ታታሪዎቹ የአቢጃን ልብስ አጣቢዎች
ታታሪዎቹ የአቢጃን ልብስ አጣቢዎች
ኮት ዲቩዋር የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘውና የኮት ዲቩዋር ከተማ በሆነችው በአቢጃን አቅራቢያ አካባቢውን እየቃኘንና የከተማዋን ውካታ እየሰማን በስተ ምዕራብ አቅጣጫ እየተጓዝን ሳለ ድንገት አንድ አስደናቂ ትዕይንት ትኩረታችንን ሳበው። በሣር በተሸፈነው ሰፊ ሜዳ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ልብሶች ተሰጥተዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የአገሬው ተወላጅ የሆኑት ወዳጆቻችን ስለ ሁኔታው በደስታ ያብራሩልን ጀመር። ይህን ያደረጉት ፋኒኮዎች ነበሩ።
ፋኒኮዎች በቡድን ተደራጅተው ልብስ የሚያጥቡ ታታሪ ሠራተኞች ናቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶችና ጥቂት ጠንካራ ሴቶች ጎሕ ሲቀድድ ጀምረው ጀንበር እስክትጠልቅ ድረስ በባንኮ ወንዝ ላይ ልብስ በማጠብ ይተዳደራሉ። እነዚህ ልብስ አጣቢዎች ፋኒኮ የሚለውን ስያሜ ያገኙት ፋኒ እና ኮ ከሚሉት ሁለት የድዩላ ቋንቋ ቃላት ነው። ፋኒ የሚለው
ቃል “ጨርቅ” ወይም “ልብስ” ማለት ሲሆን ኮ ደግሞ “ማጠብ” የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ ፋኒኮ የሚለው የድዩላ ቃል “ልብስ አጣቢ” ማለት ነው።የልብስ አጣቢው ውሎ
አስደናቂ ስለሆነው የፋኒኮዎች ሥራ ይበልጥ ለማወቅ ፈለግንና አንድ ቀን ሥራቸውን ወደሚያከናውኑበት ቦታ በጠዋት ሄድን። እዚያ ስንደርስ ሥራቸውን በሚያስገርም ፍጥነት እያከናወኑ ነበር! በድፍርሱ የባንኮ ወንዝ ላይ ድንጋዮች ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ትላልቅ የመኪና ጎማዎች ይታያሉ። በእያንዳንዱ ጎማ አጠገብ ደግሞ ልብስ አጣቢው እስከ ወገቡ በሚደርስ ውኃ ውስጥ ቆሞ ልብሶችን ያጥባል።
ልብስ አጣቢው ጠዋት ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት በየቤቱ እየሄደ የሚያጥባቸውን ልብሶች ይሰበስባል። አንዳንድ ደንበኞቹ የሚኖሩት ልብስ ከሚታጠብበት ቦታ 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። የሰበሰባቸውን ልብሶች በእጅ በሚጎተት ጋሪ ላይ ጭኖ አሊያም በጨርቅ በማሰር ጭንቅላቱ ላይ ተሸክሞ ወደ ባንኮ ወንዝ ያቀናል። እዚያም እንደደረሰ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡት የሥራ ባልደረቦቹ በየራሳቸው ቋንቋ ሰላምታ ይሰጡታል። እንደ ሚስተር ብራማ ያሉ አንዳንድ አጣቢዎች በዚህ ቦታ ላይ ለአሥርተ ዓመታት ሠርተዋል። በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት እኚህ ሰው ፈርጠም ያለ ተክለ ሰውነት አላቸው። ፋኒኮዎች ከሦስት ቀናት በስተቀር በዓመት ውስጥ ሁሉንም ቀናት ያለመታከት ይሠራሉ።
ልብስ በእጅ ማጠብ በጣም አድካሚ ሥራ ነው። አንድ ሰው ተሸክሞ ያመጣቸውን በርካታ ልብሶች ሲያወርድ አየን። ይህን ልብስ አንዲት የቤት እመቤት ብታየው ገና ማጠብ ሳትጀምር ሐሞቷ ፍስስ ሊል ይችላል! አጣቢው ልብሶቹን ውኃ ውስጥ ከዘፈዘፈ በኋላ አንድ በአንድ እያወጣ ከዘንባባ ዘይት በተሠራ ትልቅ ሳሙና እየመታ ድንጋይ ላይ ማሸት ጀመረ። አንዳንድ ጊዜ ልብሱ በጣም ያደፈ ከሆነ ቆሻሻውን ለማስለቀቅ ብሩሽ ይጠቀማል። ለመሆኑ ሰዎች ልብስ ለማሳጠብ ምን ያህል ይከፍላሉ? ለአንድ ሸሚዝ 60 የኢትዮጵያ ሳንቲም ያህል ለአንሶላ ደግሞ 1.20 ይከፍላሉ። ለካስ ፋኒኮዎች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ይህን ያህል ብዛት ያለው ልብስ የሚያጥቡት ወደው አይደለም!
