በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የስፔን የጦር መርከቦች ጉዞ አሳዛኝ መጨረሻ

የስፔን የጦር መርከቦች ጉዞ አሳዛኝ መጨረሻ

የስፔን የጦር መርከቦች ጉዞ አሳዛኝ መጨረሻ

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የሁለት አገራት የጦር መርከቦች በእንግሊዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ውጊያ አካሂደው ነበር። ይህ ጦርነት በፕሮቴስታንቶችና በካቶሊኮች መካከል የተካሄደ ነው። ይህም በ16ኛው መቶ ዘመን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በሆነችው የእንግሊዟ ቀዳማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ሠራዊትና የሮማ ካቶሊክ ተከታይ በሆነው ስፔናዊ ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ ሠራዊት መካከል የተካሄደው ጦርነት አካል ነው። ዘ ዲፊት ኦቭ ዘ ስፓኒሽ አርማዳ የተባለው መጽሐፍ “በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች በእንግሊዝና በስፔን የጦር መርከቦች መካከል የተካሄደውን ውጊያ በብርሃንና በጨለማ ኃይሎች መካከል የተደረገ የሞት ሽረት ፍልሚያ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል” ብሏል።

በዚያን ወቅት በእንግሊዝ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የስፔን የጦር መርከቦችን በሚመለከት ‘ይህንን ያህል ብዛት ያለው የጦር መርከብ አይተን አናውቅም’ በማለት ተናግረዋል። ይሁንና በጦርነቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ጉዞው ከባድ ‘ስህተት’ እንደነበረ ያሳያል። ለመሆኑ የዘመቻው ዓላማ ምን ነበር? ስኬታማ ሳይሆን የቀረውስ ለምንድን ነው?

ወረራው የተቃጣው ለምን ነበር?

እንግሊዛውያን የባሕር ላይ ዘራፊዎች የስፔንን መርከቦች ለዓመታት ይዘርፉ የነበረ ከመሆኑም በላይ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልዛቤት በስፔን አገዛዝ ላይ ላመጹት ደቾች ከፍተኛ እገዛ ታደርግ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረው ዳግማዊ ፊሊፕ እንግሊዛውያን ካቶሊኮች በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ እንዲያመክኑ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። በወቅቱ ካቶሊኮች ፕሮቴስታንቶችን እንደ መናፍቅ ይመለከቷቸው ስለነበር የጦር መርከቦቹ 180 ቀሳውስትንና ሃይማኖታዊ አማካሪዎችን ይዘው ነበር። በመርከቦቹ ላይ የሚገኙት ሠራተኞች አንድ ላይ ሰብሰብ በሚሉበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ወደ ቀሳውስቱ እየሄደ ኃጢአቱን በመናዘዝ ይቆርብ ነበር።

ፔድሮ ዴ ሪባቴኔራ የተባለ ታዋቂ ስፔናዊ ቄስ “ለእሱም ሆነ ቅድስት ለሆነችው ሃይማኖት የቆምንለት ጌታ አምላካችን ከፊት ሆኖ ይመራናል፤ እንዲህ የመሰለ አዝማች ይዘን ምንም ነገር አንፈራም” በማለት የተናገረው ነገር በወቅቱ በስፔን የነበረውን ሃይማኖታዊ ሁኔታና የንጉሡን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። እንግሊዛውያን ደግሞ በስፔናውያን ላይ የሚቀዳጁት ወሳኝ ድል የፕሮቴስታንቶችን እምነት በመላው አውሮፓ ለማስፋፋት መንገድ እንደሚጠርግላቸው ተሰምቷቸው ነበር።

የስፔን ንጉሥ የወረራ እቅድ በግልጽ የተቀመጠ ነበር። የጦር መርከቦቹ እስከ እንግሊዝ የባሕር ወሽመጥ ድረስ ከተጓዙ በኋላ ፍላንደርስ * ላይ ከሚጠብቃቸው የፓርማው መስፍንና 30,000 ከሚያክሉ ልምድ ያካበቱ ወታደሮቹ ጋር እንዲገናኙ ትእዛዝ አስተላለፈ። እነዚህ ሁለት የጦር ኃይሎች አንድ ላይ የባሕሩን ወሽመጥ ያቋርጡና ኤሴክስ የባሕር ዳርቻ ይደርሳሉ። ከዚያም በእግራቸው ወደ ለንደን በማቅናት ከተማዋን በቁጥጥር ሥር ያውላሉ። ፈሊፕ፣ እንግሊዛውያን ካቶሊኮች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነችው ንግሥታቸውን በመክዳት ከእሱ ጦር ሠራዊቶች ጋር ይቀላቀላሉ ብሎ አስቦም ነበር።

