በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ ዓለም ወዴት እያመራ ነው?

ይህ ዓለም ወዴት እያመራ ነው?

ይህ ዓለም ወዴት እያመራ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ የሚታየውን የሥነ ምግባር ውድቀት በተመለከተ ከረጅም ጊዜ በፊት እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል:- “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ . . . ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አሁን ያለንበትን ዓለም ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል ቢባል እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም። የሚገርመው ግን ትንቢቱ የተጻፈው የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ ነው! ይህ ትንቢት የሚጀምረው “በመጨረሻው ዘመን” በማለት ነው። ታዲያ ‘የመጨረሻው ዘመን’ የሚሉት ቃላት ምን ያመለክታሉ?

የምን ‘መጨረሻ?’

‘የመጨረሻው ዘመን’ ተብሎ የተተረጎመው ዘ ላስት ዴይስ የሚለው የእንግሊዝኛ አገላለጽ በጣም የተለመደ ሆኗል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ እንኳ በመቶዎች በሚቆጠሩ መጻሕፍት ርዕሶች ውስጥ እነዚህ ቃላት ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ ለንባብ የበቃውን ዘ ላስት ዴይስ ኦቭ ኢኖሰንስ—አሜሪካ አት ዋር 1917-1918 የተባለውን መጽሐፍ እንመልከት። መጽሐፉ በመቅድሙ ላይ እንደገለጸው “ዘ ላስት ዴይስ” (የመጨረሻው ዘመን) የሚለውን አገላለጽ የሚጠቀምበት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ዝቅጠት የታየበትን የተወሰነ ጊዜ ለማመልከት ነው።

የመጽሐፉ መቅድም በመቀጠል “በ1914 አገሪቱ [ዩናይትድ ስቴትስ] በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ለውጥ ማድረግ ጀመረች” ብሏል። እርግጥ ነው፣ 1914 ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዓለም አቀፍ ጦርነት የጀመረበት ዓመት ነው። መጽሐፉ “ይህ በሁለት ሠራዊቶች መካከል የተደረገ ተራ ግጭት ሳይሆን የዓለም መንግሥታት እርስ በርስ የተፋለሙበት አጠቃላይ ጦርነት ነበር” ብሏል። ቆየት ብለን እንደምንመለከተው ይህ ጦርነት የተከሰተው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ብሎ በሚጠራው ጊዜ መጀመሪያ ላይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓለም ከመጥፋቱ በፊት ‘የመጨረሻው ዘመን’ የተባለ አንድ የተወሰነ ጊዜ እንደሚኖር ያስተምራል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ” በማለት ከዚህ ቀደም የጠፋ ዓለም እንደነበር ይገልጻል። በዚያን ጊዜ የተባለው ዘመን የትኛው ነው? የጠፋውስ ዓለም ምንድን ነው? ጥንት በኖኅ ዘመን የነበረው ‘የኃጢአተኞች ዓለም’ ነው። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም ይጠፋል። ይሁን እንጂ ኖኅና ቤተሰቡ እንደተረፉ ሁሉ አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች ከፊታችን ካለው ጥፋት ይድናሉ።—2 ጴጥሮስ 2:5 የ1954 ትርጉም፤ 3:6፤ ዘፍጥረት 7:21-24፤ 1 ዮሐንስ 2:17

ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን ምን ተናግሯል?

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ‘በጥፋት ውሃ ስለተጥለቀለቁበት’ ስለ ‘ኖኅ ዘመንም’ ተናግሯል። ከጥፋት ውኃው ቀደም ብሎ ማለትም በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም ከመጥፋቱ በፊት የነበረውን ሁኔታ “የዓለም መጨረሻ” ብሎ በጠራው ጊዜ ውስጥ ከሚታዩት ነገሮች ጋር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 24:3, 37-39) “የዓለም መጨረሻ” የሚለውን አባባል አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች “የዘመኑ መጨረሻ” በማለት ተርጉመውታል።—ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እና ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን

ኢየሱስ ይህ ዓለም ከመጥፋቱ በፊት በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። ጦርነትን አስመልክቶ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” ብሏል። የታሪክ ምሑራን ይህ መሆን የጀመረው በ1914 መሆኑን ተገንዝበዋል። በመሆኑም ቀደም ሲል የተጠቀሰው መጽሐፍ መቅድም 1914ን አስመልክቶ ሲናገር “በሁለት ሠራዊቶች መካከል . . . ሳይሆን የዓለም መንግሥታት እርስ በርስ የተፋለሙበት አጠቃላይ ጦርነት” መጀመሪያ እንደነበር ገልጿል።

ኢየሱስ ትንቢቱን በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው።” አክሎም ‘ክፋት እየገነነ’ እንደሚሄድ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7-14) በእርግጥም በዘመናችን ይህ ሁኔታ ሲፈጸም ተመልክተናል። በዛሬው ጊዜ የሥነ ምግባር ውድቀት እየጨመረ መሄዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ነው!

