በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክሪስማስ ደሴትን የጎበኘንበት ምክንያት

ክሪስማስ ደሴትን የጎበኘንበት ምክንያት

ክሪስማስ ደሴትን የጎበኘንበት ምክንያት

ፊጂ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ከሚገኙት 33 የኪሪባቲ * ደሴቶች መካከል ትልቋ የኪሪቲማቲ ወይም የክሪስማስ ደሴት ናት። ይህች ደሴት 388 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አላት። ይህም ከቀሪዎቹ 32 የኪሪባቲ ደሴቶች አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ጋር እኩል ነው። በኪሪባቲ ደሴቶች ላይ 92,000 ሰዎች የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 5,000 የሚያህሉት በክሪስማስ ደሴት ላይ የሚኖሩ ናቸው።

ከአንዱ በስተቀር ሁሉም የኪሪባቲ ደሴቶች በኮራል ክምችት ሳቢያ የተፈጠሩ ናቸው። የክሪስማስ ደሴት ከቆዳ ስፋቱ አንጻር ሲታይ በኪሪባቲ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ከሚገኙ የኮራል ደሴቶች ትልቋ ናት!

ከዚህም በተጨማሪ ክሪስማስ ደሴት በዓለም ላይ አዲስ ቀን የሚጠባባት የመጀመሪያ ቦታ በመሆኗ ትታወቃለች። በዚህም ምክንያት አዲስ ቀንና አዲስ ዓመት የሚጀምረውም ሆነ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት መታሰቢያ * የመሳሰሉ ዓመታዊ በዓላት መጀመሪያ የሚከበሩት በዚህች ደሴት ላይ ነው።

ከዚህም በላይ፣ ይህች ደሴት በሐሩር ክልል ለሚኖሩ የባሕር ላይ ወፎች ምቹ የመራቢያ ስፍራ ነች። በቅርብ ጊዜም 25 ሚሊዮን ለሚያክሉ ሱቲ ተርን የሚባሉ ጥቁርና ነጭ ወፎች መኖሪያ መሆኗ ታውቋል።

ወፎች ብቻ ይኖሩበት የነበረ ምድር

እንግሊዛዊው አሳሽ ካፒቴን ጄምስ ኩክ በ1777 በገና ዋዜማ እዚህች ደሴት ላይ በደረሰበት ወቅት ሰው የሚባል ነገር አልነበረም። የወፎቹ ቁጥር ግን እጅግ በርካታ ነበር። ኩክ ደሴቲቱን ክሪስማስ * ብሎ ሰየማት። ለበርካታ ዓመታት ደሴቲቱ ከወፎች በስተቀር ሰው አይኖርባትም ነበር።

አንዴ ለጉብኝት እዚያ በሄድንበት ወቅት የዱር አራዊት ጥበቃ ክፍሉ ኃላፊ አካባቢውን በደንብ አስጎበኘን። ይህ ግለሰብ ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየመራን ስንሄድ በጣም የሚያማምሩት ነጫጭ ተርኖች ክንፋቸውን እያማቱ ሲበሩ ሰላም ሊሉን የመጡ ይመስሉ ነበር። ለጨዋታ በሚመስል መንገድ አጠገባችን እያንዣበቡ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችንን ይከታተላሉ።

ከባሕሩ ዳርቻ ባሻገር በሚገኘው መሬት ላይ ሱቲ ተርኖች እጅብ ብለው ይታያሉ። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት እነዚህ ወፎች ወደ ክሪስማስ ደሴት የሚመጡት ለመራባት ነው። ደሴቲቱ ላይ ከደረሱ በኋላ መራቢያ ቦታቸው ላይ አርፈው ጎጆ ከመሥራታቸው በፊት ለሳምንታት፣ ቀን ከሌት እየተንጫጩ ከወዲያ ወዲህ በመብረር ሁሉም ወፎች እስኪሰባሰቡ ድረስ ይጠብቃሉ።

ጫጩቶቻቸው ከውቅያኖሱ በላይ መብረር የሚጀምሩት ሦስት ወር ገደማ ሲሆናቸው ነው። የመራቢያ ጊዜያቸው እስኪደርስ ድረስ ከአምስት እስከ ሰባት ለሚያህሉ ዓመታት ወደ የብስ አይመለሱም። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በአየር ላይ ነው። ላባዎቻቸው በቂ ቅባት ስለሌላቸው በውኃ ላይ ለረጅም ጊዜ ተንሳፍፈው መቆየት አይችሉም።

