በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀለማትን የመለየት ችግር አለብህ?

ቀለማትን የመለየት ችግር አለብህ?

ቀለማትን የመለየት ችግር አለብህ?

“ልብሴን በምለብስበት ጊዜ የመረጥኳቸው ቀለማት የሚስማሙ መሆናቸውን የምታይልኝ ባለቤቴ ናት” በማለት ሮድኒ ይናገራል። “ቁርስ በምንበላበት ጊዜ ፍሬው መብሰሉን መለየት ስለማልችል የበሰለውን ፍሬ እሷ ትመርጥልኛለች። በሥራ ቦታ ኮምፒውተሮች ላይ፣ ብዙውን ጊዜ የተለያዩ መረጃዎች ያሉበት ዝርዝር የሚለየው በቀለም ስለሆነ በአብዛኛው የትኛውን ቁልፍ መንካት እንዳለብኝ አላውቅም። መኪና በምነዳበት ጊዜ ቀይና አረንጓዴ የትራፊክ ቀለማት ለእኔ ልዩነት የላቸውም፤ ስለዚህ የበራው መብራት የላይኛው ይሁን የታችኛው ልብ ብዬ መመልከት አለብኝ። አግድም የተደረደሩ የትራፊክ መብራቶች ሲያጋጥሙኝ ግን ቀለማቱን መለየት ሊያስቸግረኝ ይችላል።”

ሮድኒ ቀለማትን የመለየት ችግር አለበት። በዘር በወረሰው እክል ምክንያት፣ ብርሃን ተቀብሎ ምስልን ወደ አእምሮ በሚልከው የዓይኑ ውስጠኛ ክፍል (በሬቲናው) ላይ ችግር አለበት። የአውሮፓ ዝርያ ካላቸው ሰዎች መካከል ከ12 ወንዶች ውስጥ አንዱ እንዲሁም ከ200 ሴቶች መካከል አንዷ የሮድኒ ዓይነት ችግር አለባቸው። * እንደ ብዙዎቹ የችግሩ ሰለባዎች ሁሉ ሮድኒም ጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ቀለማትን ማየት ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹን ቀለማት ሲመለከት የሚታየው ቀለም ጤናማ እይታ ያላቸው ሰዎች ከሚያዩት የተለየ ነው።

በሰው ዓይን ውስጥ የሚገኘው ብርሃን ተቀብሎ ምስልን ወደ አእምሮ የሚልከው ክፍል፣ በአንደኛው ጫፍ ክብ ሆኖ በሌላኛው ጫፍ እየጠበበ የሚሄድ ቅርጽ ያላቸው ሦስት ዓይነት ብርሃን ተቀባይ ሴሎች አሉት። እያንዳንዱ ሴል ዋና ዋና ቀለማት ከሆኑት ከሰማያዊ፣ ከአረንጓዴና ከቀይ የአንዱን ቀለም የሞገድ ርዝመት እንዲለይ ሆኖ የተሠራ ነው። እነዚህ ብርሃን ተቀባይ ሴሎች የተለያየ የሞገድ ርዝመት ያለውን ብርሃን የሚለዩ ሲሆን እነርሱ ለአእምሮ የሚያስተላልፉት መልእክት ቀለማትን ለመለየት ያስችለናል። * ቀለማትን የመለየት ችግር ያለባቸው ሰዎች ግን ሴሎቻቸው አንድ ወይም ከዚያ የሚበልጡ ቀለማትን የመለየት ችሎታቸው ደካማ በመሆኑ አሊያም የሚያዩት የሞገድ ርዝመት ስለሚለወጥ የሚታያቸው ቀለም የተለየ ይሆናል። ብዙዎቹ የዚህ ችግር ተጠቂዎች በቢጫ፣ በአረንጓዴ፣ በብርቱካንማ፣ በቀይና በቡናማ ቀለም መካከል ያለውን ልዩነት ማየት አይችሉም። ይህ ችግር በጥቁር ዳቦ ወይም በቢጫ ፎርማጆ ላይ አረንጓዴ ሻጋታ ቢኖር ማየት እንዳይችሉ አለዚያም ደግሞ የፀጉሩ ቀለም ወደ ቢጫ የሚወስደው ሆኖ ሰማያዊ ዓይን ባለው ሰውና አረንጓዴ ዓይን ባለው ባለ ቀይ ፀጉር ሰው መካከል ያለውን ልዩነት እንዳይለዩ ሊያደርግ ይችላል። አንድ ሰው፣ ቀይ ቀለምን የሚለዩት ብርሃን ተቀባይ ሴሎቹ በጣም ደካማ ከሆኑ ቀይ ጽጌረዳ አበባ ጥቁር ሆኖ ሊታየው ይችላል። በጣም ጥቂት ቁጥር ያላቸው የዚህ ችግር ተጠቂዎች ሰማያዊ ቀለም ማየት አይችሉም።

