ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ የሚኖረው ኪንግዝሊ “እኔ በምኖርበት አገር ክርስቲያን የሚባለው በሳምንት አንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የሚሄድ ነው” በማለት ተናግሯል። በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው ራድ ደግሞ “በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ክርስቲያኖች በአለባበስ፣ በበዓል አከባበር እንዲሁም ሴቶችን በሚይዙበት መንገድ የምዕራባውያንን ልማዶችና ባሕሎች የሚከተሉ ቡድኖች እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ” በማለት ገልጿል።
ይሁን እንጂ፣ አንድን ሰው ክርስቲያን የሚያስብለው በሳምንት አንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሄዱና የተወሰነ ኅብረተሰብን ልማዶችና ባሕሎች መከተሉ ነው? “ክርስቲያን” የሚለው ቃል ክርስቶስ የሰበከውንና ምሳሌ በመሆን ያሳየውን አመለካከት፣ ሥነ ምግባርና ባሕርይ የሚያንጸባርቅ የሕይወት መንገድ መከተልን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። * ታዲያ ክርስትና በተቋቋመበት ወቅት ሰዎች የክርስትናን ትምህርት ተግባራዊ ያደረጉት እንዴት ነበር?
የጥንቱ ክርስትና የሕይወት መንገድ ነበር
ኢየሱስ ለተከታዮቹ “የማዛችሁን ብትፈጽሙ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:14) የኢየሱስ ትምህርት መላ ሕይወታቸውን ስለሚነካ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መጀመሪያ ላይ ሃይማኖታቸውን “መንገድ” በማለት ይጠሩት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:2) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ “በመለኮታዊ አመራር ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ።” (የሐዋርያት ሥራ 11:26 NW) ይህ የተቀበሉት አዲስ ስም በሰማይ የሚኖረው አባቱን ፈቃድ ለሰው ዘር ያሳወቀው ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን እንዳመኑ የሚያሳይ ነው። ይህ እምነታቸው በዙሪያቸው ከነበረው ዓለም የተለየ የሕይወት መንገድ እንዲከተሉ አድርጓቸዋል።
የክርስቶስ ትምህርቶች ተከታዮቹ እንደ ‘ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ገላትያ 5:19-21፤ ኤፌሶን 4:17-24) ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ቀደም ሲል እነዚህን ነገሮች የማድረግ ልማድ እንደነበራቸው ነግሯቸዋል። አክሎም “አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና፣ በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11
ጠብ፣ ቅናት፣ ቁጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነትና እነዚህን የመሳሰሉ’ ክፉ ድርጊቶችን በማስወገድ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች እንዲከተሉ ገፋፍተዋቸዋል። (ኧርነስት ባርንዝ ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “በጥንቶቹ የክርስትና እምነት ጽሑፎች ላይ ክርስትና ንጹሕ ሥነ ምግባር ያለውና ሕግ አክባሪ እንቅስቃሴ ሆኖ ቀርቧል። አባላቱም ጥሩ ዜጎችና ታማኝ ተገዢዎች ለመሆን ይፈልጉ ነበር። ከአረማውያን የተሳሳቱ ትምህርቶችና መጥፎ ምግባሮች የራቁ ነበሩ። በግል ሕይወታቸውም ሰላማዊ ጎረቤቶችና እምነት የሚጣልባቸው ወዳጆች ለመሆን ይጥሩ ነበር። ጭምቶች፣ ታታሪዎችና ንጹሖች እንዲሆኑ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ምግባረ ብልሹነትና ልክስክስነት በተስፋፋበት አካባቢ ቢኖሩም ለቆሙላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ታማኝ እስከሆኑ ድረስ ሐቀኞችና እውነተኞች ነበሩ። የጾታ ሥነ ምግባር አቋማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ጋብቻቸውን ያከብሩና ንጹሕ የቤተሰብ ኑሮ ይመሩ ነበር።” በጥንት ጊዜ ክርስቲያን መሆን እነዚህን ነገሮች የሚያካትት ነበር።
