በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋታቸው ምክንያት 40 ሚሊዮን የሚያህሉ ቻይናውያን ገበሬዎች መሬታቸውን አጥተዋል።ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና

በ2005 በተለያዩ የዓለም ክፍሎች 28 ከባድ ጦርነቶችና 11 አነስተኛ ግጭቶች ተከስተዋል።ቫይታል ሳይንስ 2006-2007፣ ዎርልድዎች ኢንስቲትዩት

በቶኪዮ የቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ የሚገኝ አንድ ቡድን ከ55 ኪሎ ግራም ያነሰ ክብደት ያለው፣ በተራ ባትሪ የሚሠራና በሰው የሚንቀሳቀስ በጣም ቀላል አውሮፕላን በተሳካ ሁኔታ ለበረራ አበቃ። አውሮፕላኑ በ59 ሴኮንዶች ውስጥ 391 ሜትር መጓዝ ችሏል።ማይኒቺ ዴይሊ ኒውስ፣ ጃፓን

ኔዘርላንድ ውስጥ “የግል ድረ ገጾችን” ከሚቃኙ ከ12 እስከ 20 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል “40 በመቶ የሚሆኑት ወንዶችና 57 በመቶ የሚሆኑት ልጃገረዶች ምስላቸው በድረ ገጽ በቀጥታ እየተሰራጨ እያለ በካሜራው ፊት ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ወይም አንድ ዓይነት ወሲባዊ እንቅስቃሴ እንዲያሳዩ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።”ሩትገርስ ኒሶ ግሩፕ፣ ኔዘርላንድ

የቪዲዮ ጨዋታዎች ሱስ ይሆናሉ?

“የቪዲዮ ጌም ወይም ጨዋታ ከመጠን በላይ መጫወት በአእምሮ ላይ የሚያስከትለው ውጤት የአልኮል ወይም የካናቢስ ሱሰኝነት ከሚያስከትለው ውጤት ጋር ተመሳሳይ ነው።” ይህን የተናገሩት በርሊን፣ ጀርመን በሚገኘው ሻሪታ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ሱሰኝነትን በሚመለከት ጥናት በማካሄድ ላይ ያለውን አንድ ቡድን የሚመሩት ራልፍ ታሌማን የሚባሉ የሥነ ልቦና ተመራማሪ ናቸው። የኮምፒውተር ጨዋታዎችን ከመጠን በላይ መጫወት የሚፈጥረው ስሜት በተጫዋቹ አንጎል ውስጥ ዶፓሚን የሚባል ንጥረ ነገር በብዛት እንዲሰራጭ ሊያደርግ እንደሚችል ይታሰባል፤ ይህ ንጥረ ነገር ደግሞ የኋላ ኋላ “ሱስ” ሊሆን የሚችል የእርካታ ስሜት ይፈጥራል። እንዲህ ያለው ሁኔታ የቪዲዮ ጨዋታዎችን ከሚያዘወትሩ ሰዎች መካከል 10 በመቶ በሚያህሉት ላይ ሊከሰት እንደሚችል አንድ ጥናት አመልክቷል።

ሀብታሞች ብዙውን ጊዜ “ስጋትና ጭንቀት” ያጠቃቸዋል

ቻይና ዴይሊ የተባለ አንድ የቤይጂንግ ጋዜጣ “ሀብታሞች ስጋትና ጭንቀት ያጠቃቸዋል” በማለት ገልጿል። በአማካይ የ275 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ባለ ሀብት በሆኑ የምሥራቅና የደቡብ ቻይና ነዋሪዎች ላይ ጥናት ተካሂዶ ነበር። በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ሀብታም ሰዎች “ለሃይማኖት፣ ለትዳር፣ ለሕይወት፣ ለሥራና ለገንዘብ ያላቸውን አመለካከት” ያጠኑት ተመራማሪዎች “አብዛኞቹ ሚሊየነሮች ለገንዘብ ያላቸው ፍቅርም ሆነ ጥላቻ እኩል እንደሆነ” ደርሰውበታል። ለቀረበላቸው መጠይቅ መልስ ከሰጡት ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከበሬታ ከማትረፍና ስኬታማ ከመሆን ውጪ “ገንዘብ ያስገኘላቸው ዋነኛው ነገር ብስጭት” እንደሆነ ተናግረዋል።

የእርሻ ሥራ ለአእምሮ ሕሙማን ያለው ጠቀሜታ

በቅርቡ ከ14 አገሮች የተውጣጡ ከ100 የሚበልጡ ምሑራን የእርሻ ሥራን፣ ትምህርትንና ጤናን አጣምሮ ስለሚይዘው ግሪን ኬር የተባለ ጽንሰ ሐሳብ ለማጥናት በስታቫንገር፣ ኖርዌይ ተሰብስበው ነበር። ኤን አር ኬ የተባለ አንድ የዜና ማሰራጫ እንደዘገበው ለብዙ ዓመታት የአእምሮ ሕመም የነበረባቸው አንዳንድ ሰዎች የእርሻ ሥራ ከጀመሩ በኋላ የአእምሮ ሕክምና በሚሰጥባቸው ተቋማት እየሄዱ ክትትል ማድረግ አላስፈለጋቸውም። የእርሻ ሥራ “ለአእምሮና ለአካል ጤንነት ጠቃሚ” ነው። በኖርዌይ ከ600 የሚበልጡ የእርሻ ተቋማት ግሪን ኬር ከተባለው ጥናት ጋር ተባብረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፤ ይህም ተጨማሪ ገቢ አስገኝቶላቸዋል።

የቤተ ክርስቲያን ጉልላቶች ጥቅም ላይ ዋሉ

“[በአሜሪካ የሚገኙት] የኒው ኢንግላንድ አብያተ ክርስቲያናት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣውን በጀታቸውን ለመደጎም የሚያስችል መፍትሔ አገኙ፤ ይህ ሊሆን የቻለው ውብ የሆኑ ጉልላቶቻቸውን የሞባይል ስልክ አንቴናዎችን መስቀያ ቦታ ለተቸገሩ የሽቦ አልባ ስልክ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ማከራየት በመጀመራቸው ነው” በማለት ኒውስዊክ መጽሔት ዘግቧል። በመኖሪያ አካባቢዎች የሞባይል ስልክ መልእክቶችን መቀበያና ማሰራጫ አንቴናዎች የሚተከሉት በተፈቀደባቸው ቦታዎች ብቻ ነው፤ ነዋሪዎች ደግሞ የአካባቢያቸውን ውበት የሚያበላሹ አንቴናዎች በአቅራቢያቸው እንዲተከሉ አይፈልጉም። ስለዚህ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች መሣሪያቸውን በቤተ ክርስቲያን ጉልላቶች ውስጥ እየገጠሙ ነው። ለአብያተ ክርስቲያናት የምክር አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ድርጅት ፕሬዚዳንት ሲናገሩ “አንቴና የተከልንበት የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት ጉልላቱን ለሦስት ኩባንያዎች አከራይቷል፤ ቤተ ክርስቲያኑ ከዚህ ቀደም ምንም አገልግሎት ሰጥቶ ከማያውቀው ከዚህ ቦታ በየዓመቱ 74,000 የአሜሪካ ዶላር እያገኘ ነው” ብለዋል።