ቀለማትን የመለየት ችግርና ልጆች

ቀለማትን የመለየት ችግር ብዙውን ጊዜ በዘር የሚወረስና አንድ ሰው ሲወለድ ጀምሮ የሚኖር ሲሆን ችግሩ ያለባቸው ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ቀለማቱን መለየት የሚችሉበትን መንገድ ሳይታወቃቸው ይፈጥራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ ቀለማት መካከል ያለውን ልዩነት ማየት ባይችሉም ደመቅ ወይም ፈዘዝ ማለታቸውን በማስተዋል እነዚህን ልዩነቶች ለቀለማቱ ከሚሰጣቸው ስሞች ጋር ያዛምዷቸዋል። በተጨማሪም ግዑዝ ነገሮችን በቀለማቸው ሳይሆን በውጪያዊ ሁኔታቸውና በልስላሴያቸው ወይም በሻካራነታቸው መለየትን ይለምዱ ይሆናል። እንዲያውም ብዙ ወጣቶች ቀለማትን የመለየት ችግር እንዳለባቸው በልጅነታቸው ሳይታወቃቸው ያድጋሉ።

ትምህርት ቤቶች፣ በተለይም በመዋዕለ ሕፃናት ያሉ ተማሪዎችን ለማስተማር የተለያዩ ቀለማት ያላቸው የማስተማሪያ መሣሪያዎችን ስለሚጠቀሙ ወላጆችና አስተማሪዎች ቀለማት የመለየት ችግር ያለበትን ልጅ ትምህርት የመቀበል ችግር እንዳለበት በማሰብ ሊሳሳቱ ይችላሉ። እንዲያውም አንዲት መምህርት፣ አንድ የአምስት ዓመት ልጅ ሥዕሎችን ቀለም በሚቀባበት ጊዜ ደመናን ሮዝ፣ ሰዎችን አረንጓዴ፣ የዛፎችን ቅጠሎች ደግሞ ቡናማ ቀለም በመቀባቱ ቀጥታዋለች። ቀለማትን የመለየት ችግር ላለበት ልጅ እነዚህ ቀለማት ምንም ስህተት የሌላቸው ይመስሉት ይሆናል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ባለ ሥልጣናት ልጆች ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ቀለማትን የመለየት ፈተና ዘወትር እንዲሰጣቸው ሐሳብ ማቅረባቸው ትክክል ነው።

ለዚህ ችግር እስካሁን ፈውስ ባይገኝለትም እንኳ ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ችግሩ እየባሰ አይሄድም፤ እንዲሁም ለሌላ ዓይነት የዓይን እክሎች አያጋልጥም። * ያም ቢሆን ግን ቀለማትን መለየት አለመቻል ሊያበሳጭ የሚችል እክል ነው። ይሁን እንጂ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ያለባቸውን ማንኛውንም ከአለፍጽምና ጋር የተያያዘ ችግር ያስወግድላቸዋል። በመሆኑም ማንኛውም ዓይነት የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች የይሖዋን ሥራዎች ውበታቸው ምንም ሳይጓደል ለማየት ይታደላሉ።—ኢሳይያስ 35:5፤ ማቴዎስ 15:30, 31፤ ራእይ 21:3, 4

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ቀለማትን የመለየት ችግር ሁሉንም ዘሮች ሊያጠቃ ቢችልም ነጭ የቆዳ ቀለም ባላቸው ሰዎች ዘንድ በጣም የተለመደ ነው።

^ አን.4 ብዙ እንስሳት ቀለማትን የሚያዩበት መንገድ ከእኛ የተለየ ቢሆንም ቀለማትን መለየት ይችላሉ። ለምሳሌ ውሾች ሁለት ዓይነት ብርሃን ተቀባይ ሴሎች ብቻ ያሏቸው ሲሆን አንዱ ሰማያዊ፣ ሌላው ደግሞ በቀይና በአረንጓዴ መካከል ያለ ቀለምን የሚለዩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወፎች አራት ዓይነት ብርሃን ተቀባይ ሴሎች ስላሏቸው ሰዎች እንኳ ሊያዩት የማይችሉትን አልትራቫዮሌት የሚባለውን የብርሃን ጨረር መለየት ይችላሉ።

^ አን.8 ቀለማትን የመለየት ችግር አንዳንድ ጊዜ በበሽታ ምክንያት ሊመጣ ይችላል። ዕድሜህ እየገፋ ሲሄድ ቀለማትን በመለየት ችሎታህ ረገድ ለውጥ እንዳለ ካስተዋልክ የዓይን ሐኪም ብታማክር ጥሩ ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

