በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጨርቅ ማቅለም—ጥንትና ዛሬ

ጨርቅ ማቅለም—ጥንትና ዛሬ

ጨርቅ ማቅለም—ጥንትና ዛሬ

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ቀለማት በስሜታችን ላይ ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጡ አስተውለሃል? በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች ጨርቆች ቀለም እንዲኖራቸው ለማድረግ ማቅለም የሚባለውን ሂደት ሲጠቀሙ መኖራቸው ምንም አያስደንቅም።

ልብሶችንና ቁሳቁሶችን ወይም እነዚህን ለመሥራት የሚያገለግሉ ብትን ጨርቆችን ስንገዛ ቀለማቸው የማይለቅ መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። ጨርቆች ቀለም እንዲይዙ ለማድረግ የሚሠራበትን ሂደትና ባሕላዊ የማቅለም ዘዴዎች እንዴት እያደጉ እንደመጡ ለማወቅ በሰሜን እንግሊዝ ብራድፈርድ ከተማ የሚገኝ አንድ የአቅላሚዎች ማኅበር ያዘጋጀውን የቀለማት ሙዚየም ጎበኝተን ነበር። * በዚያም ለብዙ ዘመናት ጨርቅን ለማቅለም ሲያገለግሉ የነበሩ እምብዛም የማይታወቁ የአንዳንድ ንጥረ ነገሮችን ናሙና ተመልክተናል።

ባለፉት ዘመናት ጥቅም ላይ የዋሉ ማቅለሚያዎች

እስከ 19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ ጨርቆችን ለማቅለም የሚያገለግሉት ንጥረ ነገሮች ሙሉ በሙሉ የሚገኙት እንደ ዕፅዋት፣ ነፍሳትና ጠንካራ ሽፋን ያላቸው የባሕር እንስሳት ከመሳሰሉ የተፈጥሮ ምንጮች ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሰማያዊ ቀለም የሰናፍጭ ዝርያ ከሆነ ተክል (1)፣ ቢጫ ቀለም ዌልድ ከተባለ ተክል (2)፣ እንዲሁም ቀይ ቀለም እንሶስላን ከሚመስል ተክል ይገኝ ነበር። ሎግዉድ ከተባለ ዛፍ ጥቁር ቀለም ይገኛል። አርኪል ተብሎ የሚጠራ የሻጋታ ዓይነት ፈዛዛ የወይን ጠጅ ቀለም ለመሥራት ያገለግላል። ሙሬክስ ከተባለው የባሕር ቀንድ አውጣ ዛጎል ደግሞ በጣም ውድ የሆነ የጢሮሱ ወይን ጠጅ በመባል የሚታወቅ ደማቅ ወይን ጠጅ ቀለም ማውጣት ይቻላል (3)። ይህ ቀለም ሮማውያን ነገሥታት የሚለብሷቸውን አልባሳት ለማቅለም ያገለግል ነበር።

የሮም ነገሥታት ከመነሳታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት፣ ታዋቂና ሀብታም የሆኑ ሰዎች ተፈጥሯዊ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የተቀለሙ አልባሳት ይለብሱ ነበር። (አስቴር 8:15) ለምሳሌ ቀይ ቀለም ከርመስ ከተባሉት እንስት ነፍሳት ይመረት ነበር (4)። በጥንቷ እስራኤል ቤተ መቅደስ የሚገኙትን ዕቃዎችና የሊቀ ካህናቱን አልባሳት ለማዘጋጀት ያገለገለው ቀይ ማግ የተቀለመው ከእነዚህ ነፍሳት በተገኘው ቀለም ሳይሆን አይቀርም።—ዘፀአት 28:5፤ 36:8

የማቅለም ሂደት

በሙዚየሙ ውስጥ ለእይታ የቀረቡት ነገሮች እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ የማቅለም ሂደቶች፣ ክር ወይም ጨርቅ በማቅለሚያ ውሁድ ውስጥ ከመንከር ያለፈ ብዙ ሥራ ማከናወን ይጠይቃሉ። በአብዛኛው በማቅለሙ ሂደት ላይ ቀለሙ ከክሩ ጋር እንዲጣበቅ የማድረግ ኃይል ያለው ኬሚካል መጠቀም ያስፈልጋል። ይህን ኬሚካል መጠቀም ክሩ ቀለም እንዲይዝ ከማድረጉም በላይ በውኃ ሲታጠብ ቀለሙ እንዳይለቅ ይረዳዋል። ለዚህ ዓላማ የሚውሉ የተለያዩ ኬሚካሎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ አንዳንዶቹ አደገኛ ናቸው።

