በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ካሉት ሰዎች ቁጥር የሚበልጥ ቴሌቪዥን አላቸው።” ይህም ሲባል ለ2.55 ሰዎች 2.73 ቴሌቪዥኖች አሉ ማለት ነው። “ሃምሳ በመቶ በሚያህሉ አሜሪካውያን ቤት ውስጥ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ቴሌቪዥን አለ።”አሶሺየትድ ፕሬስ፣ ዩ ኤስ ኤ

በመላው ደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በየቀኑ 82 ልጆች “ሌሎችን ልጆች አስገድዶ በመድፈር ወይም በሚያሳፍር መንገድ በመደብደብ ወንጀል” ተከስሰው ይቀርባሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ከተከሳሾቹ መካከል አብዛኞቹ ጥቃቱን ለመፈጸም “ያነሳሳቸው በቴሌቪዥን ያዩት ድርጊት እንደሆነ” ተናግረዋል።ዘ ስታር፣ ደቡብ አፍሪካ

በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ምርታማነትን ይቀንሳል

አንዳንድ ስፔናውያን ከእንቅልፍ ጋር በተያያዘ ያላቸው መጥፎ ልማድ በምርታማነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ባርሴሎና የሚገኝ የአንድ የእንቅልፍ ክሊኒክ አስተዳዳሪ የሆኑት ዶክተር ኤድዋርድ ኢስቲቪል እንደገለጹት ስፔናውያን ከሌሎች አውሮፓውያን በተለየ መልኩ ቀደም ብለው ከመኝታቸው እንደሚነሱ፣ ረዥም ሰዓት እንደሚሠሩና ራታቸውንም አምሽተው እንደሚበሉ እንዲሁም የእንቅልፍ ሰዓታቸው በአማካይ ከ40 ደቂቃ የሚያንስ እንደሆነ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የእንቅልፍ ማነስ እንደ መነጫነጭ፣ የማስታወስ ችሎታ መቀነስና የመንፈስ ጭንቀት ያሉ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ዶክተር ኢስቲቪል ሲያስጠነቅቁ “የአእምሮ ሥራ ወይም ትኩረት የሚጠይቅ ሌላ ዓይነት ሥራ የሚሠራ ማንኛውም ሰው በየቀኑ ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓት መተኛት ይኖርበታል” ብለዋል።

ስንዴን ለሙቀት ማመንጫነት መጠቀም ነውር አይደለም?

ቤትን ለማሞቅ ሲባል ስንዴን የመሰለ ነገር ማቃጠል ነውር ነው? የስንዴ ዋጋ እየቀነሰ ሲሄድ የነዳጅ ዋጋ ግን እየናረ በመሆኑ አንድ ገበሬ ምርቱን ሸጦ ነዳጅ ከመግዛት ይልቅ ስንዴውን ለሙቀት ማመንጫነት መጠቀም ይበልጥ የሚያዋጣው መሆኑን ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ዞንታግስጻይቱንግ የተባለ የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። ገበሬው 2.5 ኪሎ ግራም ስንዴ ለማምረት 20 የአሜሪካ ሳንቲም የሚያስወጣው ሲሆን ለሙቀት ማመንጫነት ቢጠቀምበት ግን ከ1 ሊትር ነዳጅ የሚያገኘውን ሙቀት ያካክስለታል። የ1 ሊትር ነዳጅ ዋጋ ደግሞ 60 ሳንቲም ነው። በመሆኑም ጋዜጣው “ሌሎች ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ እህልን ማቃጠል” አግባብነት አለው? የሚል አሳሳቢ ጥያቄ አንስቷል።

የሊቀ ጳጳሱ ጉብኝት መነገጃ ሆነ

ሊቀ ጳጳሱ በ2006 ጀርመንን በጎበኙበት ወቅት ባለፋብሪካዎች፣ ነጋዴዎችና የቱሪዝም ድርጅቶች ከጉብኝቱ ጠቀም ያለ ትርፍ ለማግኘት ከፍተኛ ዝግጅት አድርገው ነበር። ቤተ ክርስቲያኗም በበኩሏ የተወሰኑ ዕቃዎችን ገበያ እንደ ልብ ለመቆጣጠር ስትል በሽርክና ለመሥራት ተዋውላ ነበር። ለገበያ ከቀረቡት የማስታወሻ ዕቃዎች መካከል መቁጠሪያዎች፣ ሻማዎች፣ በጠርሙስ የታሸገ ጠበል፣ የቡና ሲኒ፣ ቆብ፣ ካናቴራዎች፣ የቁልፍ መያዣዎችና የቫቲካን ባንዲራዎች ይገኙበታል። ደር ሽፒገል የተሰኘው ጋዜጣ እንደሚከተለው በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ኢየሱስ ክርስቶስ . . . ነጋዴዎችን ከቤተ መቅደሱ ኣባሯል፤ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግን የወጣላት ነጋዴ ሆናለች።”

የቪዲዮ ጨዋታዎች ያደነዘዟቸው ሰዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአይዋ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የሥነ ልቦና ተመራማሪዎች “የዓመጽ ድርጊቶችን የሚያሳዩ የቪዲዮ ጨዋታዎችን አዘውትረው የሚጫወቱ ሰዎች በገሐዱ ዓለም የሚዘገንን ነገር ቢያዩ ምንም አይመስላቸውም” በማለት ተናግረዋል። ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት እንዲህ ላሉት ጨዋታዎች ራስን ማጋለጥ “የጥላቻ ስሜት፣ ንዴት፣ የልብ ምትና የአተነፋፈስ ፍጥነት እንዲጨምር ብሎም ሰዎች ዕብሪተኛ እንዲሆኑ ያደርጋል።” ተመራማሪዎቹ የጥናቱ ተካፋዮች የዓመጽ ድርጊት ያለባቸውንም ሆነ የሌለባቸውን የቪዲዮ ጨዋታዎች ሲጫወቱ ከቆዩ በኋላ ወዲያውኑ በፊልም የተቀረጹ እውነተኛ የዓመጽ ድርጊቶችን እንዲመለከቱ በማድረግ የልብ ምታቸውንና በስሜታቸው ላይ የሚከሰተውን ለውጥ ተከታትለው ነበር። የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው “የዓመጽ ድርጊቶችን የሚያሳዩ የቪዲዮ ጨዋታዎችን የሚጫወቱ ሰዎች ዓመጹን ሙሉ በሙሉ ‘ስለሚለምዱት’ የኋላ ኋላ በአካላቸው ላይ ምንም ዓይነት የመረበሽ ስሜት አያስከትልባቸውም።”