ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት መመሥረት ምን ችግር አለው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት መመሥረት ምን ችግር አለው?
ጄሲካ * አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ ነበር። ችግሩ የጀመረው ጄረሚ የተባለ የክፍሏ ልጅ በእርሷ ላይ ዓይኑን እንደጣለ ባወቀችበት ጊዜ ነበር። ጄሲካ እንዲህ ብላለች:- “በጣም ቆንጆ ልጅ ነው፤ በዚያ ላይ ጓደኞቼ በጣም ጨዋ ልጅ እንደሆነና እንደዚህ ያለ ልጅ እንደማላገኝ ይነግሩኝ ነበር። ብዙ ሴቶች ከእርሱ ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ሞክረው ነበር፤ እርሱ ግን አልፈለጋቸውም። እርሱ የወደደው እኔን ብቻ ነበር።”
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጄረሚ ጓደኛው እንድትሆን ጄሲካን ጠየቃት። ጄሲካ “የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ የእኔ ዓይነት እምነት ከሌለው ሰው ጋር ጓደኝነት መመሥረት እንደማይፈቀድልኝ ነገርኩት። ጄረሚ ግን ‘ወላጆችሽ ሳያውቁ ለምን ጓደኝነት አንመሠርትም?’ የሚል ሐሳብ አመጣ” በማለት ተናግራለች።
እናንተስ አንድ የወደዳችሁት ሰው እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ቢያቀርብላችሁ ምን ምላሽ ትሰጣላችሁ? ጄሲካ መጀመሪያ ላይ በጄረሚ ሐሳብ ተስማምታ እንደነበረ ስታውቁ ትገረሙ ይሆናል። ጄሲካ “ከእርሱ ጋር ጓደኝነት ከመሠረትኩ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርበት ለማስተማር አጋጣሚ አገኛለሁ በማለት ራሴን አሳምኜ ነበር” ብላለች። ታዲያ መጨረሻቸው ምን ሆነ? ይህን በኋላ እንመለስበታለን። በመጀመሪያ ግን እንደ ጄሲካ ያሉ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ክርስቲያን ወጣቶች እንኳ ሳያውቁት እንዲህ ባለ ወጥመድ ውስጥ ሊወድቁ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
አንዳንድ ወጣቶች በድብቅ ጓደኝነት የሚጀምሩት ለምንድን ነው?
አንዳንድ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት የሚመሠርቱት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነው። በብሪታንያ የምትኖረው ሱዛን “ገና በአሥርና በአሥራ አንድ ዓመታቸው የወንድና የሴት ጓደኛ ያላቸው ልጆች አጋጥመውኛል!” ብላለች። እነዚህ ልጆች ምን አስቸኮላቸው? አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ ምክንያት የሚሆነው ከተቃራኒ ጾታ ጋር የመቀራረብ ተፈጥሯዊ ፍላጎትና
እኩዮች የሚያሳድሩት ከፍተኛ ተጽዕኖ ነው። በአውስትራሊያ የምትኖረው ሎይስ “በዚህ ዕድሜ የጾታ ፍላጎትን የሚያነሳሱ ሆርሞኖች የሚጨምሩ ከመሆኑም ሌላ በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች በሙሉ ጓደኛ ይዘው ትመለከታላችሁ” በማለት ተናግራለች።ይሁን እንጂ አንዳንዶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት የሚመሠርቱት ለምንድን ነው? በብሪታንያ የሚኖረው ጄፍሪ “ምናልባት ወላጆቻቸው ስለ ጉዳዩ ቢሰሙ ምን ይላሉ ብለው ስለሚፈሩ ነው” በማለት ተናግሯል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ዴቪድም ተመሳሳይ ስሜት አለው። “ወላጆቻቸው እንደማይፈቅዱላቸው ስለሚያውቁ አይነግሯቸውም” ብሏል። በአውስትራሊያ የምትኖር ጃን የተባለች ልጅ ደግሞ እንዲህ በማለት ሌላ ምክንያት ጠቅሳለች:- “ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት መመሥረት ልጆች በራሳቸው እንደሚመሩ የሚገልጹበት መንገድ ነው። እናንተ ትልቅ ሰው እንደሆናችሁ ብታስቡም ወላጆቻችሁ እንደዚያ አድርገው እንደማይመለከቷችሁ ከተሰማችሁ ለእነርሱ ሳትነግሯቸው የፈለጋችሁትን ነገር ለማድረግ ትወስናላችሁ። እንዳያውቁባችሁ ማድረግ ቀላል ነው።”
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆቻችሁ መታዘዝ እንደሚኖርባችሁ ይናገራል። (ኤፌሶን 6:1) ወላጆቻችሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት እንዳትመሠርቱ ከከለከሏችሁ እንዲህ ያደረጉበት በቂ ምክንያት ይኖራቸዋል። ለምሳሌ ወላጆቻችሁ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ፣ ጓደኝነት እንድትመሠርቱ የሚፈልጉት የእምነት ባልንጀራችሁ ከሆነ ሰው ጋር ብቻ ነው፤ ያውም እንዲህ እንድታደርጉ የሚፈልጉት ሁለታችሁም ማግባት በምትችሉበት ዕድሜ ላይ ከደረሳችሁ ብቻ ነው። * ሆኖም እንደሚከተሉት ዓይነት ሐሳቦች ቢመጡባችሁ አይግረማችሁ:-
▪ ከእኔ በስተቀር ሁሉም ጓደኛ ስላለው ባይተዋርነት ይሰማኛል።
▪ እምነቴን የማይጋራ ሰው ወድጃለሁ።
▪ ለማግባት በሚያስችል ዕድሜ ላይ ባልገኝም ከአንድ ክርስቲያን ጋር ጓደኝነት መመሥረት እፈልጋለሁ።
ወላጆቻችሁ እንዲህ ያሉ ሐሳቦች እንዳሏችሁ ቢረዱ ምን እንደሚሏችሁ አስቀድማችሁ ታውቁ ይሆናል። ደግሞም ወላጆቻችሁ እንደዚያ ማለታቸው ትክክል እንደሆነ ልባችሁ ያውቀዋል። ያም ሆኖ ግን በጃፓን የምትኖረው ማናሚ የተሰማት ዓይነት ስሜት ይኖራችሁ ይሆናል። እንዲህ ብላለች:- “ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት እንድመሠርት የሚደረግብኝ ግፊት በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት ላለመጀመር የወሰድኩት አቋም ትክክል መሆኑን የምጠራጠርበት ጊዜ አለ። በዛሬው ጊዜ ላሉ ወጣቶች ጓደኛ ሳይዙ መኖር የማይታሰብ ነገር ነው።” በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አንዳንዶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት የመሠረቱ ሲሆን ይህንንም ከወላጆቻቸው ደብቀዋል። እንዴት?
“ሁኔታውን ለማንም እንዳንናገር ተነገረን”
“በድብቅ ጓደኝነት መመሥረት” የሚለው ሐሳብ በራሱ ይህ ድርጊት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማታለል እንደሆነ ይጠቁማል። አንዳንዶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር የመሠረቱት ጓደኝነት እንዳይታወቅባቸው ለማድረግ ማንኛውንም ግንኙነት የሚያደርጉት በስልክና በኢንተርኔት አማካኝነት ነው። ሰው ፊት ሲሆኑ፣ የተለየ ግንኙነት እንደሌላቸው ለማስመሰል ይጥራሉ፤ ሆኖም በኢንተርኔትና በሞባይል ስልክ አማካኝነት የሚለዋወጡት መልእክት እንዲሁም በስልክ የሚያወሩት ነገር በእርግጥ ጓደኝነት እንደ መሠረቱ የሚያሳይ ነው።
በናይጄሪያ የሚኖረው ካሌብ፣ ወጣቶች የሚጠቀሙበትን ሌላ የረቀቀ ዘዴ ሲገልጽ “በድብቅ ጓደኝነት የጀመሩ አንዳንድ ወጣቶች ስለሚያወሩት ነገር እኩዮቻቸው እንዳያውቁባቸው ለማድረግ ሲሉ አንዳንድ ለየት ያሉ ቃላትንና ቅጽል ስሞችን ይጠቀማሉ” ብሏል። ወጣቶች የሚጠቀሙበት ሌላው ዘዴ ደግሞ በኋላ ላይ ብቻቸውን ተነጥለው ለመውጣት እንዲያመቻቸው በቡድን ሆነው የሚያከናውኑትን ነገር ማዘጋጀት ነው። በብሪታንያ የሚኖረው ጄምስ እንዲህ ብሏል:- “በአንድ ወቅት የተወሰንን ወጣቶች በአንድ ዝግጅት ላይ እንድንገኝ ተጋብዘን ነበር። ይህ ሁሉ የተዘጋጀው ግን ከቡድኑ ውስጥ ሁለቱ ልጆች አንድ ላይ እንዲሆኑ ታስቦ ነው፤ ከዚያም ሁኔታውን ለማንም እንዳንናገር ተነገረን።”
ጄምስ እንደተናገረው አብዛኛውን ጊዜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት የሚመሠረተው በጓደኞች ትብብር ነው። በስኮትላንድ የሚኖረው ካረል “ቢያንስ አንድ ሰው ስለ ሁኔታው ማወቁ አይቀርም፤ ሆኖም ‘እንዳትናገር’ ስለሚባል ዝም ለማለት ይመርጣል” ብሏል።
ብዙውን ጊዜ ደግሞ ዓይን ያወጣ ውሸት ትናገሩ ይሆናል። በካናዳ የምትገኘው ቤዝ “ብዙ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር የመሠረቱትን ጓደኝነት ከወላጆቻቸው የሚደብቁት የት እንደሚሄዱ ሲጠይቋቸው ውሸት በመናገር ነው” ብላለች። በጃፓን የምትገኘው ሚሳኪ እንዲህ ማድረጓን ተናግራለች:- “ታሪኮችን በጥንቃቄ እፈጥራለሁ። በወላጆቼ ዘንድ ያለኝን አመኔታ ላለማጣት ስል ከተቃራኒ ጾታ ጋር ከመሠረትኩት ጓደኝነት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ካልሆነ በስተቀር ሌላ ውሸት ላለመናገር እጠነቀቅ ነበር።”
በድብቅ ጓደኝነት መመሥረት የሚያስከትላቸው ችግሮች
ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት ለመመሥረት ከተፈተናችሁ አሊያም በአሁኑ ወቅት እንዲህ እያደረጋችሁ ከሆነ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ማለት ያስፈልጋችኋል:-
▪ ይህ የማታለል ድርጊት ወዴት ያመራኛል? ይህንን ምሳሌ 13:12 “ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል” ይላል። በእርግጥ የምትወዱትን ሰው ልብ ማሳመም ትፈልጋላችሁ?
ሰው በቅርቡ የማግባት ሐሳብ አለህ? በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ኢቫን “የማግባት እቅድ ሳይኖራችሁ ጓደኝነት መመሥረት የማትሸጡትን ዕቃ የማስተዋወቅ ያህል ነው” በማለት ተናግሯል።▪ እያደረግሁ ያለሁትን ነገር በተመለከተ ይሖዋ አምላክ ምን ይሰማዋል? መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው” ይላል። (ዕብራውያን 4:13) በመሆኑም እናንተም ሆናችሁ ጓደኛችሁ፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የመሠረታችሁትን ጓደኝነት ለመደበቅ ብትሞክሩ ይሖዋ ጉዳዩን አስቀድሞ እንደሚያውቀው እርግጠኞች ሁኑ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዋሻችሁ ጉዳዩ ሊያሳስባችሁ ይገባል። ምክንያቱም ይሖዋ አምላክ ውሸትን አጥብቆ ይጠላል። በእርግጥም ይሖዋ በዋነኝነት እንደሚጠላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተዘረዘሩት ነገሮች አንዱ “ሐሰተኛ ምላስ” ነው።—ምሳሌ 6:16-19
ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት መመሥረታችሁ፣ ጉዳዩን በይፋ አድርጋችሁት ቢሆን ኖሮ የምታገኙትን ጥበቃ እንደሚያሳጣችሁ ግልጽ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ጓደኝነት የመሠረቱ አንዳንዶች በሥነ ምግባር ብልግና መውደቃቸው የሚያስገርም አይደለም። በአውስትራሊያ የምትኖረው ጃን በትምህርት ቤት ከሚገኝ አንድ ልጅ ጋር በድብቅ ጓደኝነት የመሠረተች ጓደኛዋ ሁለት ዓይነት ኑሮ እንደምትኖር አስተውላ ነበር። ጃን “አባቷ የወንድ ጓደኛ እንዳላት ሲያውቅ ልጅቷ አርግዛ ነበር” ብላለች።
በመሆኑም ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት መሥርተህ ከሆነ ጉዳዩን በተመለከተ ከወላጆችህ ወይም ከአንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ጋር መነጋገርህ ጥበብ ይሆናል። ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት የመሠረተ ጓደኛ ካለህ ድርጊቱን በመደበቅ ከእርሱ ጋር መተባበር የለብህም። (1 ጢሞቴዎስ 5:22) ይህ ግንኙነት በጣም ጎጂ ውጤቶችን ቢያስከትል ምን ይሰማሃል? በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተጠያቂ የምትሆን አይመስልህም? የስኳር በሽታ ያለበት ነገር ግን በድብቅ ጣፋጭ ምግቦችን የሚበላ አንድ ጓደኛ አለህ እንበል። ስለ ሁኔታው ብታውቅና ጓደኛህ ለማንም እንዳትናገር ቢለምንህ ምን ታደርጋለህ? በጣም የሚያሳስብህ ምንድን ነው? የጓደኛህን ሁኔታ መደበቅ መቻልህ ነው ወይስ የእርሱን ሕይወት ለማዳን ስትል አንድ እርምጃ መውሰድህ?
ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት የመሠረተ የምታውቁት ሰው ካለም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጓደኝነታችን እስከ መጨረሻው ይበላሻል ብላችሁ አትጨነቁ! እውነተኛ ጓደኛ የሆነ ሰው ይህን ያደረጋችሁት ለእርሱ ጥቅም ብላችሁ መሆኑን ከጊዜ በኋላ መገንዘቡ አይቀርም።—ምሳሌ 27:6
“ምን ማድረግ እንዳለብኝ አወቅሁ”
መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ጄሲካ ከእርሷ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ያጋጠማትን የአንዲት ክርስቲያን ተሞክሮ ስትሰማ ሐሳቧን ቀየረች። ጄሲካ “ያቺ እህት ግንኙነቷን እንዴት እንዳቆመች ስሰማ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አወቅሁ” ብላለች። ግንኙነቱን
ማቋረጥ ቀላል ነበር? አልነበረም! ጄሲካ “በሕይወቴ የወደድኩት ያንን ልጅ ብቻ ነበር፤ ለበርካታ ሳምንታት ሥራዬ ማልቀስ ብቻ ሆኖ ነበር” ብላለች።ይሁንና ጄሲካ ሌላም ነገር ተገንዝባለች፤ ለጊዜው መጥፎ አካሄድ ተከትላ የነበረ ቢሆንም እንኳ ይሖዋን የምትወድ ሲሆን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ትፈልጋለች። ግንኙነቱን ማቋረጧ ያስከተለባት ሥቃይ ውሎ አድሮ እየቀነሰ ሄደ። ጄሲካ “አሁን ከይሖዋ ጋር ያለኝ ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተሻለ ነው። የሚያስፈልገንን መመሪያ በትክክለኛው ወቅት ስለሚሰጠን በጣም አመስጋኝ ነኝ!” በማለት ተናግራለች።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ስሞች ተለውጠዋል።
^ አን.9 በጥር 2007 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መጀመር የምችለው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ በገጽ 27 ላይ ጎላ ብለው የተጻፉትን ሦስት ሁኔታዎች መለስ ብለህ ተመልከት፤ ከእነዚህ መካከል የአንተን ስሜት የሚገልጸው የትኛው ነው?
▪ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት ሳትመሠርት ችግሩን ማስተካከል የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በድብቅ የሚመሠረት ጓደኝነት ሁሉ ስህተት ነው?
ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ የሚመሠረት ጓደኝነት ሁሉ ስህተት ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ማግባት በሚያስችላቸው ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ይበልጥ ለመተዋወቅ ፈልገው ጉዳዩን ለጊዜው በምስጢር መያዝ ፈለጉ እንበል። ምናልባትም ይህን ያደረጉት ቶማስ እንዳለው “ሰዎች ‘መቼ ነው የምትጋቡት?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት እንዳያፋጥጧቸው ፈልገው ይሆናል።”
ሌሎች ሳያስፈልግ ግፊት ማድረጋቸው ጎጂ ውጤት ሊኖረው ይችላል። (ማሕልየ መሓልይ 2:7) በመሆኑም አንዳንድ ጥንዶች ግንኙነት እንደጀመሩ ሰሞን ራሳቸውን ከሰው አግልለው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገቡ ቢጠነቀቁም ጉዳዩን በምስጢር መያዙ የጥበብ እርምጃ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። (ምሳሌ 10:19) የ20 ዓመቷ አና “እንዲህ ማድረጋቸው ሁለቱም ጉዳዩን በሚገባ አስበውበት የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ጊዜ ይሰጣቸዋል። እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ ከደረሱ በኋላ ሰዎች እንዲያውቁት ማድረግ ይችላሉ” ብላለች።
በዚህም ወቅት ቢሆን ግንኙነታችሁን ስለ ጉዳዩ የማወቅ መብት ካላቸው ሰዎች ለምሳሌ ከወላጆቻችሁ መደበቁ ስህተት ይሆናል። ጓደኝነታችሁን አስመልክቶ በግልጽ ለመናገር ካልፈለጋችሁ እንዲህ ለማድረግ የመረጣችሁት ለምን እንደሆነ ራሳችሁን ጠይቁ። ምክንያታችሁ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ከተጠቀሰችው ከጄሲካ ጋር የሚመሳሰል ነው? ወላጆቻችሁ የሚቃወሙበት በቂ ምክንያት እንደሚኖራቸው ተሰምቷችኋል?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ
ቀደም ሲል የቀረበውን ርዕስ ካነበባችሁ በኋላ ‘ወንድ ወይም ሴት ልጄ እኔ ሳላውቅ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መሥርቶ/መሥርታ ይሆን?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። አንዳንድ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት ለመመሥረት የሚፈተኑት ለምን እንደሆነ በርካታ ወጣቶች ለንቁ! መጽሔት የሰጡትን አስተያየት አንብቡ፤ ከዚያም በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ቆም ብላችሁ አስቡ።
▪ “አንዳንድ ልጆች ቤተሰባቸው የሚፈልጉትን ነገር አያሟላላቸውም፤ ስለዚህ በቤታቸው ውስጥ ያጡትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ወንድ ወይም ሴት ጓደኛ ለመያዝ ይወስናሉ።”—ዌንዲ
ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን የልጆቻችሁን ስሜታዊ ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ ማሟላት የምትችሉት እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ልታደርጓቸው የሚገቧችሁ ማሻሻያዎች አሉ? ካሉስ እነዚህ ማሻሻያዎች ምንድን ናቸው?
▪ “የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ከሌላ አገር የመጣ አንድ ተማሪ የሴት ጓደኛው እንድሆን ጠየቀኝ። እኔም ተስማማሁ። እጁን ትከሻዬ ላይ ጣል የሚያደርግ ጓደኛ ማግኘቱ ጥሩ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር።”—ዳያን
ዳያን የእናንተ ልጅ ብትሆን ኖሮ ጉዳዩን እንዴት ታዩት ነበር?
▪ “የሞባይል ስልክ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት ለመመሥረት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ወላጆች ስለ ጉዳዩ ምንም የሚያውቁት ነገር አይኖርም!”—አኔት
የልጆቻችሁን የሞባይል ስልክ አጠቃቀም በተመለከተ ምን ቅደመ ጥንቃቄ ማድረግ ትችላላችሁ?
▪ “ወላጆች፣ ልጆቻቸው ከማን ጋር ምን እያደረጉ እንደሆነ በቅርበት ካልተከታተሉ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት መመሥረት በጣም ቀላል ይሆናል።”—ቶማስ
የልጃችሁን ነፃነት ሳትጋፉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በቅርበት መከታተል የምትችሉባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን?
▪ “ልጆች ቤት በሚሆኑበት ወቅት ብዙ ጊዜ ወላጆች ቤት አይገኙም። ወይም ወላጆች፣ በልጆቻቸው ላይ ከመጠን በላይ እምነት ስለሚጥሉባቸው ከሌሎች ጋር ወደተለያዩ ቦታዎች እንዲሄዱ ይፈቅዱላቸዋል።”—ኒኮላስ
ስለ ልጃችሁ የቅርብ ጓደኛ እስቲ አስቡ። አብረው ሲሆኑ ምን እንደሚሠሩ በእርግጠኝነት ታውቃላችሁ?
▪ “ወላጆች ከልክ በላይ ጥብቅ ከሆኑ ልጆች ከተቃራኒ ጾታ ጋር በድብቅ ጓደኝነት ሊመሠርቱ ይችላሉ።”—ፖል
የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልተጣሱ ድረስ ‘ምክንያታዊ’ ለመሆን ጥረት ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?—ፊልጵስዩስ 4:5 NW
▪ “በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለሁ ለራሴ ጥሩ ግምት ስላልነበረኝ የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት እጓጓ ነበር። ስለዚህ ጎረቤት ጉባኤ ከሚገኝ አንድ ወንድም ጋር በኢንተርኔት መጻጻፍ ጀመርኩና ከእርሱ ጋር ፍቅር ያዘኝ። ይህ ወንድም የተለየሁ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርግ ነበር።”—ሊንዳ
ሊንዳ የሚያስፈልጓትን ነገሮች እዚያው ቤቷ ውስጥ ማሟላት የሚቻልባቸው አንዳንድ ጤናማ መንገዶች ምንድን ናቸው?
ይህን ርዕስም ሆነ በዚህ ገጽ ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ከወንድ ወይም ከሴት ልጃችሁ ጋር ለመወያየት ለምን አትጠቀሙበትም? ልጆቻችሁ በድብቅ ጓደኝነት እንዳይጀምሩ ለማድረግ ዋነኛው መድኃኒት ልባዊና ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግ ነው። የወጣቶችን ፍላጎት መረዳት ጊዜና ትዕግሥት ቢጠይቅም የምታገኙት በረከት ግን የሚክስ ነው።—ምሳሌ 20:5