በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሙዚቃ፣ ለሕይወትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ ፍቅር

ለሙዚቃ፣ ለሕይወትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ ፍቅር

ለሙዚቃ፣ ለሕይወትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ ፍቅር

ቦሪስ ጉላሼቭስኪ እንደተናገረው

ሁለት ጊዜ የልብ ሕመም ያጋጠመው በስድሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ማየት የተሳነው ሰው በዓይነ ሕሊናችሁ ይታያችሁ። ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ስላገኘ እያለቀሰ አምላክን ያመሰግናል። ከ11 ዓመት በፊት እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ።

በቺርካሲ አውራጃ ውስጥ በምትገኘው ጺቡልዬቭ ተብላ በምትጠራው የዩክሬን መንደር በ1930 ተወለድኩ። የስታሊን የጭቆና አገዛዝ ሰፍኖ በነበረበት ማለትም በ1937 አባቴ “በአገር መክዳት” ወንጀል ተከሶ ወህኒ ወረደ። ቤታችን የተወረሰ ከመሆኑም በላይ ከሚያውቁን ሰዎች መካከል አብዛኞቹ አገለሉን። ብዙም ሳይቆይ ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ተይዘው ታሰሩ። ያ ወቅት እርስ በርስ መተማመን የጠፋበት እንዲሁም መከዳዳትና ፍርሃት የነገሰበት ነበር።

አባቴ ከታሰረ ከሁለት ወራት በኋላ እህቴ ሊና ተወለደች። እኔ፣ እናቴ፣ ሊናና ወንድሜ ኒኮላይ ክረምቱን መስኮትም ሆነ ማሞቂያ በሌላት አንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ አሳለፍን። ከዚያ በኋላ በአያታችን ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። እኔና ኒኮላይ ለቤተሰቡ እንጨት በመፍለጥና አንዳንድ ነገሮችን በመጠገን ቤተሰቡን እንረዳ ነበር። የእጅ ሙያ ያስደስተኝ ስለነበር ጫማዎች እሠራ ነበር። የአናጢነት ሙያም ነበረኝ። በተጨማሪም ሙዚቃ እወድ ስለነበር ከኮምፖንሳቶ ባላላይካ የሚባል የሙዚቃ መሣሪያ ሠርቼ መጫወት ተለማመድኩ። ከጊዜ በኋላ ጊታርና ማንዶሊን ለመድኩ።

ገና ልጅ ሳለሁ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጠመቅሁ። የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርትና ሥርዓት ስላልገባኝ አምላክ የለም ብሎ ማመን የተሻለ እንደሆነ ተሰማኝ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የኮምሶሞል (የወጣት ኮሚኒስቶች ማኅበር) አባል ሆንኩ። ከዚያም አጋጣሚ ስናገኝ ከሌሎች የማኅበሩ አባላት ጋር በመሆን አምላክ አለመኖሩን ለማሳመን በአምላክ ከሚያምኑ ሰዎች ጋር እንከራከር ነበር።

የማየት ችሎታዬን አጣሁ

በ1941 ይኸውም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ጦር በሶቭየት ኅብረት ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ሠራዊቱ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያልፈው የእኛን መንደር አቋርጦ ነበር። መጋቢት 16, 1944 በአቅራቢያችን ቦምብ ፈንድቶ የማየት ችሎታዬን አጣሁ። በዚህ ጊዜ ተስፋ መቁረጥ የተሰማኝ ከመሆኑም ሌላ ሕመሙ ያሠቃየኝ ነበር።

ጦርነቱ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ዞሮ ጀርመኖች ወደኋላ ለማፈግፈግ ሲገደዱ በአካባቢው የነበረው ጦርነት ጋብ አለ። በዚህ ጊዜ በአትክልት ስፍራ እየተዘዋወርኩ ወፎች ሲዘምሩ አዳምጥ ነበር። እናቴ ሁኔታዬ ስለሚያሳዝናት ቮድካ የተባለ መጠጥ ትሰጠኝ የነበረ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች ደግሞ ሙዚቃ እንድጫወትላቸው በግብዣ ላይ እንድገኝ ይጠሩኛል። ሲጋራ አጨስ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሐዘኔን ለመርሳት የአልኮል መጠጥ እጠጣ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እንዲህ ማድረጌ ምንም እንደማይረዳኝ ተገነዘብኩ።

