ ደግሞ በጣም ከምትቀርቡት ግለሰብ ጋር የሚያወዳድሯችሁ ከሆነ እንድትቀኑና እንድትናደዱ ሊያደርጓችሁ ይችላሉ” ብላለች። ሚያ ወላጆቿና አስተማሪዎቿ ሁልጊዜ ከታላቅ እህቷ ጋር እንደሚያወዳድሯት ስለሚሰማት እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚፈጥረውን ስሜት ታውቀዋለች። “እርሷ በእኔ ዕድሜ በነበረችበት ጊዜ ያከናወነቻቸውን ነገሮች ይነግሩኛል” ብላለች። ታዲያ ይህ በሚያ ላይ ምን ስሜት አሳደረ? “ከእህቴ ጋር ውድድር እንደገጠምኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እናደድባታለሁ” ብላለች።በእርግጥም ሰዎችን ማወዳደር ጎጂ ሊሆን ይችላል። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ በሐዋርያቱ መካከል የጦፈ “ክርክር ተነሣ።” ምክንያቱ ምን ነበር? አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር ራሳቸውን በማወዳደር “ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ” እየተከራከሩ ነበር። (ሉቃስ 22:24) ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ከሌሎች ጋር መወዳደር ጎጂ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ። ይሁን እንጂ ሰዎችን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ሁልጊዜ ጎጂ ነው?
ከሌሎች ጋር መወዳደር የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን ወጣቱን ዳንኤልንና ሦስት ዕብራውያን ጓደኞቹን እንመልከት። የባቢሎን ንጉሥ ለእነዚህ ወጣቶች ያቀረበላቸው ምግብ በአምላክ ሕግ ውስጥ የተከለከለ ስለነበር ለመብላት ፈቃደኞች አልነበሩም። (ዘሌዋውያን 11:4-8) ዳንኤል፣ እነርሱን ለመንከባከብ የተሾመው መጋቢ ሊረዳቸው ፈቃደኛ እንዲሆን ለማሳመን ሲል እርሱንና ሦስቱን ጓደኞቹን እንዲፈትናቸው ሐሳብ አቀረበ። በአምላክ ሕግ መሠረት ተቀባይነት ያላቸውን ምግቦች ለአሥር ቀናት ያህል ከተመገቡ በኋላ መጋቢው እነዚህን ዕብራውያን በንጉሡ ቤት ካሉት ሌሎች ወጣቶች ጋር እንዲያወዳድራቸው ጠየቀው። ውጤቱስ ምን ሆነ?
መጽሐፍ ቅዱስ “ከዐሥር ቀን በኋላም [ዕብራውያኑ] የንጉሡን መብል ከበሉት ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ ጤናማዎችና ሰውነታቸው የወፈረ ሆነው ተገኙ” ይላል። (ዳንኤል 1:6-16) ዳንኤልና ጓደኞቹ የተሻሉ ሆነው የተገኙት በተፈጥሯቸው ከሌሎቹ የሚበልጡ ስለነበሩ እንዳልሆነ ልብ በል። የእነዚህ ዕብራውያን ወጣቶች ሰውነት እንዲያምር አስተዋጽኦ ያደረገው ዋናው ነገር አምላክ ለሕዝቡ የሰጠውን ሕግ መታዘዛቸው ነው።
አንተስ ከእነዚህ ወጣቶች ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ አጋጥሞሃል? የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መመሪያዎች የምትከተል ከሆነ ከሌሎች ወጣቶች ለየት ብለህ መታየትህ አይቀርም። ከሌሎች የተለየህ መሆንህን የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ሊደነቁና ‘ሊሰድቡህ’ ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 4:3, 4) ሌሎች ግን የምታሳየው ጥሩ ምግባር የሚያፈራቸውን መልካም ውጤቶች ያስተውሉ ብሎም ስለ ይሖዋ ለመማር ይነሳሱ ይሆናል። (1 ጴጥሮስ 2:12) በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ከሌሎች