በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአበባ ዱቄት—ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ብናኝ

የአበባ ዱቄት—ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ብናኝ

የአበባ ዱቄት—ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ብናኝ

ጸደይ ሲመጣ ንቦች ሥራ የሚበዛባቸው ሲሆን አየሩም በአበባ ዱቄት ይሞላል። በአለርጂ የሚሰቃዩ ሰዎች የአበባ ዱቄትን እንደ በረከት ሳይሆን እንደ እርግማን የሚያዩት ይመስላል። ይሁን እንጂ የአበባ ዱቄትን የጤና ጠንቅ ከሆኑ ነገሮች መካከል ከመፈረጃችን በፊት በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይህ ብናኝ ምን ሚና እንደሚጫወት እንመልከት። ይህ ብናኝ ለሕይወታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስናውቅ መገረማችን አይቀርም።

ለመሆኑ የአበባ ዱቄት ምንድን ነው? ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ “የአበባ ዱቄት፣ አበባ በሚያወጡና በሌሎች ተክሎች ወንዴ ክፍል ውስጥ የሚዘጋጅ ጥቃቅን ዘሮች የያዘ ብናኝ ነው” በማለት ያብራራል። በአጭር አነጋገር ተክሎች የአበባ ዱቄት የሚያዘጋጁት ለመራባት ነው። ሰዎችን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ልጅ የሚጸንሱት የሴቷ እንቁላል ከወንዱ ዘር ጋር ተገናኝቶ ሲዳብር ነው። በተመሳሳይም የአንድ አበባ ሴቴ ክፍል ዳብሮ ፍሬ እንዲያስገኝ ከተፈለገ ከወንዴው ክፍል የሚወጣ የአበባ ዱቄት ያስፈልገዋል። *

የአበባ ዱቄት ቅንጣቶች በጣም ደቃቅ ከመሆናቸው የተነሳ በአጉሊ መነጽር ካልሆነ በስተቀር ልናያቸው አንችልም። እንዲያውም በአጉሊ መነጽር ያዩ ተመራማሪዎች እንደሚመሠክሩት የእያንዳንዱ ተክል የአበባ ዱቄት መጠንም ሆነ ቅርጽ ከሌላው የተለየ ነው። የአበባ ዱቄት በቀላሉ ስለማይበሰብስ ብዙውን ጊዜ የሳይንስ ሊቃውንት ከመሬት ውስጥ ቆፍረው ባወጧቸው የአበባ ዱቄቶች ላይ ምርምር በማድረግ አንዱ ከሌላው የሚለይበትን “አሻራ” ማጥናት ችለዋል። እንዲህ ያለው ጥናት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ሰዎች ያለሟቸው የነበሩትን የተክል ዓይነቶች ለይተው ለማወቅ አስችሏቸዋል። እንዲያውም የዘሩ ዓይነት የተለያየ መሆኑ አበቦች የራሳቸውን ዝርያ ለይተው እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።

የአበባ ዱቄት የሚሰራጭበት መንገድ

ብዙ ተክሎች የአበባ ዱቄታቸው ከእንቡጡ ውስጥ ከወጣ በኋላ ከቦታ ቦታ የሚሰራጨው በነፋስ አማካኝነት ነው። ውኃም የአንዳንድ የውኃ ላይ ተክሎችን የአበባ ዱቄት ለማሰራጨት ያገለግላል። ነፋስ የአበባ ዱቄቶችን በተገቢው ቦታ ላይ የማድረስ አጋጣሚው ጠባብ በመሆኑ በዚህ ዘዴ ብቻ የሚራቡ ዛፎችና ተክሎች ከፍተኛ መጠን ያለው የአበባ ዱቄት ያመርታሉ። * በአለርጂ የሚሰቃዩ ሰዎች በጣም የሚቸገሩት እንዲህ ባለው ወቅት ነው።