አስተማሪ የሆነችው አክስቴ ማየት ለተሳናቸው ሰዎች የተዘጋጁ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሰምታ ስለነበር እናቴ እኔንም እዚያ እንድታስገባኝ አግባባቻት። በ1946፣ በዛሬው ጊዜ ካሚያኔትስ ፐዲልስኪ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ገብቼ መማር ጀመርኩ። ብሬይል ማንበብና መጻፍ ተማርኩ። ከዚህም በተጨማሪ ሙዚቃ መማሬን ቀጠልኩ። ኮንሰርቲና የተባለ ከአኮርዲዮን ጋር የሚመሳሰል የሙዚቃ መሣሪያ በመለማመድ ብዙ ሰዓት አሳልፍ ነበር። የትምህርት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር የማደርገውን ጥረት ተመልክቶ የእሱን አኮርዲዮን እንድጫወት ፈቀደልኝ። ፒያኖ መጫወትም ተማርኩ።

ቤተሰብ መሠረትኩ

በ1948 በቅርብ ትረዳኝ ከነበረች አስተማሪዬ ጋር ተጋባን። የቀድሞ ባሏን በጦርነቱ ያጣችው ይህች ሴት ሁለት ሴቶች ልጆች አሏት። ትምህርት ከጨርስኩ በኋላ እሷ ቤት የገባሁ ሲሆን በተቻለኝ መጠን ጥሩ ባልና አባት ለመሆን እጥር ነበር። ቤተሰቡን የማስተዳድረው ሙዚቃ በመጫወት ነው። ከዚያም በ1952 ወንድ ልጅ ወለድን።

ለቤተሰቤ ቤት ለመሥራት አንዳንድ ዝግጅቶችን አደረግሁ። መሠረቱንና ግድግዳውን ያሠራሁት ሠራተኞችን ቀጥሬ ሲሆን አብዛኞቹን ነገሮች የሠራሁት ግን እኔ ራሴ ነኝ። ማየት የተሳነኝ ስለሆንኩ ሥራዬን የማከናውነው በመዳበስና ነገሮችን በአእምሮዬ በመሳል ነው። አንድ እንጨት በእጄ እይዝና እነካካዋለሁ፤ ከዚያም በአእምሮዬ ለመሳል እሞክራለሁ። የእንጨት መሣሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዕቃዎችን የምሠራው በዚህ መንገድ ነው። የብረት መሣሪያዎችን ከፋብሪካ አዘዝኩ። የጡብ ምድጃና ሌሎች የቤት ዕቃዎችንም ሠራሁ።

የፓይፕ ኦርኬስትራ

ተጨማሪ የሙዚቃ ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ ሙዚቀኝነትን ሥራዬ አድርጌ ያዝኩ። የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በሚገባ መጫወት ከተለማመድኩ በኋላ የፓይፕ መሣሪያ መጫወት ተማርኩ። አንድ ጊዜ ከቀርከሃ የተሠራ አነስተኛ የፓይፕ መሣሪያ ጠገንኩ። ከጊዜ በኋላ ይህን የሙዚቃ መሣሪያ መሥራት ለመድኩ። በወቅቱ የሙዚቃ ባለሙያዎች መጠኑ በተለቀ መጠን የሚያወጣው ድምፅ እየቀጠነ የሚሄድ ስለሚመስላቸው ወፍራም ድምፅ የሚያወጣ ፓይፕ መሥራት አይቻልም ብለው ያስቡ ነበር። የፓይፕ ኦርኬስትራ ያልነበረውም በዚህ ምክንያት ነው።

ይሁን እንጂ የተለያየ ድምፅ እንዲያወጣ የሚያደርግ መሣሪያ የተገጠመለት ፓይፕ ለመሥራት ቻልኩ። ይህም የድምፁን መጠን መቀነስ ሳያስፈልግ ወፈር ያለ ድምፅ የሚያወጡ የተለያዩ ፓይፖችን መሥራት እንደሚቻል የሚያሳይ ነው። ከጊዜ በኋላ የተለያዩ ድምፆችን የሚያወጡ ልዩ ልዩ ፓይፖችን መሥራት ጀመርኩ።

