በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከግብጽ ተነስተው ወደተለያዩ ከተሞች ተጉዘዋል

ከግብጽ ተነስተው ወደተለያዩ ከተሞች ተጉዘዋል

ከግብጽ ተነስተው ወደተለያዩ ከተሞች ተጉዘዋል

ጣሊያን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“መሠረታቸው ከሆነችው ከግብጽ ተነስተው [ወደተለያዩ ቦታዎች] ‘በመጓዝ’ ላስገኛቸው ታላቅ ሥልጣኔ ሕያው ማስረጃ ሆነዋል” በማለት አርቼኦ የተባለው የጣሊያን መጽሔት ዘግቧል። አብዛኞቹ ከረጅም ጊዜያት በፊት ግብጽን የለቀቁ ሲሆን እንደ ኢስታንቡል፣ ለንደን፣ ፓሪስ፣ ሮም እና ኒው ዮርክ ወዳሉት ከተሞች መጥተዋል። ሮምን የሚጎበኙ ሰዎች፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ የታወቁ አደባባዮች የተዋቡት በእነርሱ እንደሆነ መመልከት ይችላሉ። እያወራን ያለነው ወደተለያዩ ቦታዎች ስለተጓዙት ሐውልቶች ነው!

እነዚህ ሐውልቶች፣ መጠናቸው እያነሰ የሚሄድ አራት ማዕዘን ድንጋዮችን በመደራረብ የሚሠሩ ሲሆን ጫፋቸው አካባቢ እንደ ፒራሚድ ሾጠጥ ያለ ቅርጽ ይኖራቸዋል። ጥንታዊ የሆነው ሐውልት ዕድሜው 4,000 ዓመት ገደማ ሲሆን በቅርብ ተሠራ የሚባለው ደግሞ 2,000 ዓመት ገደማ ሆኖታል።

ሐውልቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚሠሩት ከቀይ ድንጋይ ነው፤ የጥንቶቹ ግብጻውያን ቋጥኞችን በመፈልፈል አንድ ወጥ በሆነ ድንጋይ ሐውልቶቹን ከሠሯቸው በኋላ በመቃብሮችና በቤተ መቅደሶች ፊት ያቆሟቸው ነበር። አንዳንዶቹ ሐውልቶች በጣም ረጃጅሞች ናቸው። በሮም አደባባይ ላይ የቆመው በጣም ረጅም የሆነው ሐውልት 32 ሜትር ርዝመት ሲኖረው 4,623 ኩንታል ገደማ ይመዝናል። አብዛኞቹ ሐውልቶች ሃይሮግሊፍ በሚባለው የጥንቶቹ ግብጻውያን ይጠቀሙበት በነበረው ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልት ያጌጡ ናቸው።

እነዚህ ሐውልቶች የተሠሩት የፀሐይ አምላክ የሆነውን ራ ለማክበር ነበር። ይህ አምላክ ጥበቃ ስላደረገላቸውና የግብጽ ነገሥታት ድል እንዲቀዳጁ ስለረዳቸው ለማመስገን እንዲሁም አንድ ነገር እንዲያደርግላቸው ለመለመን እነዚህን ሐውልቶች ሠርተውለታል። ሐውልቶቹ በግብጽ ፒራሚዶች መልክ የተሠሩ እንደሆኑ ይታሰባል። የሐውልቶቹ ቅርጽ ለምድር ብርሃንና ሙቀት የሚሰጡትን የፀሐይ ጨረሮች የሚያመለክት ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ሐውልቶቹ የግብጽ ፈርዖኖችን ለማክበር ያገለግሉ ነበር። በሐውልቶቹ ላይ የተቀረጹት ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በርካታ የግብጽ ገዢዎች “ራ የሚወደው” ወይም “እንደ . . . አቱም ውብ የሆነ” ተብለዋል፤ አቱም የምትጠልቀው ፀሐይ አምላክ እንደሆነ ይታመን ነበር። ስለ አንድ ፈርዖን ወታደራዊ ችሎታ የሚገልጽ ሐሳብ የተቀረጸበት አንድ ሐውልት “ባዕድ አገራትን በሚረጋግጥና ዓመጸኞችን በሚገድል በሬ እንደተመሰለው እንደ ሞንቱ [የጦርነት አምላክ] ኃያል ነው” ይላል።

የመጀመሪያዎቹ ሐውልቶች ይቆሙ የነበሩት ጁኑ (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኦን ተብላለች) በተባለችው የግብጻውያን ከተማ ነበር፤ ጁኑ የሚለው ስም “የዓምድ ከተማ” የሚል ትርጉም እንዳለው የሚታሰብ ሲሆን ይህም ሐውልቶቹን ሊያመለክት ይችላል። ጁኑ የተባለችው ከተማ የግብጻውያን የፀሐይ አምልኮ ዋና ማዕከል ስለነበረች ግሪኮች ሂሊዮፖሊስ ብለው ይጠሯት ነበር፤ ትርጉሙም “የፀሐይ ከተማ” ማለት ነው። ሂሊዮፖሊስ የሚለው የግሪክኛ ስም “የፀሐይ ቤት” የሚል ትርጉም ካለው ቤት ሺሜሽ ከሚለው የዕብራይስጥ ስም ጋር ተመሳሳይ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውና ትንቢቶችን የያዘው የኤርምያስ መጽሐፍ ‘በግብጽ ምድር የሚገኙት የፀሐይ አምላክ ቤተ ጣዖት ሐውልቶች [“የቤት ሴሜስ ዓምዶች፣” የ1879 ትርጉም]’ እንደሚሰባበሩ ይናገራል። ይህ አባባል የሂሊዮፖሊስን ሐውልቶች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሐውልቶች የጣዖት አምልኮን የሚወክሉ ስለነበሩ አምላክ አውግዟቸዋል።—ኤርምያስ 43:10-13

