በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእሳት እራት ለእራት

የእሳት እራት ለእራት

የእሳት እራት ለእራት

ዛምቢያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አንዳንድ ሰዎች ትል መብላት ይቅርና ማሰቡ እንኳ ይከብዳቸዋል። ሌሎች ግን እንደነዚህ ያሉ አጥንት አልባ ነፍሳትን መብላት ያስደስታቸዋል። በአባጨጓሬነት ደረጃ ላይ የሚገኘውና ኢምብራሲያ ቤሊና በመባል የሚታወቀው የእሳት እራት በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በብዙዎች ዘንድ የሚወደድ ምግብ ነው። በዚያ አካባቢ ይህ ትል ሞፔን ከሚባል ዛፍ ላይ ስለማይጠፋ በአብዛኛው ሞፔን በመባል ይታወቃል። በርካታ የገጠር ማኅበረሰቦች እጥፍ ዘርጋ እያለ የሚጓዘውን ይህን ገንቢ ምግብ መሰብሰብ የሚጀምሩበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት ይጠባበቃሉ። የካላሃሪ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ኬት ሌገት የተባሉ ሰው እነዚህን አባጨጓሬዎች አስመልክተው ሲናገሩ “ከፍተኛ የፕሮቲን ምንጮች ናቸው” ብለዋል። በተጨማሪም ትሎቹ ብዙውን ጊዜ ደረቅ የሆነውንና ለምነት የጎደለውን በሣር የተሸፈነ ምድር ሥነ ምሕዳር በመጠበቅ ረገድ ጠቃሚ ሚና ይጫወታሉ።

በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ዝናብ ደቡባዊ አፍሪካን በስፋት ሲያዳርስ መሬቱ እንደገና ሕይወት ይዘራል። በዚህ ወቅት መሬት ውስጥ ተቀብረው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙሽሬዎች የሚያማምሩ እሳት እራቶች ይሆናሉ። በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጥቃቅን እንቁላሎቻቸው እድገት አድርገው ወደ እጭነት ይቀየራሉ፤ ከዚያም በቀለማት ያሸበረቁ አባጨጓሬዎች ይሆናሉ። እነዚህ ፈርጠም ፈርጠም ያሉ አባጨጓሬዎች ሲታዩ ቋሊማ ይመስላሉ።

እንደ ካሳቫና በቆሎ ያሉ በስታርች የበለፀጉ ሰብሎች በሚዘወተሩባቸው አካባቢዎች አባጨጓሬዎቹ ተጨማሪ ምግብ ሆነው ያገለግላሉ። ብዙዎቻችን እነዚህን አባጨጓሬዎች ከዚህ ቀደም በምግብነት አናውቃቸው ይሆናል፤ ሆኖም ከ60 በመቶ በላይ የሆነ የፕሮቲን ይዘት ያላቸው መሆኑ በተለይ ምርጥ ፕሮቲን ውድ በሆነባቸው ወይም እንደልብ በማይገኝባቸው አካባቢዎች የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ለምግብነት የሚውሉ አባጨጓሬዎች ከሥጋ ወይም ከዓሣ የማይተናነስ የምግብ ይዘት ስላላቸው አንድ አዋቂ ሰው በየዕለቱ ከሚያስፈልገው የፕሮቲን፣ የቫይታሚንና የማዕድን ፍጆታ ውስጥ ሦስት አራተኛውን ማሟላት ይችላሉ። አዎን፣ እነዚህ ጥቃቅን ፍጥረታት በጣም ገንቢ ምግብ ናቸው!

ለገበያ የሚሆን እህል የሚያመርቱ ገበሬዎች በማዕድናት በበለጸጉት በእነዚህ ነፍሳት ላይ የከፈቱት ኬሚካላዊ ጦርነት አባጨጓሬ ተመጋቢዎችን ግራ እንዳጋባቸው ጥርጥር የለውም። በሚሊዮን የሚቆጠሩት እነዚህ ፍጥረታት ምግባቸውን ሲበሉ ብዙውን ጊዜ ለምግብነት የማይውሉትንና አንዳንዴም መርዛማነት ያላቸውን ቅጠሎች ጠቃሚ ወደሆነ መኖነት ይለውጧቸዋል። ይህን ሁሉ ለማከናወን ግን ውድ የሆነ የግብርና መሣሪያ አይጠቀሙም፤ እንዲሁም እንደ እንስሳት ሐኪሞች ክፍያ አይጠይቁም! በእጅ የሚሰበሰቡት አባጨጓሬዎች ብዙ ውጣ ውረድ የማይጠይቁ በጣም ጠቃሚ ምግብ ናቸው።

