“ክርስቶስን ተከተሉ!”
“ክርስቶስን ተከተሉ!”
የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ
ይህ የሦስት ቀን የአውራጃ ስብሰባ በግንቦት ወር ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተጀምሮ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከተሞች ውስጥ ይደረጋል። ስብሰባው በ2008ም መደረጉን ይቀጥላል። በብዙ ቦታዎች ላይ ስብሰባው ዓርብ ዕለት ጠዋት 3:20 ላይ በሙዚቃ ይጀመራል። የእያንዳንዱ ዕለት ፕሮግራም በኢየሱስ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
የዓርብ ዕለት ስብሰባ ጭብጥ ‘የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን ተመልከቱ’ የሚል ነው። (ዕብራውያን 12:2) የመክፈቻው ንግግር “‘ክርስቶስን’ መከተል ያለብን ለምንድን ነው?” የሚል ርዕስ አለው። “ኢየሱስ ታላቁ . . . (ሙሴ፣ ዳዊት እና ሰሎሞን) በመሆን የሚጫወተውን ሚና መረዳት” በሚል ርዕስ ሦስት ክፍሎች ያሉት ተከታታይ ንግግር ይቀርባል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የስብሰባውን ጭብጥ በሚያብራራውና “ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተው ልዩ ሚና” የሚል ርዕስ ባለው ንግግር ይደመደማል።
ዓርብ ዕለት የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የሚጀምረው “‘መሲሑን አገኘነው’!” በሚል ንግግር ነው። ከዚያም “‘በእርሱ ዘንድ የተሰወረውን’ ሀብት ፈልጎ ማግኘት” በሚል ርዕስ ንግግር ይቀርባል። አምስት ክፍሎች ያሉትና “የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑራችሁ” የሚል ጭብጥ ያለው የአንድ ሰዓት ተከታታይ ንግግር “‘በደግነት ተቀበላቸው፣’” “‘እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ’” እና “‘እስከ መጨረሻው ወደዳቸው’” የሚሉትንም ንግግሮች አካትቶ ይዟል። የከሰዓት በኋላው ክፍለ ጊዜ “‘በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል’” በሚለው ንግግር ይደመደማል።
የቅዳሜው ስብሰባ ጭብጥ ደግሞ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ . . . እነርሱም ይከተሉኛል” የሚል ነው። (ዮሐንስ 10:27) የአገልግሎታችንን ጥራት ማሻሻል ስለምንችልባቸው መንገዶች ጠቃሚ ሐሳቦችን የያዘ “በአገልግሎታችሁ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ” የሚል የአንድ ሰዓት ተከታታይ ንግግር ይቀርባል። ከዚያም “ክርስቶስ ‘ጽድቅን ወዷል፤ ዐመፃንም ጠልቷል’—እናንተስ?” እና “ልክ እንደ ኢየሱስ ‘ዲያብሎስን ተቃወሙ’” የሚሉት ንግግሮች ከቀረቡ በኋላ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በጥምቀት ንግግር ይደመደማል። ከንግግሩ በኋላ ብቃቱን የሚያሟሉ ዕጩዎች ይጠመቃሉ።
የቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ስብሰባ ስድስት ክፍሎች ባሉት ተከታታይ ንግግር ይጀምራል። ንግግሮቹ “ብዙዎችን አትከተሉ፣” “ልባችሁ የተመኘውንና ዓይናችሁ ያየውን አትከተሉ፣” “ከንቱ ነገሮችን አትከተሉ፣” “ሐሰተኛ መምህራንን አትከተሉ፣” “ተረቶችን አትከተሉ” እና “ሰይጣንን አትከተሉ” የሚል ርዕስ አላቸው። ቀጥሎ ከሚቀርቡት ንግግሮች መካከል “‘ከይሖዋ የተማሩ መሆን’ ያለው ብልጫ” እና “ወደ መንጋው እንዲመለሱ እርዷቸው” የሚሉት ይገኙበታል። የዕለቱ ፕሮግራም የሚደመደመው የስብሰባው ጉልህ ክፍል በሚሆነው “ና፣ ተከታዬ ሁን” በሚለው ንግግር ይሆናል።
የእሁዱ ስብሰባ ጭብጥ “እኔን መከተልህን አታቋርጥ” የሚል ነው። (ዮሐንስ 21:19 NW) “ክርስቶስን ላለመከተል ‘ምክንያት አትፍጠሩ’” የሚለውን ንግግር ተከትሎ “ከተራራው ስብከት የምናገኛቸው ውድ ዕንቁዎች” የሚል ባለ ስድስት ክፍል ተከታታይ ንግግር ይቀርባል። ይህ ተከታታይ ንግግር “መንፈሳዊ ነገሮችን የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፣” “በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ” እና “ስጡ፤ ይሰጣችኋል” እንደሚሉት ባሉ የኢየሱስ አባባሎች ላይ ያተኮረ ነው። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ “እውነተኞቹ የክርስቶስ ተከታዮች እነማን ናቸው?” በሚለው የሕዝብ ንግግር ይደመደማል። የከሰዓት በኋላውን ስብሰባ ለየት የሚያደርገው የኤልሳዕ አገልጋይ ስለነበረው ስለ ግያዝ ስግብግብነት በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ የሚቀርበው ጥንታዊ አለባበስ የሚንጸባረቅበት ድራማ ነው። የአውራጃ ስብሰባው የሚደመደመው “ፈጽሞ የማይበገረውን መሪያችንን ክርስቶስን መከተላችሁን አታቋርጡ!” በሚለው ንግግር ይሆናል።
በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አሁኑኑ እቅድ ያውጡ። እርስዎ በሚኖሩበት አካባቢ ስብሰባው የት እንደሚካሄድ ለማወቅ በአቅራቢያዎ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄደው መጠየቅ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ይችላሉ። በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ በመጋቢት 1, 2007 እትሙ ላይ የአውራጃ ስብሰባው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድባቸውን ከተሞች ዝርዝር ይዞ ወጥቷል።