ድንጋዩን መፈንቀልና ማጓጓዝ

በግብጽ፣ አስዋን ከተማ አካባቢ ተጋድሞ የሚገኘው ለሐውልት መሥሪያ የተዘጋጀ ድንጋይ፣ ሐውልቶች እንዴት ይሠሩ እንደነበረ ይጠቁመናል። በትልቅነቱ አንደኛውን ደረጃ የያዘው ይህ ቋጥኝ ተፈንቅሎ የወጣው ከዚሁ አካባቢ ነበር። ሐውልቶችን የሚሠሩ ሰዎች ለዚህ ዓላማ የሚሆናቸውን ተስማሚ ቋጥኝ ከመረጡ በኋላ ድንጋዩን ከላይ ጠርበው ያስተካክሉታል፤ ከዚያም በጎንና ጎኑ ጉድጓድ ይቆፍራሉ። ቋጥኙን ከመሬቱ ውስጥ ለመፈንቀልም ከሥሩ ጉድጓድ ይቆፍሩና እንጨት ይከቱበታል። የጥንት ግብጻውያን ካወጧቸው ቋጥኞች ሁሉ በክብደቱ ተወዳዳሪ የሌለው ወደ 11,888 ኩንታል የሚመዝነው አንድ ወጥ ድንጋይ የተፈነቀለው በዚህ መንገድ ነበር፤ ይህ ሐውልት ተሠርቶ ቢያልቅ ኖሮ ወደ አባይ ወንዝ ተወስዶ ወደሚፈለገው ቦታ በጀልባ ይጓጓዝ ነበር።

ሠራተኞቹ፣ በአስዋን አካባቢ የሚገኘው ሐውልት ሊጠገን በማይችል ሁኔታ እንደተሰነጠቀ ሲመለከቱ እዚያው እንደተጋደመ ተዉት። ይህ ሐውልት ተሠርቶ ቢያልቅ ኖሮ 42 ሜትር ርዝመትና መሠረቱ ደግሞ 4 ሜትር በ4 ሜትር ስፋት ይኖረው ነበር። እነዚህ ሐውልቶች ተሠርተው ካለቁ በኋላ እንዴት እንደሚያቆሟቸው እስካሁን ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው።

ከግብጽ ወደ ሮም

በ30 ከክርስቶስ ልደት በፊት ግብጽ፣ የሮም ግዛት ሆነች። የተለያዩ የሮም ንጉሠ ነገሥታት ዋና ከተማቸውን ከፍተኛ ዝና ባተረፉ ሐውልቶች ማስዋብ በመፈለጋቸው 50 ያህል ሐውልቶች ወደ ሮም ተጋዙ። እነዚህን ሐውልቶች ለማጓጓዝ፣ ለዚህ ዓላማ የሚውል ለየት ያለ ፕላን በመንደፍ ግዙፍ መርከቦችን መሥራት አስፈልጎ ነበር። ሐውልቶቹ ሮም ከደረሱ በኋላም ቢሆን ከፀሐይ አምልኮ ጋር መያያዛቸው አልቀረም።

የሮም አገዛዝ ሲገረሰስ ሮም የዘራፊዎች ሲሳይ ሆነች። አብዛኞቹ ሐውልቶችም በወደቁበት ተረስተው ቀሩ። ይሁን እንጂ የተለያዩ ጳጳሳት ከዚህች ጥንታዊት ከተማ ፍርስራሾች መካከል የተወሰዱትን ሐውልቶች በድጋሚ ለማቆም ፈልገው ነበር። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ሐውልቶቹ “የግብጻውያን ንጉሥ ለፀሐይ ያቆማቸው” እንደሆኑና በአንድ ወቅት “ርኩስ ለሆኑት የአረማውያን ቤተ መቅደሶች ከንቱ ክብር ያመጡ እንደነበር” ተናግራለች።

በሊቀ ጳጳስ ሲክስተስ አምስተኛ የግዛት ዘመን (1585-1590) የመጀመሪያው ሐውልት በድጋሚ ሲቆም፣ ክፉ መንፈስን ለማስወጣትና የአምላክን በረከት ለማግኘት ጸሎት ይቀርብ እንዲሁም ፀበል ይረጭና ዕጣን ይጨስ ነበር። አንድ ጳጳስ በቫቲካኑ ሐውልት ፊት ቆመው “ቅዱሱን መስቀል እንድትሸከም እንዲሁም ከአረማውያን ርኩሰትና ከማንኛውም መንፈሳዊ ክፋት እንድትጸዳ አዝሃለሁ” በማለት ይዘምሩ ነበር።

አንድ ጎብኚ በዛሬ ጊዜ በሮም የቆሙትን ሐውልቶች ሲመለከት ድንጋዮቹን ለመፈንቀል፣ ለማጓጓዝና ሐውልቶቹ ከተሠሩ በኋላ ለማቆም ምን ያህል ልዩ ችሎታ እንዳስፈለገ በማሰብ ይደነቅ ይሆናል። ለፀሐይ አምልኮ ያገለግሉ የነበሩ ሐውልቶች የጳጳሳቱን ከተማ ለማስዋብ መቆማቸውን ሲመለከትም ይገረም ይሆናል፤ በእርግጥም አስገራሚ ቅንጅት ነው!

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉክሶር፣ ግብጽ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒው ዮርክ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓሪስ