በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመንፈሳዊ ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት

በመንፈሳዊ ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት

በመንፈሳዊ ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት

በቁሳዊ ነገሮች ሀብታም ለመሆን ትኩረት የታከለበት ጥረት ማድረግና መሥዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋል። በመንፈሳዊ ሀብታም ለመሆንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ “በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ” ብሎ ሲናገር ይህን መግለጹ ነበር። (ማቴዎስ 6:20) መንፈሳዊ ሀብት በራሱ አይከማችም። አንድ ሰው የባንክ ሒሳብ መክፈቱ ብቻ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሀብታም ሊያደርገው እንደማይችል ሁሉ ሃይማኖተኛ መሆኑ ብቻም በመንፈሳዊ ሀብታም አያደርገውም። ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና ለመመሥረት፣ መንፈሳዊ ሰው በመሆን እድገት ለማድረግና በመንፈሳዊ ባሕርያት ሀብታም ለመሆን የሚፈልግ ሰው ቆራጥ መሆን፣ ጊዜ መዋጀት፣ ትኩረት የታከለበት ጥረት ማድረግና መሥዋዕትነት መክፈል ይኖርበታል።—ምሳሌ 2:1-6

በሥጋዊም በመንፈሳዊም ሀብታም መሆን ትችላለህ?

አንድ ሰው በመንፈሳዊ ሀብታም ሆኖ በቁሳዊ ነገሮች ረገድም ባለጸጋ ሊሆን አይችልም? እንዲህ ማድረግ ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን የሚችለው ከሁለቱ አንዱን ብቻ ነው። ኢየሱስ “እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም” ብሏል። (ማቴዎስ 6:24ለ) ለምን? ምክንያቱም መንፈሳዊ ሀብትን ለማግኘት የሚደረግ ጥረትና ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ እርስ በርስ ስለሚጋጩ ነው። አንዱ ለሌላው እንቅፋት ይሆናል። በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ ሀብት እንዲያከማቹ ከመናገሩ በፊት “በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት ማከማቸት ተዉ” ብሏል።—ማቴዎስ 6:19 NW

አንድ ሰው የኢየሱስን ምክር ችላ ብሎ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሀብትን ለማግኘት የሚጥር ከሆነ ምን ይደርስበታል? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል።” (ማቴዎስ 6:24ሀ) አንድ ሰው ሁለቱንም ሀብቶች ለማግኘት የሚጥር ከሆነ፣ መንፈሳዊ ነገሮችን የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ተሰምቶት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ቢያከናውንም እንኳ እንዲህ ማድረጉ ለሥጋዊ ሥራው እንቅፋት እንደሆነበት ሊያስብ ይችላል። የኑሮን ጭንቀቶች ለመቋቋም እንዲረዳው በአምላክ ላይ በመመካት ፈንታ በዋነኝነት በገንዘብና ገንዘብ በሚገዛቸው ነገሮች ሊተማመን ይችላል። ሁኔታው ኢየሱስ እንዲህ በማለት እንደተናገረው ነው:- “ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናል።”—ማቴዎስ 6:21

እያንዳንዱ ክርስቲያን ጊዜውን፣ ትኩረቱንና ልቡን የሚሰጠው ለምን እንደሆነ ከመወሰኑ በፊት ከላይ እንደተጠቀሰው ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በቁም ነገር ሊያስብበት ይገባል። አምላክ፣ አንድ ክርስቲያን ምን ያህል ሀብት ሊኖረው እንደሚገባ የተወሰነ ገደብ ስላላበጀ ብቻ ከስግብግብነት እንድንርቅ የሚያሳስቡት ማስጠንቀቂያዎች ምንም ቅጣት አያስከትሉም ማለት አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ችላ ብለው በቁሳዊ ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የሚነሱ ሁሉ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በመንፈሳዊ ይጎዳሉ እንዲሁም አእምሯዊና ስሜታዊ ሥቃይ ይደርስባቸዋል። (ገላትያ 6:7) በተቃራኒው ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ሰዎች ደስተኞች እንደሚሆኑ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3) ፈጣሪያችንና ልጁ ለደስታችንና ለደኅንነታችን የሚበጀው ከሁሉ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ እንደሚያውቁ ጥርጥር የለውም!—ኢሳይያስ 48:17, 18

