በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በደመ ነፍስ ከሚገኝ ጥበብ የሚልቅ መመሪያ

በደመ ነፍስ ከሚገኝ ጥበብ የሚልቅ መመሪያ

በደመ ነፍስ ከሚገኝ ጥበብ የሚልቅ መመሪያ

“የግል የሥነ ምግባር አቋም የሚባለው፣ አንድ ሰው የሚያደርጋቸው ምርጫዎች ከሥነ ምግባር አንጻር ትክክል መሆን አለመሆናቸው የሚመዘንባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ሳይኖሩ እንዲሁ በነጻነት የሚያደርገው ምርጫ ከሆነ በዚህ ሳቢያ የሚፈጠረውን የሥነ ምግባር ክፍተት ለመሙላትና ተገቢ ምግባር እንዲኖር ለማድረግ መንግሥታት የሚያወጡትን ሕግ መጠቀም የግድ ነው።”—ዶክተር ዳንኤል ካለሃን

አብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሥነ ምግባር ክፍተት፣ መንግሥታት ወንጀልን ለመግታት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሕግጋት እንዲያወጡ እያስገደዳቸው በመሆኑ የዶክተር ካለሃን ስጋት እውን ሆኗል። ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የናይጄሪያ እናቶች የመሪዎች ስብሰባ ላይ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት የአገሪቱ የወደፊት ሁኔታ በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው ገልጸው ነበር። ፕሬዚዳንቱን ያሳሰባቸው የፖለቲካ ሥርዓቱ ወይም ድህነት ሳይሆን “ከዚህ ይበልጥ ከባድ የሆነ ችግር” ብለው የጠሩት “በቤተሰብ፣ በሥራ ቦታ፣ በማኅበረሰቡና በአገሪቱ ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው መሠረታዊ የሥነ ምግባር [ደንቦች] መሸርሸር” ነበር።

በብሪታንያ በ1,736 እናቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው “የሥነ ምግባር እሴቶች በፍጥነት በማሽቆልቆላቸውና ነጠላ ወላጆች በመበራከታቸው የተነሳ ባሕላዊው የቤተሰብ ተቋም እየተንኮታኮተ ነው።” በቻይናም ቢሆን ሥነ ምግባር በፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው። በዚያ አገር ያሉ ሰዎች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከብዙ ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት እንደሚፈጽሙ ታይም መጽሔት ዘግቧል። ከ100 ከሚበልጡ ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት እንደፈጸመች በጉራ የምትናገር አንዲት ቻይናዊት ወጣት “የራሴ ሕይወት እስከሆነ ድረስ ያሻኝን ማድረግ እችላለሁ” ብላለች።

የሥነ ምግባር አቋም መሸርሸር በሥልጣን ላይ ባሉት ሰዎችም ዘንድ ይታያል። ጃቬድ አክባር የተባሉ ሰው በካናዳ ቶሮንቶ ስታር ጋዜጣ ላይ “ሰዎች፣ በሥነ ምግባር ረገድ መሪዎቻቸውን ጥሩ ምሳሌ እንደሆኑ አድርገው መመልከት አቁመዋል” በማለት ተናግረዋል። እኚህ ሰው እንደገለጹት ፖለቲከኞች፣ የትላልቅ ድርጅቶች ሥራ አስኪያጆች ሌላው ቀርቶ የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ሳይቀሩ “ተገቢ የሥነ ምግባር ጥንካሬ እንደሚጎድላቸው ይታያል።”

ሥነ ምግባር እያሽቆለቆለ ያለው ለምንድን ነው?

ሥነ ምግባር እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ያደረጉት ነገሮች በርካታ ናቸው። ከእነዚህም አንዱ በባሕላዊ የሥነ ምግባር እሴቶች ላይ የማመጽ መንፈስ መስፋፋቱ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ክፍል በተካሄደ አንድ የሕዝብ አስተያየት ጥናት መሠረት ጥያቄ ከቀረበላቸው የኮሌጅ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ “ትክክልና ስህተት የሚባለው ነገር በግል አመለካከት ላይ የተመካ እንደሆነ” ይሰማቸዋል።