ቀለማትን የመለየት ችግር መኖሩ የሚታወቅበት ምርመራ

አንድ ሰው ያለበትን ቀለም የመለየት ችግር ዓይነትና ችግሩ ምን ያህል ሥር የሰደደ እንደሆነ ለማወቅ የሚደረጉት ምርመራዎች በአብዛኛው የሚከናወኑት፣ ግለሰቡ ቀለማቸውና ድምቀታቸው በሚለያይ ነጥቦች የተሠሩ ንድፎችን እንዲመለከት በማድረግ ነው። በሠፊው ጥቅም ላይ የዋለው ኢሺሃራ ተብሎ የሚጠራው ምርመራ 38 የሚያህሉ የተለያዩ ንድፎችን የያዘ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጤናማ ዓይን ያለው ሰው ከእነዚህ ንድፎች አንዱን በቀን ብርሃን ሲመለከት 42 እና 74 ቁጥሮችን (በስተግራ በኩል) ማየት አለበት፤ ብዙዎችን የሚያጠቃው ቀይና አረንጓዴ ቀለማትን የመለየት ችግር ያለበት ሰው ግን ከላይ ምንም ቁጥር የማይታየው ሲሆን ከታች ደግሞ 21 ቁጥርን ይመለከታል። *

ምርመራው ችግር መኖሩን ካሳየ፣ አንድ የዓይን ሐኪም ችግሩ ግለሰቡ ሲወለድም ጀምሮ የነበረ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት የመጣ ለይቶ ለማወቅ እንዲቻል ተጨማሪ ምርመራዎች እንዲደረጉ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 እነዚህ ሥዕላዊ መግለጫዎች የቀረቡት ምሳሌ ለመስጠት እንዲያገለግሉ ብቻ ነው። ችግሩን ለይቶ ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎች ብቃት ባለው ባለሙያ መከናወን ይኖርባቸዋል።

[ምንጭ]

በገጽ 18 ላይ የሚገኙት ቀለማትን የማየት ችሎታን መፈተኛ ሰሌዳዎች:- Reproduced with permission from the Pseudoisochromatic Plate Ishihara Compatible (PIPIC) Color Vision Test 24 Plate Edition by Dr. Terrace L. Waggoner/www.colorvisiontesting.com

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ይህ ችግር በአብዛኛው ወንዶችን የሚያጠቃው ለምንድን ነው?

በዘር የሚወረስ ቀለማትን የመለየት ችግር የሚተላለፈው X በሚባለው ክሮሞሶም አማካኝነት ነው። ሴቶች ሁለት X ክሮሞሶሞች ያሏቸው ሲሆን ወንዶች ግን አንድ X እና አንድ Y ክሮሞሶም አሏቸው። በመሆኑም አንዲት ሴት በX ክሮሞሶም አማካኝነት የማየት ችግር ብትወርስም ጤናማ በሆነው ክሮሞሶም ውስጥ ያለው ባሕርይ አስተላላፊ ጂን (በራሂ) ሊያሸንፍና የማየት ችሎታዋ ደህና ሊሆን ይችላል። በX ክሮሞሶሙ አማካኝነት የማየት ችግር የወረሰ ወንድ ግን ይህንን ችግር ሊያስተካክልለት የሚችል ሌላ X ክሮሞሶም የለውም።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቀለም መለየት የምንችልበት መንገድ

በምናያቸው ነገሮች ላይ የሚንጸባረቀው ብርሃን ኮርኒያ በሚባለው ስስ የሆነ የዓይን ውጨኛ ሽፋንና በዓይናችን ሌንስ በኩል አልፎ ብርሃንን ተቀብሎ ምስልን ወደ አእምሮ በሚልከው የዓይን ክፍል (ሬቲና) ላይ ያርፋል።

ኮርኒያ

ሌንስ

ሬቲና

ምስሉ የሚታየው ተገልብጦ ቢሆንም በኋላ አእምሮ ያስተካክለዋል

ኦፕቲክ ነርቭ የሚባለው የዓይናችን ነርቭ ምስሎችን ወደ አእምሮ ያስተላልፋል

ሬቲና ወይም ምስልን ወደ አእምሮ የሚልከው የዓይን ክፍል፣ ኮን እና ሮድ የሚባሉ ሴሎች አሉት። እነዚህ ሁለቱ በጥምረት ሲሠሩ የተሟላ እይታ እንዲኖር ይረዳሉ

ሮድ

ኮን

ኮን የሚባሉት ሴሎች ቀይ፣ አረንጓዴ ወይም ሰማያዊ ብርሃንን የሚለዩ ናቸው

ቀይ

አረንጓዴ

ሰማያዊ

[ሥዕሎች]

ጤናማ እይታ ላለው ሰው የሚታየው ምስል

ቀለማትን የመለየት ችግር ላለበት ሰው የሚታየው ምስል