በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቶሌዶ—የመካከለኛውን ዘመን የተለያየ ባሕል አጣምራ የያዘች ከተማ

ቶሌዶ—የመካከለኛውን ዘመን የተለያየ ባሕል አጣምራ የያዘች ከተማ

ቶሌዶ—የመካከለኛውን ዘመን የተለያየ ባሕል አጣምራ የያዘች ከተማ

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በአይቤሪያን ባሕረ ገብ መሬት መሃል ላይ አንድ የጥቁር ድንጋይ ኮረብታ ይገኛል፤ ይህ ኮረብታ በሦስት አቅጣጫ ታጉስ በሚባለው ወንዝ ተከብቧል። ወንዙ ለዘመናት መሬቱን ሲሸረሽረው መቆየቱ በኮረብታው ዙሪያ ለሚገኘው አካባቢ መከታ ሆነው የሚያገለግሉ አለቶች እንዲኖሩ አድርጓል። ቶሌዶ የተባለችው ከተማ የተቆረቆረችው ከመሬት ከፍ ብሎ በሚገኘውና ወታደራዊ ጠቀሜታ ባለው በዚህ አካባቢ ነው፤ ስለ ስፔንና ስለ ባሕሏ ሲነሳ ይህቺ ከተማም አብራ ትታወሳለች።

ጠባብና ጠመዝማዛ የሆኑት የጥንቷ ቶሌዶ ጎዳናዎች በዛሬው ጊዜ የሚጎበኛትን ሰው በሐሳብ ወደ መካከለኛው ዘመን ይዘውት ይነጉዳሉ። የከተማዋ በሮች፣ ግንቦችና ድልድዮች በሙሉ የመካከለኛውን ዘመን መልክ የሚያንጸባርቁ ሲሆን ቶሌዶ ከታላላቆቹ የአውሮፓ ከተሞች አንዷ የነበረችበትን ዘመን ያስታውሱናል።

ይሁን እንጂ ቶሌዶ ከሌሎች የአውሮፓ ከተሞች ጋር ብዙም አትመሳሰልም። የባቡር ጣቢያዋም እንኳ የሩቅ ምሥራቅ አገሮችን አሠራር የተከተለ ነው። የቶሌዶን ታሪካዊ ሐውልቶችና የእደ ጥበብ ውጤቶች ቀረብ ብለን ስንመለከታቸው ባለፉት በርካታ መቶ ዘመናት በዚህች ከተማ ውስጥ ተስፋፍተው የነበሩትን የተለያዩ ባሕሎች አሻራ እናያለን። የዛሬ 700 ዓመታት ገደማ ቶሌዶ እጅግ በበለጸገችበትና በውስጧ በርካታ ሥራዎች በተከናወኑበት ወቅት ይህቺ ከተማ የመካከለኛው ዘመን ባሕሎች መናኸሪያ ሆና ነበር።

የተለያዩ ባሕሎች

ሮማውያን ወደ ስፔን ከመምጣታቸው አስቀድሞ የኬልቲክና አይቤሪያን ሕዝቦች በዚህ ቁልፍ ቦታ አነስተኛ ከተማ ሠርተው ነበር። ሮማውያን የከተማዋን ስም ቶሌተም (“ከፍ ያለ” የሚል ትርጉም ካለው ቶሊተም ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው) ብለው ከለወጡት በኋላ ከጠቅላይ ግዛት ዋና ከተሞቻቸው አንዷ አደረጓት። ሊቪ የሚባለው ሮማዊ ታሪክ ጸሐፊ ቶሌዶን “[የተፈጥሮ] አቀማመጧ ጠንካራ ምሽግ የሆነላት ትንሽ ከተማ” በማለት ገልጿታል። የሮም አገዛዝ ከወደቀ በኋላ፣ ቪዚጎት ተብለው የሚጠሩት የጥንታዊ ጀርመን ሕዝቦች ስፔንን ድል አድርገው ሲይዙ ቶሌዶ ዋና ከተማቸው እንድትሆን መረጧት። በስድስተኛው መቶ ዘመን ንጉሥ ራካርድ የአርዮስን እምነት ያወገዘው በቶሌዶ ነበር፤ ይህም ስፔን የወግ አጥባቂ ካቶሊኮች ማዕከል እንድትሆን ቶሌዶ ደግሞ ለዋናው ሊቀ ጳጳስ መቀመጫ ሆና እንድታገለግል መንገድ ጠርጓል።

ቶሌዶ የሙስሊም ከሊፋ ግዛት በሆነች ጊዜ ግን ከዚያ በፊት የነበረው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ተለወጠ። የዚህች ጥንታዊት ከተማ ጠባብ መንገዶች ከ8ኛው እስከ 11ኛው መቶ ዘመን በዘለቀው በዚህ ወቅት የተሠሩ ነበሩ። የሙስሊሞች ተቻችሎ የመኖር መርህ በቶሌዶ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶችና ሙር ተብለው የሚጠሩት ሕዝቦች ከተለያዩ ባሕሎቻቸው ጋር አብረው እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። በመጨረሻም በ1085 የካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረው ንጉሥ አልፎንሶ ስድስተኛ ከተማዋን ድል አድርጎ ያዘ። አገዛዙ ቢለወጥም እነዚህ ባሕሎች ለበርካታ መቶ ዘመናት ተቻችለው ኖረዋል።

ቶሌዶ ካሏት በጣም አስደናቂ ታሪካዊ ሐውልቶች መካከል ብዙዎቹ በመካከለኛው ዘመን የተሠሩ ናቸው። የካቶሊክ ገዢዎች ከተማዋን ዋና ከተማቸው ያደረጓት ሲሆን አይሁዳውያን የሆኑ ዜጎቿ ደግሞ እደ ጥበብንና የንግድ እንቅስቃሴዎችን አስፋፍተዋል፤ የእጅ ሙያ ያላቸው ሙስሊሞችም በሕንፃ ሥራዎች ረገድ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የሦስቱ የተለያዩ ሃይማኖቶች ምሑራን በቶሌዶ በነበረው የተርጓሚዎች ቡድን ውስጥ አብረው ሠርተዋል። እነዚህ ምሑራን በ12ኛውና በ13ኛው መቶ ዘመን በርካታ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ወደ ላቲንና ስፓንኛ ቋንቋዎች ተርጉመዋል። ለእነዚህ ተርጓሚዎች ምስጋና ይግባቸውና፣ የአረብ ሥልጣኔ ያከማቸው ሰፊ ሳይንሳዊ እውቀትም ለምዕራባውያን ሊደርሳቸው ችሏል።

በ14ኛው መቶ ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ዜጎች በጅምላ ሲጨፈጨፉ ቀደም ሲል በቶሌዶ የነበረው ሃይማኖታዊ መቻቻል አከተመለት። ኮሎምበስ አሜሪካን ባገኘበት ወቅት በቶሌዶ የስፓኒሽ ኢንኩዊዚሽን ፍርድ ቤት ተቋቁሞ አይሁዳውያንም ሆኑ ሙስሊሞች ወደ ካቶሊክ እምነት ከመለወጥና ከአገር ከመባረር አንዱን እንዲመርጡ ይገደዱ ነበር።

የቀድሞ ክብሯን የሚያስታውሱ ሐውልቶች

በዛሬው ጊዜ በቶሌዶ ከተማ ውስጥ ከመቶ በላይ ታሪካዊ ሐውልቶች ይገኛሉ። በዚህ ታሪካዊ ሀብት የተነሳ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቋቋመው የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ቶሌዶን የዓለም ቅርስ ከተማ በማለት ሰይሟታል። በመካከለኛው ዘመን ከተከናወኑት በጣም አስደናቂ ግንባታዎች መካከል ሁለቱ በታጉስ ወንዝ ላይ የተዘረጉት ድልድዮች ሲሆኑ አንዱ በምሥራቅ በኩል ሌላው ደግሞ በምዕራብ በኩል ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ ናቸው። ቶሌዶን ሊጎበኝ የመጣ ማንኛውም ሰው፣ በግንብ ወደተከበበችው ጥንታዊት ከተማ የሚያስገባውን ፕዌርታ ንዌቫ ዴ ቢሳግራ በመባል የሚታወቀውን ትልቅ በር ሳያስተውል አይቀርም።

በቶሌዶ ሁለት ሰማይ ጠቀስ ሐውልቶች ከርቀት ጎልተው ይታያሉ። አልካዛር ተብሎ የሚጠራው ባለ አራት ማዕዘን ትልቅ ምሽግ በስተ ምሥራቅ በኩል ይገኛል። ይህ ምሽግ ባለፉት በርካታ መቶ ዓመታት ውስጥ የሮም ገዢዎች መኖሪያ፣ የቪዚጎት ነገሥታት ቤተ መንግሥት፣ የአረቦች ምሽግና የስፔን ነገሥታት መኖሪያ በመሆን አገልግሏል። አሁን ደግሞ የጦር ሠራዊት ሙዚየምና በርካታ ሥራዎችን የያዘ ቤተ መጻሕፍት ይገኝበታል። ይሁን እንጂ ቶሌዶ በዋነኝነት ሃይማኖታዊ ከተማ ስለሆነች በከተማዋ መካከል ጎልቶ የሚታየው ጎቲክ በሚባለው የመካከለኛው መቶ ዘመን የሕንፃ አሠራር የተገነባ ግዙፍ ካቴድራል ነው።—በገጽ 17 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

በቶሌዶ የሚገኘው ካቴድራልም ሆነ ሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት፣ በቶሌዶ ይኖር የነበረ የሥነ ጥበብ ሰው በሠራቸው ሥዕሎች ያጌጡ ናቸው። ይህ የሥነ ጥበብ ሰው ኤል ግሬኮ በመባል ይታወቅ የነበረ ሲሆን ትርጉሙም “ግሪኩ” ማለት ነው። ሙሉ ስሙ ዶሜኒኮስ ቴኦቶኮፑሎስ ይባል ነበር። ዶሜኒኮስ ይኖርበት በነበረው በጥንቱ የአይሁዳውያን ሰፈር በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሥዕሎቹ የሚገኙበት ቤተ መዘክር አለ።

ቶሌዶን በስተ ደቡብ በኩል ከሚገኙት ኮረብቶች ላይ ሆኖ ለሚመለከታት በጣም የምታምር መስላ ትታይ ይሆናል። ይሁን እንጂ የቶሌዶን ውበት ይበልጥ ማስተዋል የሚቻለው ጠባብ በሆኑት መንገዶቿ ላይ በመዘዋወር ነው። ጎብኚው ለተወሰነ ጊዜ መንገዱ ይጠፋው ይሆናል፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ማራኪ በሆኑት ጥንታዊ አሠራር ያላቸው መተላለፊያዎችና ጥንታዊ ሕንፃዎች እንዲሁም እጅግ ባጌጡ ሰገነቶችና የሰዎችን ቀልብ የሚስቡ የስጦታ ዕቃዎች በሚሸጡባቸው ሱቆች መመሰጡ አይቀርም።

ምንም እንኳ ይህቺ ጥንታዊት ከተማ የማትሰለች ብትሆንም ጎብኚው ተሰናብቷት መሄዱ ግድ ነው። ቶሌዶን ለመሰናበት ተመራጭ የሆነው ቦታ ደግሞ የታጉስ ወንዝ ደቡባዊ ዳርቻ ነው። ቀኑ እየመሸ ሲሄድ ለመጥለቅ ያቆለቆለችው ጀንበር፣ በከተማዋ ላይ ፍም የሚመስል ብርሃን ትፈነጥቃለች፤ ግርማ ሞገስ የተላበሱት የቶሌዶ ሐውልቶችም ከተማዋ በአንድ ወቅት የነበራትን ብልጽግና አሁንም የሚያንጸባርቁ ይመስላሉ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የቶሌዶ ሦስት ባሕሎች

በመካከለኛው መቶ ዘመን ቶሌዶ ውስጥ ሦስት የተለያዩ ሰፈሮች የነበሩ ሲሆን ካቶሊኮች፣ አይሁዶችና ሙስሊሞች በየራሳቸው ሕግና ባሕል መሠረት ይኖሩ ነበር። እነዚህ ሃይማኖቶች ከነበሯቸው ጥንታዊ የአምልኮ ቦታዎች መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ ሆነዋል።

በአሁኑ ጊዜ ክሪስቶ ደ ላ ሉስ በመባል የሚታወቀው የአሥረኛው መቶ ዘመን መስጊድ የሙስሊም የእጅ ባለሞያዎች ለሚታወቁበት የጡብ ሥራ ጥበብ ምሳሌ የሚሆን ነው። ይህ መስጊድ የሚገኘው በከተማው ውስጥ ባለጸጋ ሙስሊሞች ይኖሩበት በነበረው መዲና በሚባለው አካባቢ ነው።

በመካከለኛው መቶ ዘመን የተሠሩት ሁለት ምኩራቦች በአንድ ወቅት ከከተማዋ ሕዝብ አንድ ሦስተኛ የሚሆን የአይሁድ ማኅበረሰብ በቶሌዶ ይኖር እንደነበረ ይመሠክራሉ። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ምኩራቦች ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንነት ተቀይረዋል። ከእነዚህ ውስጥ በዕድሜ የሚበልጠው ሳንታ ማሪያ ላ ብላንካ የሚባለው ሲሆን ከላይ እንደሚታየው መስጊድ ሁሉ የዚህ ምኩራብ ውስጠኛ ክፍል እጅግ ያጌጡ ብዙ አምዶች አሉት። ኤል ትራንሲቶ (በስተ ቀኝ የሚታየው) የሚባለው ይበልጥ ሰፊ የሆነው ምኩራብ በአሁኑ ጊዜ የሴፋርዲ አይሁዶች ባሕል የሚታይበት ሙዚየም ሆኗል።

ጎቲክ በሚባለው ዘዴ የታነጸው በስፔን በግዙፍነቱ አንደኛ የሆነው ካቴድራል ግንባታ የተጀመረው በ13ኛው መቶ ዘመን ሲሆን ተሠርቶ እስኪያልቅ ከ200 ዓመታት በላይ ፈጅቷል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ልዩ ሰይፎችና ጣፋጩ የለውዝ ጥፍጥፍ

የከተማዋ አንጥረኞች ከሁለት ሺህ ለሚበልጡ ዓመታት ሰይፍ ይሠሩ ስለነበረ ቶሌዶ የሚለው ስም ሲነሳ ከፍተኛ ጥራት ያለው ብረት ይታወስ ነበር። የሐኒባል ሠራዊትም ሆነ የሮም ወታደሮች በቶሌዶ በተሠሩ ሰይፎች ይጠቀሙ ነበር። በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሙስሊም አንጥረኞች በቶሌዶ በተሠሩ ሰይፎችና ወታደሮች በሚጠቀሙባቸው የብረት ልብሶች ላይ ቅርጽ በመሥራት ማስጌጥ ጀመሩ። በዚህ ገጽ ላይ በስተ ግራ በኩል የሚታየውን የቶሌዶ ሰይፍ እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል። (በጥር 22, 2005 እንግሊዝኛ ንቁ! ላይ የወጣውን “በብረት ላይ የተሠሩ የወርቅ ቅርጾች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ከሚገኙት የታሪክ ማስታወሻ ቁሳቁሶች የሚሸጡባቸው ሱቆች ውስጥ አብዛኞቹ የመካከለኛውን ዘመን የሚመስሉ ከብረት የተሠሩ የወታደር ልብሶችና ሰይፎችን በየዓይነቱ ለገበያ ያቀርባሉ። እነዚህ ሰይፎች ለገዙአቸው ሰዎች ማስታወሻ ከመሆናቸው ባሻገር በፊልሞች ላይ ይታያሉ እንጂ ለጦርነት አያገለግሉም።

በቶሌዶ የሚታየው ሌላው ነገር ደግሞ የለውዝ ጥፍጥፍ ምርት ሲሆን ይህም አረቦች ከተማዋን ድል አድርገው ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው። ስፔን ሙስሊሞች ከመምጣታቸው አስቀድሞም ሰፋፊ የለውዝ እርሻዎች የነበሯት ቢሆንም የለውዝ ጥፍጥፍ ለመሥራት በጣም አስፈላጊ የሆነው ስኳር ግን አልነበራትም። ሙስሊሞች ከተማዋን ድል አድርገው ከተቆጣጠሯት በኋላ በ50 ዓመታት ውስጥ በደቡባዊ ስፔን የሸንኮራ አገዳ እርሻዎች መታየት ጀመሩ። በ11ኛው መቶ ዘመን፣ የለውዝ ጥፍጥፍ የቶሌዶ መታወቂያ ለመሆን የበቃ ሲሆን ይህም ከዚያ ጊዜ አንስቶ በሙያው የተካኑ ሰዎች የሚደሰቱበት ነገር ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ በቶሌዶ የለውዝ ጥፍጥፍ ብቻ የሚሸጥባቸው ሱቆች የሚገኙ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የለውዙ ጥፍጥፍ በትንንሽ ቅርጾች መልክ ይዘጋጃል። ቶሌዶን ለመጎብኘት የሄደ ሰው ይህን ጣፋጭ ምግብ ካልቀመሰ ጉብኝቱ የተሟላ አይሆንም።

[ምንጭ]

Agustin Sancho

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፖርቹጋል

ስፔን

ማድሪድ

ቶሌዶ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳን ማርቲን ድልድይ