በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለሕክምናው ሳይንስ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክተዋል”

“ለሕክምናው ሳይንስ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክተዋል”

“ለሕክምናው ሳይንስ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክተዋል”

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

የይሖዋ ምሥክሮች ከሕክምና ጋር በተያያዘ ደም አልባ ሕክምናዎችን እንደሚመርጡ በዓለም ዙሪያ ይታወቃል። አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ይህን የይሖዋ ምሥክሮች አቋም ይተቻሉ። ይሁንና በብሔራዊ የዕጢ ሕክምና ተቋም ውስጥ ዋና የቀዶ ሕክምና ዶክተር የሆኑት አንኬል ሄሬራ በሜክሲኮ ሲቲ በሚታተመውና ሰፊ ስርጭት ባለው ሪፎርማ የተሰኘ ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ሞኞች አሊያም ጭፍን አመለካከት ያላቸው ሰዎች አይደሉም። . . . ከዚህ ይልቅ የሕክምና ባለሞያዎች ብዙ ደም እንዳይፈስ የማድረጉን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ በማድረግ ለሕክምናው ሳይንስ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።”

ዶክተር ሄሬራ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ እንዲቻል ሰመመን የሚሰጡ ባለሙያዎችንና የቀዶ ሕክምና ዶክተሮችን ያካተተ አንድ ቡድን አቋቁመው ነበር። በአኔስቲዚኦሎጂስትነት የሚያገለግሉትና የዚህ ቡድን አባል የሆኑት ዶክተር ኢስዲሮ ማርቲኔዝ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል:- “ትክክለኛው የሰመመን አሰጣጥ ሂደት ብዙ ደም እንዳይፈስ የሚረዱ ዘዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ አቋም በማክበር ልንረዳቸው እንችላለን።”

ሪፎርማ በጥቅምት 2006 እንደዘገበው በደም ምትክ የሚሰጡ ከ30 በላይ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ደም ሥሮችን መተኮስ፣ ደም እንዳይፈስ ለማገድ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎችን ኬሚካል ባለው ለየት ያለ ፋሻ መሸፈንና የደምን መጠን የሚጨምሩ መድኃኒቶችን መስጠት ይገኙበታል። *

ሜክሲኮ ሲቲ በሚገኘው ላ ራዛ የተባለ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ ዋና የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሞይሰስ ካልዴሮን በርካታ ቀዶ ሕክምናዎችን ያለ ደም አድርገዋል። ሪፎርማ በተባለው ጋዜጣ ላይ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ደም በመስጠት የሚካሄደው ሕክምና ጉዳት አያስከትልም ማለት አይደለም። ቫይረሶችን፣ ባክቴሪያ ወይም ጥገኛ ነፍሳትን ወደ ሌላው ሰው የማስተላለፍ አደጋ አለ። በተጨማሪም የኩላሊትንና የሳንባን አሠራር የሚያዛባ አለርጂ ሊያስከትል ይችላል።” ዶክተር ካልዴሮን እነዚህን አደጋዎች አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ሁሉንም ታካሚዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ አድርገን በመቁጠር ቀዶ ሕክምና እናደርግላቸዋለን። ብዙ ደም እንዳይፈስ ለማድረግ እንጥራለን፣ የፈሰሰውን ደም ለመተካትና ታካሚው ብዙ ደም እንዳይፈሰው የሚረዱ መድኃኒቶችን ለመጠቀም እንሞክራለን።”

ጋዜጣው የይሖዋ ምሥክሮች ለአቋማቸው መሠረት የሆነውን ቁልፍ ጥቅስ ማለትም የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29ን ጠቅሶ ነበር። በዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያት የሚከተለውን መመሪያ አስተላልፈዋል:- “ከእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ለእኛም መልካም መስሎ ታይቶናል፤ ይኸውም:- ለጣዖት ከተሠዋ ነገር፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከዝሙት ርኩሰት እንድትርቁ ነው።”

ሜክሲኮ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚገኘው የሆስፒታል መረጃ ዴስክ በአገሪቱ ውስጥ በደም ምትክ የሚሰጡ አማራጭ የሕክምና ዓይነቶችን አስመልክቶ ለሐኪሞች መረጃ በመስጠት የሚያገለግሉ 950 የበጎ ፈቃድ ሠራተኞችን ያቀፉ 75 የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች እንዳሉ ሪፖርት አድርጓል። በሜክሲኮ የይሖዋ ምሥክሮችን ያለ ደም ለማከም ፈቃደኛ የሆኑ ወደ 2,000 ገደማ የሚሆኑ ዶክተሮች ይገኛሉ። በዚያ አገር የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህ ሐኪሞች ለሚያደርጉላቸው ትብብር ከፍተኛ አድናቆት አላቸው፤ ይህ ደግሞ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ታካሚዎችንም በተሻለ መንገድ ለማከም አስችሏል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ንቁ! እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ስለሚገነዘብ የትኛውንም ያለ ደም የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት አያበረታታም።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶክተር አንኬል ሄሬራ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶክተር ኢስዲሮ ማርቲኔዝ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶክተር ሞይሰስ ካልዴሮን