በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ‘እውነተኛ ወደሆነው ሕይወት’ እንዲመራህ ፍቀድ

አምላክ ‘እውነተኛ ወደሆነው ሕይወት’ እንዲመራህ ፍቀድ

አምላክ ‘እውነተኛ ወደሆነው ሕይወት’ እንዲመራህ ፍቀድ

መንገድ መሪ ከሆነ ማንኛውም ሰው የሚፈለገው ዋነኛ ባሕርይ እምነት የሚጣልበት መሆን ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን ይሖዋን የሚያውቁ ሁሉ እሱ ከማንም በላይ እምነት የሚጣልበት አካል እንደሆነ ጽኑ እምነት አላቸው። እሱ ‘አይዋሽም።’ (ቲቶ 1:2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር ያስገባቸው ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢያሱ ይሖዋ እምነት የሚጣልበት መሆኑን መሥክሯል። ለሕዝቡ ንግግር ሲያደርግ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል” ብሏል።—ኢያሱ 23:14

ከኢያሱ ዘመን ወዲህ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተፈጽመዋል። ከዚህ ቀደም አምላክ የተናገራቸው ብዙ ትንቢቶች መፈጸማቸው ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተነገሩት ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ለማመን ጠንካራ መሠረት ይሆነናል። ከእነዚህ ትንቢቶች ውስጥ አብዛኞቹ አምላክ ለምድርና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ያለውን ዓላማ የሚመለከቱ ናቸው።

አምላክ ከሚሰጠው መመሪያ ትጠቀማለህ?

የፍቅር ተምሳሌት የሆነው ይሖዋ አሁንም ሆነ ለዘላለም ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። (ዮሐንስ 17:3፤ 1 ዮሐንስ 4:8) አዎን፣ አምላክ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ይኸውም ዘላለማዊ ሕይወት እንድናገኝ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) ይህም በመሆኑ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን በመታዘዝ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ለሰዎች በደስታ ያካፍላሉ። (ማቴዎስ 24:14) በአሁኑ ጊዜ ይህን ሥራ በ235 አገሮች እያከናወኑ ሲሆን ምሥራቹ በምድር ላይ ባሉ በሁሉም አገሮች እየተዳረሰ ነው ማለት ይቻላል!

የአምላክ መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ራእይ 11:15) በኢየሱስ አገዛዝ ሥር ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመገዛት አሻፈረኝ የሚሉ ክፉዎች ሁሉ ይጠፋሉ። (መዝሙር 37:10፤ 92:7) ከዚያ በኋላ “ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።”—ኢሳይያስ 11:9

በዚህች ፕላኔት ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው አምላክን “በመንፈስና በእውነት” በሚያመልክበትና ለፍቅራዊ አመራሩና ፍጹም ለሆኑት መሥፈርቶቹ በፈቃደኝነት በሚገዛበት ወቅት የሚኖረውን ሰላምና ስምምነት አስበው! (ዮሐንስ 4:24) በዚያን ጊዜ ሰዎች አምላክ ተስፋ የሰጠውን “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ያጣጥማሉ!

ይሁን እንጂ አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው የአምላክን አመራር የሚቀበሉና ሕይወት የሚያገኙ ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂቶች ናቸው። (ማቴዎስ 7:13, 14) አንተስ ከእነሱ መካከል ለመሆን ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምርና በአምላክ ምክር እንድትመራ ልባዊ ግብዣ ያቀርቡልሃል። እንዲህ በማድረግ ይሖዋ ምን ያህል ቸር እንደሆነ ራስህ ‘መቅመስ’ ትችላለህ። (መዝሙር 34:8) ወፎች በደመ ነፍስ እየተመሩ ወዳሰቡበት ቦታ እንደሚደርሱ ሁሉ ይሖዋም ታማኞቹን በገነት ውስጥ ወደሚያገኙት ሕይወት ይመራቸዋል።—ሉቃስ 23:43

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የዋሆች ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።”—ማቴዎስ 5:5

“ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:11

“የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ . . . እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት . . . አይኖርም።” —ራእይ 21:3, 4

“ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22