አንዳንድ የማቅለም ሂደቶች መጥፎ ሽታ ይፈጥራሉ። ተርኪ ሬድ በተባለው ደማቅ ቀይ ቀለም ለመንከር የሚከናወነው ረጅምና ውስብስብ ሂደት ከእነዚህ መካከል የሚጠቀስ ነው። ከጥጥ የተሠሩ ጨርቆችን ለማቅለም የሚውለው ይህ ደማቅ ቀይ ቀለም በፀሐይ፣ በእጥበትና በማንጫ ኬሚካሎች እንኳ አይለቅም። በአንድ ወቅት ይህ የማቅለም ሂደት እስከ አራት ወር የሚፈጁ 38 ደረጃዎች ነበሩት! በሙዚየሙ ለእይታ ከቀረቡት በጣም የሚያማምሩ ልብሶች መካከል አንዳንዶቹ በዚህ ቀለም የተነከሩ ናቸው (5)

ሰው ሠራሽ ማቅለሚያዎች ተፈለሰፉ

ሰው ሠራሽ የሆነው የመጀመሪያው ማቅለሚያ የተፈለሰፈው በ1856 በዊልያም ሄንሪ ፐርኪን ነው። ፐርኪን ሞቭ ወይም ሞቪን ብሎ የጠራውን ደማቅ ወይን ጠጅ ቀለም እንዴት እንደሠራ በሙዚየሙ ማብራሪያ ተሰጥቶ ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ደማቅ የሆኑ ብዙ ሰው ሠራሽ ማቅለሚያዎች ተመርተው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከ8,000 የሚበልጡ አርቲፊሻል ማቅለሚያዎች አሉ (6)። አሁንም ድረስ በብዛት የሚሠራባቸው ተፈጥሯዊ ማቅለሚያዎች ሎግዉድ እና ከነፍሳት የሚመረተው ካቺኒል ብቻ ናቸው።

ሙዚየሙ እንደ ሬዮን ያሉ ሰው ሠራሽ ጨርቆችን ለማቅለም በዛሬው ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ልዩ የአሠራር ሂደቶች አብራርቷል። አሁን በጣም ተወዳጅ የሆነው ቪስኮስ የተባለው የሬዮን ዓይነት ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ የዋለው በ1905 ነበር። ቪስኮስ ሬዮን በኬሚካላዊ ይዘቱ ከጥጥ ጨርቅ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ በዚያን ጊዜ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩትን ማቅለሚያዎች መጠቀም ተችሏል። ይሁንና እንደ አሲቴት ሬዮን፣ ፖሊስተር፣ ናይለን እና አክሬሊክስ ለመሰሉት ይበልጥ ዘመናዊ የሆኑ ሰው ሠራሽ የጨርቅ ዓይነቶች በርካታ አዳዲስ ማቅለሚያዎችን ማምረት አስፈላጊ ሆኗል።

የማይለቁ ቀለሞችን ለማምረት የተደረገ ጥረት

ቀለማቸው የሚለቅ ልብሶችን ወይም ጨርቆችን መግዛት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ይሁንና ብዙዎቹ ጨርቆች በፀሐይ ብርሃን ወይም እንደ ሳሙና ባሉ ኬሚካሎች በተደጋጋሚ ከታጠቡ ቀለማቸው ይለቃል። አንዳንድ ጨርቆች በላብ ምክንያት ወይም ከሌሎች ልብሶች ጋር ሲታጠቡ ቀለማቸው ሊቀየር ይችላል። አንድ ጨርቅ ሲታጠብ ቀለሙ መልቀቅ አለመልቀቁ የተመካው የማቅለሚያው ሞለኪውሎች ከክሩ ጋር በተጣበቁበት መጠን ላይ ነው። ጨርቁ በተደጋጋሚ መታጠቡና የመነቸከ ቆሻሻ በሚያስለቅቁ ሳሙናዎች መፈተጉ ቀለሙ እየለቀቀ እንዲሄድ ያደርገዋል። ቀለም አምራቾች ምርቶቻቸው ደረጃውን በጠበቀ መጠን የፀሐይ ብርሃንን፣ እጥበትን፣ ሳሙናዎችንና ላብን መቋቋም የሚችሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ፍተሻ ያደርጋሉ።

የቀለማት ሙዚየሙን መጎብኘታችን ልብሶቻችን ከምን እንደተሠሩ ይበልጥ እንድናስተውል አድርጎናል። ከዚህም በላይ ልብሶቻችን በተደጋጋሚ ቢታጠቡም ቀለማቸው እንዳይለቅ የሚያደርጉትን የረቀቁ ዘዴዎች እንድናውቅ አስችሎናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ሶሳይቲ ኦቭ ዳየርስ ኤንድ ከለሪስትስ የተባለው ይህ የአቅላሚዎች ማኅበር የቀለማትን ሳይንስ ለማሳደግ ይሠራል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከ1-4 ያሉት ፎቶዎች:- Courtesy of the Colour Museum, Bradford (www.colour-experience.org)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶ ቁጥር 5:- Courtesy of the Colour Museum, Bradford (www.colour-experience.org); ፎቶ ቁጥር 6:- Clariant International Ltd., Switzerland