በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በካናዳ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ለኤሌክትሪክ ፍጆታ ከሚያወጡት ገንዘብ ውስጥ 5 በመቶ የሚያህለውን የሚከፍሉት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሣሪያዎች ያለ አንዳች አገልግሎት በርተው በሚቆዩበት ጊዜ ለሚባክነው የኃይል መጠን ነው።ናሽናል ፖስት፣ ካናዳ

የሕዝብ አስተያየትን መሠረት ያደረገ አንድ ጥናት እንደጠቆመው ሩሲያውያን፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለው ከሚጠቅሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል “ሙስናን” መዋጋት እና “የዋጋ ንረትን ማረጋጋት” ይገኙበታል።ፕራዳ፣ ሩሲያ

አንድ ጥናት እንዳመለከተው በታይዋን ከ5ኛና ከ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ 26.4 በመቶ የሚሆኑት “ራሳቸውን የማጥፋት ሐሳብ ይመጣባቸዋል።”ዘ ቻይና ፖስት፣ ታይዋን

“በዩናይትድ ስቴትስ ቴክኖሎጂው በአንድ መቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ አማካዩን ሳምንታዊ የሥራ ቀን በ38 በመቶ ለመቀነስ የረዳ ቢሆንም ሠራተኞች ትርፍ ጊዜ ሊኖራቸው አልቻለም፤ ለዚህ ዋነኞቹ ምክንያቶች ወደ ሥራ ለመመላለስ ረጅም ሰዓት የሚያጠፉ መሆኑ፣ ብዙ አዋቂ ሰዎች ትምህርት መጀመራቸውና የቤት ውስጥ ሥራ መጨመሩ ናቸው።”ፎርበስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ከ2003 እስከ 2004 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አየር የተለቀቀው የአካባቢን ሙቀት የሚጨምር ጋዝ መጠን በ1.6 በመቶ ጨምሯል። ይህም “ከአሥር በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ከታየው መጠን ከፍተኛው ነው።”ሮይተርስ፣ ኦስሎ፣ ኖርዌይ

ቻይና የውኃ ችግር ገጠማት

ቻይና “በውኃ ብክለትና በንጹሕ ውኃ እጥረት” እየተሠቃየች ነው። አብዛኞቹ ከተሞች ቆሻሻ ውኃን አጣርቶ እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል መሣሪያ ያላቸው ቢሆንም ብዙዎቹ እነዚህን መሣሪያዎች የሚያንቀሳቅሱበት ገንዘብ የላቸውም። “አብዛኞቹ የአገሪቱ ወንዞች፣ ሐይቆችና ግድቦች ከኢንዱስትሪዎችና ከመኖሪያ ቤቶች በሚወጣ ቆሻሻ ውኃ እንዲሁም ከእርሻዎች ላይ በጎርፍ ተጠርገው በተወሰዱ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች የተበከሉ ናቸው” በማለት ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው መጽሔት ዘግቧል። ከዚህም በላይ “ወደ 300 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለመጠጥ የሚሆን ንጹሕ ውኃ አያገኝም።” ይህ መጽሔት ሁኔታውን “አስከፊ” በማለት የገለጸው ሲሆን ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው።

“እናንተ እነማን ናችሁ? የይሖዋ ምሥክሮች?”

ባለፈው ዓመት የማሳ ማሪቲማ ፒዮምቢኖ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ያቀረቡላቸውን ጥሪ የተቀበሉ ወጣት ካቶሊኮች ኤልባ በተባለች አንዲት ትንሽ የጣሊያን ደሴት የባሕር ዳርቻ ላይ እየተዝናኑ የነበሩ አገር ጎብኚዎችን ቀርበው አነጋግረዋቸው ነበር። ጳጳሱ፣ ወጣቶቹ ክርስቲያኖች ነን የሚሉና በክርስቲያንነታቸው መቀጠል የሚፈልጉ ከሆነ እምነታቸውን ለሌሎች ማሳወቅ እንዳለባቸው ነግረዋቸው ነበር። ይህ ሁኔታ ጎብኚዎቹን አስገረማቸው። ኢል ቴምፖ የተሰኘው ጋዜጣ በዘገበው መሠረት በአብዛኛው ወጣቶቹ ያገኙት ምላሽ “እናንተ እነማን ናችሁ? የይሖዋ ምሥክሮች?” የሚል ነበር።

ወሲባዊ ይዘት ያለው ሙዚቃ

“ጸያፍና ስለ ወሲብ የሚያወሱ ግጥሞች” ያላቸውን ሙዚቃዎች የሚያዳምጡ ወጣቶች “ሌላ ዓይነት ዘፈኖችን ከሚመርጡት ወጣቶች” ቀደም ብለው “የጾታ ግንኙነት መፈጸም ሊጀምሩ” እንደሚችሉ አሶሺየትድ ፕሬስ ያቀረበው አንድ ጥናት አመልክቷል። በተጨማሪም “ወንዶች ‘የጾታ ስሜት እንደሚያስቸግራቸው፣’ ሴቶች ደግሞ ይህንን ስሜት ለማርካት እንደተፈጠሩ አድርገው የሚገልጹ ብሎም ወሲባዊ ድርጊቶችን በግልጽ የሚጠቅሱ ዘፈኖች ስለ ወሲብ በግልጽ ከማይናገሩና ጾታዊ ቅርርብን ከዘላቂ ቁርኝት አንጻር ከሚጠቅሱ ዘፈኖች ይልቅ ያለ ዕድሜ ወሲባዊ ስሜትን የመቀስቀስ ኃይላቸው ከፍተኛ ነው” በማለት ተናግሯል። ዘገባው “ወላጆች፣ አስተማሪዎችና ወጣቶቹ ራሳቸው የሙዚቃው ግጥሞች ስለሚያስተላልፏቸው መልእክቶች በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልጋቸዋል” በማለት መክሯል።

አባካኝ ተመጋቢዎች

በ2004 አውስትራሊያውያን 4.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ምግብ ሳይጠቀሙበት እንደጣሉ ዚ አውስትራሊያ ኢንስቲትዩት የተሰኘ የምርምር ተቋም ዘገበ። ይህም አውስትራሊያውያን በ2003 ወደ ውጭ ከላኩት የእርዳታ ገንዘብ ከ13 እጥፍ የሚበልጥ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ አውስትራሊያውያን ፈጽሞ ወይም እምብዛም ላልተጠቀሙባቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች በየዓመቱ ያወጡት ወጪ 8.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል። ይህ የገንዘብ መጠን አገሪቱ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለመንገድ ሥራ ከምታወጣው ወጪ የሚበልጥ ነው።