ከሥነ ጥበብ ይበልጥ ዘለቄታ ያለው ነገር
ከሥነ ጥበብ ይበልጥ ዘለቄታ ያለው ነገር
ራኬል ኮኢቪስቶ እንደተናገረችው
በ1950፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለሞቱ ሰዎች ክብር ሊሠራ የታሰበውን የመታሰቢያ ሐውልት አስመልክቶ ያቀረብኩት የመወዳደሪያ ሐሳብ አገር አቀፍ ውድድሩን አሸነፈ። ይሁንና ከአንድ ዓመት በኋላ ከጥቁር ድንጋይ የሠራሁት ግዙፍ የመታሰቢያ ሐውልት ፊንላንድ በምትገኘው ቱሱላ ከተማ ውስጥ በልዩ ሥነ ሥርዓት ሲመረቅ በበዓሉ ላይ አልተገኘሁም። ይህ የሆነበትን ምክንያት ልንገራችሁ።
የተወለድኩት በ1917 ሲሆን ቤተሰባችን በደቡባዊ ፊንላንድ በሚገኝ ገጠራማ መንደር ውስጥ ይኖር ነበር። ከዚህ ቤተሰብ ስምንት ልጆች መካከል እኔ የመጨረሻዋ ነኝ። ድኾች ብንሆም ደስተኛና የተረጋጋሁ ነበርኩ። ወላጆቼ ምክንያታዊና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ እንድንሰጥ አስተምረውናል። እንዲያውም ቤተሰባችን አባቴ ለገዛው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ግምት ነበረው።
ልጅ እያለሁ በእንጨት ትንንሽ ሐውልቶችን እሠራ ነበር። በጣም ጥሩ ተሰጥኦ ስለነበረኝ ዘመዶቻችን ሥነ ጥበብ እንድማር አበረታቱኝ። ከጊዜ በኋላ ሄልሲንኪ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ሥነ ጥበብ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ለመማር ያቀረብኩት ማመልከቻ ተቀባይነት አገኘ። ያደግሁት ገጠር ስለነበር የፊንላንድ ሥነ ጥበብ ማዕከል በሆነው በዚህ ትምህርት ቤት የማየው ነገር ሁሉ በጣም ያስደንቀኝ ነበር። በ1947 ስመረቅ በዚህ ዓለም ወስጥ አንድ ዘላቂ ነገር መተው እንደምችል አስቤ ነበር።
ለውጥ ያደረግሁበት ጊዜ
ከጊዜ በኋላ ግን በግቦቼ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አደረግሁ። አንድ ቀን እህቴ አውኔ ወደ እኔ መጥታ “እውነትን አገኘሁ!” በማለት በአድናቆት ነገረችኝ። ይህን ያለችው “አምላክ እውነተኛ ይሁን” የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ካነበበች በኋላ ሲሆን እኔ ግን ብዙም አልተደነቅሁም ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አብራኝ የምትማር አንዲት ልጅ ይህንን መጽሐፍ ይዛ አየሁ። መጽሐፉን ሳጣጥልባት “አትሳቂ! ይህ መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንድትችዪ ይረዳሻል” በማለት ተቆጣችኝ። መጽሐፉን ከተቀበልኳት በኋላ ምንም ሳላቋርጥ ከዳር እስከ ዳር አነበብኩት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመጽሐፉ ስቄ አላውቅም፤ እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት እውነት መሆኑን አመንኩ። እንዲሁም ይሖዋ አምላክ ከሥነ ጥበብ ላገኘው የማልችለውን ነገር ይኸውም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ከፊቴ እንደዘረጋልኝ ተገነዘብኩ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኘሁበት ወቅት ስብሰባቸው ላይ እንድገኝ አልጋበዙኝም ነበር፤ በመሆኑም ስብሰባዎቹ የተዘጋጁት ለሃይማኖቱ አባላት ብቻ እንደሆነ ተሰማኝ። ስለዚህ እኔው ራሴ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እችል እንደሆነ ጠየቅኳቸው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሁሉም ሰው መገኘት እንደሚችል ሳውቅ በጣም ተደሰትኩ። በስብሰባዎች ላይ መገኘቴ እምነቴን
ስላጠናከረልኝ ራሴን ለይሖዋ ለመወሰን ቆረጥኩ። ከዚያም ኅዳር 19, 1950 በመጠመቅ ይህን ውሳኔዬን ለሕዝብ ይፋ አደረግሁ። በጣም ደስ የሚለው እህቴም በዚሁ ዕለት የተጠመቀች ሲሆን ከጊዜ በኋላ አራቱ እህቶቼና ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።ምን ዓይነት የሥራ መስክ መምረጥ ይኖርብኛል?
