በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሁለት የተለያዩ ባሕሎች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቻለሁ ምን ባደርግ ይሻለኛል?

በሁለት የተለያዩ ባሕሎች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቻለሁ ምን ባደርግ ይሻለኛል?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

በሁለት የተለያዩ ባሕሎች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቻለሁ ምን ባደርግ ይሻለኛል?

“ቤተሰቦቼ ጣሊያናውያን ስለሆኑ ፍቅራቸውንና ስሜታቸውን በነፃነት ይገልጻሉ። አሁን የምንኖረው ብሪታንያ ውስጥ ነው። እዚህ ደግሞ ሰዎች በጣም ቁጥብ ናቸው። ከሁለቱም ባሕሎች ሳልሆን እንደቀረሁ ሆኖ ይሰማኛል። ብሪታንያዊ እንዳልባል ጣሊያናዊነት ያጠቃኛል፤ ጣሊያናዊ እንዳልባል ደግሞ ብሪታንያዊነት ያጠቃኛል።”—ዦዝዌ፣ እንግሊዝ

“ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪዬ በሚናገርበት ወቅት እሱን እንዳየው ነግሮኛል። ይሁን እንጂ አባቴ ሲናገር ዓይን ዓይኑን ካየሁት ነውር እንደሆነ ይነግረኛል። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገብቶኛል።”—ፓትሪክ፣ በፈረንሳይ የሚኖር አልጄሪያዊ

አባትህ ወይም እናትህ ከሌላ አገር የመጡ ናቸው?

አዎ አይደለም

በትምህርት ቤት ውስጥ የሚነገረው ቋንቋና ያለው ባሕል በቤታችሁ ውስጥ ካለው የተለየ ነው?

አዎ አይደለም

በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደተለያዩ አገሮች የሚፈልሱ ሲሆን ብዙዎቹ ከባድ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። በሄዱበት አገር የሰዉ ቋንቋ፣ ባሕልና አለባበስ ከለመዱት የተለየ ይሆንባቸዋል። በዚህም ምክንያት እነዚህ ሰዎች ይፌዝባቸዋል። ከቤተሰቧ ጋር ከዮርዳኖስ ወደ ሰሜን አሜሪካ የሄደችው ኑር የተባለች አንዲት ወጣት ያጋጠማትም ይኸው ነበር። እንዲህ ብላለች:- “አለባበሳችን የተለየ በመሆኑ ሰዎች ያሾፉብን ነበር። አሜሪካውያን ምን እንደሚያስቃቸው በጭራሽ ሊገባን አልቻለም።”

ናድያ የተባለች አንዲት ወጣት ያጋጠማት ችግር ደግሞ ከዚህ የተለየ ነበር። ሁኔታውን እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “የተወለድኩት በጀርመን ነው። ወላጆቼ ጣሊያናውያን ስለሆኑ የምንናገረው ጀርመንኛ የተለየ ቅላፄ አለው። በመሆኑም የትምህርት ቤት ልጆች ‘የማትሻሻል መጤ’ ይሉኛል። ጣሊያን ስሄድ ደግሞ የምናገረው ጣሊያንኛ የጀርመንኛ ቅላፄ እንዳለው ተረዳሁ። በዚህም ምክንያት ከሁለቱም እንዳልሆንኩ ይሰማኛል። የትም ብሄድ የምታየው እንደ ባዕድ አገር ሰው ነው።”

እንዲህ ያሉ ልጆች የሚያጋጥሟቸው ሌሎች ችግሮች ምንድን ናቸው? በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እየኖሩ ስኬታማ መሆን የሚችሉትስ እንዴት ነው?