ይሁን እንጂ ፊሊፕ ያወጣው እቅድ ከባድ ችግር ነበረው። አምላክ እንደሚረዳው የተማመነ ቢሆንም ሁለት መሰናክሎች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ አላስተዋለም ነበር። እነዚህም የእንግሊዝ ባሕር ኃይል ጥንካሬና ከፓርማው መስፍን ጋር የሚገናኙበት ቦታ ላይ መርከቦቹን ለማቆም የሚያስችል ምቹ ወደብ አለመኖሩ ናቸው።

ብዛት ቢኖራቸውም በሚገባ ያልተቀናጁ የጦር መርከቦች

ፊሊፕ የሜቲና ሲዶንያን መስፍን የጦር መርከቦቹ አዛዥ አድርጎ ሾመው። መስፍኑ በባሕር ላይ ስለሚደረግ ውጊያ የነበረው እውቀት አነስተኛ ቢሆንም ልምድ ያላቸውን ካፒቴኖች በአጭር ጊዜ ማደራጀት የቻለ ጎበዝ ሰው ነበር። ከእነዚህ ካፒቴኖች ጋር አንድ ላይ ሆነው የጦር ኃይል የመሠረቱ ሲሆን ለዚህ ትልቅ የባሕር ኃይል ደግሞ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ምግብና ውኃ ለማቅረብ ጥረት አደረጉ። ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጣውን ጦር አንድ ለማድረግ መረጃ የሚለዋወጡባቸውን ዘዴዎች እንዲሁም አሰላለፋቸውን በጥንቃቄ ነደፉ።

በመጨረሻም ወደ 20,000 የሚጠጉ ወታደሮችንና 8,000 መርከበኞችን የጫኑት 130 መርከቦች ግንቦት 29, 1588 ከሊዝበን ወደብ ተነሱ። ሆኖም በጉዟቸው ላይ ያጋጠማቸው ኃይለኛ ማዕበል ጉዳት ስላደረሰባቸው መርከባቸውን ለመጠገንና ተጨማሪ ስንቅ ለመያዝ ከስፔን በስተ ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ላ ኮሩኛ የተባለች ከተማ መቆም ግድ ሆነባቸው። የስንቁ እጥረትና የወታደሮቹ መታመም በጣም ያሰጋው የሜቲና ሲዶንያው መስፍን ሁኔታውን ግልጽልጽ አድርጎ ለንጉሡ ጻፈለት። ነገር ግን ንጉሡ በእቅዱ መሠረት ወደፊት እንዲገፉ አዘዛቸው። በሚገባ መቀናጀት ያልቻለው የባሕር ኃይል ጉዞውን በመቀጠል ከሊዝበን ከተነሳ ከሁለት ወራት በኋላ የእንግሊዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ደረሰ።

በእንግሊዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ የተደረገው ጦርነት

የስፔን ባሕር ኃይል ከእንግሊዝ በስተ ደቡብ ምዕራብ በምትገኘው በፕላይማውዝ የባሕር ጠረፍ ሲደርስ የእንግሊዙ ባሕር ኃይል የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ እየተጠባበቀ ነበር። ሁለቱም ወገኖች የነበራቸው የመርከብ ቁጥር ተመጣጣኝ ቢሆንም አሠራራቸው ግን የተለያየ ነበር። የአጭር ርቀት የጦር መሣሪያዎች የተጠመዱባቸው የስፔን መርከቦች በባሕሩ ላይ የቆሙት ራቅ ብለው ነበር። እነዚህ መርከቦች ከፊትና ከኋላ የተገጠመላቸው የጦር መሣሪያ ተንሳፋፊ ምሽግ አስመስሏቸዋል። ስፔኖች ከአንዱ መርከብ ወደ ሌላኛው እየተዘዋወሩ በማጥቃት በጠላቶቻቸው ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት የሚያስችል የጦር ስልትም ነድፈው ነበር። የእንግሊዝ መርከቦች አጭርና ፈጣኖች ሲሆኑ ረጅም ርቀት የሚወነጨፉ የጦር መሣሪያዎች ተገጥመውላቸዋል። ካፒቴኖቻቸው ወደ ጠላት ጦር በጣም ሳይጠጉ ከርቀት ሆነው የስፔን መርከቦችን ለማጥፋት የሚያስችላቸውን እቅድ ተከትለዋል።

