በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቋሚ ፕሮግራም አውጡ፤ ፕሮግራማችሁንም በጥብቅ ተከተሉ

ቋሚ ፕሮግራም አውጡ፤ ፕሮግራማችሁንም በጥብቅ ተከተሉ

5

ቋሚ ፕሮግራም አውጡ፤ ፕሮግራማችሁንም በጥብቅ ተከተሉ

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አዋቂዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያከናውኗቸው የተለመዱ ተግባራት አሉ። ሥራ፣ አምልኮና መዝናኛም እንኳን ሳይቀር የሚከናወኑት በተመደበላቸው ፕሮግራም መሠረት ነው። ወላጆች፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀምንና ፕሮግራማቸውን በጥብቅ መከተልን ለልጆቻቸው ካላስተማሯቸው ይጎዷቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “አንድ ልጅ የሚከተላቸው ደንቦችና ፕሮግራሞች ካሉት ከስጋት ነጻ እንደሚሆንና እንደሚረጋጋ እንዲሁም ራስን መግዛትንና በራስ መተማመንን እንደሚማር ጥናቶች ያሳያሉ” በማለት በሥነ ልቦና መስክ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሎረንስ ስታይንበርግ ተናግረዋል።

ተፈታታኝ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሕይወት በጥድፊያ የተሞላ ነው። ብዙ ወላጆች ረዥም ሰዓት ስለሚሠሩ አዘውትረው ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት በቂ ጊዜ አይኖራቸውም። ቋሚ ፕሮግራም አውጥቶ በዚያ መሠረት መመላለስ ራስን መገሠጽን ይጠይቃል፤ እንዲሁም ልጆች መጀመሪያ ላይ ፕሮግራሙን ለመከተል ፈቃደኞች ስለማይሆኑ ይህንን ለማሸነፍ ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል።

መፍትሔው ምንድን ነው? “ሁሉም በአግባብና በሥርዐት ይሁን” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ውስጥ የተገለጸውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጉት። (1 ቆሮንቶስ 14:40) ለምሳሌ ያህል፣ ብልህ የሆኑ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ገና ትንሽ እያሉ ሁልጊዜ ማታ ማታ የሚተኙበት ቋሚ ሰዓት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ከመተኛታቸው በፊት ያለው ጊዜ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የሁለት ትናንሽ ሴቶች ልጆች እናት የሆነችውና በግሪክ የምትኖረው ታቲያና እንዲህ ብላለች:- “ልጆቼ ሊተኙ አልጋቸው ውስጥ ሲገቡ አጠገባቸው ሆኜ እየደባበስኳቸው እነሱ ትምህርት ቤት እያሉ እኔ ምን ስሠራ እንደዋልኩ እነግራቸዋለሁ። ከዚያም እነሱ በዚያ ቀን ካከናወኗቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ሊነግሩኝ ይፈልጉ እንደሆነ እጠይቃቸዋለሁ። እነሱም ዘና ስለሚሉ ብዙውን ጊዜ ያጋጠሟቸውን ነገሮች እንዲሁም ስሜታቸውን በግልጽ ይነግሩኛል።”

የታቲያና ባል የሆነው ኮስታስ ለልጆቹ ታሪክ ያነብላቸዋል። “ልጆቹ ስለ ታሪኩ የተሰማቸውን ይናገራሉ፤ ብዙውን ጊዜም ውይይቱ ቀስ በቀስ አቅጣጫው ይቀየርና እነሱ ስለሚያሳስባቸው ነገር ማውራት ይጀምራሉ። ልጆቼ ምን እንደሚያሳስባቸው እንዲነግሩኝ በቀጥታ ብጠይቃቸው ኖሮ በቀላሉ አይነግሩኝም ነበር” በማለት ይናገራል። እርግጥ ነው፣ ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ በመኝታ ሰዓታቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ትፈልጉ ይሆናል። ያም ቢሆን ይህንን ልማድ ከቀጠላችሁበት ልጆቻችሁም በዚያ ሰዓት ከእናንተ ጋር ማውራታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ።

በተጨማሪም ቤተሰቦች በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ አብረው የመመገብ ልማድ ቢኖራቸው ጥሩ ነው። እንዲህ ለማድረግ የምግብ ሰዓቱን እንደ አስፈላጊነቱ መለዋወጥ ያስፈልግ ይሆናል። የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የሆነው ቻርልስ እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ከሥራ ወደ ቤት የምመለሰው አምሽቼ ነው። ባለቤቴ እኔ እስክመጣ ድረስ ለልጆቹ ትንሽ መክሰስ ሰጥታ ታቆያቸዋለች፤ ሆኖም በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን መመገብ እንድንችል ሁላችንም እስክንሰባሰብ ድረስ ሁልጊዜ ራት ሳይበሉ እንዲቆዩ ታደርጋለች። አንድ ላይ ስንሰባሰብ የዕለቱን ውሏችንን እንወያያለን፤ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንከልሳለን፤ ስለገጠሙን ችግሮች እናወራለን፤ እንዲሁም አብረን እንስቃለን። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ቤተሰባችን ደስተኛ እንዲሆን ለማድረግ ምን ያህል እንደጠቀመን ጠበቅ አድርጌ መግለጽ እፈልጋለሁ።”

በዚህ ረገድ እንዲሳካላችሁ ከፈለጋችሁ፣ ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ እንዲህ ዓይነቱን ልማድ እንዳታዳብሩ እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ። “ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ” የሚያበረታታውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ አውሉት።—ፊልጵስዩስ 1:10

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያደርጉትን የሐሳብ ግንኙነት ለማሻሻል ሌላስ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሁሉም በአግባብና በሥርዐት ይሁን።1 ቆሮንቶስ 14:40