በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልባቸው በሐዘን የተሰበረና እምነታቸው የጠፋ ሰዎች

ልባቸው በሐዘን የተሰበረና እምነታቸው የጠፋ ሰዎች

ልባቸው በሐዘን የተሰበረና እምነታቸው የጠፋ ሰዎች

“አካባቢው በሙሉ በሬሳ ተሸፍኖ ስለነበር ቤታችን የነበረበትን ቦታ እንኳ ማግኘት አልቻልንም።” ይህን የተናገረው በታኅሣሥ 2004 የሚኖርበት መንደር በሱናሚ የወደመበት አንድ የስሪላንካ ተወላጅ ነው። ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ርዕሶችን የሚያትት አንድ የጋዜጣ አዘጋጅ ይህን አደጋ በተመለከተ በጻፈው አምድ ላይ አንዳንድ ጊዜ ወደ አምላክ የሚጸልየው “በንዴት ጥርሱን ነክሶ” እንደሆነ ተናግሯል።

ብዙ ሰዎች የተፈጥሮ አደጋ ሲደርስባቸው አምላክ እየቀጣቸው እንዳለ ሆኖ ይሰማቸዋል። አንድ ጸሐፊ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለውን አውሎ ነፋስ “የአምላክ በትር” በማለት ገልጾታል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ካትሪና ተብሎ እንደተሰየመው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ያሉት ክስተቶች “ኃጢአተኛ በሆኑ ከተሞች” ላይ የወረደው “የአምላክ ቁጣ” መግለጫዎች እንደሆኑ ተናግረዋል። በስሪላንካ የሚኖሩ አክራሪ የቡድሂዝም እምነት ተከታዮች ሱናሚ የመጣው በክርስቲያኖች ምክንያት እንደሆነ የተሰማቸው ሲሆን ይህም በመካከላቸው የነበረውን ሃይማኖታዊ መከፋፈል አባብሶታል። የሂንዱ ቤተ መቅደስ ኃላፊ የሆኑ አንድ ሰው ደግሞ ሰዎች ትክክለኛ ሥነ ምግባር ስለሌላቸው ሺቫ የተባለው አምላክ እንደተቆጣ ያምናሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አንድ የቡድሂዝም እምነት ሃይማኖታዊ መሪም የተፈጥሮ አደጋዎችን አስመልክተው ሲናገሩ “እነዚህ ነገሮች ለምን እንደሚደርሱ የምናውቀው ነገር የለም። በዚህ ምድር ላይ የምንኖረው ለምን እንደሆነ እንኳ አናውቅም” ብለዋል።

አንተስ የፈራረሱ ቤቶችን እንዲሁም በሐዘን ቅስማቸው የተሰበረና የሞቱ ሰዎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ስትመለከት ‘አምላክ ይህ ሁሉ መከራ እንዲኖር የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቃለህ? ወይስ ‘አምላክ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱ የፈቀደበት በቂ ምክንያት አለው፣ ሆኖም ምክንያቱን ለእኛ አልነገረንም’ ብለህ ታስባለህ? የሚቀጥሉት ርዕሶች ይህን ጉዳይ ያብራራሉ። በተጨማሪም የተፈጥሮ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ቢነገር ወይም አደጋ ቢከሰት ሰዎች በአደጋው የመጎዳት ወይም የመሞት አጋጣሚያቸውን ለመቀነስ ሊወስዷቸው የሚችሏቸውን አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች ይገልጻሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ሃይማኖታዊ መሪዎች አምላክ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲደርሱ የሚፈቅድበትን ምክንያት አያውቁም