በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ማምለክ አስደሳች ሊሆን ይችላል?

አምላክን ማምለክ አስደሳች ሊሆን ይችላል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አምላክን ማምለክ አስደሳች ሊሆን ይችላል?

ክርስቲያን እንደሆነች የምትናገር አንዲት ሴት “በአምላክ አምናለሁ እወደዋለሁም” በማለት ጽፋለች። አክላም “ቤተ ክርስቲያን መሄድ ግን አሰልቺ ሆኖብኛል” ብላለች። አንተም እንደዚህ ይሰማሃል? የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች አሰልቺ፣ እርካታ የማያስገኙ አልፎ ተርፎም ደስታ የሚያሳጡ መሆናቸው ሰዎች አምላክን በራሳቸው መንገድ ማምለክ እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል።

በቅርቡ አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው በርካታ ሰዎች ራሳቸው በፈለጉት መንገድ አምላክን ማምለክ ጀምረዋል። ይሁንና አምላክን በማምለክ ደስታ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ይህ ዓይነቱ አካሄድ እርካታ አያስገኝላቸውም። ለምን? ምክንያቱም ከነበሩበት ቤተ ክርስቲያን እንዲርቁ ያደረጋቸው ደስታ ማጣት በዚህም ወቅት የሚያጋጥማቸው መሆኑ ነው።

ይህ ሁኔታ የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሳል:- ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መሠረት መኖር አሰልቺና ደስታ የሚያሳጣ ነው?’ በፍጹም! አንድ መዝሙራዊ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈራቸው የሚከተሉት ቃላት ይህን ያረጋግጡልናል:- “ኑ፤ ደስ እያለን ለእግዚአብሔር እንዘምር፤ . . . ኑ፤ እናምልከው፤ እንስገድለትም፤ በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ፊት እንንበርከክ።”—መዝሙር 95:1, 6

ሌላ መዝሙራዊ ደግሞ “አንተ ብቻ፣ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል [ነህ]” በማለት ለይሖዋ በአድናቆት ዘምሯል። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ተብሎ የተጠራ ሲሆን የጥንቶቹም ሆኑ ዛሬ ያሉት አገልጋዮቹም እሱን ማምለካቸው ደስታ እንዳስገኘላቸው ገልጸዋል።—መዝሙር 83:18፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW

ደስታ ለማግኘት የሚረዳው ቁልፍ

አምላክን በማምለክ ደስታ እንድናገኝ የሚረዳን ቁልፍ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ሲል ያደረገውን ነገር መገንዘብ ነው። ይሖዋ ምን አድርጎልናል? “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።”—ዮሐንስ 3:16

መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ አምላክ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” የሚፈልግ መሆኑን ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) እውነትን ማወቅ ሲባል ግን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማወቅ ማለት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የምናነበውን ነገር ‘ማስተዋል’ ይኖርብናል። ይህም ጥልቀት ያለው ጥናት ማድረግን ይጠይቃል። (ማቴዎስ 15:10) እንዲህ ማድረጋችን ‘የአምላክን እውቀት እንድናገኝ’ ያስችለናል። ይህ ደግሞ የሚያስደስት ነገር ነው!—ምሳሌ 2:1-5

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመቄዶንያ ከተማ በሆነችው በቤርያ የነበሩ ሰዎች እንዲህ ያለውን ደስታ አግኝተው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ቃል ሲያስተምራቸው “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል።” እነዚህ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናት አሰልቺ ወይም ደስታ የሚያሳጣ ቢሆንባቸው ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ጉጉት አይኖራቸውም ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 17:11

ኢየሱስ “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፤ ይጠግባሉና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:6) ለረጅም ጊዜ በረሃብ ሲሰቃዩ ኖረው በቂ ምግብ ማግኘት እንደቻሉ ሰዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜም ብዙዎች መንፈሳዊ ረሃባቸውን በማስታገሳቸው እርካታ አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ልክ እንደ ቤርያ ሰዎች ‘አማኞች’ ሆነዋል።—የሐዋርያት ሥራ 17:12

የሕይወት መንገድ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ‘መንገዱን’ ተከትለዋል። ይህ ቃል በሐዋርያት ሥራ 9:2 ላይ የተጠቀሰ ሲሆን ቀደም ሲል የነበሩት ክርስቲያኖች የተከተሉትን አዲስ የሕይወት ጎዳና ያመለክታል። ዛሬም አምላክን በማምለክ ደስታ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል። አስተሳሰባቸውና አኗኗራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት እውነቶች መለወጥ ይኖርበታል።