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ እያለሁ በሥነ ጥበቡ መስክ ጥሩ እድገት እያሳየሁ ነበር። ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ በኋላ ለአንድ የቅርጻ ቅርጽ ፕሮፌሰር ረዳት በመሆን መሥራት ጀመርኩ። ከዚያም መግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለሞቱ ሰዎች የሚሠራውን የመታሰቢያ ሐውልት በሚመለከት የተደረገውን አገር አቀፍ ውድድር አሸነፍኩ። ለዚህ ሥራ የሰጠሁት ርዕስ “ወጥቶ መቅረት” የሚል ነበር፤ ርዕሱ ለጦርነት ያለኝን የተስተካከለ አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። (ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 26:52) ከአምስት ሜትር የሚበልጥ ርዝመት ያለው ይህ ሐውልት ሲመረቅ በቦታው አልተገኘሁም ነበር፤ ምክንያቱም የምረቃው በዓል ብሔራዊ ስሜት የተንጸባረቀበት ሲሆን ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረተው እምነቴ ጋር ይጋጭ ነበር።
በሥነ ጥበብ መስክ ያለኝ ዝና እያደገ ሄዶ ታዋቂ በመሆኔ ምክንያት ከየአቅጣጫው ጥሩ ሥራዎች ይመጡልኝ ጀመር። ነገር ግን ቅድሚያ የምሰጣቸውን ነገሮች ማመዛዘን ጀመርኩ። ይህን ሥራዬን ብወደውም እንኳ ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ያለኝ ፍላጎት ይበልጥ ነበር። ከዚህም የተነሳ በ1953 አቅኚ (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን የሚጠሩበት ስም ነው) ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ።
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ይህንን ተሰጥኦዬን በደንብ እንዳልተጠቀምኩበት ይነግሩኝ ነበር። ነገር ግን በቅርጻ ቅርጽ ሥራ የማገኘው ማንኛውም ስኬት ጊዜያዊ እንደሆነ ተገንዝቤ ነበር። ከጥቁር ድንጋይ የተሠሩ ሐውልቶች እንኳ ከጊዜ በኋላ መፈረካከሳቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ አቅኚ ብሆን አብዛኛውን ጊዜዬን ሌሎች ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ እንዲያገኙ ለመርዳት ልጠቀምበት እችላለሁ! (ዮሐንስ 17:3) እርግጥ ቅርጻ ቅርጽ መሥራቴን እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ ማለት አይደለም። አልፎ አልፎ ራሴን ለማስደሰትና የምሠራቸውን ነገሮች በመሸጥ ወጪዎቼን ለመሸፈን ስል ትንንሽ ቅርጻ ቅርጾችን እሠራለሁ።
ወደ ገጠር ተዛወርኩ
በሄልሲንኪ ለአራት ዓመት በአቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ በ1957 የፊንላንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በደቡባዊ ኦስትሮቦትኒያ በምትገኘው ያላስያርቫይ በተባለች የገጠር ከተማ እንዳገለግል ጋበዘኝ። የተመደብኩት ቀደም ሲል እዚያው ስታገለግል ከቆየችው አሥራ ሰባት ዓመት ከምበልጣት አንጃ ኬቶ ከተባለች እህት ጋር ነበር። አንጃን ባላውቃትም እንኳ ምድቤን በደስታ ተቀብዬ ወደዚያ ሄድኩ። በዚያ አካባቢ ያለነው የይሖዋ ምሥክሮች እኔና እሷ ብቻ ስለነበርን አብዛኛውን ጊዜ አብረን እናገለግል ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የማንነጣጠል ጓደኛሞች ሆንን።
