በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰርከስ ትርኢት ማሳየት የተውኩበት ምክንያት

የሰርከስ ትርኢት ማሳየት የተውኩበት ምክንያት

የሰርከስ ትርኢት ማሳየት የተውኩበት ምክንያት

ማርሴሎ ኔኢም እንደተናገረው

የተወለድኩት በሞንቴቪዴዮ፣ ኡራጓይ ነው። ወላጆቼ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ቢሆኑም ምንም ሃይማኖት አልነበራቸውም። እናቴ የአራት ዓመት ሕፃን ሳለሁ በአደጋ ስለሞተች ያሳደጉኝ ዘመዶቼ ናቸው፤ እነርሱም እኔን በመልካም ሥነ ምግባር ኮትኩተው ለማሳደግ ጥረት አድርገዋል። ዕድሜዬ 20 ዓመት ሲሞላ፣ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርኩ የተለያዩ አገሮችንና ባሕሎችን ለማየት ወሰንኩ።

በኮሎምቢያ ሳለሁ በሰርከስ ትርኢት ማሳያ ቦታ በረዳትነት መሥራት ጀመርኩ። የሰርከስ ትርኢት የሚያሳዩት ሰዎች፣ ሕዝቡ በጭብጨባ አድናቆቱን ሲገልጽላቸው በጣም ደስተኞች እንደሚመስሉ ስመለከት እኔም እንደነርሱ ለመሆን ፈለግሁ። በመሆኑም በዓለም ላይ በጣም ትንሽ ከሆኑት ብስክሌቶች በአንዷ ላይ ትርኢት ማሳየት እስክችል ድረስ የምለማመድባቸውን ብስክሌቶች መጠን ቀስ በቀስ እየቀነስኩ ተለማመድኩ። ርዝመቷ 12 ሴንቲ ሜትር የሆነችውን ይህቺን ብስክሌት በአንድ እጄ ልይዛት እችላለሁ። በአብዛኛው የደቡብ አሜሪካ ክፍል ታዋቂ መሆን ጀመርኩ። በ25 ዓመት ዕድሜዬ ሜክሲኮ ሄጄ በርካታ የሰርከስ ትርኢቶችን አሳይቻለሁ።

ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ

የሰርከስ ሕይወቴን ወድጄው ነበር። ወደ ብዙ ቦታዎች እጓዛለሁ፤ የማርፈው ምርጥ በሆኑ ሆቴሎች ውስጥ ሲሆን የምመገበውም ታዋቂ ሰዎች ብቻ በሚስተናገዱባቸው ምግብ ቤቶች ውስጥ ነበር። ይህ ሁሉ ሆኖም ሕይወቴ ትርጉም የለሽ እንደሆነ ይሰማኝ የነበረ ሲሆን ለወደፊቱም ይህ ነው የምለው ተስፋ አልነበረኝም። አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ሕይወቴን የሚለውጥ ነገር ተከሰተ። የሰርከሱ አስተናባሪ ከሰው የተቀበለውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ሰጠኝ። * ትርኢት አሳይቼ ከጨረስኩ በኋላ መጽሐፉን ማንበብ ጀመርኩ፤ እኩለ ሌሊት አልፎም እንኳ ማንበቤን አላቆምኩም። መጽሐፉ ለመረዳት ቀላል ባይሆንልኝም በራእይ መጽሐፍ ላይ ስለተገለጸው ቀይ አውሬና ስለ ጋለሞታዋ የተሰጠው ማብራሪያ ትኩረቴን ሳበው። (ራእይ 17:3 እስከ 18:8) ከዚያም ለመኖሪያነትም ጭምር ልጠቀምበት የገዛሁትን መኪና በማጸዳበት ጊዜ የዚሁ መጽሐፍ አሳታሚዎች ያዘጋጁትን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚል ርዕስ ያለው ሌላ መጽሐፍ አገኘሁ።* ይህ መጽሐፍ ለመረዳት ቀለል ያለ በመሆኑ መስበክ እንዳለብኝ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም። ስለዚህ ወዲያውኑ የተማርኩትን ነገር ላገኘሁት ሰው ሁሉ መንገር ጀመርኩ።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጌ ማግኘት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ለሰርከሱ አስተናባሪ ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተሰኘውን መጽሐፍ የሰጠችው የይሖዋ ምሥክር ስልክ ቁጥር በመጽሐፉ ላይ ነበረ። ስለዚህ ደወልኩላትና አባቷ በቲዩዋና፣ ሜክሲኮ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘኝ። በዚያ የተመለከትሁት ፍቅር ያስደነቀኝ ከመሆኑም በላይ እውነተኛው ሃይማኖት ይህ መሆኑን እንዳምን አደረገኝ። የሰርከስ ትርኢት በምናሳይበት ከተማ ሁሉ በአካባቢው በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እገኝና ጽሑፎች ወስጄ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለማገኛቸው ሰዎች አሰራጭ ነበር።