ጋር መወዳደር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ከሌሎች ጋር መወዳደር ጠቃሚ የሚሆንበት ሌላም መንገድ አለ። ለአብነት ያህል፣ ራስህን ከእህቶችህ ወይም ከወንድሞችህ ጋር በማወዳደር በቤት ውስጥ መሥራት የሚገባህን ያህል እንደሠራህ ታስብ ይሆናል። ወላጆችህ ግን እንደ አንተ አይሰማቸው ይሆናል። ወላጆችህ አመለካከትህን ለማስተካከል ሲሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰን አንድ ግለሰብ እንደ ምሳሌ በመውሰድ ዝንባሌህንና ተግባርህን ከዚያ ሰው ጋር እንድታወዳድር ሊነግሩህ ይችላሉ።
ለምሳሌ ኢየሱስ፣ ጌታና መምህር ቢባልም የደቀ መዛሙርቱን እግር ለማጠብ ፈቃደኛ እንደነበረ ይጠቅሱልህ ይሆናል። (ዮሐንስ 13:12-15) ከዚያም ኢየሱስ የነበረው ዓይነት የትሕትናና የታታሪነት ዝንባሌ እንድታዳብር ሊያበረታቱህ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስም ወጣት አረጋዊ ሳይል ክርስቲያኖች በአጠቃላይ ሁልጊዜ ራሳቸውን ከክርስቶስ ጋር በማወዳደር ‘የእርሱን ፈለግ ለመከተል’ እንዲጥሩ ያበረታታል። (1 ጴጥሮስ 2:21) በዚህ መንገድ ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር፣ ትሑቶች እንድንሆን እንዲሁም ይሖዋን ይበልጥ የሚያስደስተውን ባሕርይ እንድናዳብር ይረዳናል።
አሉታዊ በሆነ መልኩ ከሌሎች ጋር መወዳደር የሚያሳድረውን ስሜት መቋቋም
ሰዎች ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ወይም ከእኩዮችህ ጋር በማወዳደር ሲወቅሱህ ልትበሳጭና ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። እንዲህ ያለውን ሁኔታ መቋቋም የምትችለው ምሳሌ 19:11 የ1980 ትርጉም) ማስተዋል እንዴት ሊረዳህ ይችላል? ለአንተ ባይመስልህም፣ ወላጆችህ ወይም አስተማሪዎችህ ከሌሎች ጋር የሚያወዳድሩህ ስለ አንተ ከልባቸው ስለሚያስቡ ነው። ካቲ እንዲህ ብላለች:- “አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ሲያወዳድረኝ ‘እኔን ለመርዳት እየሞከረ ያለው እንዴት ነው?’ በማለት ራሴን እጠይቃለሁ።” ካቲ፣ ሰዎች የሚሰነዝሩትን ሐሳብ አዎንታዊ በሆነ መንገድ መመልከቷ ተስፋ እንዳትቆርጥ ወይም እንዳትበሳጭ እንደሚረዳት ተገንዝባለች።
እንዴት ነው? ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የቍጣን ስሜት መቆጣጠር አስተዋይነት ነው” ብሏል። (ይሁን እንጂ ሰዎች ሁልጊዜ ከሌሎች ጋር እንደሚያወዳድሩህ የሚሰማህ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ለምሳሌ ወላጆችህ ከእህትህ ወይም ከወንድምህ ጋር አሉታዊ በሆነ መልኩ ሁልጊዜ እንደሚያወዳድሩህ ይሰማህ ይሆናል። ወላጆችህ እንዲህ ሲያደርጉ ምን እንደሚሰማህ በአክብሮት ልትነግራቸው ትችላለህ። ወላጆችህ አንተን ከሌሎች ጋር ማወዳደራቸው የሚያሳድርብህን መጥፎ ስሜት አላስተዋሉ ይሆናል።
ሆኖም “ለመናገርም” ሆነ ‘ዝም ለማለት ጊዜ’ እንዳለው አስታውስ። (መክብብ 3:7) ወላጆችህ ወይም ሌሎች ሰዎች አሉታዊ በሆነ መልኩ ሲያወዳድሩህ በንዴት ገንፍለህ ከመናገር ይልቅ ከተረጋጋህ በኋላ ሐሳብህን ግለጽላቸው። እንዲህ ካደረግህ ሐሳብህ ይበልጥ ኃይል ይኖረዋል።—ምሳሌ 16:23