ቀደም ሲል ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎችን የሚጫወቱ ኦርኬስትራዎች አደራጅቼ ነበር። ከእነዚህ ኦርኬስትራዎች አንዱ ማየት የተሳናቸው ሙዚቀኞችን ብቻ ያቀፈ ነበር። ከዚያም በ1960 ፓይፕ ብቻ የሚጫወት ኦርኬስትራ አቋቋምኩ። ይህ ኦርኬስትራ በሶቭየት ኅብረት ምናልባትም በዓለም ላይ በዓይነቱ ብቸኛው ነው።

አዳዲስ ግኝቶችና ጥያቄ የፈጠሩብኝ ነገሮች

በ1960 አንድ ቀን የሙዚቃ መሣሪያዎቼን ሊጠግንልኝ የመጣ ባለሙያ ስለ ሃይማኖት አንስቶ ያወያየኝ ጀመር። እኔም ከዚህ ቀደም እንደማደርገው ሁሉ አምላክ የለም ብዬ ተከራከርኩት። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን ሊያነብልኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። እኔም መጽሐፍ ቅዱስ አንብቤ ስለማላውቅ በሐሳቡ ተስማማሁ።

ያዕቆብ ቤተሰቡን ለመርዳት ጠንክሮ ስለ መሥራቱ የሚናገረው ታሪክ ልቤን ነካው። ዮሴፍን ወንድሞቹ ለባርነት እንደሸጡትና በዚያም የደረሰበትን መከራ እንዲሁም ወንድሞቹን ይቅር እንዳላቸው የሚናገረውን ታሪክ ስሰማ አለቀስኩ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 37, 39-45) ሌሎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም እንድናደርግ የሚያበረታታውን ወርቃማውን ሕግ ሲያነብልኝ ደስ አለኝ። (ማቴዎስ 7:12) መጽሐፍ ቅዱስን እንዳውቀውም ሆነ እንድወደው ያደረገኝ እንዲህ ያለው አጋጣሚ ነበር።

ከዚህ ጓደኛዬ ጋር ወደ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ። እዚያም በብሬይል የተጻፈ “አዲስ ኪዳን” በስጦታ አገኘሁና ትኩረት ሰጥቼ አነበው ጀመር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረውና የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን በሚያስተምረው ትምህርት መካከል ልዩነት እንዳለ አስተዋልኩ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክና ኢየሱስ ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሆኑና አምላክ ከኢየሱስ እንደሚበልጥ ይናገራል። (ማቴዎስ 3:16, 17፤ ዮሐንስ 14:28፤ የሐዋርያት ሥራ 2:32) ይሁን እንጂ ባፕቲስቶች አምላክና ኢየሱስ አንዳቸው ከሌላው እንደማይበልጡና የሥላሴ ክፍል እንደሆኑ አድርገው ያስተምራሉ። ሆኖም እያንዳንዷን ቃል በሚገባ እየቆጠርኩ “አዲስ ኪዳንን” በተደጋጋሚ ጊዜያት ስላነበብኩ ይህ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌለ ተገነዘብኩ።

በእጃችን በነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ “ሲኦል” የሚለው ቃል ይገኝ ነበር። ስለዚህ ዘላለማዊ የማቃጠያ ቦታ እንደሆነ አድርገው የሚያስተምሩት ሲኦል ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናዬ ለመሳል ሞከርኩ። ይህም ፍርሃት ለቀቀብኝ! መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ፍቅር እንደሆነ ስለሚናገር እሱ እንዲህ ያለ ቦታ ይፈጥራል ብሎ ማሰብ ከበደኝ። (1 ዮሐንስ 4:8) ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን ስለ ሲኦልም ሆነ ባፕቲስቶች ስለሚያስተምሯቸው ሌሎች ትምህርቶች የነበረኝ ጥርጣሬ እየጨመረ መጣ።

በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠሙኝ ትልልቅ ለውጦች

በ1968 የእንጀራ ልጆቼ ትዳር መሥርተው ልጆች አፍርተው ነበር። ከባለቤቴ ጋር ከፍተኛ አለመግባባት የተፈጠረውም በዚያን ጊዜ አካባቢ ነው። ያንን ወቅት መለስ ብዬ ሳስበው አንዳችን ለሌላው ፍቅርም ሆነ ትዕግሥት ባለማሳየታችን ይቆጨኛል። ከባለቤቴ ጋር የነበረን አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ተፋታን። ከዚያ በኋላ የመሠረትኳቸው ሁለት ትዳሮችም ቢሆኑ በፍቺ አከተሙ።