በዚህ መሃል በትክክለኛው መንገድ ላይ እየተጓዝኩ መሆኔን ይበልጥ የሚያሳምነኝ ሌላ ነገር አጋጠመኝ። የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ፤ ይህ ክርስቲያኖች ሊያመልጣቸው የማይገባ በዓል መሆኑን አስረድተውኝ ነበር። ነገር ግን ዕለቱ የመክፈቻ ትርኢት ከምናሳይበት ምሽት ጋር በመገጣጠሙ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት ፈጽሞ እንደማልችል አሰብኩ። ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ አጥብቄ ጸለይኩ፤ ከዚያም አንድ የሚያስገርም ነገር ተፈጸመ። የሰርከስ ትርኢቱ መታየት ሊጀምር ሁለት ሰዓት ሲቀረው መብራት ጠፋ! በመሆኑም ወደ መታሰቢያው በዓል ለመሄድና ከዚያ ስመለስ ትርኢቱን ለማሳየት ቻልኩ። ይሖዋ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ ተሰማኝ።

በአንድ ወቅት ባንክ ወረፋ እየጠበቅሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትራክቶችን ለሰዎች እሰጥ ነበር። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ አየኝና ለቅንዓቴ አድናቆቱን ገለጸልኝ። ከዚያም በጉባኤ የሚሰጠውን መመሪያ ተከትዬ በተደራጀ መንገድ እንድሰብክ አበረታታኝ። ይህን ለማድረግ እንድችል በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልገኝም ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ገለጸልኝ። ይህን ለውጥ ለማድረግ እያሰብኩ ሳለሁ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባለ የሰርከስ ቡድን ውስጥ ከፍተኛ ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ አገኘሁ። በዚህ ወቅት ልቤ ተከፈለ። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መሄድ ፈልጌ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህን ሥራ ብቀበል በጀመርኩት የሕይወት መንገድ መቀጠል እችል እንደሆነ እርግጠኛ አልነበርኩም። ይህ የመጀመሪያ ፈተናዬ ነበር፤ እኔም ይሖዋን ላሳዝነው አልፈለግሁም። የሥራ ባልደረቦቼ ያደረግሁትን ውሳኔ ማመን ቢከብዳቸውም ሰርከሱን ትቼ በመውጣት በጉባኤ አዘውትሬ መሰብሰብ ጀመርኩ፤ ረዥም የነበረውን ጸጉሬን ቆረጥኩት። እንዲሁም ይሖዋን ለማገልገል እንድችል በአኗኗሬ ላይ ሌሎች ለውጦችም አደረግሁ።

የማልቆጭበት አርኪ ሕይወት

በ1997 የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ከመጠመቄ ትንሽ ቀደም ብሎ ሁለተኛ ፈተና ገጠመኝ፤ ወጪዬ ሁሉ ተሸፍኖልኝ በማያሚ በሚገኝ አንድ ታዋቂ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የሰርከስ ትርኢት ለማቅረብ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመሄድ ሌላ አጋጣሚ አገኘሁ። እኔ ግን ለመጠመቅና ራሴን ለይሖዋ ስወስን ከገባሁት ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ስለፈለግሁ፣ የፕሮግራሙ ተወካዮች በውሳኔዬ ቢገረሙም ይህንን አጋጣሚ እንደማልቀበል ነገርኳቸው።

አንዳንድ ሰዎች የሰርከስን ሕይወት ስለተውኩ ይቆጨኝ እንደሆነ ይጠይቁኛል። እኔም ከይሖዋ ጋር የመሠረትኩትን ወዳጅነትና የእርሱን ፍቅር ቀድሞ በነበረኝ ሕይወት በፍጹም እንደማልለውጠው እነግራቸዋለሁ። የሙሉ ጊዜ ክርስቲያን አገልጋይ በመሆን የማከናውነው አዲሱ ሥራዬ በዚህ ዓለም ላይ የሰዎችን የአድናቆት ጭብጨባ፣ ዝና፣ ወይም ብዙ ሀብት የሚያስገኝልኝ ባይሆንም አሁን እንደ ቀድሞው ባዶነት አይሰማኝም። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖርና እናቴን በትንሣኤ መልሼ የማግኘት ውድ ተስፋ አግኝቻለሁ።—ዮሐንስ 5:28, 29

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።