ነፋስ የበርካታ ዓይነት ዛፎችንና ሣሮችን የአበባ ዱቄት ለማሰራጨት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ቢሆንም ተራርቀው የበቀሉ ተክሎች ይበልጥ ውጤታማ የሆነ ዘዴ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ዕፅዋት የአበባ ዱቄት በተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኙ ተመሳሳይ የዕፅዋት ዓይነቶች የሚሰራጨው እንዴት ነው? እንዲህ ያለውን ተግባር ስኬታማ በሆነ መንገድ የሚያከናውኑት የሌሊት ወፎች፣ ወፎችና ነፍሳት ናቸው! ይሁን እንጂ እነዚህ ፍጥረታት ለሚሰጡት አገልግሎት ወሮታ እንዲከፈላቸው ይፈልጋሉ።

አበቦቹ ለእነዚህ ፍጥረታት ጣፋጭ የአበባ ማር ያቀርቡላቸዋል። ፍጥረታቱ የአበባ ማሩን ለመቅሰም አበባው ላይ ሲያርፉ የአበባው ዱቄት ገላቸው ላይ መጣበቁ አይቀርም። ተጨማሪ የአበባ ማር ፍለጋ ወደ ሌላ አበባ ሲሄዱ ደግሞ ከበፊቱ አበባ ላይ የወሰዱትን ዱቄት እዚያ ላይ ያራግፋሉ።

በተለይ ወይና ደጋ የአየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች የአበባ ዱቄት የማሰራጨቱን ተግባር በአብዛኛው የሚያከናውኑት ነፍሳት ናቸው። እነዚህ ነፍሳት የአበባ ማርና የአበባ ዱቄት ለመቅሰም ሲሉ በየቀኑ ቁጥር ሥፍር በሌላቸው አበቦች ላይ ያርፋሉ። * ሜይ ቤረንባውም የተባሉ አንዲት ፕሮፌሰር “ነፍሳት ለሰው ልጅ ጤንነት ከሚያበረክቱት ጠቃሚ አስተዋጽኦ መካከል የጎላ ስፍራ የሚይዘው . . . የአበባ ዱቄት በማሰራጨት የሚያከናውኑት እምብዛም የማይስተዋል አገልግሎታቸው ሳይሆን አይቀርም” በማለት ተናግረዋል። የፍራፍሬ ዛፎች ጥሩ ምርት መስጠታቸው በአብዛኛው የተመካው ነፍሳት ከአንዱ አበባ ወደ ሌላው አበባ ዘር በማሰራጨታቸው ላይ ነው። በመሆኑም የአበባ ዱቄት ከአንዱ ዛፍ ወደ ሌላው ዛፍ መሰራጨቱ ለሕይወታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ መገንዘብ ትችላለህ።

ነፍሳቱን የሚማርካቸው ምንድን ነው?

አበቦች ዘር የማሰራጨት አገልግሎት የሚሰጡትን ፍጥረታት መማረክ አልፎ ተርፎም መመገብ ይኖርባቸዋል። ታዲያ አበቦች ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ምናልባት ለእነዚህ ነፍሳት ፀሐይ ለመሞቅ የሚያስችል ምቹ ማረፊያ ያዘጋጁ ይሆናል። በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ ማራኪ በሆነው መልካቸውና መዓዛቸው አማካኝነት የአበባ ማርና ዱቄት እንዳላቸው ያስተዋውቃሉ። እንዲሁም ብዙ አበቦች ነጠብጣብ ወይም ሽንትር ጣል ጣል ባደረገባቸው ቅጠሎቻቸው አማካኝነት ነፍሳቱ ወዴት አቅጣጫ መሄድ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። በዚህ መንገድ ዘር የሚያሰራጩት ነፍሳት የአበባ ማር ሊያገኙ የሚችሉት የት እንደሆነ መረጃ ያገኛሉ።