የፖለቲካ ጸሐፊ የሆኑት ዝቢግኒየቭ ብራዥኒስኬ ለሥነ ምግባር እሴቶች ማሽቆልቆል ምክንያት የሆነውን ሌላ ነገር ጠቅሰዋል። በዛሬው ጊዜ የሚገኘው ኅብረተሰብ “የግል ፍላጎትን ወዲያውኑ በማርካት ላይ ያተኮረ ሲሆን የሰዎች ባሕርይ በዋነኝነት የተመሠረተው የሕይወት ትልቁ ዓላማ የግልና የጋራ ደስታ ማግኘት እንደሆነ በሚገልጽ መርሕ ላይ ነው” በማለት ጽፈዋል። ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ የግል ውሳኔ የማድረግ ነፃነት፣ ስግብግብነት እንዲሁም የራስን እርካታ መፈለግ ማራኪ መስለው ይቀርቡ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት እንዲሁም ከሌሎች ጋር የተሻለ ዝምድና ለመመሥረት ያስችላሉ?

ኢየሱስ “ጥበብ . . . በሥራዋ ጸደቀች” ብሏል። (ማቴዎስ 11:19) ሰዎች የሥነ ምግባር እሴቶችን አሽቀንጥረው በመጣላቸው ከስጋት ተላቀው ይበልጥ ደስተኞች ሆነዋል? እንዲህ ዓይነቱ አኗኗር ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዳንዶቹ እያደር እየባሰ የመጣ አለመተማመን፣ ስጋት፣ የትዳር መፍረስ፣ ልጆች ያለ አባት ወይም ያለ እናት ማደጋቸው፣ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች መዛመት፣ ያልተፈለጉ እርግዝናዎች፣ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትና ዓመጽ ናቸው። እነዚህ እውነታዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት ሰዎች በእርካታና በስኬት ፈንታ ሐዘንና ውድቀት እያጋጠማቸው ነው።—ገላትያ 6:7, 8

የአምላክ ነቢይ የነበረው ኤርምያስ በዘመኑ ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ችግሮች ከተመለከተ በኋላ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ኤርምያስ 10:23) በእርግጥም አምላክ፣ ከእሱ ተነጥለን ትክክልና ስህተት የሆነውን ራሳችን እንድንወስን አድርጎ አልፈጠረንም። ለእኛ ጠቃሚ የመሰለን ነገር ጎጂ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 14:12 ላይ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያደርሳል” በማለት ይናገራል።

ከውስጥ የሚዋጋን ጠላት!

በሥነ ምግባር ጉዳዮች ረገድ መመሪያ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ልባችን ሊያታልለን ስለሚችል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በኤርምያስ 17:9 ላይ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?” ይላል። አንድ ሰው ተንኮለኛ እንደሆነ እያወቅህ ታምነዋለህ? እንደማታምነው የታወቀ ነው! ሆኖም እያንዳንዳችን ተንኮለኛ የሆነ ልብ አለን። በመሆኑም አምላክ የሚከተለውን ቀጥተኛና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል:- “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል።”—ምሳሌ 28:26 የ1954 ትርጉም

ይህ ጥቅስ ማድረግ የሚገባንን ቁልፍ ነገር ይገልጽልናል:- ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት በራሳችን ችሎታ ከመታመን ይልቅ በአምላካዊ ጥበብ መመላለስ ያስፈልገናል፤ በዚህም ራሳችንን ከብዙ ወጥመዶች እናድናለን። ከዚህም በላይ ውድ የሆነችው ጥበብ ከልብ ለሚፈልጓት ሁሉ በቀላሉ ትገኛለች። የአምላክ ቃል “ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል” ይላል።—ያዕቆብ 1:5

“በፍጹም ልብህ” በአምላክ ታመን

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪያችን ሲገልጽ “እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው” ይላል። (ዘዳግም 32:4) አዎን፣ ይሖዋ እንደ ግዙፍ ዓለት ነው። በአካባቢያችን ምንም ዓይነት ለውጥ ቢከናወን እርሱ አስተማማኝ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መመሪያ እንደሚሰጠን ሙሉ በሙሉ ልንተማመንበት እንችላለን። ምሳሌ 3:5, 6 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል” ይላል።

