በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግርማ ሞገስ የተላበሰ ግዙፍ ቋጥኝ

ግርማ ሞገስ የተላበሰ ግዙፍ ቋጥኝ

ግርማ ሞገስ የተላበሰ ግዙፍ ቋጥኝ

ካናዳ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ለብዙ ዘመናት ለዓሣ አጥማጆችም ሆነ ለባሕረተኞች አቅጣጫ የሚጠቁም አስተማማኝ ምልክት ሆኖ አገልግሏል። ገጣሚዎች፣ ጸሐፊዎችና አርቲስቶች በሥራቸው አሞግሰውታል። አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ ይህን ግዙፍ ቋጥኝ “ምስጢራዊና ፍጹም ማራኪ” ሲል ገልጾታል። በሴንት ሎውረንስ ባሕረ ሰላጤ፣ በጋስፔ ባሕረ-ገብ መሬት ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ የሚገኘው ፐርስ ሮክ የተባለው ግዙፍ ቋጥኝ፣ በሚያንጸባርቀው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ሰማያዊ ውኃ ላይ ግርማ ሞገስ ተላብሶ ቆሟል። ይህ ግዙፍ ቋጥኝ ርዝመቱ 430 ሜትር፣ ወርዱ ደግሞ 90 ሜትር ገደማ ሲሆን ቁመቱ ከ88 ሜትር ይበልጣል።

በአንድ ወቅት፣ ደፋር የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቀጥ ብሎ የቆመውን አቀበት ወጥተው ከወፎች ጎጆ እንቁላል ይለቅሙ ነበር። ይሁን እንጂ በ1985 የክዊቤክ መንግሥት ይህንን ግዙፍ ቋጥኝና፣ ቋጥኙን መኖሪያቸው ያደረጉትን ወፎች ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ፐርስ ሮክና በአቅራቢያው የሚገኘው ቦናቬንቸር ደሴት ወፎች የሚጠበቁበት ክልል እንዲሆን ደነገገ። የሰሜኑ ጋኔት የተባለው የባሕር ወፍ በብዛት ከሚራባባቸው በዓለም የሚገኙ ሥፍራዎች መካከል ሁለተኛ ደረጃ የያዘው የቦናቬንቸር ደሴት ነው።

አንዳንዶች፣ ፐርስ ሮክ በጥንት ጊዜ ከደረቁ መሬት ጋር የተያያዘ እንደነበረና እስከ አራት የሚደርሱ መሹለኪያ ቅስቶች እንደነበሩት ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ ግን በባሕሩ በኩል ባለው የቋጥኙ ጫፍ ላይ ከሚገኘው ከ30 ሜትር በላይ ስፋት ካለው አንድ ቅስት በቀር ሌሎቹ ተደፍነዋል። የባሕሩ ውኃ በሚሸሽበት ጊዜ የአሸዋ ደለል ግዙፉን ቋጥኝ ከደረቁ ምድር ጋር ያገናኘዋል። ውኃው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለአራት ሰዓት ያህል ስለሚቆይ ደፋር የሆኑ ሰዎች እስከ ቋጥኙ ግርጌ ድረስ በእግራቸው መጓዝ ይችላሉ። ከዚያም ቅስቱ ጋር ለመድረስ ለ15 ደቂቃ ያህል በውኃው ውስጥ እየተደነቃቀፉና እየተንቦራጨቁ በቋጥኙ ግርጌ ጥግ ጥጉን ይሄዳሉ።

ጀብደኛ የሆኑ ጎብኚዎች ሊጠነቀቁበት የሚገባ ነገር አለ። ተፈረካክሰው በወደቁ አለቶች ላይ እየተረማመደ በከባድ ትግል ውኃው ወደሚሾልክበት ቅስት የደረሰ አንድ ጎብኚ እንዲህ ብሏል:- “በየተወሰነ ደቂቃው አለቶች እየተናዱ ወደ ውኃው ሲገቡ አነስተኛ የቦምብ ፍንዳታ የሚመስል . . . አስፈሪ ድምፅ ይሰማል። አንዱ አለት ከሌላው ጋር ሲጋጭ ጥይት የተተኮሰ ይመስላል።”

ብዙ ጎብኚዎች እንዳስተዋሉት ፐርስ ሮክ እጅግ የሚማርክ ውበት አለው። ሆኖም ይህ ውበት ዕጹብ ድንቅ የሆነችው ምድራችን ከምትለግሳቸው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መስህቦች መካከል አንዱ ብቻ ነው። የምድራችን መስህቦች ዓይነታቸውም ሆነ ብዛታቸው ለቁጥር የሚያዳግት ነው። አንተም ብትሆን እንደነዚህ ዓይነት ቦታዎችን ስትመለከት ‘የአምላክን ድንቅ ሥራዎች ቆም ብለህ ለማሰብ’ ተገፋፍተህ ይሆናል።—ኢዮብ 37:14

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Mike Grandmaison Photography