የባሕልና የቋንቋ ልዩነቶች የሚፈጥሩት ክፍተት

ከሌላ አገር የመጡ ወላጆች ያሏቸው ልጆች በቤት ውስጥም እንኳ የባሕል ልዩነት ያጋጥማቸዋል። እንዴት? አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ከወላጆቻቸው ይበልጥ ከአዲስ ባሕል ጋር ቶሎ ይላመዳሉ። ለምሳሌ፣ አና ከቤተሰቧ ጋር ወደ እንግሊዝ በሄደችበት ወቅት የስምንት ዓመት ልጅ ነበረች። አና እንዲህ ብላለች:- “እኔና ወንድሜ ለመልመድ ያን ያህል አልከበደንም። ማዲራ በተባለችው አነስተኛ የፖርቹጋል ደሴት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ለኖሩት ወላጆቻችን ግን ሁኔታው ከባድ ነበር።” የካምቦዲያ ዜግነት ያላቸው ወላጆቿ ወደ አውስትራሊያ ሲመጡ የሦስት ዓመት ልጅ የነበረችው ቮየን “ወላጆቼ አዲሱን ባሕልና አካባቢ በደንብ መልመድ አልቻሉም። እንዲያውም አባቴ ስሜቱንና አመለካከቱን ስለማልረዳለት ብዙውን ጊዜ ይናደድብኝ ነበር” በማለት ተናግራለች።

ይህ ዓይነቱ የባሕል ልዩነት ወላጆችን ከልጆች በሚለያይ ገደል ሊመሰል ይችላል። ቋንቋቸው መለያየቱ ደግሞ በገደሉ ዙሪያ እንደተገነባ አጥር በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ይበልጥ ሊያሰፋው ይችላል። ልዩነቱ መፈጠር የሚጀምረው ልጆች ከወላጆቻቸው ቀድመው አዲሱን ቋንቋ ሲለምዱ ነው። ልጆች የወላጆቻቸውን ቋንቋ እየረሱ መጥተው ከወላጆቻቸው ጋር ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት ሲቸግራቸው ልዩነቱ በጣም ይሰፋል።

አሁን 14 ዓመት የሞላው ኢየን ቤተሰቦቹ ከኢኳዶር ወደ ኒው ዮርክ ከመጡ በኋላ በመካከላቸው እንዲህ ያለ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር። ኢየን እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አሁን ከስፓንኛ ይልቅ እንግሊዝኛ መናገር ይቀናኛል። የትምህርት ቤት አስተማሪዎቼና ጓደኞቼ የሚናገሩት እንግሊዝኛ ነው። እኔና ወንድሜም የምንግባባው በእንግሊዝኛ ነው። አእምሮዬ በእንግሊዝኛ ቃላት ስለተሞላ ስፓንኛ እየጠፋኝ ነው።”

የአንተስ ሁኔታ ከኢየን ጋር ይመሳሰላል? ቤተሰቦችህ ከአገራቸው የወጡት ልጅ ሳለህ ከነበረ የአፍ መፍቻ ቋንቋህ ወደፊት በምን መንገድ ሊጠቅምህ እንደሚችል አልተገነዘብክ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ቋንቋው እንዳይጠፋብህ ምንም ዓይነት ጥረት አላደረግህ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኑር እንዲህ ብላለች:- “አባቴ ቤት ውስጥ በአረብኛ እንድንናገር ይገፋፋን ነበር። እኛ ግን በዚህ ቋንቋ ማውራት አንፈልግም ነበር። አረብኛ መማሩን እንደ ተጨማሪ ሸክም ቆጥረነው ነበር። ጓደኞቻችን የሚያወሩት በእንግሊዝኛ ነው። የምናያቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በሙሉ የሚተላለፉት በእንግሊዝኛ ነው። ታዲያ አረብኛ ማወቁ ምን ያደርግልናል?”