በ1981 ከካሚያኔትስ ፐዲልስኪ፣ ዮሽካር ኦላ ወደምትባል ከተማ ተዛወርኩ። ከሞስኮ በስተ ምሥራቅ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በዚህች ከተማ 35 ዓመት ኖሬያለሁ። እዚያም አንዳንድ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራቴን ቀጠልኩ። ካቋቋምኳቸው ኦርኬስትራዎች መካከል አንዱ 45 አባላት የነበሩት ሲሆን የተለያዩ የፓይፕ ዓይነቶችን ይጫወታል። ከእነዚህ ፓይፖች መካከል ትንሽ የምትባለው 20 ሴንቲ ሜትር ርዝመትና አንድ ሴንቲ ሜትር ዲያሜትር ያላት ስትሆን የምታወጣውም ቀጭን ድምፅ ነው። ትልቁ ደግሞ ርዝመቱ 3 ሜትር፣ ዲያሜትሩ ሃያ ሴንቲ ሜትር ሲሆን ወፍራም ድምፅ ያወጣል። የሙዚቃ ዝግጅታችን በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከመተላለፉም በላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወርን ለሕዝብ አሳይተናል።

በ1986 በተካሄደውና በመላው ሶቭየት ኅብረት የሚገኙ በርካታ ሙዚቀኞች በተካፈሉበት ውድድር ላይ ለፓይፕ እድገት ላደረግሁት አስተዋጽኦ የምሥክር ወረቀትና ሜዳሊያ ተሰጠኝ። ከዓመታት በኋላ ሶሎ ፎር ፓይፕ፣ ኦር ዘ ፌይሪ ቴል ኦቭ ኤ ሙዚሽያን የሚል ጥናታዊ ፊልም ወጣ። ይህንን አስመልክቶም ማሪስካያ ፕራቭዳ የተሰኘ ጋዜጣ “በዚህ ፊልም ላይ የሚታየው ቦሪስ ኒኮላይቪች ጉላሼቭስኪ በሩሲያ ውስጥ በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ የፓይፕ ኦርኬስትራ በማቋቋሙ ልዩ የምሥክር ወረቀት ተሰጥቶታል” በማለት ዘግቦ ነበር።

እውነትን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት

ወደ ዮሽካር ኦላ በተዛወርኩበት ወቅት ማየት ለተሳናቸው ሰዎች የተዘጋጁ በርካታ መጻሕፍት የሚገኙበት ቤተ መጻሕፍት አባል ሆንኩ። የካቶሊክ፣ የጴንጤቆስጤና የሜቶዲስት እምነቶች ምን እንደሚያስተምሩ አወቅሁ። ወደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም እሄድ ነበር። በጣም የሚገርመው እነሱም የሚያስተምሩት ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ከሰማሁት የተለየ አልነበረም። እነዚህ ትምህርቶች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እንዳልሆኑ አስቀድሜ አውቄ ነበር።

አሌክሳንደር ሜን የተባለ የኦርቶዶክስ ቄስ አምላክ ያህዌህ የተባለ ስም እንዳለው ጽፎ ነበር። እንዲሁም ይህ ግለሰብ አይሁዳውያን በአንድ ወቅት ንጹሑን አምልኮ ይከተሉ እንደነበርና ከጊዜ በኋላ እምነታቸው በአረማውያን ትምህርቶችና በጣዖት አምልኮ እንደተበከለ ተናግሯል። የዚህ ሰው ጽሑፎች ትኩረቴን ስለሳቡት እውነትን ለማግኘት የነበረኝን ፍላጎት አነሳሱልኝ።