በእርግጥም ‘የራሳችንን ጠጉር እንኳ ከሚቆጥረው’ ፈጣሪያችን የተሻለ መመሪያ ማን ሊሰጠን ይችላል? (ማቴዎስ 10:30) ከዚህም በላይ ይሖዋ በማንኛውም ወቅት፣ ሌላው ቀርቶ እውነታውን መቀበል በሚከብደን ጊዜም ጭምር ሐቁን እንዲነግረን የሚገፋፋው ፍቅር ያለው እውነተኛ ወዳጃችን መሆኑን አረጋግጧል።—መዝሙር 141:5፤ ምሳሌ 27:6

በተጨማሪም ይሖዋ ለሚሰጠን መመሪያ እንድንገዛ እንደማያስገድደን ልብ በል። ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስተን እንድንታዘዘው ይፈልጋል። “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” ይለናል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ወዳለው አምላክ ለመቅረብ አትገፋፋም? ከዚህም ሌላ አምላክ፣ በዓለም ላይ በስፋት በተሰራጨውና በመንፈስ አነሳሽነት ባስጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ጥበቡን በቀላሉ እንድናገኘው አድርጓል!—2 ጢሞቴዎስ 3:16

የአምላክ ቃል መንገድህን እንዲያበራልህ ፍቀድ

መዝሙራዊው ቅዱሳን ጽሑፎችን አስመልክቶ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 119:105) ለእግራችን መብራት የሆነ ነገር፣ አጠገባችን የሚገኝን አደጋ እንድናይ የሚያስችለን ሲሆን የመንገድ ብርሃን ደግሞ ከፊት ለፊታችን ያለውን ጎዳና ያበራልናል። በአጭር አነጋገር የአምላክ ቃል በሁሉም ዘርፎች፣ ማለትም የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ሕይወታችንን በሚነኩ ጉዳዮች ረገድ ጥበብ የሚንጸባረቅበትና ከሥነ ምግባር አንጻር ትክክለኛ የሆነ ውሳኔ እንድናደርግ በመርዳት ከአደጋ ተጠብቀን እንድንኖር ሊመራን ይችላል።

ለአብነት ያህል የተራራውን ስብከት ተመልከት። ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ በተመዘገበው አጭር ንግግር ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ደስታ፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ጥላቻ፣ ስለ ምሕረት፣ ስለ ሥነ ምግባር፣ ስለ ጸሎት፣ ሀብትን ስለማሳደድና እንደዚያ ዘመን ሁሉ ዛሬም አስፈላጊ ስለሆኑ ሌሎች ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ተናግሯል። የተናገራቸው ነገሮች ጥልቅ ማስተዋል የተንጸባረቀባቸው ስለነበሩ “ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ።” (ማቴዎስ 7:28) አንተ ራስህ ጥቂት ጊዜ ወስደህ ያንን ስብከት ለምን አታነበውም? በትምህርቱ መደነቅህ አይቀርም።

የአምላክን እርዳታ “ለምኑ”

እውነቱን ለመናገር በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ከኃጢአት ጋር በውስጣችን የምናደርገውን ትግል ከውጊያ ጋር ያመሳስለዋል። (ሮሜ 7:21-24) ይሁን እንጂ በአምላክ እርዳታ በዚህ ውጊያ ማሸነፍ ይቻላል። ኢየሱስ “ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ . . . ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል” ብሏል። (ሉቃስ 11:9, 10) አዎን፣ ይሖዋ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት በሚመራው ጠባብ መንገድ ላይ ለመጓዝ ልባዊ ጥረት የሚያደርግ ማንኛውንም ሰው ከመርዳት ወደኋላ አይልም።—ማቴዎስ 7:13, 14

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ሲጀምር የትንባሆ ሱሰኛ የነበረውን የፍራንክን ምሳሌ እንመልከት። ፍራንክ 2 ቆሮንቶስ 7:1ን አንብቦ እሱ ያለበት ሱስ በአምላክ ዓይን ሲታይ ‘ሥጋን የሚያረክስ’ መሆኑን ከተረዳ በኋላ ትንባሆ ማጨሱን ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። ይሁን እንጂ ከውሳኔው ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ቀላል አልሆነለትም። እንዲያውም በአንድ ወቅት ለማጨስ በጣም ከመፈለጉ የተነሳ መሬት ላይ በጉልበቱ እየዳኸ የወዳደቁ የሲጋራ ቁራጮችን እስከመፈለግ ደርሶ ነበር!