ለእኔ ወደ ያላስያርቫይ መሄድ ማለት ወደ ሥነ ጥበቡ ዓለም ከመምጣቴ ማለትም ከሃያ ዓመት በፊት ከነበርኩበት የገጠር ሕይወት ጋር ተመሳሳይ ወደሆነ ሕይወት መመለስ ማለት ነው። በተለይ የክረምቱ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ አንዳንዴ እስከ ወገባችን በሚደርስ የአመዳይ በረዶ ክምር ላይ ለመጓዝ እንገደዳለን። ምቹ ባልሆነ ከእንጨት የተሠራ አንድ ክፍል ቤት ውስጥ እንኖር ነበር። ውኃ የምንቀዳው በአቅራቢያችን ከሚገኝ ምንጭ ሲሆን አንዳንዴ ቀድተን ያመጣነው ውኃ በረዶ ተጋግሮበት ያድራል። ቢሆንም የሚያስፈልገንን ነገር አጥተን አናውቅም። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) በሥራ ተጠምደን ያሳለፍናቸው እነዚያ ዓመታት አስደሳች ነበሩ።
በረከት በሚያስገኝ ሥራ መጠመድ
በመጀመሪያ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ለእኛ ጥሩ አመለካከት ስላልነበራቸው ጥረታችን ያን ያህል ውጤት የሚያስገኝ አይመስልም ነበር። ሰዎች ስለ ሥራችን ጥሩ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለመርዳት ስንል በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን እና ዘ ሀፒነስ ኦቭ ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ እንደሚሉት ያሉ ፊልሞችን ለማሳየት ዝግጅት አደረግን። እነዚህ ፊልሞች ሰዎች ስለ እኛም ሆነ ስለ ድርጅታችን ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዲሁም ሥራችን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ እንዲያስተውሉ ረድተዋል። እነዚህን ፊልሞች ለማየት በርካታ ሰዎች ይሰበሰቡ ነበር።
በአንድ ወቅት ኤሮ ሙራይነን የተባለ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ውስጥ ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን የተባለውን ፊልም አሳይቶ ነበረ። አዳራሹ ጢም ብሎ ሞልቶ ስለነበር እንደምንም ብዬ አንደኛው ጥግ ላይ ቦታ አገኘሁ። ሁለቱንም እግሬን የማሳርፍበት ቦታ ስላልነበረ ግድግዳውን ተደግፌ በአንደኛው እግሬ ብቻ መቆም ግድ ሆኖብኝ ነበር። ፊልሙ ካለቀ በኋላ ብዙ ሰዎች ቀርበው ሌላ ጊዜ እንድናነጋግራቸው ይጠይቁን ነበር።
ገበሬዎች በሚኖሩበት መንደር ውስጥ ስናገለግል በካሴት የተቀዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ለማሰማት አንድ ትልቅ ቴፕ እንጠቀም ነበር። በአንድ ወቅት፣ በአንድ ቤተሰብ ቤት ውስጥ ከምሽቱ 1:00 ላይ በካሴት የተቀዳ ንግግር ለማሰማት ተነጋገርንና የመንደሩን ነዋሪዎች በሙሉ ጠራን። ያን ቀን ከመምሸቱ በፊት እንመለሳለን ብለን በማሰብ በጠዋት ተነስተን 25 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ በሚገኝ አንድ መንደር ለማገልገል በብስክሌት ሄድን። ይሁን እንጂ እዚያ መንደር ስናገለግል ውለን ወደ ቤታችን ለመመለስ ስንነሳ ቀደም ሲል የጣለው ዝናብ መንገዱን አጨቅይቶት ነበር።
ትንሽ ቆይቶ ብስክሌቶቻችንን ጭቃ ስለያዛቸው ተሸክመን ወደ ቤታችን መሄድ ግድ ሆነብን። ቤት ስንደርስ የቀጠሯችን ሰዓት አልፎአል። ከዚያም ያንን ትልቅ ቴፕ ተሸክመን ከምሽቱ 4:00 ላይ ቀጠሯችን ቦታ ደረስን። ሰው ሁሉ ተስፋ ቆርጦ ወደየቤቱ ይሄዳል የሚል እምነት ነበረን፤ የሚገርመው ግን የመንደሩ ነዋሪዎች እስከዚያ ሰዓት ድረስ ቁጭ ብለው እየጠበቁን ነበር! ንግግሩን ካሰማናቸው በኋላ አስደሳች ውይይት አደረግን። እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ ወደ ቤታችን ስንመለስ በጣም የደከመን ቢሆንም ደስታችን ወደር አልነበረውም!