የስፔን ባሕር ኃይል አዛዥ የእንግሊዝ መርከቦች የሚያደርጉትን ከፍተኛ እንቅስቃሴና እሳት የሚተፉ መሣሪያዎቻቸውን ለመመከት የግማሽ ጨረቃ ቅርጽ የመስለ አሰላለፍ በመከተል ለመከላከል አቀደ። የረጅም ርቀት መሣሪያዎች የተገጠሙላቸው ጠንካራ መርከቦች ጫፍና ጫፍ ላይ ተሰለፉ። የጠላት ጦር ከየትኛውም አቅጣጫ ይምጣ የጦር መርከቦቹ ፊታቸውን ወደዚያ አዙረው ልክ ጎሽ አንበሳን በቀንዶቹ ለማጥቃት እንደሚጋፈጥ ፊት ለፊት ይጋፈጡታል።

እነዚህ ሁለት የጦር ኃይሎች በእንግሊዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ሁለት ጊዜ ያህል ቀለል ያለ ውጊያ አካሄዱ። በእነዚህ ውጊያዎች ስፔናውያን የተጠቀሙበት የመከላከያ ስልት ውጤታማ መሆኑ የታየ ሲሆን የእንግሊዝ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ መሣሪያዎች አንድም የስፔን መርከብ ማስመጥ ሳይችሉ ቀሩ። በዚህም ምክንያት የእንግሊዝ ካፒቴኖች ይህንን አሰላለፍ ለመስበርና ይበልጥ ቀረብ ብለው ለመዋጋት አሰቡ። ነሐሴ 7 ቀን ያሰቡት ተሳካላቸው።

የሜቲና ሲዶንያው መስፍን በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት የጦር መርከቦቹን ይዞ ከፓርማው መስፍንና ከወታደሮቹ ጋር ወደተቀጣጠሩበት ቦታ አመራ። ከዚያም ይህ መስፍን ለፓርማው መስፍን የላከው መልእክት መልስ እስኪመጣ ድረስ መርከቦቹ በፈረንሳይ የባሕር ጠረፍ ላይ በምትገኘው በካሌ መልሕቃቸውን እንዲጥሉ አዘዘ። እንግሊዛውያኑ የስፔን መርከቦች መልሕቃቸውን እንደጣሉና ራሳቸውን ለጥቃት እንዳመቻቹ ሲሰማቸው ተቀጣጣይ መሣሪያዎችን የጫኑ ስምንት መርከቦችን ላኩ። በዚህ ወቅት አብዛኞቹ የስፔን መርከብ ካፒቴኖች ከአደጋው ለማምለጥ መሸሽ ጀመሩ። ከዚህም በተጨማሪ ኃይለኛው ነፋስና የባሕሩ ሞገድ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ይገፋቸው ነበር።

በማግስቱ ማለዳ ላይ ዋነኛው ጦርነት ተካሄደ። የእንግሊዝ መርከቦች ወደ ስፔኖች ጠጋ ብለው ተኩስ በመክፈት ቢያንስ ሦስት መርከቦችን ከማውደማቸውም ሌላ በበርካታዎቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ። ስፔኖች በቂ መሣሪያ ስላልነበራቸው የሚሰነዘርባቸውን ኃይለኛ ጥቃት ዝም ብሎ ከመቀበል ውጪ ምንም ማድረግ አልቻሉም።