ሞፔን ትሎች ጠፍ የሆነውን መሬት ወደ ለምነት በመቀየር እንዲሁም የአካባቢውን ሥነ ምሕዳራዊ ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዲህ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የአፍሪካ ዝሆን ግዙፍነትና የምግብ ፍጆታው በጣም አስደናቂ ቢሆንም ምግብን የማዋሃድ ብቃቱ ከሞፔን ትል ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አባጨጓሬዎች ከዝሆኖች ጋር በተመሳሳይ የግጦሽ መሬት ላይ ቢሰማሩ አጭር በሆነው የስድስት ሳምንታት ዕድሜያቸው ውስጥ ከዝሆኖቹ በአሥር እጥፍ የሚበልጥ ሣርና ቅጠል እምሽክ አድርገው ሊበሉና አራት እጥፍ የሚሆን ፍግ ሊያመርቱ ይችላሉ። አንድ አባጨጓሬ ሲያድግ መጠኑ ሲቀፈቀፍ ከነበረው 4,000 ጊዜ ያህል የሚበልጥ መሆኑ እምብዛም አያስገርምም! በመሆኑም አባጨጓሬዎችን ጥርግ አድርጎ መሰብሰብ በአፈሩ ለምነትና በአካባቢው ሥነ ምሕዳራዊ ሚዛን ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ለመሆኑ እነዚህ አባጨጓሬዎች የሚሰበሰቡት እንዴት ነው? በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች በዓመቱ ውስጥ ዝናብ በሚጥልባቸው ሁለት ወቅቶች የሞቴን ትሎችን ይሰበስባሉ። ትሎቹን ለተወሰኑ ሳምንታት ይሰበስቡና የሆድ ዕቃቸውን አውጥተው ይቀቅሏቸዋል፤ ከዚያም እንዲደርቁ ያሰጧቸዋል። ይሁን እንጂ ለምግብነት ከሚውሉት የሞፔን ትል ዝርያዎች መካከል አንዳንዶቹን መሰብሰብም ሆነ ማዘጋጀት ልዩ ጥንቃቄ ይጠይቃል። አንዳንድ የአባጨጓሬ ዓይነቶች ለመከላከያነት የሚያገለግላቸው ወይም መልክ የሚጨምርላቸው ፀጉራቸው መወገድ ይኖርበታል። በተጨማሪም አንዳንዶቹ አባጨጓሬዎች ለሰው መርዛማነት ያላቸውን ተክሎች ስለሚመገቡ እነርሱን ለምግብነት ማዘጋጀቱ ጥንቃቄ ያሻዋል። አባጨጓሬዎች ከተበለቱና ከደረቁ በኋላ ከርሸም ከርሸም እየተደረጉ ሊበሉ ቢችሉም ብዙውን ጊዜ ወጥ ውስጥ ይጨመራሉ አሊያም ከቲማቲምና ከቀይ ሽንኩርት ጋር ተጠብሰው ይቀርባሉ።

ይህን ጽሑፍ ካነበብክ በኋላ አባጨጓሬዎችን የመብላቱን ሐሳብ ለመሞከር ትነሳሳ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ይህን የባዕድ አገር ምግብ የመብላት ሐሳቡ እንኳ ያንገሸግሽህ ይሆናል። ይሁን እንጂ በአፍሪካ ለሚኖሩ በርካታ ቤተሰቦች ከፍተኛ የፕሮቲን ምንጭ እንደሆኑና ገቢ እንደሚያስገኙ አትዘንጋ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሞፔን ትል ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው መሆኑ ተፈላጊነቱን ከፍ ያደርገዋል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሞፔን ትል አጭር በሆነው የስድስት ሳምንት ዕድሜው፣ መጠኑ ሲቀፈቀፍ ከነበረው 4,000 ጊዜ ያህል ይጨምራል