ከዚህም የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን ‘በቀድሞ ሕይወታችሁ የነበራችሁን አሮጌ ሰውነት አውልቃችሁ ጣሉ’ ሲል አሳስቧቸዋል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ቀጥሎ እንደገለጸው ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” ልበሱ።—ኤፌሶን 4:22-24 *

ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ለውጦችን በማድረግ ይህንን ምክር ሥራ ላይ ማዋላችን የእርካታና የደስታ ምንጭ ይሆንልናል። የምንደሰትበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? ጳውሎስ የቈላስይስ ክርስቲያኖች ‘ለጌታ እንደሚገባ ለመኖርና በሁሉም እሱን ደስ ለማሰኘት’ በሕይወታቸው አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ጽፎላቸው ነበር። (ቈላስይስ 1:10) በእርግጥም እንድንደሰት የሚያደርገን ዋነኛው ምክንያት እውነተኛው አምላክ በአኗኗራችን መደሰቱን ማወቃችን ነው! ከዚህም በላይ አምላክ “በሁሉም” ነገር እሱን ደስ ማሰኘት የምንችልበትን ሁኔታ አመቻችቶልናል። ይህንንም ያደረገው የምንሠራቸውን ስህተቶች ይቅር በማለት ነው።

እያንዳንዳችን ኃጢአት ስለምንሠራ የአምላክን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገናል። ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 1:15 ላይ “ክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” በማለት ገልጿል። ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ መሥዋዕት ማድረጉ ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። በመሆኑም አንድ እውነተኛ የአምላክ አገልጋይ ኃጢአቱ ይቅር ሲባልለት ከባድ ሸክም የተነሳለት ያህል እፎይታ ይሰማዋል። ይህ ሰው ንጹሕ ሕሊና ሊኖረው እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ከልብ እስካደረገ ድረስ ለሚሠራው ኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ እርግጠኛ ስለሚሆን ሊደሰት ይችላል።

ለደስታ ምክንያት የሚሆን ሌላ ነገር

አንድ ሰው እውነተኛውን አምላክ የሚያመልከው ብቻውን አይደለም። መዝሙራዊው ዳዊት “‘ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ’ ባሉኝ ጊዜ፣ ደስ አለኝ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 122:1) በእርግጥም ከሌሎች የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ጋር አዘውትሮ መሰብሰብ ደስታችንን በእጅጉ ይጨምርልናል።

አንድ ሰው በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰዎቹ በደግነትና እኛን ለመርዳት ካላቸው ጉጉት የተነሳ ጥሩ አቀባበል ያደረጉልን ሲሆን ይህ ደግሞ እርስ በርስ እንደሚቀራረቡ የሚያሳይ ነው። አብዛኞቹ ወጣቶች የረጉና የሰከኑ በመሆናቸው እነሱም ሆኑ ወላጆቻቸው ሊኮሩ ይገባቸዋል። እንዲህ ባለ አስደሳች ስብሰባ ላይ እንድገኝ በመጋበዜ በእጅጉ የተደሰትኩ መሆኑን መናገር እወዳለሁ።”

ከረጅም ጊዜ በፊት እንደኖረው እንደ ዳዊት ሁሉ አንተም ይሖዋን ለማምለክ ከሚያስችሉህ አጋጣሚዎች ደስታ ማግኘት ትችላለህ። ዳዊት “እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉት፤ በፍስሓ ዝማሬ ፊቱ ቅረቡ” ብሏል። (መዝሙር 100:2) እውነተኛውን አምላክ ከትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስተው የሚያገለግሉ ሁሉ አምልኳቸው አስደሳች እንደሚሆን መጠበቅ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 ኤፌሶን ምዕራፍ 4​ን እና ቈላስይስ ምዕራፍ 3​ን በማንበብ እንዲህ ያለው ለውጥ ምን ነገሮችን እንደሚጨምር የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት ትችላለህ።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ የእውነተኛው አምልኮ መሠረቱ ምንድን ነው?—1 ጢሞቴዎስ 2:3-6

▪ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በአምልኳችን ደስታ ከማግኘት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?—1 ጢሞቴዎስ 1:15

▪ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አምላክን በማምለክ የምታገኘውን ደስታ የሚጨምሩልህ እንዴት ነው?—መዝሙር 100:1-5

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሌሎች ጋር ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ደስታ ይጨምራል