በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የልጃችሁን ስሜት ተረዱለት

የልጃችሁን ስሜት ተረዱለት

6

የልጃችሁን ስሜት ተረዱለት

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸው ሰዎች ማለትም ወላጆቻቸው፣ ስሜታቸውን እንዲረዱላቸው ይፈልጋሉ፤ ወላጆችም እንዲህ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ስሜታቸውን አውጥተው ሲናገሩ በተደጋጋሚ ጊዜያት የልጆቹን ሐሳብ የሚቃወሙ ከሆነ ልጆቹ ነፃ ሆነው ወላጆቻቸውን ለማነጋገር አይነሳሱም፤ ከዚህም በላይ ልጆቹ የራሳቸው ስሜትና አስተሳሰብ ሊኖራቸው እንደሚችል እንኳ መጠራጠር ሊጀምሩ ይችላሉ።

ተፈታታኝ የሚሆነው ለምንድን ነው? ልጆች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አጋንነው መግለጽ ይቀናቸዋል። በእርግጥ፣ ልጆች የሚናገሩት አንዳንዱ ነገር ወላጆች ሲሰሙት የሚያሸብር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የተበሳጨ ልጅ “መኖር አስጠላኝ” ብሎ ሊናገር ይችላል። * በዚህ ጊዜ ወላጅ ወዲያው የሚሰጠው መልስ “ምን ሆንኩ ብለህ ነው ደግሞ መኖር የሚያስጠላህ?” የሚል ሊሆን ይችላል። ወላጆች የልጁን አሉታዊ ስሜት እንደተረዱ መግለጻቸው ይህ ዓይነቱ ስሜት ተቀባይነት እንዳለው እንዲሰማው ያደርጋል ብለው ይሰጉ ይሆናል።

መፍትሔው ምንድን ነው? “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቊጣም የዘገየ ይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርጉ። (ያዕቆብ 1:19) ይሖዋ አምላክ ብዙዎቹ ታማኝ አገልጋዮቹ ያደረባቸው አሉታዊ ስሜት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገብ በማድረግ ስሜታቸውን እንደሚረዳላቸው አሳይቷል። (ዘፍጥረት 27:46፤ መዝሙር 73:12, 13) ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ በጣም ከባድ ፈተና በደረሰበት ጊዜ ሞቱን እንደሚመኝ ተናግሯል።—ኢዮብ 14:13

አንዳንዶቹ የኢዮብ አመለካከቶችና ስሜቶቹ መታረም ያስፈልጋቸው እንደነበረ በግልጽ ማየት ይቻላል። ሆኖም ይሖዋ፣ የኢዮብን ስሜቶች ከማስተባበል ወይም እንዳይናገር ከመከልከል ይልቅ ልቡን እንዲያፈስ በትዕግሥት በመፍቀድ አክብሮታል። ይሖዋ ኢዮብን በደግነት ያረመው ኢዮብ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ነበር። አንድ ክርስቲያን አባት ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “ይሖዋ በጸሎት አማካኝነት የልቤን አውጥቼ እንድነግረው የሚፈቅድልኝ በመሆኑ እኔም ልጆቼ አዎንታዊም ሆኑ አሉታዊ ስሜቶቻቸውን አውጥተው እንዲነግሩኝ መፍቀዴ ተገቢ እንደሆነ ይሰማኛል።”

ልጃችሁ፣ “በጭራሽ እንደዚህ ሊሰማህ አይችልም” ወይም “እንደዚህ ብለህማ ልታስብ አትችልም” እንድትሉት የሚገፋፋ ነገር ሲናገር ኢየሱስ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት የሰጠውን በሰፊው የታወቀ መመሪያ አስታውሱ። (ሉቃስ 6:31) ለምሳሌ ያህል፣ በሥራ ቦታችሁ ደግነት የጎደለው ነገር ተፈጽሞባችኋል ወይም ምናልባት በራሳችሁ ድክመት የተነሳ ተበሳጭታችኋል እንበል። ለቅርብ ጓደኛችሁ፣ በሥራ ቦታችሁ ያለውን ሁኔታ መቋቋም እንዳልቻላችሁ በመግለጽ ብስጭታችሁን ገለጻችሁለት። ጓደኛችሁ ምን እንዲላችሁ ትፈልጋላችሁ? እንደዚያ ሊሰማችሁ እንደማይችልና ችግሩ የመጣው በራሳችሁ ጥፋት እንደሆነ እንዲነግራችሁ ትፈልጋላችሁ? ወይስ “መቼም ሁኔታው በጣም ከብዶህ መሆን አለበት። ውሎህ አስቸጋሪ ነበር ማለት ነው” ቢላችሁ ትመርጣላችሁ?

ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች፣ ምክር የሚሰጣቸው ሰው ስሜታቸውንና ያጋጠማቸውን ችግር በደንብ እንደሚረዳላቸው ከተሰማቸው ምክሩን መቀበል ቀላል ይሆንላቸዋል። የአምላክ ቃል “የጠቢብ ሰው ልብ አንደበቱን ይመራል፤ ከንፈሮቹም ዕውቀትን ያዳብራሉ” ይላል።—ምሳሌ 16:23

ልጆቻችሁ የምትሰጧቸውን ማንኛውንም ምክር በቁም ነገር እንዲመለከቱት ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ልጆች ሕይወታቸውን ስለ ማጥፋት የሚሰነዝሩትን ማንኛውንም ሐሳብ አቅልላችሁ አትመልከቱት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል።ምሳሌ 18:13