በወቅቱ ተነስቶ የነበረው ኃይለኛ ማዕበል እንግሊዞች የሚሰነዝሩትን ጥቃት እንዲያቋርጡ አስገደዳቸው። በማግስቱ ጠዋት የስፔን መርከቦች የቀራቸውን መሣሪያ ይዘው ግማሽ ጨረቃ የመሰለ ቅርጽ በመሥራት ከጠላቶቻቸው ጋር ውጊያ ለመግጠም ተዘጋጁ። ይሁንና እንግሊዛውያን ተኩስ ከመክፈታቸው በፊት ኃይለኛው ነፋስና ሞገዱ የስፔን መርከቦችን እየገፋ ወሰዳቸው። ነፋሱ ጋብ ባይል ኖሮ መርከቦቹን በኔዘርላንድ የባሕር ጠረፍ ወደሚገኘው ዚላንድ የተባለ አሸዋማ ቦታ ወስዶ ይቀረቅራቸው ነበር።

ስፔናውያን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ እያሉ ነፋሱ አቅጣጫውን ቀይሮ መርከቦቹን ወደ ሰሜን ገፋቸው። ይሁንና ወደ ካሌ ለመመለስ ሲያስቡ መንገዱ በእንግሊዞች ተዘግቶ ነበር። ነፋሱም ቢሆን ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉትን የስፔን መርከቦች ወደ ሰሜን አቅጣጫ መግፋቱን አላቆመም። የሜቲና ሲዶንያው መስፍን ምንም አማራጭ ስላልነበረው በተቻለ መጠን በርካታ መርከቦችንና ሰዎችን ለማዳን ጦርነቱን አቋርጦ ለመመለስ ወሰነ። ወደ ስፔን የተመለሰውም በስኮትላንድና በአይርላንድ ዞሮ ነበር።

ማዕበልና የመርከብ አደጋ

ጉዳት የደረሰባቸው የስፔን መርከቦች ወደ አገራቸው ያደረጉት ጉዞ በጣም አስቸጋሪ ነበር። የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ከመሆኑም ሌላ የውኃ መያዣ በርሜሎቹ ያፈስሱ ስለነበር በቂ ውኃ አልነበራቸውም። እንግሊዛውያን በሰነዘሩት ጥቃት አብዛኞቹ መርከቦች የተጎዱ ሲሆን በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ጥቂቶቹ ነበሩ። በሰሜን ምዕራብ አየርላንድ የባሕር ጠረፍ ሲደርሱ ለሁለት ሳምንታት የቆየ ከባድ ማዕበል አጋጠማቸው። በዚህም ምክንያት አንዳንድ መርከቦች የደረሱበት ጠፋ! ሌሎች ደግሞ ከአየርላንድ የባሕር ጠረፍ ጋር ተላተሙ።

ከዘመቻው ከተመለሱት መርከቦች መካከል የመጀመሪያው መስከረም 23 በሰሜናዊ ስፔን ወደምትገኘው ሳንታንደር የተባለች የወደብ ከተማ ደረሰ። ወደ እንግሊዝ ከዘመቱት መካከል ወደ ሊዝበን መመለስ የቻሉት 60 መርከቦችና ግማሽ የሚያህሉት ሰዎች ብቻ ነበሩ። በሺህ የሚቆጠሩትን ባሕር በላቸው። ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ በጦርነቱ በደረሰባቸው ጉዳት ወይም ወደ አገራቸው ሲመለሱ ባጋጠማቸው በሽታ ምክንያት ሞተዋል። በሕይወት ተርፈው ስፔን የባሕር ዳርቻ የደረሱትም እንኳ መከራቸው አላበቃም ነበር።

ዘ ዲፊት ኦቭ ዘ ስፓኒሽ አርማዳ የተባለው መጽሐፍ ብዙዎቹ ስፔን ወደብ የደረሱ ቢሆንም “የሚላስ የሚቀመስ ስላልነበራቸው በረሃብ አልቀዋል” ብሏል። ይኸው መጽሐፍ ላሬዶ በተባለ የስፔን ወደብ አንዲት መርከብ “ሸራውን የሚሰበስብና መልሕቅ የሚጥል በቂ ሰው ስላልነበራት” ለግጭት መዳረጓን ተናግሯል።

የስፔን መርከቦች ሽንፈት ምን ትርጉም አለው?

