በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል?

ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል?

የሚከተሉትን ጥያቄዎች በደንብ አስቡባቸውና መልስ ስጡ:-

አሁን ካላችሁ አመለካከት አንጻር የትዳር ጓደኛችሁ እንዲሆን የምታስቡት ሰው ሊያሟላቸው ይገባል የምትሏቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ከታች በሰፈረው ዝርዝር ላይ በጣም አስፈላጊ ናቸው በምትሏቸው አራት ባሕርያት ላይ ምልክት አድርጉ።

․․․․․․ መልከ ቀና

․․․․․․ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው

․․․․․․ ተግባቢ

․․․․․․ እምነት የሚጣልበት

․․․․․․ ተወዳጅ

․․․․․․ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው

․․․․․․ ተጫዋች

․․․․․․ ሕይወቱን በግብ የሚመራ

ገና ለጋ ወጣት ሳላችሁ የወረት ፍቅር ይዟችሁ ያውቃል? ከላይ ከተገለጹት መካከል በዚያን ወቅት ያንን ሰው በጣም እንድትወዱት ባደረጋችሁ ባሕርይ ላይ ምልክት አድርጉ።

ላይ ከተጠቀሱት ባሕርያት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ መጥፎ አይደሉም። ሁሉም ደስ የሚሉ ናቸው። ሆኖም ለጋ ወጣት ሳላችሁ የወረት ፍቅር በያዛችሁ ወቅት ያንን ሰው የወደዳችሁት በስተግራ በኩል እንደተጠቀሱት ባሉ ቶሎ ትኩረትን በሚስቡ ባሕርያት ተማርካችሁ ነው ቢባል አትስማሙም?

እያደጋችሁ ስትመጡ ግን ግለሰቡ በስተቀኝ በኩል እንደተጠቀሱት ያሉ በጣም አስፈላጊ ባሕርያት ይኖሩት እንደሆነ ለመመርመር የማስተዋል ችሎታችሁን መጠቀም ትጀምራላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ በሰፈራችሁ ውስጥ በጣም ቆንጆ የምትባለው ልጅ እምነት የሚጣልባት እንዳልሆነች ወይም በክፍላችሁ ውስጥ በጣም ተወዳጅ የሆነው ልጅ ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም እንደሌለው መገንዘብ ትጀምሩ ይሆናል። የጾታ ፍላጎት የሚያይልበትን ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ካለፋችሁ’ ‘ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ቶሎ ትኩረትን ከሚስቡ ባሕርያት ይልቅ በውስጣዊ ማንነት ላይ እንደምታተኩሩ የታወቀ ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:36 NW

ማንኛውም ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆን ይችላል?

በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ በተለያዩ ሰዎች ተማርካችሁ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሁሉ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆኑ ይችላሉ ማለት አይደለም። እርግጥ የተሻለ ሰው እንድትሆኑ የሚረዳችሁና እናንተም የተሻለ እንዲሆን የምትረዱት የዕድሜ ልክ ጓደኛ እንደምትፈልጉ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 19:4-6) ታዲያ ይህ ሰው ማን ሊሆን ይችላል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችሁ በፊት ራሳችሁን ‘በመስተዋት መመልከትና’ በሐቀኝነት መመርመር ያስፈልጋችኋል።—ያዕቆብ 1:23-25

ስለ ራሳችሁ ይበልጥ ለማወቅ እንድትችሉ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክሩ:-

ምን ጠንካራ ጎኖች አሉኝ?

․․․․․․

ደካማ ጎኖቼስ ምንድን ናቸው?

․․․․․․

ምን ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች አሉኝ?

․․․․․․

ራስን ማወቅ እንዲህ ቀላል አይደለም፤ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን በመጠየቅ ስለ ራሳችሁ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ትችላላችሁ። * ራሳችሁን ይበልጥ እያወቃችሁ በሄዳችሁ መጠን ደካማ ጎኖቻችሁን በማሻሻል ጠንካራ ጎናችሁን ለማጎልበት የሚረዳችሁን ሰው ለማግኘት የሚያስችል ደረጃ ላይ ትደርሳላችሁ። ታዲያ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆናችሁ የሚችል ሰው እንዳገኛችሁ ቢሰማችሁ ምን ታደርጋላችሁ?

ጓደኝነቱ ዘላቂነት ይኖረው ይሆን?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ ለወደዳችሁት ሰው ሚዛናዊ አመለካከት ይኑራችሁ። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ልታደርጉበት የሚገባችሁ ጉዳይ አለ! ማየት የምትፈልጉትን ብቻ ወደ ማየት ልታዘነብሉ ትችላላችሁ። ስለዚህ አትቸኩሉ፤ ከዚህ ይልቅ የወደዳችሁትን ሰው እውነተኛ ባሕርያት ለመረዳት ሞክሩ።

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት የመሠረቱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ማየት በሚገባቸው ላይ ሳይሆን ከወደዱት ሰው ጋር በሚያመሳስሏቸው ነገሮች ላይ ያተኩራሉ። እነዚህ ሰዎች ‘የሙዚቃ ምርጫችን ተመሳሳይ ነው፣’ ‘የሚያስደስቱን ነገሮች ተመሳሰይ ናቸው፣’ ‘በሁሉም ነገር እንስማማለን!’ ማለት ይቀናቸዋል። ይሁንና ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ካለፋችሁ በውጪያዊ ባሕርያት አትሸነፉም። የግለሰቡን “የውስጥ ሰውነት” ወይም ውስጣዊ ማንነት ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋችኋል።—1 ጴጥሮስ 3:4፤ ኤፌሶን 3:16

ለምሳሌ በምትስማሙባቸው ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በምትጋጩበት ወቅት ግለሰቡ ምን ዓይነት ባሕርይ እንደሚያሳይ ብታስተውሉ ስለ ውስጣዊ ማንነቱ ይበልጥ ማወቅ ትችላላችሁ። በሌላ አባባል፣ ይህ ሰው አለመግባባቶችን የሚፈታው እንዴት ነው? እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ይላል? “ቁጣ” ወይም “ስድብ” ይቀናዋል? (ገላትያ 5:19, 20፤ ቈላስይስ 3:8) ወይስ ነገሩ የምርጫ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ ሰላም ለመፍጠር ሲል ምክንያታዊ ወደ መሆን ያዘነብላል?—ያዕቆብ 3:17 NW

ሌላም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ አለ። ይህ ሰው እናንተን መቆጣጠር ይፈልጋል? ወይም ቀናተኛ ነው? የምታደርጉትን እያንዳንዱን ነገር እንድታሳውቁት ይፈልጋል? ኒኮል የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ለእኔ ብቻ ካልሆናችሁ የሚለው መንፈስና ቅናት ችግር እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው። የት እንደሚሄድ/እንደምትሄድ አልተነገረኝም በሚል ሰበብ የሚጨቃጨቁ ጓደኛሞች እንዳሉ ሰምቻለሁ። እንዲህ ያለው ባሕርይ ችግር መኖሩን የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ ይሰማኛል።”

ሌሎች ስለ ጓደኛችሁ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? ይህን ለማወቅ ግለሰቡን በደንብ የሚያውቁትን በጉባኤው ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ማነጋገሩ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይህ ሰው መልካም ስም እንዳለውና እንደሌለው ሊነግሯችሁ ይችላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2 *

ግንኙነታችሁን ማቋረጥ ይኖርባችሁ ይሆን?

ለጓደኝነት የመረጣችሁት ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ እንደማይሆን ከተገነዘባችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ግንኙነቱን ማቋረጡ ጥበብ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል።—ምሳሌ 22:3 *

ከጊዜ በኋላ ከሌላ ሰው ጋር አዲስ ግንኙነት ትጀምሩ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ጥሩ ተሞክሮ ስለሚኖራችሁ ግንኙነታችሁን በሚመለከት ሚዛናዊ አመለካከት እንደምትይዙ ምንም ጥርጥር የለውም። ምናልባት በዚህ ወቅት “ይህ ሰው ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆነኝ ይችላል?” ለሚለው ጥያቄ አዎን የሚል መልስ ትሰጡ ይሆናል!

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.25 ራሳችሁን የምትጠይቋቸውን ተጨማሪ ጥያቄዎች ለማግኘት በጥር 2007 ንቁ! መጽሔት ገጽ 30 ላይ የሚገኘውን “ለማግባት ዝግጁ ናችሁ?” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከቱ።

^ አን.31 በተጨማሪም ከገጽ 19-20 ላይ ባሉት ሣጥኖች ውስጥ የሚገኙትን ጥያቄዎች ተመልከት።

^ አን.33 ስለዚህ ጉዳይ ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 2001 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 12-14 ላይ ያለውን ሐሳብ ተመልከት።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ጥሩ የትዳር ጓደኛ እንድትሆኑ ሊያደርጓችሁ የሚችሉ ምን ግሩም ባሕርያት አሏችሁ?