ያደረግሁት ቁርጥ ውሳኔ

ካቋቋምኳቸው ኦርኬስትራዎች መካከል በአንዱ ውስጥ የማየት ችሎታዋ በጣም ደካማ የሆነ ሊዛ የምትባል አንዲት ሙዚቀኛ ነበረች። በ1990 ከዚህች ሙዚቀኛ ጋር ተጋባን። እሷም ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥሩ አመለካከት ነበራት። በዚያው ዓመት ከእህቴ ከሊና ጋር የምትኖረውን እናቴን ለመጠየቅ ቤላሩስ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ባራኖቪቺ ሄድኩ። በእናቴ ግፊት ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩና ከጊዜ በኋላ ቆረብኩ። ይህ የሆነው በሶቭየት ኅብረት ፖለቲካዊ ተሃድሶ በተካሄደበት ዘመን ነበር። ቀሳውስቱም ስብከታቸው በፖለቲካው ለውጥ ላይ ያተኮረ ሆኖ ነበር። በዚህ ጊዜ እየፈለግሁት ያለው እውነት ይህ አለመሆኑን ተረዳሁ።

በ1994 ሁለት ጊዜ ከባድ የልብ ሕመም አጋጠመኝ። በዚያው ዓመት እናቴ አረፈች። እንዲህ ያለ ተደራራቢ ችግር ቢያጋጥመኝም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤን አላቋረጥኩም። እስከዚያን ጊዜ ድረስ “አዲስ ኪዳንን” 25 ጊዜ ያህል አንብቤዋለሁ። ከዚያ በኋላ ግን መቁጠሬን አቆምኩ። ይሁን እንጂ ማንበቤን በቀጠልኩ ቁጥር የተለያዩ ጥያቄዎች ያጋጥሙኝ ነበር። በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያለ ማንም እርዳታ በራሴ ጥረት ብቻ መረዳት እንደማልችል ግልጽ እየሆነልኝ መጣ።

የእውነት ብርሃን

በ1996 ዮሽካር ኦላ ሳለን የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጥተው አነጋገሩን። ጋዜጦች አደገኛ ኑፋቄ እንደሆኑ ይዘግቡ ስለነበር ለእነሱ ጥርጣሬ ነበረኝ። ሆኖም ‘ምን ሊያደርጉኝ ይችላሉ?’ ብዬ አሰብኩ። መጀመሪያ የጠየቅኳቸው ስለ ሥላሴ ነበር። እነሱም ቃሉም ሆነ ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ ገለጹልኝ። እኔም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሼ ስለነበር በጣም ደስ አለኝ።

በሩሲያ ሲኖዶስ ፈቃድ ከታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም የሚገኝበትን ዘፀአት 6:3ን ሳነብ ልቤ በደስታ ፈነደቀ። የተለያዩ ሃይማኖቶች ይህን ስም ከሰዎች በመደበቅ የሠሩት ተንኮል አስገረመኝ። የይሖዋ ምሥክሮች በፈጣሪ ስም መጠራታቸውና ስሙን ለሌሎች ማሳወቃቸው ደግሞ አስደሰተኝ!—ኢሳይያስ 43:10

በይሖዋ ምሥክሮቹ ላይ የጥያቄ መዓት አዥጎደጎድኩባቸው። ካነሳኋቸው ጥያቄዎች መካከል “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሲኦል የሚናገረው ለምንድን ነው? በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሩሲያ ሲኖዶስ ትርጉም ምድር እንደምትቃጠል የሚናገረው ለምንድን ነው?” የሚሉት ይገኙበታል። ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ሲሰጡኝ ለዓመታት ስፈልገው የነበረውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ። ከደስታዬ የተነሳ እያለቀስኩ ተንበርክኬ አምላክን አመሰገንኩ።

ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ስብሰባዎቻቸው ይዘውኝ ይሄዱ ጀመር። ተሰብሳቢዎቹ በትኩረት የሚያዳምጡ መሆናቸው አስደነቀኝ። አንድ ተናጋሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲጠቅስ ተሰብሳቢዎቹ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አውጥተው ይከታተላሉ። ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞኝ አያውቅም። በስብሰባው ላይ በኢሳይያስ 35:5 ላይ የተመሠረተውና “የዕውራን ዓይን ሲገለጥ” በማለት የሚጀምረው መዝሙር ተዘመረ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በሳምንት አራት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ አምላክ መከራና ጦርነት እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች የሚያስከትሉትን ሥቃይ እንዴት እንደሚያስቀር ተማርኩ። አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ቃል እንደገባ ማወቄ በጣም አስደነቀኝ። (ዘፍጥረት 1:28፤ ኢሳይያስ 65:17-25፤ ራእይ 21:1-5) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይበልጥ ግልጽ ስለሆነልኝ ኅዳር 16, 1997 ራሴን ለአምላክ ወስኜ ተጠመቅሁ።

