በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድሆች ምን ተስፋ አላቸው?

ድሆች ምን ተስፋ አላቸው?

ድሆች ምን ተስፋ አላቸው?

ተግተው የሚሠሩ ሰዎች የድካማቸውን ያህል የሚከፈላቸው እስከሆነ ድረስ ለመኖር ጠንክሮ መሥራት ምንም ስህተት የለውም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ምን እንዳለ ተመልከት:- “ለሰዎች፣ . . . ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።”—መክብብ 3:12, 13

ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ሠራተኞቹ የሚያገኙት ክፍያ በቂ አይደለም። ይህም ብዙዎቹ በድህነት እንዲማቅቁና የዕለት ኑሯቸውን ማሸነፍ ትግል እንዲሆንባቸው አድርጓል። በዚህም የተነሳ ‘ደስ ለመሰኘትም ሆነ እርካታ ለማግኘት’ አይችሉም። ዓለማችን እጅግ የበለጸገች ብትሆንም በምድር ላይ ከሚኖሩ ሰዎች ግማሽ ያህሉ ከዚህ ሀብት ተጠቃሚዎች አይደሉም።

አምላክ ለድሆች ያስባል

የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ አያስደስተውም። ይሖዋ ለድሆች ይራራል። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] የጭቍኖችንም ጩኸት አልዘነጋም” ይላል። (መዝሙር 9:12) ይሖዋ ለድሆች የሚያስብ አምላክ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ምስኪኑም ራሱን በአንተ ላይ ይጥላል፤ ለድኻ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ” ይላል። (መዝሙር 10:14) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ችግረኛ ስለሆኑ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንደሚናገር ተመልከት። * አዎን፣ አምላክ እያንዳንዱን ሰው የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ስለሚያስፈልገው ወይም ስለሚያስፈልጋት ነገርም ያስባል። ለእርሱ እያንዳንዱ ሰው ውድ ከመሆኑም በላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይሰማዋል። ይሖዋ የተለያየ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች ከእርሱ እንዲማሩ ብሎም ወዳጆቹ እንዲሆኑ ይጋብዛል።

ሰዎች ከአምላክ ሊማሩ የሚገባቸው ነገር ለሌሎች ርኅራኄ ማሳየትንና ችግራቸውን መረዳትን ነው። የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በመካከላቸው እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ስላለ በግለሰብ ደረጃ እርስ በርስ ይከባበራሉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ለተከታዮቹ “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:8) ስለዚህ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ በኑሮ ደረጃ መድልዎ የማይደረግበት የዚህ የወንድማማች ማኅበር አካል ናቸው። አንዱ ለሌላው የሚያስብ ከመሆኑም ሌላ በችግር ጊዜ እርስ በርስ ይበረታታሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ድህነት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቀነስ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ትንባሆ በማጨስና የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ በመጠጣት ሰውነትን ማርከስ በአምላክ ፊት የተጠላ ድርጊት እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 20:1፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) አንድ ሰው በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተመራ የሚኖር ከሆነ ገንዘቡን ጎጂ በሆኑ ልማዶች ከማባከን መቆጠብ ይችላል። ሲጋራ በማጨስ ወይም በስካር ምክንያት ከሚመጡ በሽታዎች ራሱን ከመጠበቁም በላይ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሕክምና ወጪ ከማውጣት ይድናል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ፍቅረ ንዋይንና ስግብግብነትን እንዲያስወግዱ ያስተምራል። (ማርቆስ 4:19፤ ኤፌሶን 5:3) ስለዚህ የአምላክ ቃል በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠውን ምክር የሚቀበል ሰው ቁማር በመጫወት ገንዘቡን አያባክንም።

መጽሐፍ ቅዱስ በከፍተኛ ድህነት የሚማቅቁ ሰዎችም እንኳ በዕለታዊ ሕይወታቸው ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። እስቲ የሚከተሉትን ተሞክሮዎች ተመልከት:-