በሥነ ምግባር በዘቀጠው በዚህ ዓለም ውስጥ አኗኗራችን ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሥነ ምግባር ዝቅጠትንና ‘አሳፋሪ ምኞት’ የነበራቸውን ሰዎች አስመልክቶ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ሴቶቻቸውም እንኳ ለባሕርያቸው የሚገባውን ግንኙነት ባሕርያቸው ላልሆነው ግንኙነት ለወጡ። እንደዚሁም ወንዶች ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ።”—ሮሜ 1:26, 27

ታሪክ ጸሐፊዎች እንደተናገሩት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ማኅበረሰብ በሥነ ምግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዘቀጠ በመሄዱ “በቁጥር አነስተኛ የነበረው የክርስቲያኖች ቡድን ተድላ ያሳበደውን አረማዊ ዓለም በመንፈሳዊ አቋሙና በመልካም ምግባሩ ይኮንነው ነበር።” ይህ ሁኔታ እኛም እንዲህ እያልን ራሳችንን እንድንጠይቅ ሊያደርገን ይገባል:- ‘ስለ ራሴም ሆነ በጓደኝነት ስለምመርጣቸው ሰዎች ምን ማለት ይቻላል? በሥነ ምግባር በዘቀጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ስኖር በአኗኗሬ ከሌሎች የተለየሁ ሆኜ እታያለሁ?’—1 ጴጥሮስ 4:3, 4

በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ ለመኖር ያለብን ትግል

በዙሪያችን ያለው ዓለም በሥነ ምግባር የተበላሸ ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለብን’ ሆነን እንድንገኝ ያስተምረናል። ይህን ለማድረግ ምንጊዜም “የሕይወትን ቃል” አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል። (ፊልጵስዩስ 2:15, 16) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ክርስቲያኖች በሥነ ምግባር ብልግና ሳይበከሉ መኖር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይጠቁመናል። ክርስቲያኖች በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነው መኖር ከፈለጉ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት በጥብቅ መከተልና ቃሉ የያዘው የሥነ ምግባር መሥፈርት ከሁሉ የተሻለ የሕይወት መመሪያ መሆኑን አምነው መቀበል ይኖርባቸዋል።

“የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ሰዎች ከእርሱ ወገን እንዲሰለፉ ለማድረግ ይጥራል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን ‘የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን እንደሚለውጥ’ ይናገራል። እርሱ የሚያደርገውን በማድረግ የሚያገለግሉት ሰዎችም ቢሆኑ ከእርሱ የተለዩ አይደሉም። (2 ቆሮንቶስ 11:14, 15) እነዚህ አገልጋዮች፣ ሰዎች ነጻነትና ደስታ እንደሚያገኙ ቃል ይገባሉ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች” ናቸው።—2 ጴጥሮስ 2:19

እንዲህ ዓይነቱ ማባበያ ሊያታልልህ አይገባም። የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ችላ የሚሉ ሰዎች አሳዛኝ ውጤት ይገጥማቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ “ሥርዐትህን ስለማይሹ፣ ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 119:155፤ ምሳሌ 5:22, 23) ይህን አባባል እናምንበታለን? ከሆነ አእምሯችንንና ልባችንን ጎጂ ከሆኑ ፕሮፓጋንዳዎች እንጠብቅ።

ይሁን እንጂ ብዙዎች ‘የማደርገው ነገር በሕግ የሚያስጠይቅ እስካልሆነ ድረስ ምንም ችግር የለውም’ የሚል የተሳሳተ አመለካከት አላቸው። ሆኖም እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል አይደለም። በሰማይ የሚኖረው አባታችን በፍቅር ተነሳስቶ የሥነ ምግባር ደንቦችን ሰጥቶናል። ይህን ያደረገው አንተን ለመጠበቅ እንጂ ሕይወት አሰልቺ እንዲሆንብህና ነጻነት እንድታጣ ብሎ አይደለም። አንተን ‘የሚበጅህን ያስተምርሃል።’ በተጨማሪም ክፉ ነገር እንዳይደርስብህ እንዲሁም በሕይወትህ ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው አምላክን ማገልገል “ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ” እንዲኖረን ያደርጋል። አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘው የዘላለም ሕይወት ማለትም ‘እውነተኛው ሕይወት’ ይህ ነው!—ኢሳይያስ 48:17, 18፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 6:19

የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች የተማርነውን ተግባራዊ አለማድረጉ ውሎ አድሮ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር አወዳድረው። አምላክን በመስማት የእርሱን ሞገስ ማግኘት በእርግጥም ከሁሉ የተሻለ የሕይወት መንገድ ነው! አምላክ “የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል” በማለት ቃል ገብቷል።—ምሳሌ 1:33

በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆነ ሕዝብ

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓለም ሲጠፋ ክፉ ሰዎች እንደማይኖሩ ይናገራል። በተጨማሪም “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ” ይላል። (መዝሙር 37:10, 11፤ ምሳሌ 2:20-22) ፈጣሪያችን የሚያስተምረውን ጤናማ ትምህርት የማይከተሉትን ጨምሮ ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ የሚመላለሱ በሙሉ ስለሚጠፉ ምድራችን ንጹሕ ትሆናለች። አምላክን የሚያፈቅሩ ሰዎች መላዋን ምድር በማልማት ቀስ በቀስ ወደ ገነትነት ይለውጧታል። ይህች ገነት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ይኖሩባት ከነበረችው ገነት ጋር ተመሳሳይ ትሆናለች።—ዘፍጥረት 2:7-9

ገነት በሆነችው ውብ ምድር ላይ መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን ገምት! በዚያ ለመኖር ከሚታደሉት መካከል ከሞት የሚነሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል። አምላክ እንዲህ በማለት የሰጣቸውን ተስፋዎች ልብ በል:- “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።” “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዓለም በጠፋበት ወቅት አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ሰዎች ተርፈዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ ዓለም ከጠፋ በኋላ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች