በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አንድ ጥናት እንዳመለከተው በተፈጥሯዊ መንገድ ከመውለድ ጋር ሲወዳደር ሴቶች በቀዶ ሕክምና እንዲወልዱ ማድረግ በወሊድ ጊዜ የመሞታቸውን አጋጣሚ ከሦስት እጥፍ በላይ ከፍ ያደርገዋል።—ኦብስቴትሪክስ ኤንድ ጋይነኮሎጂ፣ ዩ ኤስ ኤ

ስቲቨን ሆኪንግ የተባሉት የሳይንስ ሊቅ በኢንተርኔት ላይ የሚከተለውን ጥያቄ ለሕዝብ አቅርበው ነበር:- “በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በአካባቢያዊ ሁኔታ ረገድ በችግር እየታመሰ ባለው ዓለም ውስጥ የሰው ዘር ከአሁን በኋላ 100 ዓመት መኖር እንዴት ይችላል?” ከአንድ ወር በኋላ ሳይንቲስቱ እንዲህ ብለዋል:- “እኔ መልሱን አላውቀውም። ጥያቄውን ያቀረብኩትም ሰዎች ስለ ሁኔታው እንዲያስቡበትና ከፊታችን የተደቀኑትን አደገኛ ሁኔታዎች እንዲገነዘቡ ለማድረግ ነው።”—ዘ ጋርዲያን፣ ብሪታንያ

በየዓመቱ 37 ሚሊዮን ከሚሆነው የታንዛኒያ ሕዝብ መካከል ከ14 እስከ 19 ሚሊዮን ያህሉ በወባ ይሠቃያል። “በሽታው በዚያች አገር በየዓመቱ 100,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል።”ዘ ጋርዲያን፣ ታንዛኒያ

ዓሦች ውኃን ከብክለት ይከላከላሉ

በርካታ የሰሜን አሜሪካ ከተሞች ለመጠጥ የሚጠቀሙበትን ውኃ ጥራት ለመቆጣጠር፣ በአካባቢያቸው የሚከሰተውን የኬሚካል ብክለት በፍጥነት በሚለዩ ብሉጊልስ ተብለው በሚጠሩ የዓሣ ዝርያዎች እየተጠቀሙ ነው። አሶሲዬትድ ፕሬስ ያቀረበው ሪፖርት ሁኔታውን እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ዓሦቹ ማዘጋጃ ቤቱ ቶሎ ቶሎ በሚቀይራቸው የውኃ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ይለቀቃሉ፤ ከዚያም መርዛማ ነገሮች ሲኖሩ በዓሦቹ አተነፋፈስ፣ የልብ ምትና በሚዋኙበት መንገድ ላይ የሚከሰተውን ለውጥ የሚመዘግቡ ለ24 ሰዓት የሚሠሩ መሣሪያዎች ይቀመጣሉ።” ዘገባው አክሎ እንደገለጸው በአንድ ወቅት በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ “ቤንዚን መፍሰሱን ዓሦቹ ከማንኛውም . . . [የመርዛማ ነገሮች] መመርመሪያ መሣሪያ ሁለት ሰዓት ቀድመው ጠቆሙ።” በዚህም የተነሳ ባለ ሥልጣኖቹ መርዛማ ኬሚካሎች ለሕዝብ ወደሚለቀቀው ውኃ ውስጥ እንዳይገቡ ማገድ ችለዋል።

የኒኮቲን መጠን ተጨምሯል

የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ የተዘጋጁ ዘመቻዎች ሲጋራ አጫሾች ማጨስ እንዲያቆሙ ሲያበረታቱ ቢቆዩም የትንባሆ ኩባንያዎች ደግሞ “ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ [የኒኮቲኑን መጠን] በ10 በመቶ” በመጨመር “ሲጋራ ይበልጥ ሱስ የሚያስይዝ እንዲሆን ለማድረግ በድብቅ” ሲሠሩ መቆየታቸውን ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ዘግቧል። የአጫሾችን ልማድ በመኮረጅ የተሠራ አዲስ መመርመሪያ መሣሪያ እንዳመለከተው የትንባሆ ኩባንያዎች “አዳዲስ ወጣት አጫሾችን ለማጥመድና የቆዩ ሱሰኞችም ማጨሳቸውን እንዳያቆሙ ለማድረግ” እየጣሩ ነው። በምርመራዎቹ እንደታየው “በሁሉም ዓይነት [ሲጋራዎች] ውስጥ ማለት ይቻላል፣ አጫሾችን ከሱስ እንዳይላቀቁ የሚያደርግ ከፍተኛ መጠን ያለው ኒኮቲን ይገኛል።”

በአእምሮ የሚመራ ሰው ሠራሽ እጅ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖርና በአደጋ ምክንያት ሁለቱም እጆቹ ከትከሻው ጀምሮ የተቆረጡበት አንድ ሰው በአሁኑ ጊዜ በአእምሮ በሚመራ ሰው ሠራሽ እጅ እየተጠቀመ ነው። ግለሰቡ በሰው ሠራሽ እጆቹ ተጠቅሞ መሰላል መውጣት፣ ቀለም መቀባትና አልፎ ተርፎም የልጅ ልጆቹን ማቀፍ ይችላል። “የግራ እጁ በአእምሮው የሚመራ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ነው” በማለት ዘ ኬብል ኒውስ ኔትዎርክ ያብራራል። ሰውየው “‘እጅህን እጠፍ’ ብሎ ሲያስብ በቀዶ ሕክምና አማካኝነት በተዘረጉለት ነርቮች በኩል የሚተላለፉት የኤሌክትሪክ መልእክቶች እጁ እንዲታጠፍ ያደርጋሉ።” መልእክት አስተላላፊ ኤሌክትሮዶች አእምሮ ያመነጫቸውን የጡንቻ እንቅስቃሴዎች በእጁ ላይ ወዳለው ኮምፒውተር ያስተላልፋሉ። ኮምፒውተሩም በሰው ሠራሹ እጅ ላይ ያሉትን ሞተሮች በማንቀሳቀስ እጆቹን የጤነኛ ሰው እጆች ከሚያደርጉት ጋር የሚመሳሰሉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።

በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ዝርያዎች!

የታሂቲው ፌኑዋ ኢንፎ የተሰኘ ጋዜጣ እንደገለጸው በየዓመቱ ወደ 17,000 የሚጠጉ አዳዲስ ዝርያዎች እየተገኙ ነው። ከእነዚህ አዳዲስ ዝርያዎች ውስጥ ሦስት አራተኛ ገደማ የሚሆኑት ነፍሳት ናቸው፤ 450 ዓይነት የጀርባ አጥንት ያላቸው ፍጡራንም የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 250 የዓሣ ዝርያዎችና ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ አጥቢዎች ተገኝተዋል። አዲስ ከተገኙት አጥቢ እንስሳት መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የአይጥ ዝርያዎችና የሌሊት ወፎች ሲሆኑ ጋዜጣው እንደዘገበው “በየዓመቱ በአማካይ ከትላልቆቹ አጥቢ እንስሳት ወገን የሆነ አንድ ዝርያ ይገኛል።” ይህም የሳይንስ ሊቃውንቱን አስገርሟቸዋል። ከተገኙት አዳዲስ ዝርያዎች መካከል ዛፎችና ዕፅዋትም ይገኙበታል።