አጣቢዎች በርከት ያለ ልብስ ተሸክመው ሲመጡ ስታይ ‘የአንዱን ሰው ልብስ ከሌላው እንዴት መለየት ይችላሉ?’ የሚል ጥያቄ ይመጣብህ ይሆናል። እኛም ፋኒኮዎቹ በሕንድ እንዳሉት ልብስ አጣቢዎች አንድ ዓይነት ምስጢራዊ የመለያ ኮድ ይጠቀሙ ይሆናል ብለን አስበን ነበር። ሆኖም ፋኒኮዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ ከእነርሱ በጣም የተለየ ቢሆንም ውጤታማ ነው።
ስለ ሁኔታው ጠለቅ ያለ እውቀት ያለው አስጎብኚያችን ፋኒኮዎቹ ምን ዓይነት ዘዴ እንደሚጠቀሙ አብራራልን። በመጀመሪያ ደረጃ አጣቢው የሚያጥባቸውን ልብሶች በሚሰበስብበት ወቅት የቤተሰቡን አባላት አካላዊ ሁኔታ ልብ ብሎ ስለሚመለከት እያንዳንዱ ልብስ የማን እንደሆነ ማስታወስ ይችላል። ልብሶቹን ለመለየት ምንም ዓይነት ምልክት አይጠቀምም። ይልቁንም የልብሶቹን እጅጌ ወይም መቀነት በመጠቀም የአንድን ቤተሰብ ልብስ አንድ ላይ ያስራል። በሚያጥብበትም ጊዜ የአንዱ ቤተሰብ ልብስ ከሌላው ጋር እንዳይቀላቀልበት ጥንቃቄ ያደርጋል። ያም ሆኖ ግን ማስታወስ ከባድ እንደሆነ ስለተሰማን ወደ አንዱ ፋኒኮ ቀረብ ብለን ልብስ ተምታቶበት ወይም ተቀያይሮበት ያውቅ እንደሆነ ጠየቅነው። በፊቱ ላይ ‘ፋኒኮ በፍጹም ልብስ አይምታታበትም!’ የሚል ስሜት አነበብን።
ማንኛውም ሰው ወደ ባንኮ ወንዝ ሄዶ ልብስ አጣቢ መሆን ይችላል? በፍጹም! ሥራውን ለመጀመር እያንዳንዱ ሰው ሊከተለው የሚገባ ጥብቅ ደንብ አለ። ፋኒኮ መሆን የሚፈልግ ሰው ልምድ ባለው አጣቢ የሚሠለጥንበት የሦስት ወር የሙከራ ጊዜ ይሰጠዋል። የደንበኞቹን ልብስ የማስታወስ ችሎታውን የሚያዳብረውም በዚህ ወቅት ነው። በዚህ ረገድ ካልተሳካለት ሌላ ሥራ እንዲፈልግ ይነገረዋል። ይሁን እንጂ አዲሱ ፋኒኮ ጥሩ ችሎታ እንዳለው ከታመነበት መጠነኛ ገንዘብ ከፍሎ ጎማውን
የሚያስቀምጥበት ቦታ ይሰጠዋል። ለእርሱ በተሰጠው በዚህ ቦታ ላይ ማንም ሌላ ሰው ማጠብ አይችልም።ከዘንባባ ዘይት የሚሠራ ሳሙና
ሳሙና ለልብስ አጣቢዎች ቀኝ እጃቸው ነው። ስለዚህ ጀማሪ ልብስ አጣቢ ከዘንባባ ዘይት የሚሠራውን ሳሙና አጠቃቀም በተመለከተም ሥልጠና ይሰጠዋል። በአጠባው ወቅት ሦስት የተለያየ ቀለም ያላቸው ሳሙናዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነጭና ቢጫ ቀለም ያላቸውን ሳሙናዎች ብዙም ያልቆሸሹ ልብሶችን ለማጠብ የሚገለገሉባቸው ሲሆን ጠቆር ያለውን ደግሞ ላደፉ ልብሶች ይጠቀሙበታል። የሳሙናው ቀለም የጠቆረው በተሠራበት ንጥረ ነገር ማለትም በዘንባባው ዘይት ምክንያት ነው። እያንዳንዱ ፋኒኮ በየቀኑ ቢያንስ አሥር ሳሙናዎችን ስለሚጠቀም በአቅራቢያው ያሉ የሳሙና አምራቾች ለአጣቢዎቹ ያለማቋረጥ ያቀርቡላቸዋል።