ጉብኝታችንን ስንቀጥል ብላክ ኖዲ የሚባሉት የተርን ዝርያዎች ጎጇቸው ውስጥ ጫጩቶቻቸውንና እንቁላሎቻቸውን ታቅፈው ተመለከትን። እነዚህ የባሕር ላይ ወፎች ለጫጩቶቻቸው ጎጆ ሲሠሩ ነጫጮቹ ተርኖች ግን እንዲህ አያደርጉም። ነጮቹ ተርኖች እንቁላሎቻቸውን የሚጥሉት በዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ነው። የሚገርመው ጫጩቶቻቸው ጠንካራ እግርና ጥፍር ኖሯቸው ስለሚፈለፈሉ ወዲያውኑ ቅርንጫፉን ቆንጥጠው መያዝ ይችላሉ። እነዚህ ጫጩቶች ገና እንደተፈለፈሉ ቅርንጫፎቹን ሙጭጭ አድርገው መያዛቸውን ስንመለከት በጣም ተደነቅን። ወተት የመሰለ ላባና ጥቁር ምንቃር ያላቸው ወላጆቻቸውም ቢሆኑ በጣም የሚያማምሩ ናቸው።

ከዚያም አለፍ እንዳልን ሺርዎተር የተባለች የወፍ ዝርያ ጥላ ሥር ሆና እንቁላሎቿን ታቅፋ በጥርጣሬ ዓይን ትመለከተን ነበር። ሽብልቅ የሚመስል ጅራት ያላቸው ሺርዎተሮች በዓለም ላይ በብዛት የሚገኙት በክሪስማስ ደሴት ነው። ፖሊኔዥያን ስቶርም ፔትረል እና ፊንክስ ፔትረል የተባሉት የወፍ ዝርያዎች ከሚራቡባቸው ቦታዎች መካከል ክሪስማስ ደሴት ትገኝበታለች። እዚህች ደሴት ላይ ከሚራቡት በርካታ የወፍ ዝርያዎች መካከል ባለ ቀይ ጅራቷ የሐሩር ክልል ወፍ፣ ጭምብል ያጠለቀች የምትመስለው ቡቢ፣ ቡናማዋ ቡቢ፣ ባለ ቀይ እግሯ ቡቢ፣ ቡናማዋ ኖዲ እና ፍሪጌት ይገኙበታል።

ፍሪጌት የተባሉት ወፎች እንደ ልብ የማንዣበብ ችሎታ ያላቸው ሲሆን ይህም ማራኪ የሆነ የመገለባበጥ ትርዒት እንዲያሳዩ፣ በአየር ላይ እንዳሉ ከሌሎች ወፎች ዓሣ እንዲነጥቁና ዓሣ አጥማጆች የሚጥሉትን ቅንጥብጣቢ ጨልፈው እንዲወስዱ ያስችላቸዋል። እነዚህ ወፎች በውኃ ላይ ማረፍ ስለማይችሉ ተፈጥሮ ያደለቻቸው ይህ ችሎታ በጣም ያስፈልጋቸዋል። እንደ ሱቲ ተርኖች ሁሉ እነሱም ላባቸው ውኃ ላይ ለመንሳፈፍ የሚያስችል በቂ ቅባት የለውም፤ ከዚህም በተጨማሪ ከጫፍ ጫፍ ሲለካ ወደ ሁለት ሜትር የሚጠጋው ክንፋቸው በአንድ ጊዜ ተነስተው መብረርን አዳጋች ያደርግባቸዋል።

እዚያ እንደደረስን አካባቢ ያየናት ትንሿ ቡናማ ወፍ የፓስፊክ ወርቃማ ፕሎቨር ነች። ከቦታ ቦታ እንደሚፈልሱት ሌሎች በርካታ ወፎች ሁሉ የዚህች ወፍ ዝርያዎችም ክሪስማስ ደሴትን የሚጠቀሙበት ኃይላቸውን ለማደስ የሚያስችላቸውን ምግብ ለመቃረምና ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ ነው። ወፎቹ እዚህ ቦታ የሚያርፉት ከአርክቲክ ክልል በላይ ከሚገኘው የመራቢያ ቦታቸው ተነስተው ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ ነው። እነዚህ የረጅም ርቀት ተጓዦች ያላቸው ጥሩ የበረራ ችሎታ ከሆኖሉሉ፣ ሃዋይ በስተ ደቡብ 2,100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደዚህ ሥፍራ እንዲደርሱ ይረዳቸዋል።