እያደግህ ስትሄድ ግን የአፍ መፍቻ ቋንቋህን አቀላጥፈህ መናገርህ ያለውን ጥቅም መገንዘብ ትጀምራለህ። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በቀላሉ ትጠቀምባቸው የነበሩ ቃላት እንኳ ይጠፉብህ ይሆናል። በእንግሊዝ የሚኖሩ ቻይናውያን ወላጆች ያሉት የ13 ዓመቱ ማይክል “ሁለቱ ቋንቋዎች ተደባለቁብኝ” ብሏል። ከኮንጎ (ኪንሻሳ) ወደ ለንደን የመጣችው የ15 ዓመቷ ኦርኔል “ለእናቴ በሊንጋላ ቋንቋ አንድ ነገር ልነግራት እፈልግና ያቅተኛል። ምክንያቱም በአብዛኛው የምናገረው በእንግሊዝኛ ነው” ብላለች። ካምቦዲያውያን ወላጆች ያሏትና በአውስትራሊያ የተወለደችው ሊ የወላጆቿን ቋንቋ አቀላጥፋ መናገር ባለመቻሏ ትቆጫለች። እንዲህ ብላለች:- “ለወላጆቼ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ምን እንደሚሰማኝ ላስረዳቸው ስፈልግ ቋንቋቸውን በደንብ ስለማላውቅ እንደዚያ ማድረግ ይቸግረኛል።”

ልዩነቱን ማጥበብ አስፈላጊ የሆነባቸው ምክንያቶች

የመጀመሪያ ቋንቋህ በተወሰነ መጠንም ከጠፋብህ ተስፋ አትቁረጥ። የቋንቋ ችሎታህን እንደገና ማሻሻል ትችላለህ። በመጀመሪያ ግን እንዲህ ማድረግህ የሚያስገኘውን ጥቅም መገንዘብ ይኖርብሃል። ጥቅሞቹ ምንድን ናቸው? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዦዝዌ እንዲህ ብሏል:- “የወላጆቼን ቋንቋ የተማርኩት ከእነሱ ጋር በስሜት ይበልጥ እንድንግባባ፣ ከምንም በላይ ደግሞ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አብረን እንድንካፈል ስለፈለግሁ ነው። ቋንቋቸውን መማሬ ስሜታቸውን እንድረዳላቸው አስችሎኛል፤ እነሱም ቢሆኑ ስሜቴን እንዲረዱልኝ አስችሏቸዋል።”

በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች ቋንቋቸውን ለሚናገሩ ሌሎች ስደተኞች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ሲሉ የወላጆቻቸውን ቋንቋ አቀላጥፈው ለመናገር ጥረት እያደረጉ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) የአምስት ዓመት ልጅ እያለ ወደ ለንደን የመጣው ሳሎማኡ እንዲህ ብሏል:- “ቅዱሳን መጻሕፍትን በሁለት ቋንቋዎች ማስረዳት መቻል በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው። የመጀመሪያ ቋንቋዬን ረስቼው ነበር ማለት ይቻላል፤ አሁን ግን ያለሁት በፖርቹጋል ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ስለሆነ እንግሊዝኛንም ሆነ ፖርቹጋልኛን አቀላጥፌ መናገር እችላለሁ።” በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ የሚኖረው የ15 ዓመቱ ኦሌግ “ሌሎችን መርዳት መቻሌ ያስደስተኛል። ፈረንሳይኛ እንዲሁም የሩሲያና የሞልዶቫ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማስረዳት እችላለሁ” ብሏል። ኑር አረብኛ የሚችሉ ወንጌላውያን እንደሚያስፈልጉ ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች:- “አሁን የረሳሁትን ቋንቋ ለማስታወስ መማር ጀምሬአለሁ። አመለካከቴ ተለውጧል። አሁን ስህተቴ እንዲነገረኝ እፈልጋለሁ። መማርም እፈልጋለሁ።”

የወላጆችህን ቋንቋ እንደገና አቀላጥፈህ ለመናገር ምን ማድረግ ትችላለህ? አንዳንድ ቤተሰቦች፣ ቤት ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ብቻ የሚነጋገሩ ከሆነ ልጆች ሁለቱንም ቋንቋዎች በደንብ መናገር እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። * ወላጆችህ ቋንቋውን መጻፍ እንዲያስተምሩህ ልትጠይቃቸውም ትችላለህ። ጀርመን ውስጥ ያደገውና አፍ መፍቻ ቋንቋው ግሪክኛ የሆነው ስቴሊስ እንዲህ ብሏል:- “ወላጆቼ በየዕለቱ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ያወያዩኝ ነበር። ጥቅሱን ጮክ ብለው ሲያነቡልኝ እጽፈዋለሁ። አሁን ግሪክኛም ሆነ ጀርመንኛ ማንበብና መጻፍ እችላለሁ።”