ከፍተኛ የሥራ አጦች ቁጥር ባለበት አገር በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥራ የምትሠራ አንዲት ሴት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ፈቃድ ጠየቀች። አለቃዋ እንዲህ ያለ ጥያቄ በማቅረቧ ከሥራዋ ሊያባርራት ይችል የነበረ ቢሆንም ፈቃድ መስጠቱ እርሷንም ሆነ ሌሎች ሠራተኞችን አስገረማቸው። ከዚህም በላይ አለቃዋ በፋብሪካው ውስጥ መሥራቷን እንድትቀጥል እንደሚፈልግ የነገራት ከመሆኑም ሌላ “ምሳሌ የምትሆን ሠራተኛ” እንደሆነች በመናገር አወደሳት። እንዲህ ያለው ውጤት ሊገኝ የቻለው ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ይህች ሠራተኛ አኗኗሯ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነበር። “በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር ለመኖር“ ስለምትፈልግ አትዋሽም ወይም አትሰርቅም፤ በመሆኑም በታማኝነት ረገድ ጥሩ ስም አትርፋ ነበር። (ዕብራውያን 13:18) ከዚህም በላይ በቆላስይስ 3:22, 23 ላይ ያለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሠረታዊ ሥርዓት በመታዘዝ ሥራዋን የምታከናውነው ‘በሙሉ ልቧ’ ነበር። ቀጣሪዎቿን በመታዘዝ በእያንዳንዱ የሥራ ቀን በትጋት ለመሥራት ትጥር ነበር።

እርግጥ ነው፣ ዛሬ ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት ራስ ወዳድነት የነገሠበትና ከምንም ነገር በላይ ትርፍ ለማጋበስ ቅድሚያ የሚሰጥበት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ የሚከተሉ ሰዎችም በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስከኖሩ ድረስ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማግኘት ትግል ይጠይቅባቸው ይሆናል። ነገር ግን እንዲህ ያሉ ሰዎች በፈጣሪያቸው ዘንድ ንጹሕ ሕሊና አላቸው፤ እንዲሁም “የተስፋ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ምስጋና ይግባውና ከፊታቸው የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ይጠብቃሉ።—ሮሜ 15:13

ድህነትን ለማስወገድ የሚረዳ ዘላቂ መፍትሔ

ይሖዋ ድሆችን የሚጨቁኑ ሰዎችን እንደሚጠላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ፍትሕ የጐደለውን ሕግ ለሚያወጡ፣ ጭቈና የሞላበትን ሥርዐት ለሚደነግጉ ወዮላቸው! የድኾችን መብት ለሚገፉ፣ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው!” (ኢሳይያስ 10:1, 2) ዛሬ ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚቆጣጠሩት ሰዎች ድሆችን ቸል ያሉት ሆን ብለውም ይሁን ባለማወቅ፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ጨቋኝ የሆነውን ሥርዓት ሲያስወግደው እነርሱንም ያጠፋቸዋል።

ነቢዩ ኢሳይያስ እነዚህን ጨቋኞች እንዲህ በማለት አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ ጠይቋቸዋል:- “በምትጐበኙበት ቀን ምን ይውጣችኋል? ጥፋት ከሩቅ ሲመጣስ ምን ትሆናላችሁ?” (ኢሳይያስ 10:3) ይሖዋ፣ ሰዎች ሕልውናውን ለማራዘም ደፋ ቀና የሚሉለትን ይህን ፍትሕ አልባ ሥርዓት በመደምሰስ እነዚህን ክፉዎች ከምድር ያጠፋቸዋል።

ይሁን እንጂ የአምላክ ዓላማ በጨቋኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከፍትህ መጓደል ነጻ የሆነ ሕይወት እንዲመሩም ያስችላቸዋል። ከሁሉም የተሻለ መንግሥት በመጠቀም የሰው ልጆች በአጠቃላይ አርኪና ከድህነት ነጻ የሆነ አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ ያደርጋል። በዚያን ወቅት ሀብታም ለመሆን በርካታ ገንዘብን በውርስ ማግኘት፣ ከተዋጣላቸው ነጋዴዎች ጋር የንግድ ሽርክና መፍጠር አሊያም ጥሩ ችሎታ ያለህ ነጋዴ መሆን አያስፈልግህም። ታዲያ እነዚህ ለውጦች እንደሚመጡ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

የሰው ዘሮችን እንዲገዛ በይሖዋ የተሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት የሚጠብቀንን አስደናቂ ጊዜ “ዳግመኛ ልደት” በማለት ጠርቶታል። (ማቴዎስ 19:28 የ1954 ትርጉም) ይህ ቃል መታደስን ይኸውም ሕይወትን እንደ አዲስ መጀመርን የሚያመለክት ነው። ኢየሱስ “ዳግመኛ ልደት” የሚለውን ቃል በመጠቀም አፍቃሪው ፈጣሪያችን ይሖዋ፣ ጻድቅ ለሆኑ ሰዎች ከዓላማው ጋር የሚስማማ ሕይወት እንደሚሰጣቸው ጎላ አድርጎ ተናግሯል። ይሖዋ ለሰው ዘሮች ከሚያመጣቸው በርካታ በረከቶች መካከል አንዱ ዛሬ አብዛኛውን የሰው ልጅ የሚደቁሰውን የኢኮኖሚ ችግር ለዘለቄታው ማስወገድ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን አገዛዝ አስመልክቶ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሯል:- “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤ ደማቸውም በእርሱ ፊት ክቡር ነው።”—መዝሙር 72:12-14