አብዛኛውን ጊዜ ጠንካራ ጎንህ ላይ የምታተኩር ከሆነ ሰዎች አሉታዊ በሆነ መልኩ ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩህ ብዙም ላትጎዳ ትችላለህ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን “ወጣትነትህን ማንም አይናቅ” ብሎት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 4:12) ጢሞቴዎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል በተሾመበት ወቅት ከሌሎቹ አንጻር ሲታይ ወጣት ነበር። በመሆኑም አንዳንዶች ጢሞቴዎስን በዕድሜ ከሚበልጡትና የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሌሎች ወንዶች ጋር በማወዳደር ነቅፈውት ሊሆን ይችላል። ሆኖም እንደነዚህ ያሉት ነቀፌታዎች መሠረት የሌላቸው ነበሩ። ጢሞቴዎስ ወጣት ቢሆንም ከጳውሎስ ጋር በመጓዙ ብዙ ተሞክሮዎችን አካብቷል። የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚችልም ያውቅ ነበር። ከዚህም በላይ ጢሞቴዎስ ለመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ከልቡ ያስብላቸው ነበር።—1 ቆሮንቶስ 4:17፤ ፊልጵስዩስ 2:19, 20
ስለዚህ በሌላ ጊዜ አንድ ሰው አሉታዊ በሆነ መልኩ ከሌሎች ጋር ሲያወዳድርህ ‘ይህ ነቀፌታ መሠረት ያለው ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ነቀፌታው በተወሰነ መጠንም ቢሆን እውነት ከሆነ ከተሰጠህ ሐሳብ ትምህርት ለማግኘት ጥረት አድርግ። ይሁን እንጂ “ለምን እንደ ወንድምህ አትሆንም?” እንደሚል ዓይነት ማስተካከል ያለብህን ነገር ለይቶ የማይጠቅስ ነቀፌታ ከሆነ ሁኔታውን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመመልከት ጥረት አድርግ። ከተሰጠህ ሐሳብ ጠቃሚ ትምህርት ለማግኘት ጥረት አድርግ።
ይሖዋ አምላክ የአንተን ማንነት የሚለካው ፍጹም ካልሆኑ ሌሎች ሰዎች ጋር በማወዳደር አይደለም። (ገላትያ 6:4) ውጪያዊ መልክህን ሳይሆን ውስጣዊ ማንነትህን በመመልከት ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ ይረዳል። (1 ሳሙኤል 16:7) በእርግጥም ይሖዋ ማንነትህን ብቻ ሳይሆን ምን ዓይነት ሰው ለመሆን እየጣርክ እንዳለህም ይመለከታል። (ዕብራውያን 4:12, 13) ስህተት ልትሠራ እንደምትችል ያውቃል፤ እንዲሁም ባሉህ መልካም ባሕርያት ላይ ያተኩራል። (መዝሙር 130:3, 4) ይህንን ሐቅ ማወቅህ ሰዎች ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩህ የሚሰማህን ስሜት ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል።
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚለው ቋሚ አምድ ሥር የወጡ ሌሎች ርዕሶችንም ማግኘት ይቻላል
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ ሰዎች ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩህ የምትበሳጨው ምን ዓይነት ሐሳብ ሲሰነዝሩ ነው?
▪ ወላጆችህ ሁልጊዜ ከሌሎች ጋር የሚያወዳድሩህ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“አንድ ሰው፣ ‘እንደ እገሌ መሆን አለብሽ’ በማለት የሌላ ሰው ስም እየጠቀሰ ምክር ከሚሰጠኝ ይልቅ መጀመሪያ ላይ መልካም ባሕርያቶቼን ካጎላ በኋላ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ያሉብኝን ድክመቶች ቢነግረኝ እመርጣለሁ።”—ናታሊ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች ከሌሎች ጋር ሲያወዳድሩህ ምን እንደሚሰማህ በአክብሮት ልትነግራቸው ትችላለህ