አበቦች ነፍሳቱን የሚስቡበት መንገድ ከአበባ አበባ ይለያያል። አንዳንዶቹ ዝንቦችን ለመሳብ ብስባሽ የሚመስል ጠረን ያመነጫሉ። ሌሎች ደግሞ ዘር የያዙት ነፍሳት ተግባራቸውን ሳያሳኩ እንዳይሄዱ ለማድረግ የማታለያ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ቢ ኦርኪድስ የሚባሉት የአበባ ዓይነቶች ተጓዳኝ የሚፈልጉ ንቦችን የሚያማልል ንብ የሚመስል መልክ አላቸው። አንዳንድ አበቦች ነፍሳትን ማርከው ወደራሳቸው ከሳቡ በኋላ የሚለቋቸው ግዳጃቸውን ከፈጸሙ በኋላ ነው። የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪ የሆኑት ማልኮም ዊልኪንስ “በዕፅዋት ዓለም የአበባ ዱቄት ተሰራጭቶ የሴቴው ክፍል እንዲዳብር የሚያደርገውን ዓቢይ ተግባር ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ፣ ዝንፍ የማይል ወይም ረቂቅ የሆነ ጥበብ የለም” በማለት ጽፈዋል።

ፈጣሪ ዕፅዋትን ማራኪ አድርጎ በመፍጠር ዘራቸው እንዲሰራጭ ባያደርግ ኖሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕፅዋት መራባት ባልቻሉ ነበር። ኢየሱስ ይህ አስደናቂ ሥራ ምን ውጤት እንዳስገኘ ሲናገር “እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም” ብሏል።—ማቴዎስ 6:25, 28, 29

እንዲህ ያለው ሂደት በመኖሩ ምክንያት ዕፅዋት ተፈላጊውን እድገት የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ ለመኖር የሚያስፈልገንን ምግብ ያመርቱልናል። እውነት ነው፣ የአበባ ዱቄት ለአንዳንዶቻችን የጤና ቀውስ ያስከትልብን ይሆናል፤ ቢሆንም ይህን ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ብናኝ በማሰራጨት ሥራ የተጠመዱ ነፍሳት በመኖራቸው አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል። ጥሩ ምርት ማግኘት በዋነኝነት የተመካው ለፈጣሪያችን አስገራሚ የእጅ ሥራ ምሥክርነት በሚሰጠው በዚህ ግሩም የተፈጥሮ ሂደት ላይ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 የሴቴው ክፍል የሚዳብረው ከሌላ ተክል በሚመጣ የአበባ ዱቄት (cross-pollination) አሊያም በዚያው ተክል ላይ ያለው ወንዴ ክፍል በሚያመርተው የአበባ ዱቄት (self-pollination) አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ተክሉ ጤናማ የሆኑና አደጋ የመቋቋም ኃይል ያላቸውን የተለያዩ ዓይነት ፍሬዎችን ማፍራት የሚችለው ሴቴው ከሌላ ተክል በሚመጣ የአበባ ዱቄት ሲዳብር ነው።

^ አን.6 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የበርች ዛፍ አበባ እምቡጥ ብቻ እንኳ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የአበባ ዱቄት ብናኞችን ሊያሰራጭ ይችላል፤ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ አንድ የበርች ዛፍ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እምቡጦች ሊኖሩት ይችላል።

^ አን.9 ንቦች አንድ ኪሎ ግራም ማር ለመሥራት ወደተለያዩ አበቦች 10 ሚሊዮን ጊዜ መመላለስ ይጠይቅባቸዋል።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአበባ ዱቄት የሚያሰራጩ ፍጥረታት

ዝንቦችና ጥንዚዛዎች

ለውለታቸው ካልተዜመላቸው ነፍሳት መካከል እነዚህ ይገኙበታል። ቸኮሌት የምትወድ ከሆነ የካካዎ ዛፍ አበባዎችን ዱቄት በማሰራጨት ረገድ ወሳኝ ተግባር የምታከናውነውን አንዲት ትንሽ ዝንብ ማመስገንህ የተገባ ነው።