ይህን አስደሳች የወደፊት ሕይወት የማግኘቱ አጋጣሚ ለአንተም ክፍት ነው። ነገር ግን በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገውን አምላክ ያወጣውን ብቃት ለማሟላት እውቀት ማግኘትና የእውነተኛውን አምላክ ፈቃድ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ከአምላክ ቃል በምታገኘው እውቀት ላይ ተመሥርተህ ጥበብ ያለበት ውሳኔ አድርግ። አምላክ ለሁሉም የሰው ዘሮች ያዘጋጀውን አስደናቂ ተስፋ በጉጉት ተጠባበቅ። ይህ ተስፋ ሳይፈጸም ቀርቶ በፍጹም አታዝንም። የአምላክ ቃል እንዲህ የሚል ተስፋ ሰጥቷል:- “ችግረኞች ግን መቼም ቢሆን አይረሱም፤ የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም።”—መዝሙር 9:18

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 መዝሙር 35:10 እና መዝሙር 113:7 አምላክ በችግር እየተሠቃዩ ላሉ ሰዎች እንደሚያዝን የሚያሳዩ ሁለት ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወደፊት አስደሳች ሕይወት የማግኘቱ አጋጣሚ ለአንተም ክፍት ነው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወዳላቸው አገሮች መሄድ ይሻለኝ ይሆን?

የአምላክ ቃል ሰዎች የት መኖር ወይም ምን መሥራት እንዳለባቸው አይናገርም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንድ ሰው ያለበትን የገንዘብ ችግር ለማቃለል ወደ ሌላ አገር በመሄድ ረገድ የተሻለ ውሳኔ እንዲያደርግ ይረዱታል። ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎችና ከእነርሱ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልብ በል።

1. እንዲህ ለማድረግ የተነሳሳሁት ስለዚያ አገር የሚወራውን ያልተረጋገጠ ወሬ ሰምቼ ይሆን? ምሳሌ 14:15 “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” በማለት ይናገራል። በምሥራቅ አውሮፓ ይኖር የነበረ አንድ ሰው ወደበለጸገ አገር ከሄደ በኋላ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እዚህ አገር ገንዘብ ዛፍ ላይ እንደሚበቅል ቅጠል እንደሆነ ሲነገር ሰምቼ ነበር፤ ነገር ግን ይኸው እስካሁን እነዚያን ዛፎች አላገኘኋቸውም።”

2. ቤተሰቦቼ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በተመለከተ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት አለኝ? አስፈላጊ በሆኑ ነገሮችና በማይጨበጡ ምኞቶች መካከል ልዩነት እንዳለ ተገንዝቤያለሁ? የቤተሰብ ራሶች ለሚስታቸው እንዲሁም ለልጆቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን የማሟላት ግዴታ አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከዚህም በተጨማሪ አባቶች ለልጆቻቸው ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሥልጠና እንዲሰጧቸው አምላክ ይጠብቅባቸዋል። (ዘዳግም 6:6, 7፤ ኤፌሶን 6:4) አንድ አባት ከቤተሰቡ ርቆ በመሄድ ሰብዓዊ ሥራ ቢሠራ ቁሳዊ ነገሮችን ለልጆቹ ማቅረብ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ለሳምንታት፣ ለወራት ወይም ለዓመታት ከልጆቹ ርቆ የሚቆይ ከሆነ የሚያስፈልጋቸውን ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሥልጠና መስጠት አይችልም።

3. ከባለቤቴ ጋር ለረጅም ጊዜ ተለያይተን መኖራችን በምንዝር እንድንወድቅ ሊያደርገን እንደሚችል ተገንዝቤያለሁ? የአምላክ ቃል የተጋቡ ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው የጾታ ፍላጎት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያሳስባል።—1 ቆሮንቶስ 7:5

4. ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አንድ አገር መግባት ከአገሪቱ ባለ ሥልጣናት ጋር ሊያጋጨኝ እንደሚችል ተረድቻለሁ? እውነተኛ ክርስቲያኖች የአገሪቱን ሕግ ማክበር ይጠበቅባቸዋል።—ሮሜ 13:1-7

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድሃም ሆንን ሀብታም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይጠቅሙናል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ:- © Trygve Bolstad/Panos Pictures