ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠባባቂ ጸሐፊ የሆኑት ማሪያ ሲኖ የተባሉ ሴት “በአሜሪካ ከሚፈጸሙ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሚሆኑ ወንጀሎች መካከል አንዱ ሰክሮ መኪና መንዳት ነው” በማለት ተናግረዋል። በ2005 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከተከሰቱት ሞት ያስከተሉ የመኪና አደጋዎች መካከል 39 በመቶ ለሚሆኑት መንስኤው የአልኮል መጠጥ ነው።—የዩናይትድ ስቴትስ የትራንስፖርት ክፍል
▪ “በዛሬው ጊዜ በእያንዳንዱ ካሬ ኪሎ ሜትር የውቅያኖስ ውኃ ላይ ከ46,000 በላይ የሚሆኑ የፕላስቲክ ቁርጥራጮች ተንሳፈው ይገኛሉ።”—የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም
▪ “በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው ላይ [የኮምፒውተር] ጨዋታዎችን በመጫወት በየዓመቱ ግማሽ ቢሊዮን ሰዓት የሚያሳልፉ ሲሆን ሥራቸውን ባለመሥራታቸውም 10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ኪሳራ ያስከትላሉ።” ይህ ደግሞ “በሥራ ቦታ ለግል ጉዳይ መረጃ ፍለጋ ድረ ገጽ በማሰስ የሚባክነውን” ጊዜ አይጨምርም።”—ማኔጅመንት ኢሹስ የተባለ ድረ ገጽ
በልጆች ላይ የሚፈጸም የዓመጽ ድርጊት
“ለብዙ ልጆች፣ ዓመጽ በየዕለቱ የሚያጋጥማቸው የዕለታዊ ኑሯቸው ክፍል ነው” በማለት የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት ዘገባ መሠረት “በ2002 በዓለም ዙሪያ ወደ 53,000 የሚጠጉ ልጆች ተገድለዋል።” በተጨማሪም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች በግዳጅ ሥራ፣ በዝሙት አዳሪነት ወይም እርቃንን በሚያሳዩ ፊልሞችና ሥዕሎች እንዲካፈሉ ይደረጋሉ። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ በደል ይወገድ ይሆን? የዋና ጸሐፊው ዘገባ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በቤትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች እንዲህ ዓይነቱ በደል እንዳይደርስ መከላከል ከሚቻልባቸው መንገዶች መካከል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በማስተማርና በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲሁም በወላጆችና በልጆች መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲኖር ማድረግና ዓመጽ የሌለበት ጠቃሚ ቅጣት መስጠት ይገኙበታል።”
ጥሩ ወዳጆች ያሉት ሰው ዕድሜው ይረዝማል!
በርካታ ጥሩ ወዳጆች ያሉት ሰው ዕድሜው ሊረዝም እንደሚችል ጆርናል ኦቭ ኤፒዲሚዮሎጂ ኤንድ ኮሚዩኒቲ ኸልዝ የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። ዕድሜያቸው 70 ዓመት ወይም ከዚያም በላይ በሆኑ 1,500 የአውስትራሊያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት፣ አረጋውያኑ የመሠረቷቸው ወዳጅነቶች በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በዕድሜያቸው ላይ ምን ያህል ለውጥ እንዳመጡ መርምሯል። ብዙ የቅርብ ወዳጆች ያሏቸው አረጋውያን ጥቂት ወዳጆች ካሏቸው ጋር ሲወዳደሩ የመሞት አጋጣሚያቸው በ22 በመቶ ያንሳል። አረጋውያን የቅርብ ወዳጆች ያላቸው መሆኑ “የመንፈስ ጭንቀትን [በመቋቋም]፣ . . . ለራስ ጥሩ ግምት በማሳደር፣ ችግርን በማሸነፍና በሞራል ጥንካሬ ወይም ደግሞ ሕይወትን በራስ በመምራት” ረገድ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ዘገባው ይናገራል።
በዕዳ የተዘፈቁ የብሪታንያ ነዋሪዎች
“የባንክ ሒሳብ ካላቸው አዋቂዎች መካከል ከአንድ ሦስተኛ የሚበልጡት አስቸኳይ ወጪዎቻቸውን የሚሸፍኑት ከባንክ በመበደር ነው” በማለት የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ተናግሯል። በባንክ ካስቀመጡት በላይ ገንዘብ ማውጣትን የሚያመለክተው ኦቨርድራፍት በመባል የሚታወቀው ይህ ዓይነቱ ብድር፣ ለአብዛኞቹ የብሪታንያ ነዋሪዎች ያልታሰበ ጉዳይ ሲያጋጥም ብቻ የሚወሰድ መሆኑ ቀርቶ “የግድ አስፈላጊ” ሆኗል፤ 3.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ብሪታንያውያን በቋሚነት እንዲህ ዓይነቱን ብድር ይወስዳሉ። ክሬዲት አክሽን የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ኃላፊ የሆኑት ኬት ታንደር ለዚህ ዓይነቱ ልማድ ተወቃሽ የሚሆነው “ኅብረተሰቡን የተጠናወተው የፈለገውን ነገር ወዲያውኑ ካላገኘሁ የማለት አባዜ” እንደሆነ ይገልጻሉ። ታንደር እንዲህ በማለት አስጠንቅቀዋል:- “በሚሊዮን የምንቆጠር ሰዎች እየኖርን ያለነው ከአቅማችን በላይ ሲሆን ስለ ገንዘብ አያያዝ መሠረታዊ የሆነ እውቀት እንኳ የሌለን መሆኑ ደግሞ አብዛኞቻችን አኗኗራችን ምን ያህል ወጪ እያስወጣን እንዳለ ምንም እንዳናውቅ አድርጎናል።”
በምሽት የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎችና የምድር ሙቀት
ጄት አውሮፕላኖች በሰማይ ላይ በሚበሩበት ጊዜ በሚወጣው ጢስ ዙሪያ የሚፈጠረው ጤዛ የከባቢ አየሩን ሙቀት መጠን እንደሚያቃውሰው ሳይንቲፊክ አሜሪካን ይናገራል። ይህ ጤዛ ቀን ቀን ወደ ምድር የሚመጣውን የፀሐይ ብርሃን በማንጸባረቅ ከባቢ አየሩ እንዲቀዘቅዝ የሚያደርግ ሲሆን ማታ ማታ ግን ከበታቹ ያለው የከባቢ አየር ሙቀት እንዳይወጣ አምቆ ይይዛል። እንግሊዛውያን ተመራማሪዎች እንደደረሱበት “ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋት 12 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ የሚደረጉ በረራዎች ከጠቅላላው የአየር በረራ ውስጥ ሩብ ያህል ብቻ ቢሆኑም በጢሱ ዙሪያ በሚፈጠረው ጤዛ ምክንያት ከሚከሰተው የከባቢ አየር ሙቀት ውስጥ ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የሚፈጠረው በእነዚህ ሰዓታት መሆኑን” ዘገባው ይናገራል።