በልብስ ማጠቢያው አካባቢ የሚገኘውን አንድ አነስተኛ የሳሙና ማምረቻም ጎብኝተን ነበር። ሳሙና የማምረቱ ሥራ የሚጀምረው ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ነው። ሠራተኞቹ ሳሙና ለማምረት የሚያስፈልጉትን ጥሬ ዕቃዎች ማለትም የረጋ የዘንባባ ዘይት፣ ፖታሲየም ሃይድሮክሳይድ፣ ጨው፣ ሳወርሶፕ ከሚባለው ዛፍ የሚገኝ ፈሳሽ፣ የኮኮናት ዘይትና የካካዎ ቅቤ በአቅራቢያቸው ካለ ገበያ ገዝተው ያስቀምጣሉ። እነዚህ ነገሮች አካባቢን የሚበክሉ አይደሉም። ሠራተኞቹ ከላይ የተዘረዘሩትን ንጥር ነገሮች በአንድ ትልቅ ብረት ድስት ውስጥ ጨምረው እሳት ላይ ይጥዷቸዋል። ከዚያም ለስድስት ሰዓታት ካንተከተኩት በኋላ ከብረት በተሠራ ቅርጽ ማውጫ ውስጥ ያፈስሱትና እስኪደርቅ ይተዉታል። ከሰዓታት በኋላ የደረቀውን ሳሙና ይቆራርጡታል።
ከዚያም ሳሙና አምራቿ የሠራችውን ሳሙና ተለቅ ባለ ዕቃ ላይ አድርጋ በጭንቅላቷ በመሸከም ፋኒኮዎች ልብስ ወደሚያጥቡበት ቦታ ትሄዳለች። ታዲያ በወንዝ መሃል ቆሞ ልብስ እያጠበ ላለ ፋኒኮ ሳሙናውን እንዴት ልታቀብለው ትችላለች? ሳሙና የያዘውን የፕላስቲክ ዕቃ ተሸክማ እስከ ወገብ በሚደርሰው ውኃ ውስጥ ትገባና ሳሙና ለሚፈልገው አጣቢ ዕቃውን በውኃው ላይ እያንሳፈፈች ትወስድለታለች።
የሥራው ቀን ሲገባደድ
ፋኒኮው አጠባውን ሲጨርስ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ሜዳ ሄዶ ያጠበውን ልብስ ሣር ላይ አሊያም በተዘረጋ ገመድ ላይ ያሰጣዋል። መግቢያችን ላይ ትኩረታችንን እንደሳበው የገለጽነው ትዕይንት ይህ ነበር። ከዚያ በኋላ ይህ ጠንካራ ልብስ አጣቢ ትንሽ አረፍ ይላል። ከሰዓት በኋላ ረፋዱ ላይ ልብሶቹ ሲደርቁ እያንዳንዱን በጥንቃቄ ያጥፋል፤ ምናልባትም አንዳንዶቹን የከሰል ካውያ ተጠቅሞ ይተኩሳል። አመሻሹ ላይ ያጠባቸውንና የተኮሳቸውን ልብሶች በጨርቅ አንድ ላይ ካሰራቸው በኋላ ለየባለቤቶቹ ያደርሳል።
ታጥበው በረድፍ በረድፍ የተሰጡ ልብሶችን ስናይ አጣቢው ይህ ሁሉ ሥራ እንዳለበት አልገባንም ነበር። በመሆኑም የአቢጃንን ልብስ አጣቢዎች ሄደን መጎብኘታችን በዓለም ዙሪያ ስላሉ ታታሪ የሆኑ ወንድና ሴት ልብስ አጣቢዎች ያለንን ግንዛቤ እንዲሁም ለእነርሱ ያለንን አድናቆት ከፍ ስላደረገልን በጣም ተደሰትን።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኮት ዲቩዋር
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት ሳሙና አምራች ሳሙና ስትሸጥ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
PhotriMicroStock™/C. Cecil