የጥንቱ ክርስትና ተለይቶ የሚታወቅበት ሌላው ምልክት ደግሞ በቅንዓት የሚከናወነው የወንጌላዊነት ሥራ ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) በፓሪስ፣ ፈረንሳይ በሚገኘው ሶርቦኔ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዣን ቤርናርዲ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “[ክርስቲያኖች] በየቦታው እየሄዱ ላገኙት ሰው ሁሉ መናገር ነበረባቸው። በአውራ ጎዳናዎችና በከተሞች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አደባባዮችና በየቤቱ እየሄዱ ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ መናገር ነበረባቸው። ተቀባይነት ቢያገኙም ባያገኙም ለድኾችና በሀብታቸው ለተጠላለፉ ባለጠጎች መስበክ ነበረባቸው። . . . በእግር ወይም በመርከብ እየተጓዙ እስከ ምድር ጫፍ ድረስ መሄድ ነበረባቸው።”
እውነተኛ ክርስትና በዛሬው ጊዜ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙት እውነተኛ ክርስቲያኖችም በአኗኗራቸው ከሌሎች ተለይተው መታወቅ አለባቸው። ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ያወጧቸውን መመሪያዎች በጥብቅ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የሚስማማ ሕይወት ለመምራት የሚያደርጉት ጥረት ከሌሎች የተሰወረ አይደለም።
ለምሳሌ ያህል፣ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “በዓለም ላይ በጥሩ ሥነ ምግባራቸው ከተመሰገኑ ቡድኖች መካከል” የይሖዋ ምሥክሮችም እንደሚገኙበት ገልጿል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዩታ ግዛት ሶልት ሌክ ሲቲ በምትባል ከተማ የሚታተመው ዲዘርት ኒውስ የተባለ ጋዜጣ የይሖዋ ምሥክሮችን በሚመለከት እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ሰዎች ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር እንዲኖራቸው ያበረታታሉ፤ እንዲሁም ውጤታማና ሐቀኛ ዜጎችን ያፈራሉ። አባላቶቻቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ሕጎችን ይከተላሉ። ማጨስ፣ ከልክ በላይ መጠጣት፣ ዕፅ መውሰድ፣ ቁማር መጫወት እንዲሁም ልቅ የሆነ የጾታ ግንኙነትና ግብረ ሰዶም መፈጸም መንፈሳዊነትን የሚያበላሹ ልማዶች እንደሆኑ ያምናሉ። ሐቀኛ መሆንና ተግቶ መሥራት ጥሩ እንደሆነ ያስተምራሉ።”
የይሖዋ ምሥክሮች ቀናተኛ ወንጌላዊ የመሆን ኃላፊነታቸውንም በቁም ነገር ይመለከቱታል። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይህንን አስመልክቶ አስተያየት ሲሰጥ “እያንዳንዱ አባል እየቀረበ ስላለው መንግሥት በማወጅ ለይሖዋ ምሥክርነት የመስጠት . . . መሠረታዊ ግዴታ አለበት። . . . አንድ ሰው እውነተኛ ምሥክር ለመሆን ውጤታማ በሆነ መንገድ መስበክ ይኖርበታል” ብሏል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ከሕዝበ ክርስትና በርካታ ሃይማኖቶች መካከል የአንዱ አባል ከመሆን ያለፈ ነገር ይጠይቃል። ኢየሱስ ራሱ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚበዙ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:22, 23) የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች እንድትማርና በሥራ ላይ እንድታውል ይጋብዙሃል። ክርስቲያን መሆን ማለት ይህ ነው። ኢየሱስ “እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 13:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 አንድ መዝገበ ቃላት ክርስቲያን ለሚለው ቃል ‘ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ እንደሆነ የሚቀበል ወይም በእርሱ ሕይወትና ትምህርቶች ላይ የተመሠረተውን ሃይማኖት የሚከተል ሰው’ የሚል ፍቺ ሰጥቶታል።
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ ኢየሱስ ወዳጆቼ ብሎ የጠራቸው እነማንን ነው?—ዮሐንስ 15:14
▪ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከየትኞቹ ድርጊቶች መራቅ ይኖርባቸዋል?—ገላትያ 5:19-21
▪ ክርስቲያኖች በየትኛው ሥራ ላይ መካፈል ይኖርባቸዋል?—ማቴዎስ 28:19, 20
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በጥንት ዘመን እንደነበሩት ሁሉ ዛሬ ያሉት እውነተኛ ክርስቲያኖችም ቀናተኛ ወንጌላውያን ናቸው