የሌሊት ወፎችና ፖሰሞች

እንደ ኬፖክና ቤኦባብ ያሉት ግርማ ሞገስ ያላቸው ዛፎች ዘራቸው የሚሰራጨው በሌሊት ወፎች አማካኝነት ነው። ፍሩት ባትስ የሚባሉ አንዳንድ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች የአበባ ማር መቅሰም ብቻ ሳይሆን ፍሬውን በመብላትና ዘሮቹን በመበተን ለተክሉ ስርጭትም ጭምር የሚጠቅም አገልግሎት ያከናውናሉ። ፖሰም የሚባሉት የካንጋሮ ዝርያዎች የአበባ ማር ይመገባሉ። በዚህ ወቅት በጸጉራቸው ዱቄቱን ከአንዱ አበባ ወደሌላው ይዘው ይሄዳሉ።

ቢራቢሮዎችና የእሳት እራቶች

ማራኪ መልክ ያላቸው እነዚህ ነፍሳት ቀለባቸው በአብዛኛው የአበባ ማር ስለሆነ ከአንዱ አበባ ወደሌላው በሚበሩበት ጊዜ የአበባ ዱቄቱን ይዘው ይሄዳሉ። ኦርኪድስ ተብለው ከሚጠሩት የሚያምሩ አበቦች ውስጥ አንዳንዶቹ የአበባ ዱቄታቸው ሙሉ በሙሉ የሚሰራጨው በእሳት እራቶች አማካኝነት ነው።

ሰንበርድ እና ሀሚንግበርድ የሚባሉ ወፎች

እነዚህ በቀለማት ያሸበረቁ ወፎች የአበባ ማር ለመቅሰም ከአበባ ወደ አበባ ይበራሉ። በዚህ ጊዜ የአበባው ዱቄት በወፎቹ ግምባርና በደረታቸው ላይ ባሉት ላባዎቻቸው ላይ ይከማቻል።

ንቦችና ተርቦች

መነጽር አቧራ እንደሚስብ ሁሉ በጸጉር የተሸፈነው የንቦች ገላም በቀላሉ የአበባ ዱቄት የሚይዝ መሆኑ ንቦች በዕፅዋት የአበባ ዱቄት ስርጭት ረገድ ከፍተኛውን ሚና እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል። ባምብልቢ የተባለች አንዲት ትልቅ ጸጉራም ንብ ብቻ እንኳ እስከ 15,000 የሚደርሱ የአበባ ዱቄቶችን ልትሸከም ትችላለች። በ19ኛው መቶ ዘመን ከእንግሊዝ ወደ ኒው ዚላንድ ለመጡት ለእነዚህ የንብ ዝርያዎች ምስጋና ይድረሳቸውና በአሁኑ ጊዜ መስኩ በለምለም ሣር ስለተሸፈነ የአገሪቱ ከብቶች እንደ ልብ መኖ ያገኛሉ።

በምድር ላይ በዋነኝነት የአበባ ዱቄት የሚያሰራጩት ሃኒቢ የሚባሉት ንቦች ናቸው። እነዚህ ንቦች አብዛኛውን ጊዜ የሚቀስሙት በቀፏቸው አካባቢ የሚገኝን አንድ ዓይነት አበባ ነው። የነፍሳት ተመራማሪ የሆኑት ክሪስቶፈር ኦቱል ባቀረቡት ስሌት መሠረት “ሰው ከሚመገበው ምግብ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገኘው ንቦች የአበባ ዱቄት በማሰራጨት በሚያከናውኑት ተግባር አማካኝነት ነው።” እንደ ለውዝ፣ ፖም፣ ፕሪምና ቼሪ ያሉ ተክሎችን የአበባ ዱቄት ለማሰራጨት ንቦች ያስፈልጋሉ። ገበሬዎች ከእያንዳንዱ ቀፎ ለሚያገኙት አገልግሎት ለንብ አርቢዎች ዋጋ ይከፍላሉ።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቢ ኦርኪድስ የሚባሉት አበቦች