አምላክን በአንድነት ማገልገል

እኔ ከተጠመቅሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊዛም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። እንደ ልብ እንዳትንቀሳቀስ የሚያግድ የአካል ጉዳት ቢያጋጥማትም ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አድርጋ በ1998 ተጠመቀች። ወደ መጠመቂያው ገንዳ የሄደችው ሰው ተሸክሟት ነው። ሆኖም አምላክን በሙሉ ነፍስ ለማገልገል ቆርጣ ነበር። የእሽት ሕክምና የሚሰጥ ባለሙያ የቀጠርን ሲሆን ሊዛም ስፖርት መሥራት ጀመረች። ከጊዜ በኋላ ጤንነቷ ተስተካከለ። በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘቷም በላይ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ትካፈላለች። እንዲሁም ራቅ ወዳሉ ክልሎች እየሄደች ታገለግላለች።

አገልግሎት በወጣሁ ቁጥር ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጠኝ እጸልያለሁ። ከጸለይኩ በኋላ ምርኩዜን ይዤ ከቤት እወጣና በደንብ በማውቀው መንገድ ወደ አውቶቡስ ማቆሚያ እሄዳለሁ። የሰው ኮቴ ስሰማ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንስቼ ማወያየት እጀምራለሁ። አውቶቡስ ከተሳፈርኩ በኋላም ወደ መሃል አካባቢ እቀመጥና ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በማወያየት ጽሑፎችን አበረክታለሁ። ፍላጎት ያለው ሰው ሲያጋጥመኝ ስልክ ቁጥር እንለዋወጣለን።

በቅርቡ በአንድ የሕክምና ተቋም ውስጥ ከአንድ የሙዚቃ አስተማሪ ጋር የመነጋገር አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ በያዘው ጥበብ ያዘለ ምክር በጣም ስለተገረመ ወደ ቤቱ ሲመለስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከዚህም በተጨማሪ እዚያው የሕክምና ተቋም ውስጥ ማየት የተሳነው ልጅ ያለው የአንድ ፋብሪካ አስተዳዳሪ አግኝቼ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለያዘው ተስፋ ስመሠክርለት በነገሩ በጣም ተደነቀ።

ከተጠመቅሁበት ጊዜ ጀምሮ ስምንት ሰዎች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንዲሆኑ የረዳሁ ሲሆን ሌሎች በርካታ ሰዎችንም መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቻለሁ። ይሖዋ በክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አማካኝነት እኔንም ሆነ ባለቤቴን በእጅጉ እየረዳን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን የሚያነቡልን ከመሆኑም በላይ አብረን ውይይት እናደርጋለን። በጉባኤና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡ ንግግሮችንም ይቀዱልናል። ይህ ሁሉ እውነትን በልባችን ላይ ለመቅረጽ አልፎ ተርፎም ይህን እውነት ለሌሎች ማካፈል እንድንችል እገዛ አድርጎልናል። በዚህ መንገድ ጉባኤው “የብርታት ምንጭ” ሆኖልናል።—ቈላስይስ 4:11 NW

አብዛኛውን ዕድሜዬን በሙዚቃ ሙያ ላይ ያሳለፍኩ ሲሆን አሁን የመንግሥቱን ጣዕመ ዜማዎች በደስታ እዘምራለሁ። በሩሲያ ቋንቋ በተተረጎመው ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን አብዛኞቹን መዝሙሮች በቃሌ ይዣቸዋለሁ። ይሖዋ ከዚህ ክፉ ዓለም አውጥቶ ወደ እሱ እንደሳበኝና ከመንፈሳዊ ጨለማ የምወጣበትን መንገድ እንዳሳየኝ አምናለሁ። አንድ ቀን ዓይኔን ያበራልኛል ብዬ እንዳምን የሚያደርገኝም ይህ ነው።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሲ ሜጀር የሚባለውንና ወፍራም ድምፅ የሚያወጣውን ፓይፕ ስጫወት

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1960 አኮርዲዮን ስጫወት

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፓይፕ ኦርኬስትራ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከሊዛ ጋር