ለገንዘብ ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከት ምንድን ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ለገንዘብ ሊኖረን የሚገባው ተገቢ አመለካከት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ገንዘብ ጥላ ከለላ ነው’ ይላል። (መክብብ 7:12) ገንዘብን ለምግብ፣ ለልብስና ለመጠለያ የሚያስፈልጉንን ወጪዎች ለመሸፈን ስለምንጠቀምበት ከድህነት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚጠብቀን ጥላ ከለላ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ገንዘብ ከቁሳዊ ነገሮች አንጻር ማንኛውንም ነገር ለመግዛት ያስችላል። መክብብ 10:19 “ገንዘብም ካለ ሁሉ ነገር አለ” ይላል።
የአምላክ ቃል ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማሟላት እንድንችል ተግተን እንድንሠራ ያበረታታናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) እውነቱን ለመናገር፣ ሥራችንን ተግተን መሥራታችን የእርካታና የደኅንነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ክብር ያስገኝልናል።—መክብብ 3:12, 13
በተጨማሪም ጠንክረን መሥራታችን በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ለጋስ እንድንሆን ያስችለናል። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) እንዲህ ዓይነቱን ደስታ የምናገኘው ገንዘባችንን ችግር ላይ የወደቁትን በተለይ ደግሞ ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ለመርዳት ስንጠቀምበት ወይም ለምንወደው ሰው ስጦታ ስንገዛበት ነው።—2 ቆሮንቶስ 9:7፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
ኢየሱስ “ሰጪዎች ሁኑ” በማለት ተከታዮቹ አልፎ አልፎ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ የመስጠት ልማድ እንዲኖራቸው አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 6:38 NW) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት የአምላክን መንግሥት ለመስበኩ ሥራ የገንዘብ መዋጮ ከማድረግ ጋር በተያያዘም ይሠራል። (ምሳሌ 3:9) በእርግጥም በዚህ ረገድ የምናሳየው ልግስና የይሖዋና የኢየሱስ ‘ወዳጆች’ እንድንሆን ይረዳናል።—ሉቃስ 16:9
‘ከገንዘብ ፍቅር’ ተጠበቁ
ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች እምብዛም እጃቸው አይፈታም። ቢፈታም ይህንን የሚያደርጉት በአጸፋው የሚያገኙትን ጥቅም አስበው ነው። የእነዚህ ሰዎች ዋነኛ ችግር ለገንዘብ ያላቸው ፍቅር ነው፤ በመሆኑም ብዙውን ጊዜ ለሐዘን ይዳርጋቸዋል። አንደኛ ጢሞቴዎስ 6:10 “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጒጒት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል” ይላል። የገንዘብ ፍቅር ይህን ያህል እርካታ የሚያሳጣው አልፎ ተርፎም ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው?
አንዱ ምክንያት ስግብግብ ሰው ሀብት ለማካበት ያለው ፍላጎት ስለማይረካ ነው። መክብብ 5:10 “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም” ይላል። በመሆኑም ገንዘብ ወዳዶች ‘ራሳቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።’ ከዚህም በላይ ስግብግብነታቸው ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲበላሽ፣ የቤተሰብ ሕይወታቸው ደስታ የራቀው እንዲሆን ብሎም እረፍት እንዲያጡ አድርጓቸዋል። “ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን እንቅልፍ ይነሣዋል።” (መክብብ 5:12) ከምንም በላይ ግን ገንዘብን መውደድ የአምላክን ሞገስ ያሳጣል።—ኢዮብ 31:24, 28
መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የዓለም ታሪክ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ስርቆት እንደፈጸሙ፣ ፍትሕ እንዳዛቡ፣ ገላቸውን እንደሸጡ፣ ነፍስ እንዳጠፉ፣ ወዳጆቻቸውን እንደካዱ እንዲሁም እንደዋሹ የሚገልጹ በርካታ ምሳሌዎችን ይዘዋል። (ኢያሱ 7:1, 20-26፤ ሚክያስ 3:11፤ ማርቆስ 14:10, 11፤ ዮሐንስ 12:6) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት አንድን “ሀብታም” አለቃ እንዲከተለው ጋብዞት ነበር። የሚያሳዝነው ይህ ሰው ኢየሱስ ያለውን ማድረጉ የገንዘብ ጉዳት እንደሚያስከትልበት ስለተሰማው ግብዣውን ሳይቀበል ቀርቷል። በመሆኑም ኢየሱስ “ብዙ ሀብት ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው?” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 18:23, 24
አስቀድሞ እንደተነገረው በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ “ገንዘብን የሚወዱ” ስለሚሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከዚህ ወጥመድ ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከገንዘብ የሚበልጥ ነገር ስላላቸው ይህ የስግብግብነት መንፈስ ተጽዕኖ አያሳድርባቸውም።
ከገንዘብ የሚሻል ነገር
ንጉሥ ሰሎሞን ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “ጥበብም ጥላ ከለላ ነው” በማለት ተናግሯል። እንደዚህ ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው” ብሏል። (መክብብ 7:12) ሰሎሞን እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ትክክለኛ በሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀትና ጤናማ በሆነ አምላካዊ ፍርሃት ላይ ስለተመሠረተ ጥበብ መናገሩ ነበር። እንዲህ ያለው ጥበብ ከገንዘብ በላቀ መልኩ አንድን ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሊያጋጥሙት ከሚችሉ በርካታ መሰናክሎች አልፎ ተርፎም ያለ ዕድሜ በሞት ከመቀጨት ሊጠብቀው ይችላል። እንዲሁም እውነተኛ ጥበብ ልክ እንደ ዘውድ ለባለቤቱ ከፍ ያለ ክብርና ሞገስ ያስገኝለታል። (ምሳሌ 2:10-22፤ 4:5-9) በተጨማሪም ይህ ጥበብ አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ እንዲያገኝ ስለሚያስችለው “የሕይወት ዛፍ” ተብሎ ተጠርቷል።—ምሳሌ 3:18
ይህንን ጥበብ ከልባቸው የሚፈልጉ እንዲሁም ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች በቀላሉ ሊገኝ እንደሚችል ይገነዘባሉ። “ልጄ ሆይ . . . የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣ እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣ በዚያን ጊዜ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤ አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።”—ምሳሌ 2:1-6
እውነተኛ ክርስቲያኖች ከገንዘብ ይልቅ ለጥበብ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡ ገንዘብን ከሚወዱ ሰዎች በተለየ ከፍተኛ ሰላምና ደስታ እንዲሁም መረጋጋት አላቸው። ዕብራውያን 13:5 እንዲህ ይላል:- “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ ‘ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም’ ብሎአል።” ገንዘብ እንዲህ ዓይነት ዋስትና መስጠት አይችልም።
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ ገንዘብ ጥላ ከለላ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?—መክብብ 7:12
▪ አምላካዊ ጥበብ ከገንዘብ የሚበልጠው ለምንድን ነው?—ምሳሌ 2:10-22፤ 3:13-18
▪ የገንዘብ ፍቅርን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?—ማርቆስ 10:23, 25፤ ሉቃስ 18:23, 24፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10