ፍራንክ እንዲህ ያለ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ድርጊት መፈጸሙ ምን ያህል የትንባሆ ባሪያ እንደሆነ እንዲገነዘብ አደረገው። (ሮሜ 6:16) በመሆኑም እርዳታ ለማግኘት አጥብቆ ጸለየ፤ እንዲሁም በአካባቢው ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር በመቀራረቡና ጤናማ ወዳጅነት በመመሥረቱ ጎጂ ልማዱን ለማሸነፍ ችሏል።—ዕብራውያን 10:24, 25

መንፈሳዊ ፍላጎትህን አሟላ

የፍራንክ ተሞክሮ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላቅ ያለ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መመሪያ እንደሚሰጥ እንዲሁም ሰዎች ይህን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንደሚያነሳሳ ከሚያሳዩ ብዙ ተሞክሮዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው። እንግዲያውስ ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሎ መናገሩ ምንም አያስገርምም።—ማቴዎስ 4:4

የአምላክን ውድ እውነቶች ተቀብለን ተግባራዊ ስናደርግ አእምሯዊ፣ ስሜታዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ጥቅም እናገኛለን። መዝሙር 19:7, 8 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ . . . የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ [ተስፋና ስለ አምላክ ዓላማ ግልጽ ግንዛቤ በመስጠት] ዐይንን ያበራል።”

ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚሰጠን እርዳታ በሥነ ምግባር ረገድ ትክክለኛ ኮምፓስ እንዲኖረንና በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችን የተሻለ እንዲሆን በማስቻል ብቻ የተወሰነ አይደለም። ስለመጪው ጊዜም ጭምር ብርሃን ፈንጥቆልናል። (ኢሳይያስ 42:9) የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚገልጸው የአምላክን አመራር ለሚቀበሉ ሁሉ መጪው ጊዜ ብሩህ ይሆንላቸዋል።

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የምትመራበት የሥነ ምግባር “ኮምፓስ”

ሰዎች ውድ የሆነ ስጦታ ይኸውም ሕሊና አላቸው። በመሆኑም በእያንዳንዱ ብሔርና ጎሣ ውስጥ ያሉ እንዲሁም በየዘመኑ የኖሩ ሰዎች ተመሳሳይነት ያለው የሥነ ምግባር መመሪያ አላቸው። (ሮሜ 2:14, 15) ይሁን እንጂ ሕሊና ሊሳሳት የማይችል መሪ አይደለም፤ የሐሰት ሃይማኖታዊ እምነቶች፣ ሰብዓዊ ፍልስፍናዎች፣ ጭፍን ጥላቻና የተሳሳቱ ምኞቶች ሕሊና በሚሰጠው መመሪያ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ ይችላሉ። (ኤርምያስ 17:9፤ ቈላስይስ 2:8) ስለዚህ አንድ አውሮፕላን አብራሪ አቅጣጫ የሚጠቁሙትን መሣሪያዎች ማስተካከል ሊያስፈልገው እንደሚችል ሁሉ እኛም ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ኮምፓሳችንን መፈተሽና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ “ሕግ ሰጪያችን” በሆነው በይሖዋ አምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት ኮምፓሳችንን ማስተካከል ያስፈልገናል። (ኢሳይያስ 33:22) ከትውልድ ወደ ትውልድ ከሚለዋወጡት ሰብዓዊ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በተቃራኒ ፍጹም የሆኑት የአምላክ መሥፈርቶች ምንጊዜም አይለወጡም። “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል።—ሚልክያስ 3:6

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስኬትና ደስታ ለማግኘት የሚረዳ መመሪያ

ደስታ ማግኘት

“መንፈሳዊ ነገሮችን የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3 NW

“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

“ብፁዓንስ [“ደስተኞችስ፣” NW] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው።”—ሉቃስ 11:28

መተማመን እንዲኖር ማድረግ

እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።”ኤፌሶን 4:25

“ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ።”—ኤፌሶን 4:28

“ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን።”—ዕብራውያን 13:4

ጥሩ ግንኙነት መመሥረት

“ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው።”—ማቴዎስ 7:12

“[ባል] ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር።”—ኤፌሶን 5:33

“እርስ በርሳችሁ . . . ይቅር ተባባሉ።”—ቈላስይስ 3:13

አለመግባባትን ማስወገድና ልዩነቶችን መፍታት

“ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ።”—ሮሜ 12:17

“ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። . . . በደልን አይቈጥርም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

“በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ።”—ኤፌሶን 4:26