የማትጸጸትበት ምርጫ

ታዲያ የምትመርጠው አምላክን ነው ወይስ ሀብትን? ለቁሳዊ ፍላጎታችን መጠነኛ ትኩረት መስጠት እንዳለብን ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ “አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው” ብሏል። በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ተስፋቸውን በገንዘብ ሳይሆን በአምላክ ላይ እንዲያደርጉና “በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ” አበረታቷቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ 6:17, 18 የ1954 ትርጉም) ታዲያ አንተስ ትኩረት የምታደርገው በምን ላይ ነው? ምን ለማግኘት ትመርጥ ይሆን? ጳውሎስ ከጠቀሳቸው በጎ ሥራዎች ውስጥ ዋነኛው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ክርስቲያኖች፣ ተረጋግተው ለመኖርና ሕይወትን ለማጣጣም ብለው ሳይሆን ኢየሱስ በሰጣቸው በዚህ ትርጉም ያለው ሥራ ከፍተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ሲሉ ቀለል ያለ አኗኗርን የሚመርጡ ከሆነ አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር “ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።” አሁንም እንኳ ቢሆን መንፈሳዊ ሀብት ‘ከወርቅ ይልቅ የበለጠ’ መሆኑን ይገነዘባሉ።—1 ጢሞቴዎስ 6:19፤ ምሳሌ 16:16፤ ፊልጵስዩስ 1:10

የኤዲን ተሞክሮ እንመልከት። የኤዲ ቤተሰቦች የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት እርሱ ትንሽ ልጅ እያለ ነበር። በአንድ ወቅት ቤተሰቦቹ ንብረታቸውን በሙሉ በማጣታቸው ቤታቸውን ለቅቀው ለመሄድ ተገደው ነበር። ኤዲ እንደሚከተለው በማለት ይናገራል:- “ያለንን ሁሉ ብናጣ ምን እንደምንሆን ሁልጊዜ እጨነቅ ነበር። ይኸው አሁን ምንም የለንም። ምን የደረሰብን ይመስላችኋል? ምንም የከፋ ነገር አልደረሰብንም! አሁንም ቢሆን እንበላለን፣ እንጠጣለን፣ እንዲሁም እንለብሳለን። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሰጥቶናል፤ ደግሞም የኋላ ኋላ ከደረሰብን ኪሳራ አገግመናል። ይህ ተሞክሮ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:33 ላይ የገባውን ቃል በቁም ነገር እንድመለከተው አስተምሮኛል፤ ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ ከሰጠን በቁሳዊ ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ፈጽሞ መጨነቅ አያስፈልገንም።” በአሁኑ ጊዜ ኤዲ ተጓዥ አገልጋይ ሆኖ አምላክን በሙሉ ጊዜው እያገለገለ ሲሆን ባለቤቱም አብራው በዚህ አገልግሎት ትካፈላለች። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ አላቸው። ከሁሉ ይበልጥ ግን በመንፈሳዊ ሀብታሞች ናቸው።

በዋጋ የማይተመኑ ጥቅሞች

ሌቦች ሊሰርቁት ከሚችሉት በምድር ላይ ካለ ሀብት በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ሀብት ዘላቂ ነው። (ምሳሌ 23:4, 5፤ ማቴዎስ 6:20) መንፈሳዊ እድገትን መለካት አስቸጋሪ መሆኑ እውነት ነው። አንድ ሰው በቁሳዊ ሀብት ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ መለካት የሚቻል ቢሆንም በፍቅር፣ በደስታ ወይም በእምነት ረገድ ግን ምን ያህል ለውጥ እንዳደረገ በቀላሉ ማወቅ አይቻልም። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ሀብት በዋጋ ሊተመን የማይችል በረከት ያስገኛል። ኢየሱስ ለመንፈሳዊ ነገሮች ሲሉ ቤታቸውንና እርሻቸውን ማለትም መተዳደሪያቸውን እንኳ ሳይቀር ስለተዉ ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም።”—ማርቆስ 10:29, 30

ታዲያ አንተ በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጠው ለማን ነው? ለአምላክ ወይስ ለሀብት?

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ቁሳዊ ሀብትን እያሳደድክ ነው . . .

. . . ወይስ መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት እየጣርክ?