መንደሮቹ በጣም የተራራቁ ስለሆኑ በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሩሲያ ሠራሽ የሆነች አንዲት አሮጌ መኪና እንድንገዛ ረዱን። ይህ ደግሞ የስብከት ሥራችንን ይበልጥ ቀላል አድርጎልናል። ከጊዜ በኋላ የአካባቢው ጳጳስ ሰዎች ቤታቸው ተቀብለው እንዳያነጋግሩን ምዕመናኑን ባስጠነቀቁ ጊዜ መኪናችን በሰፊው የታወቀች ሆነች። ጳጳሱ ሰማያዊ መኪና ስለሚይዙ ሁለት ሴቶች ተናግረው ነበር። ይህ ማስጠንቀቂያ በጎ ውጤት አስከትሏል። ሕዝቡ የሁለቱን ሴቶች ማንነትና አደገኛ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ የማወቅ ጉጉት አድሮበት ነበር! ይህ ጉጉታቸው ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንድናደርግ አጋጣሚ ከፈተ። በእርግጥም ኢሳይያስ “በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል” በማለት የተናገራቸው ቃላት እውነት ናቸው።—ኢሳይያስ 54:17
ከጊዜ በኋላ ሥራችን ፍሬ ማፍራት ጀመረ። ፍላጎት ካላቸው ጥቂት ሰዎች ጋር ሳምንታዊ ስብሰባ ማድረግ ጀመርን። ቀስ በቀስ ይህ አነስተኛ ቡድን አድጎ በ1962 አሥራ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ ጉባኤ ተመሠረተ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ሴቶች ነበሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ እኔና አንጃ ይሊስታሮ ወደተባለች ከተማ ተዛወርን።
አስደሳች አካባቢ
አዲስ የተመደብንበት ገጠራማ አካባቢ ውብና ጸጥታ የሰፈነበት መሆኑ በጣም አስደስቶናል፤ ይበልጥ ያስደሰተን ግን ሕዝቡ ነው። በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይና የሚቀረብ ነው። እርግጥ አብዛኞቹ ሃይማኖተኞችና ከፍተኛ የሆነ ብሔራዊ ስሜት ያላቸው ነበሩ፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በቁጣ ያባርሩን ነበር፤ ሆኖም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት ያላቸውም ሰዎች ነበሩ። ብዙውን ጊዜ ሴቶቹ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተን ስናነጋግራቸው ሥራቸውን አቁመው ያዳምጡናል፤ ወንዶቹ ደግሞ ብዙ ጊዜ የማያወልቁትን ኮፍያቸውን ያወልቃሉ። አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ስናስጠና የቤተሰቡ አባላት በጠቅላላ እንዲያውም አንዳንዴ ጎረቤቶቻቸውም ጭምር መጥተው ያዳምጡ ነበር።
በአገልግሎት ላይ የማገኛቸው ሰዎች ቅንነት ለሥነ ጥበብ ያለኝን ስሜት ይቀሰቅስብኛል። ጊዜ ሳገኝ የሸክላ አፈር ተጠቅሜ ቅርጻ ቅርጽ መሥራት እጀምራለሁ። ሁልጊዜ አስደሳችና አስቂኝ የሆኑት የሰዎች ባሕርያት ስለሚማርኩኝ የሠራኋቸው ቅርጻ ቅርጾች በሙሉ ለማለት ይቻላል በሰዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው። አብዛኞቹ ቅርጻ ቅርጾች ሴቶች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ናቸው። አንድ መጽሔት የሠራኋቸውን ቅርጻ ቅርጾች አስመልክቶ “እነዚህ ቅርጻ ቅርጾች ሞቅ ያለ መንፈስና ሰላም
እንዲሁም ደስታና የመረጋጋት ስሜት ይንጸባረቅባቸዋል። . . . አልፎ ተርፎም ከእነዚህ ቅርጻ ቅርጾች በስተጀርባ ከልብ የመነጨ ሰብዓዊ ፍቅርና ሥነ ጥበባዊ ክህሎት ይታያል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። ቢሆንም ግን ለሥነ ጥበብ ከልክ ያለፈ ትኩረት ላለመስጠት እጠነቀቅ ነበር። ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል ካደረግሁት ውሳኔ ዝንፍ አላልኩም።በ1973 ዓይኔን የማላሽበት አንድ ሥራ መጣልኝ። ቫንታ፣ ፊንላንድ ውስጥ በሚሠራው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንግዳ ማቆያ ክፍል ውስጥ የሚቀመጥ አንድ ትልቅ ቅርጽ እንድሠራ ጥያቄ ቀረበልኝ። ለዚህ ሥራ የተመረጠው ርዕስ መዝሙር 96:11-13 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ነበር። ይህን ችሎታዬን ይሖዋን ለማወደስ በመጠቀሜ በጣም ደስተኛ ነኝ!