የሁለት ሕዝቦችን ባሕል የምታውቅና ምናልባትም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቋንቋዎችን መናገር የምትችል ከሆነ በጣም እንደምትጠቀም ምንም ጥርጥር የለውም። የሁለት ሕዝቦችን ባሕል ማወቅህ የሰዎችን ስሜት ለመረዳትና አምላክን አስመልክተው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያለህን አጋጣሚ ያሳድግልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ተገቢ መልስ በመስጠት ደስታን ያገኛል፤ በወቅቱም የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!” ይላል። (ምሳሌ 15:23) ከሕንዳዊ ወላጆች እንግሊዝ ውስጥ የተወለደችው ፕሪቲ “የሁለቱን አገሮች ባሕል በደንብ ስለማውቅ አገልግሎት ላይ ብዙ አልቸገርም። የሁለቱም አገር ሰዎች ምን እንደሚያምኑና ምን አመለካከት እንዳላቸው መረዳት እችላለሁ” ብላለች።

‘አምላክ አያዳላም’

ወላጆችህ ያደጉበት ባሕል በምትኖርበት አካባቢ ካለው ባሕል የተለየ በመሆኑ ምክንያት ግራ ከተጋባህ ተስፋ አትቁረጥ። የአንተ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በርካታ ሰዎች ጋር ይመሳሰላል። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሴፍ ተወልዶ ያደገው በዕብራውያን ባሕል ውስጥ ነው። ይሁንና ገና በልጅነቱ ወደ ግብፅ ተወስዶ ቀሪ የሕይወት ዘመኑን በዚያ አሳለፈ። ሆኖም ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደምንችለው የአፍ መፍቻ ቋንቋውን አልረሳም። (ዘፍጥረት 45:1-4) በዚህም ምክንያት ቤተሰቡን መርዳት ችሏል።—ዘፍጥረት 39:1፤ 45:5

ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ብዙ የተጓዘው ጢሞቴዎስ አባቱ ግሪካዊ ሲሆን እናቱ ደግሞ አይሁዳዊት ናት። (የሐዋርያት ሥራ 16:1-3) ወላጆቹ የተለያየ ባሕል ያላቸው መሆኑ እንቅፋት አልሆነበትም፤ ከዚህ ይልቅ በሚስዮናዊነት ሲያገለግል ስለ ሁለቱ ባሕሎች የነበረውን እውቀት ሌሎችን ለመርዳት እንደተጠቀመበት ግልጽ ነው።—ፊልጵስዩስ 2:19-22

አንተስ ያለህበትን ሁኔታ እንደ እንቅፋት ሳይሆን እንደ በረከት አድርገህ ትመለከተዋለህ? ‘አምላክ ለማንም እንደማያዳላ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ እንደሚቀበላቸው’ አስታውስ። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ይሖዋ የሚወድህ ማንነትህን እንጂ ዜግነትህን አይቶ አይደለም። አንተስ በዚህ ርዕስ ላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች እውቀትህንና ተሞክሮህን ያንተው ዓይነት ዘር ላላቸው ሰዎች ስለማያዳላውና አፍቃሪ ስለሆነው አምላክ ስለ ይሖዋ ለማስተማር ትጠቀምበታለህ? እንዲህ ማድረግህ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልሃል!—የሐዋርያት ሥራ 20:35

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት በጥቅምት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ልጆችን በውጭ አገር ማሳደግ የሚያስከትለው ችግርና የሚያስገኘው በረከት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ከባሕል ወይም ከቋንቋ ልዩነት ጋር በተያያዘ ምን ችግር አጋጥሞሃል?

▪ ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን የተወጣኸው እንዴት ነው?

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወላጆችህን ቋንቋ መናገርህ የቤተሰቡን አንድነት ያጠናክራል