በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብሩህ አመለካከት መያዝ ጤንነትህ እንዲሻሻል ይረዳህ ይሆን?

ብሩህ አመለካከት መያዝ ጤንነትህ እንዲሻሻል ይረዳህ ይሆን?

ብሩህ አመለካከት መያዝ ጤንነትህ እንዲሻሻል ይረዳህ ይሆን?

“ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው።ከ3,000 ዓመታት በፊት እንዲህ ብሎ የጻፈው አንድ ጠቢብ እስራኤላዊ ንጉሥ ነበር። (ምሳሌ 17:22) በዛሬው ጊዜ ዶክተሮች እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት ትክክል እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ “ደስተኛ ልብ” በተፈጥሮ የሚገኝ አይደለም።

አብዛኞቻችን ተስፋ እንድንቆርጥና አሉታዊ አመለካከት እንዲያድርብን ከሚያደርገው የኑሮ ሁኔታ ከሚያስከትልብን ጫና ማምለጥ አንችልም። ይሁንና በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት ችግሮች እያሉም ቢሆን ብሩህ አመለካከት ለመያዝ ጥረት ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

ብሩህ አመለካከት የሚለው ሐረግ “ብሩህ ተስፋ፤ የተሻለ ውጤት ይገኛል ብሎ የመጠባበቅ ዝንባሌ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ብሩህ አመለካከት ያለው ሰው ችግር ሲያጋጥመው ምን ይሰማዋል? የደረሰበትን ችግር እንደ ዘላቂ ሽንፈት አድርጎ አይመለከተውም። እንዲህ ሲባል ግን እውነታውን ከመቀበል ወደኋላ ይላል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን ተቀብሎ ጉዳዩን ይመረምራል። ከዚያም ሁኔታውን ለመቀየር ወይም ለማሻሻል አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አፍራሽ አመለካከት ያለው ሰው መከራ ሲደርስበት ብዙውን ጊዜ ራሱን መኮነን ይቀናዋል። ያጋጠመው መጥፎ ሁኔታ ዘላቂ እንደሆነና በራሱ ስንፍና፣ ብቃት ማነስ አሊያም ማራኪ ባለመሆኑ ምክንያት እንደመጣበት አድርጎ ያስባል። በዚህም ምክንያት ተስፋ ቆርጦ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ ይተዋል።

ታዲያ ብሩህ አመለካከት መያዝ ከጤንነታችን ጋር ግንኙነት አለው? እንዴታ! ሳይንቲስቶች በሮቺስተር፣ ሚኒሶታ፣ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው በማዮ ክሊኒክ ውስጥ ከ800 በሚበልጡ ሕመምተኞች ላይ ለ30 ዓመታት ባደረጉት ጥናት ብሩህ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከሌሎች የተሻለ ጤንነት እንዳላቸውና ረጅም ዕድሜ እንደሚኖሩ አረጋግጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ ተመራማሪዎቹ ብሩህ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ውጥረትን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም እንደሚችሉና ለጭንቀት የመጋለጣቸው አጋጣሚም አነስተኛ እንደሆነ መገንዘብ ችለዋል።

ይሁን እንጂ፣ ችግሮች እየበዙ በመጡበት በዚህ ዓለም ውስጥ ብሩህ አመለካከት መያዝ ቀላል አይደለም። ብዙዎች አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ቢከብዳቸው ምንም አያስገርምም። ይሁንና ይህን ችግር ለመቋቋም ምን ማድረግ ይቻላል? ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ በቀረበው ሣጥን ውስጥ ሊረዱ የሚችሉ አንዳንድ ሐሳቦችን ማግኘት ትችላለህ።

ብሩህ አመለካከት መያዝ ችግሮችን በሙሉ የሚያስወግድ ባይሆንም ጥሩ ጤንነት እንዲኖረንና አርኪ ሕይወት እንድንመራ አስተዋጽኦ ያበረክታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 15:15 የ1954 ትርጉም

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ብሩህ አመለካከት ለመያዝ የሚረዱ አንዳንድ ነጥቦች *

▪ በአንድ ነገር እንደማትደሰት ወይም ለመሥራት ያቀድከው ሥራ እንደማይሳካልህ የሚሰማህ ከሆነ ይህን ሐሳብ ከአእምሮህ አውጣው። ከዚህ ይልቅ አዎንታዊ አመለካከት ያዝ።

▪ ከሥራህ ደስታ ለማግኘት ጣር። የምትሠራው ሥራ ምንም ይሁን ምን እርካታ ሊያስገኙልህ በሚችሉ ነገሮች ላይ አተኩር።

▪ ለሕይወት አዎንታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሥርት።

▪ ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት የምትችል ከሆነ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አትበል። ከአቅም በላይ ከሆነ ግን አምነህ ተቀበል።

▪ በየዕለቱ የሚያጋጥሙህን ሦስት ጥሩ ነገሮች ጻፍ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ማዮ ክሊኒክ ባዘጋጀው ጽሑፍ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።