አቅኚ ሆኜ ባሳለፍኳቸው ዓመታት ብዙውን ጊዜ የሥነ ጥበብ ፈጠራ ውጤቶችን የምሠራው ራሴን ለማስደሰት ስል ብቻ የነበረ ቢሆንም በ1970ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚያገኙት የጡረታ አበል እንደተፈቀደልኝ ስሰማ በጣም ተገርሜ ነበር። የተደረገልኝን የገንዘብ ድጋፍ ባደንቅም በወቅቱ ‘በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ ለሥነ ጥበብ ሰጥቼ ቢሆን ኖሮ መጨረሻ ላይ የማገኘው ይህን ብቻ ነበር? ይህችን ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘቴ ቀሪውን ሕይወቴን ይበልጥ አስተማማኝ ያደርገዋል?’ ብዬ አስቤ ነበር። ይህ ገንዘብ ወደፊት ከማገኘው የዘላለም ሕይወት ሽልማት ጋር ሲነጻጸር ከቁጥር የሚገባ አይደለም!—1 ጢሞቴዎስ 6:12
ወደ ከተማ መመለስ
የ1974ን ያህል በሕይወታችንና በአገልግሎታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ዓመት የለም። በዚህ ዓመት ቱርኩ ወደተባለች ትልቅ ከተማ ተዛወርን። በወቅቱ በዚህች ከተማ በርካታ አዳዲስ ሕንፃዎች እየተገነቡ ስለነበር ብዙ ሰዎች ወደ ከተማዋ ይጎርፉ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ተጨማሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች አስፈለጉ። መጀመሪያ ላይ እዚያ በመመደባችን ብዙም ደስተኞች አልነበርንም። ብዙዎቹ ግዴለሽነት ስለሚያጠቃቸው ለከተማ ነዋሪዎች መስበክ አስቸጋሪ ይመስል ነበር። ቀስ በቀስ ግን ክልሉን ስለለመድነው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያደንቁ ብዙ ሰዎች አገኘን።
በጥቂት ዓመታት ውስጥ እኔና አንጃ ከአርባ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የመርዳት መብት አግኝተናል። እነዚህ መንፈሳዊ ልጆቻችን ልባችንን ምንኛ ደስ አሰኝተውታል! (3 ዮሐንስ 4) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጤንነቴ እያሽቆለቆለ ቢመጣም የይሖዋ እርዳታ፣ የጉባኤው ፍቅርና የአገልግሎት ጓደኛዬ የአንጃ ‘ማጽናኛ’ ፈጽሞ እንዳልተለየኝ ይሰማኛል። (ቈላስይስ 4:11፤ መዝሙር 55:22) ከ50 ዓመታት በፊት ከአንጃ ጋር ስንገናኝ ሁለታችንም ብንሆን በጓደኝነት ይህን ያህል ረጅም ጊዜ እናሳልፋለን ብለን አላሰብንም ነበር።
“ሕይወት አጭር ነው ሥነ ጥበብ ግን ዘላለማዊ ነው” የሚል አንድ አባባል አለ። እኔ ግን እንዲህ ያለ አመለካከት አልነበረኝም። ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 4:18 ላይ “የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው” በማለት ከጻፋቸው ቃላት ጋር እስማማለሁ። ‘ከሚታዩት ነገሮች’ መካከል የሚፈረጀው በሥነ ጥበብ ባለሙያነት ያገኘሁት ደስታ ሁሉ ጊዜያዊ ነው። እነዚህ ነገሮች ይሖዋን በማገልገል ካገኘሁት ደስታ ጋር በምንም ዓይነት አይወዳደሩም፤ ከዚህም በላይ የዘላለም ሕይወት አያስገኙም። ሕይወቴ ከሥነ ጥበብ ይበልጥ ዘለቄታ ባላቸው ‘የማይታዩ’ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ!
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጥቁር ድንጋይ የመታሰቢያ ሐውልት ስሠራ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአንጃ ጋር (የተቀመጠችው) በ1957
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአንጃ (በስተቀኝ) ጋር በዛሬው ጊዜ