የሃይማኖት ጦርነቶች ከዚያ በኋላም ቀጥለው የነበረ ቢሆንም የስፔን ጦር መርከቦች ሽንፈት በሰሜን አውሮፓ ለሚኖሩ ፕሮቴስታንቶች የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። ፕሮቴስታንቶቹ ድል መቀዳጀታቸውን መለኮታዊ ድጋፍ ለማግኘታቸው እንደ ማስረጃ አድርገው ይጠቅሱት ነበር። ድሉን ለማስታወስ በተዘጋጀው ሜዳልያ ላይ “ይሖዋ ነፋስ አመጣባቸው እነሱም ተበተኑ 1588” የሚል ትርጉም ያለው ጽሑፍ ተቀርጾ ነበር።

ሞደርን ዩሮፕ ቱ 1870 የተባለው መጽሐፍ “ታላቋ ብሪታንያ በ1763 በንግድም ሆነ በቅኝ ግዛት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሌላት ታላቅ አገር ሆና ብቅ አለች” በማለት እንደተናገረው ብሪታንያ ከጊዜ በኋላ የዓለም ኃያል ለመሆን በቅታለች። ኔቪ ኤንድ ኢምፓየር የተባለው መጽሐፍ እንዳለው በእርግጥም “የብሪታንያ መንግሥት በ1763 ሮም እንደገና ያንሰራራችና ግዛቷን ያስፋፋች ያህል ዓለምን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ ነበር።” ከጊዜ በኋላ ታላቋ ብሪታንያ ከቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ኅብረት በመፍጠር አንግሎ አሜሪካ የተባለውን የዓለም ኃያል መንግሥት መሠረተች።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የዓለም ኃያል መንግሥታትን አነሳስና አወዳደቅ የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አላቸው። ይህ የሆነው ቅዱሳን መጻሕፍት በዓለም ላይ በተከታታይ ስለተነሱ የዓለም ኃያል መንግሥታት ይኸውም ስለ ግብጽ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ፣ ሮምና በመጨረሻም ስለ አንግሎ አሜሪካ በርካታ መረጃዎችን ስለያዙ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹን አነሳስና አወዳደቅ ከረጅም ጊዜ በፊት ተንብዮአል።—ዳንኤል 8:3-8, 20-22፤ ራእይ 17:1-6, 9-11

በ1588 የበጋ ወራት የስፔን የጦር መርከቦች እንግሊዝን ለመውረር ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱ ከፍተኛ ትርጉም አለው። የስፔን የጦር መርከቦች ድል ከተነሱ ከ200 ዓመታት ገደማ በኋላ ታላቋ ብሪታንያ ኃያል አገር ሆና ብቅ አለች። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አፈጻጸም ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣት አገር እንድትሆን አድርጓታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ይህ ቦታ የስፓኒሽ ኔዘርላንድስ ክፍል ሲሆን በ16ኛው መቶ ዘመን በስፔን ቁጥጥር ሥር ነበር። ቦታው የሰሜን ፈረንሳይን፣ የቤልጂየምንና የሆላንድን የባሕር ጠረፎች ያጠቃልል ነበር።

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የስፔን የጦር መርከቦች ያደረጉት ጉዞ

​——​ ለዘመቻ የተጓዙበት መንገድ

–– የተመለሱበት መንገድ

X ጦርነት የተካሄደባቸው ቦታዎች

ስፔን

ሊዝበን

ላ ኮሩኛ

ሳንታንደር

ፍላንደርስ

ካሌ

ዩናይትድ ኔዘርላንድስ

ስፓኒሽ ኔዘርላንድስ

እንግሊዝ

ፕላይማውዝ

ለንደን

አየርላንድ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ፊሊፕ ዳግማዊ

[ምንጭ]

Biblioteca Nacional, Madrid

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀዳማዊት ንግሥት ኤልዛቤት

[በገጽ 24,  25ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሜቲና ሲዶንያው መስፍን የስፔን ባሕር ኃይል አዛዥ ነበር

[ምንጭ]

Cortesía de Fundación Casa de Medina Sidonia

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Museo Naval, Madrid