▪ የትዳር ጓደኛችሁ እንዲሆን ከምትፈልጉት ሰው የምትጠብቋቸው አንዳንድ ባሕርያት ምንድን ናቸው?

▪ ለጓደኝነት ስለመረጣችሁት ሰው ባሕርይ፣ ሥነ ምግባርና በሌሎች ዘንድ ስላለው ስም ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥሩ ባል ሊሆነኝ ይችላል?

ወሳኝ የሆኑ ነገሮች

ያለውን ሥልጣን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?—ማቴዎስ 20:25, 26

▪ ምን ግቦች አሉት?—1 ጢሞቴዎስ 4:15

▪ ግቦቹ ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረገ ነው?—1 ቆሮንቶስ 9:26, 27

▪ ጓደኞቹ እነማን ናቸው?—ምሳሌ 13:20

▪ ለገንዘብ ምን አመለካከት አለው?—ዕብራውያን 13:5, 6

▪ ምን ዓይነት መዝናኛ ይወዳል? —መዝሙር 97:10

▪ አለባበሱ ምን ይጠቁማል?—2 ቆሮንቶስ 6:3

▪ ለይሖዋ ያለውን ፍቅር የሚያሳየው እንዴት ነው?—1 ዮሐንስ 5:3

በጣም ወሳኝ የሆኑ ነገሮች

▪ ትጉህ ሠራተኛ ነው?—ምሳሌ 6:9-11

▪ በገንዘብ ረገድ ኃላፊነቱን መወጣት ይችላል?—ሉቃስ 14:28

▪ መልካም ስም አለው?—የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2

▪ ወላጆቹን ያከብራል?—ዘፀአት 20:12

▪ ለሌሎች ያስባል?—ፊልጵስዩስ 2:4

ችግር እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶች

▪ መቆጣት ይቀናዋል?—ምሳሌ 22:24

▪ የጾታ ብልግና እንድትፈጽሚ ለማግባባት ይሞክራል?—ገላትያ 5:19

▪ ሌሎችን በድርጊቱም ሆነ በንግግሩ ይጎዳል?—ኤፌሶን 4:31

▪ ካልጠጣ በስተቀር እንደተዝናና አይሰማውም?—ምሳሌ 20:1

▪ ቀናተኛና ራስ ወዳድ ነው?—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥሩ ሚስት ልትሆነኝ ትችላለች?

ወሳኝ የሆኑ ነገሮች

▪ በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ተገዢነቷን የምታሳየው እንዴት ነው?—ኤፌሶን 5:21, 22

▪ አለባበሷ ምን ይጠቁማል?—1 ጴጥሮስ 3:3, 4

▪ ጓደኞቿ እነማን ናቸው?—ምሳሌ 13:20

▪ ለገንዘብ ምን አመለካከት አላት?—1 ዮሐንስ 2:15-17

▪ ምን ግቦች አሏት?—1 ጢሞቴዎስ 4:15

▪ ግቦቿ ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረገች ነው?—1 ቆሮንቶስ 9:26, 27

▪ ምን ዓይነት መዝናኛ ትወዳለች?—መዝሙር 97:10

▪ ለይሖዋ ያላትን ፍቅር የምታሳየው እንዴት ነው?—1 ዮሐንስ 5:3

በጣም ወሳኝ የሆኑ ነገሮች

▪ ትጉህ ሠራተኛ ነች?—ምሳሌ 31:17, 19, 21, 22, 27

▪ በገንዘብ ረገድ ኃላፊነቷን መወጣት ትችላለች?—ምሳሌ 31:16, 18

▪ መልካም ስም አላት?—ሩት 4:11

▪ ወላጆቿን ታከብራለች?—ዘፀአት 20:12

▪ ለሌሎች ታስባለች?—ምሳሌ 31:20

ችግር እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶች

▪ ጨቅጫቃ ነች?—ምሳሌ 21:19

▪ የጾታ ብልግና እንድትፈጽም ለመገፋፋት ትሞክራለች?—ገላትያ 5:19

▪ ሌሎችን በንግግሯም ሆነ በድርጊቷ ትጎዳለች?—ኤፌሶን 4:31

▪ ካልጠጣች በስተቀር እንደተዝናናች አይሰማትም?—ምሳሌ 20:1

▪ ቀናተኛና ራስ ወዳድ ነች? —1 ቆሮንቶስ 13:4, 5