በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መለኮታዊ ሥልጠና መልካም ውጤት ያስገኛል

መለኮታዊ ሥልጠና መልካም ውጤት ያስገኛል

መለኮታዊ ሥልጠና መልካም ውጤት ያስገኛል

ልጆቻቸውን ከትንሽነታቸው ጀምሮ የሚያሠለጥኑ ወላጆች የድካማቸውን ፍሬ ያገኛሉ። በፔሩ፣ ደቡብ አሜሪካ የሚኖረው ዶሪያን የተባለ ልጅ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚካሄደው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተማሪ ክፍል ያቀረበው የአራት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። ይህ ልጅ ትምህርት በጀመረበት ወቅት ለአስተማሪውም ሆነ ለክፍሉ ተማሪዎች ገናን የማያከብርበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረዳት ይችል ነበር።

ዶሪያን የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ ስለ አባቶች ቀን ምን አመለካከት እንዳለው ወደ 500 በሚጠጉ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ፊት ንግግር እንዲያቀርብ ተጠይቆ ነበር። በኤፌሶን 6:4 ላይ ተመሥርቶ “የአባት ኃላፊነት” የሚል ርዕስ ያለው የአሥር ደቂቃ ንግግር ተዘጋጀ። በንግግሩ መደምደሚያ ላይ “ልጆች የአባቶችን ቀን በዓመት አንዴ ከማክበር ይልቅ ወላጆቻቸውን በየዕለቱ ማክበርና መታዘዝ ይኖርባቸዋል” በማለት ተናገረ።

በ1943፣ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የይሖዋ ምሥክሮች በሳምንት ውስጥ ከሚያደርጓቸው ስብሰባዎች መካከል አንዱ ሆነ። የዚህ ትምህርት ቤት ዓላማ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች የንግግር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ መርዳት ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ወላጆች ለልጆቻቸው ሊሰጡት የሚገባውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሥልጠናም ሲያግዝ ቆይቷል።—ምሳሌ 22:6

በስዊዘርላንድ የሚኖረው ዚሞን የተባለ የስድስት ዓመት ልጅ ኅዳር 2005 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ አቀረበ። ከአንድ ዓመት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ቃለ ምልልስ ተደረገለት። ዚሞን ለመንፈሳዊ ነገሮች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

ዚሞን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያስደስተዋል። ይህን ደግሞ ቢደክመው እንኳ ከስብሰባዎች ላለመቅረት ከሚያደርገው ጥረት መገንዘብ ይቻላል። ከዚህም በላይ ከቤተሰቡ አባላት ጋር በአገልግሎት ይካፈላል። በማንኛውም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች በየወሩ ከ30 እስከ 50 የሚያህሉ መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን ያበረክታል። አባቱን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነጋግረው ከመሆኑም በላይ አብሯቸው በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ያበረታታዋል።

ልጆቻቸውን ‘በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ’ የሚያሳድጉ ወላጆች ልጆቻቸው በምላሹ የጽድቅ ፍሬ ሲያፈሩላቸው እንደሚደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኤፌሶን 6:4፤ ያዕቆብ 3:17, 18

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶሪያን በትምህርት ቤት

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዚሞን በመንግሥት አዳራሽ