በሙምባይ ከደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት በሕይወት ተርፈዋል
በሙምባይ ከደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት በሕይወት ተርፈዋል
ሕንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ቀደም ሲል ቦምቤይ በመባል ትታወቅ የነበረችው ሙምባይ በፍጥነት እያደገ የሚሄድ የሕዝብ ብዛት ያላት ከተማ ስትሆን በአሁኑ ወቅት ነዋሪዎቿ ከ18 ሚሊዮን ይበልጣሉ። ከእነዚህ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚያህሉት በየቀኑ ወደ ሥራ፣ ወደ ትምህርት ቤትና ኮሌጅ፣ ወደ ገበያ ወይም ወደ ሌሎች ጉዳዮቻቸው ለመጓዝ ፈጣን በሆኑትና ቶሎ ቶሎ በሚመጡት የከተማ ባቡሮች ይጠቀማሉ። እያንዳንዱ ባለ ዘጠኝ ፉርጎ ባቡር 1,710 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት ግን ወደ 5,000 ተሳፋሪዎችን አጭቆ ይይዛል። አሸባሪዎች ሐምሌ 11, 2006 በሙምባይ ባቡሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙት ባቡሮቹ በተሳፋሪዎች በሚጨናነቁበት የሥራ መውጫ ሰዓት ላይ ነበር። አሥራ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በምዕራባዊ አቅጣጫ በሚገኘው የባቡር ሐዲድ ላይ ይጓዙ በነበሩ የተለያዩ ባቡሮች ላይ ሰባት ቦምቦች ፈንድተው ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን ከ800 በሚበልጡት ላይ ደግሞ ጉዳት አድርሰዋል።
በሙምባይና በዙሪያዋ ባሉት ከተሞች ውስጥ በሚገኙት 22 ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ በርካታ ወንድሞች በእነዚህ ባቡሮች አዘውትረው የሚጠቀሙ ሲሆን ጥቃቱ በተፈጸመበት ቀንም ባቡሮቹ ውስጥ ነበሩ። ደግነቱ በአደጋው የአንዳቸውም ሕይወት አልጠፋም፤ ይሁን እንጂ በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በወቅቱ አኒታ ከሥራ ወደ ቤት እየተመለሰች ነበር። ባቡሩ በተሳፋሪዎች ተጨናንቆ ስለነበር በቀላሉ መውረድ እንድትችል ከፍተኛ ክፍያ በሚጠይቀው ፉርጎ በር አጠገብ ቆማ ነበር። ባቡሩ በፍጥነት እየተጓዘ ሳለ ድንገት ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ተሰማና የነበረችበት ፉርጎ በጥቁር ጭስ ተሞላ። በበሩ በኩል ብቅ ብላ በስተቀኟ ስታይ እርሷ ከነበረችበት ቀጥሎ ያለው ፉርጎ ጎኑ ተገንጥሎ ከባቡሩ አካል ጋር በ45 ዲግሪ መንጠልጠሉን ተመለከተች። የሞቱ ሰዎችና የተቆረጡ የአካል ክፍሎች በዚህ ቀዳዳ በኩል በኃይል ተወርውረው ሐዲዱ ላይ ሲወድቁ ስታይ በጣም ዘገነናት። ምንም እንኳ ሁኔታው የቆየው ለጥቂት ሴኮንዶች ቢሆንም ለእርሷ ግን ዓመት መስሏት ነበር። ከዚያም ባቡሩ ቆመ። አኒታ ከሌሎች
ተሳፋሪዎች ጋር በመሆን ወደ ሐዲዶቹ ዘለለችና እግሬ አውጪኝ ብላ መሮጥ ጀመረች። አኒታ ባለቤቷን ጆንን በሞባይል ስልክ ለማግኘት ሞክራ አገኘችው። ብዙም ሳይቆይ የከተማዋ የስልክ መስመር በስጋት በተዋጡ ሰዎች የስልክ ጥሪ ተጨናነቀ። አኒታ ሁኔታውን ለባሏ እስክትነግረው ድረስ በመጠኑ የመረጋጋት መንፈስ ይታይባት ነበር፤ ከእርሱ ጋር ማውራት ስትጀምር ግን እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም። ከዚያም የተፈጠረውን ሁኔታ ነገረችውና መጥቶ እንዲወስዳት ጠየቀችው። እርሱን እየጠበቀች እያለ ኃይለኛ ዝናብ መዝነብ ጀመረና ለመርማሪዎቹ ይጠቅማቸው የነበረውን መረጃ አጠፋው።ሌላው የይሖዋ ምሥክር ክላውዲየስ ደግሞ ከቢሮው የወጣው ከሥራ መውጫ ሰዓት ቀደም ብሎ ነበር። ከዚያም በምዕራብ አቅጣጫ ወደ ከተማው ዳርቻ የሚጓዘውን ባቡር ለመያዝ ወደ ቸርችጌት ባቡር ጣቢያ ሄዶ አሥራ አንድ ሰዓት ከሃያ ላይ አንደኛ ማዕረግ ተሳፈረ። ወደ ባየንደ ለሚደረገው የአንድ ሰዓት ጉዞ ወንበር እየፈለገ እያለ በጎረቤት ጉባኤ የሚገኘውን ወንድም ጆሴፍን አየው። አንዳንድ ነገሮችን አንስተው ሲወያዩ ሰዓቱ ሳይታወቃቸው ሄደ። ከዚያም ጆሴፍ በሥራ ደክሞት ስለነበር እንቅልፍ ሸለብ አደረገው። ክላውዲየስ ባቡሩ በተሳፋሪዎች ተጨናንቆ ስለነበር የሚወርድበት ቦታ ከመድረሱ በፊት ወደ በሩ ለመሄድ ተነሳ። ክላውዲየስ እዚያ ቆሞ እያለ ጆሴፍ ከእንቅልፉ ነቅቶ ሊሰናበተው ዞር ሲል ክላውዲየስ ደግሞ የወንበሩን እጀታ ይዞ ሊያናግረው ዘንበል አለ። የክላውዲየስን ሕይወት ያተረፈለት እንዲህ ማድረጉ ሳይሆን አልቀረም። ድንገት ከፍተኛ ድምፅ ተሰማና የነበሩበት ፉርጎ በኃይል ተናወጠ፤ ከዚያም ሙሉ በሙሉ በጭስ ተሞላና ጨለማ ሆነ። ክላውዲየስ በኃይል ተወርውሮ ወንበሮቹ ሥር ወደቀ። ጆሮው ላይ ከሚያቃጭልበት ድምፅ በስተቀር ምንም የሚሰማው ነገር አልነበረም። ክላውዲየስ ቀደም ሲል ቆሞበት በነበረው ቦታ ላይ ሰፊ ቀዳዳ ተፈጥሮ ነበር። አጠገቡ ቆመው የነበሩት ተሳፋሪዎች አንድም በዚህ ቀዳዳ በኩል ወደ ውጪ ወድቀዋል አሊያም እዚያው እንዳሉ ሞተዋል። ክላውዲየስ አሳዛኝ በሆነው በዚያ ማክሰኞ ቀን ባቡሮቹን ካናወጡት ሰባት ፍንዳታዎች መካከል አምስተኛ ከነበረው አደጋ በሕይወት ተርፏል።
ክላውዲየስ ልብሶቹ ደም በደም እንደሆኑ ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። ይሁን እንጂ ደሙ ጉዳት ከደረሰባቸው ሌሎች ሰዎች የተፈናጠቀበት ነበር። ክላውዲየስ ከጆሮው ታምቡር መበጠስ፣ በአንድ እጁ ላይ ከደረሰው ቃጠሎና ከጸጉሩ መለብለብ በስተቀር ያን ያህል የከፋ ጉዳት አልደረሰበትም። ሆስፒታል ውስጥ ጆሴፍንና ባለቤቱን አንጄላን አገኛቸው። አንጄላ ከእነርሱ ቀጥሎ በነበረው ለሴቶች በተያዘ ፉርጎ ውስጥ ስለነበረች ምንም ጉዳት አልደረሰባትም። ጆሴፍ የቀኝ ዓይኑ የበለዘ ከመሆኑም በላይ የመስማት ችሎታውንም አጥቷል። እነዚህ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች በሕይወት በመትረፋቸው ይሖዋን አመስግነዋል። ክላውዲየስ ራሱን እንዳወቀ ወደ አእምሮው የመጣው የመጀመሪያ ሐሳብ ‘ሕይወት በቅጽበት ሊጠፋ በሚችልበት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ለገንዘብም ሆነ ለቁሳዊ ጥቅም መሯሯጥ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!’ የሚል እንደነበረ ተናግሯል። ከአምላኩ ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና በሕይወቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ በመስጠቱ በጣም ተደስቷል!
በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የሙምባይ ከተማ በኃይለኛ ጎርፍ፣ በሁከትና በቦምብ ፍንዳታዎች ተናውጣ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያ የሚገኙት ከ1,700 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ የቅንዓት መንፈስ አላቸው። ዓመጽ የሚባል ነገር የማይኖርበት አስደሳች አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ አዘውትረው ለሰዎች ይናገራሉ።—ራእይ 21:1-4
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ክላውዲየስ ቀደም ሲል ቆሞ በነበረበት ቦታ ላይ ሰፊ ቀዳዳ ተፈጥሮ ነበር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አኒታ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክላውዲየስ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆሴፍ እና አንጄላ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Sebastian D’Souza/AFP/Getty Images