የጉብኝታችን ዋነኛ ዓላማ

አዘውትረን ወደ ክሪስማስ ደሴት የምንሄደው ወፎችን ለማየት ሳይሆን በዚያ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብረን ለማገልገልና ለመሰብሰብ ነው። አካባቢው ገለልተኛ ክልል መሆኑ በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞች አንዳንድ ሁኔታዎች ተፈታታኝ እንዲሆኑባቸው አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ከዓመታት በፊት አንድ የይሖዋ ምሥክር ድንገት በሞተበት ወቅት ባለቤቱ የቀብር ንግግሩን ራሷ ለመስጠት ተገድዳ ነበር፤ ምክንያቱም በአካባቢው በዚህ ረገድ ሊረዳት የሚችል ሰው አልነበረም። ይህች እህት በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት በርካታ ሰዎች ሙታን ያላቸውን ተስፋ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንዲያውቁ ፈልጋ ነበር።—ዮሐንስ 11:25፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

በክሪስማስ ደሴት ላይ በጥሩ ሁኔታ ከተተረጎሙ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተጨማሪ በሃገሬው ቋንቋ የተዘጋጁ ጥቂት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በተጨማሪ በጊልበርት ቋንቋ ባለ ቀለም መጠበቂያ ግንብ በየወሩ ያትማሉ። በዓለም ላይ ይህን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር ከ100,000 በታች ሆኖ ሳለ በዚህ ቋንቋ ጽሑፎች መውጣታቸው ብዙዎችን አስደንቋቸዋል። እንዲህ ያሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በዚያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎቻቸውን አዘውትረው እንዲያደርጉና ኢየሱስ የሰጠውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበክ ተልእኮ እንዲወጡ አስችሏቸዋል።—ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25

ጎብኚዎች የሚያጋጥማቸው አንዱ ችግር የትራንስፖርት እጥረት ነው። ይሁን እንጂ፣ በክሪስማስ ደሴት ላይ አንድ ሰው በቴነሲ አድርጎ ከለንደን ወደ ፖላንድ ለመጓዝ የሚፈጅበት ሦስት ሰዓት ብቻ ነው! ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ባናና፣ ለንደን፣ ፓሪስ፣ ፖላንድ፣ ቴነሲና ታፓኬ በዚያ የሚገኙ የመንደሮች ስሞች ናቸው። እነዚህ መንደሮች ስማቸውን ያገኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ደሴቲቱን ከጎበኙት አንዳንድ ሰዎች ጋር በተያያዘ ነው።

አንድ ጊዜ ለጉብኝት እዚያ በሄድንበት ወቅት አንድ ጥሩ ዶክተር ወደ ፖላንድ አብረነው እንድንሄድ ጋበዘን። ይህም በዚያ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ የመስበክ አጋጣሚ ከፍቶልናል። እዚያ የቆየነው ለሁለት ሰዓታት ብቻ ቢሆንም ሁሉንም ቤቶች አዳርሰናል ለማለት ይቻላል። ያነጋገርናቸው ሰዎች ሁሉ የያዝነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በአድናቆት ያዳመጡን ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ጽሑፎችን ወስደዋል። በተለይ ጽሑፎቹ በራሳቸው ቋንቋ የተዘጋጁ መሆናቸው በጣም አስገርሟቸዋል።

በክሪስማስ ደሴት ላይ የሚኖሩት እነዚህ ሰዎች በጣም የሚወደዱ ናቸው። እዚያ ያየናቸው ወፎችም ከልባችን የሚጠፉ አይደሉም። ከረጅም ጊዜ በፊት ካፒቴን ኩክ ደሴቲቱ “ለወፎች” ብቻ የምትሆን መኖሪያ እንደሆነች ተሰምቶት ነበር። ዛሬ ግን በዚያ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። እንደ ወፎቹ ሁሉ እነሱም መኖሪያቸውን በዚያ አድርገዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ኪሪባቲ ቀደም ሲል ጊልበርት ተብላ ትጠራ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የኪሪባቲ ደሴት 16ቱን የጊልበርት ደሴቶች ብቻ ሳይሆን በፊንክስና በላይን ሥር የሚገኙ ደሴቶችን እንዲሁም የባናባን ደሴት አጠቃልላ ይዛለች።

^ አን.5 የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት የሞቱን መታሰቢያ በዓመት አንድ ጊዜ ያከብራሉ።—ሉቃስ 22:19

^ አን.8 ክሪስማስ የምትባል ሌላ ደሴት በሕንድ ውቅያኖስ ላይም ትገኛለች።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ካርታዎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ክሪስማስ ደሴት

ባናና

ታፓኬ

ለንደን

ፓሪስ

ፖላንድ

በዓለም ላይ አዲስ ቀን የሚጠባበት መስመር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍሪጌት ወፎች

[ምንጭ]

GaryKramer.net

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነጭ ተርን

[ምንጭ]

©Doug Perrine/ SeaPics.com

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቡናማ ቡቢዎች

[ምንጭ]

Valerie & Ron Taylor/ ardea.com

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአካባቢው የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስናገለግል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

GaryKramer.net