በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጠያቂው አምላክ ነው?

ተጠያቂው አምላክ ነው?

ተጠያቂው አምላክ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:8) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ፍትሐዊና መሐሪ ነው። “እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።”—ዘዳግም 32:4

ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ ችሎታና ጣልቃ ገብቶ የማስቆም ኃይል አለው። ከዚህ ሐቅና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት የአምላክ ባሕርያት አንጻር ብዙ ሰዎች፣ አምላክ “የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲደርሱ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?” ብለው ቢጠይቁ እውነት አላቸው። * ይህን ጥያቄ ያቀረቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገነዘቡት አምላክ ራሱ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ውስጥ አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ቀጥሎ የቀረበውን ሐሳብ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

የአምላክን ፍቅር ናቁ

አምላክ፣ ለመጀመሪያ ወላጆቻችን ደስተኛና ከስጋት ነፃ ሆነው ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ሰጥቷቸው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ከዚህም በላይ እነሱና ዘሮቻቸው “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” በማለት የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሲያከብሩ አምላክ በቁጥር እየጨመረ የሚሄደውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ሁልጊዜ እንደሚንከባከበው እርግጠኞች መሆን ይችሉ ነበር።—ዘፍጥረት 1:28

የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን፣ ሆን ብለው የአምላክን ትእዛዝ በመጣስና ከእሱ ተነጥለው ራሳቸውን ለመምራት በመምረጥ በፈጣሪያቸው ላይ ጀርባቸውን አዞሩ። (ዘፍጥረት 1:28፤ 3:1-6) አብዛኞቹ ዘሮቻቸውም የእነሱን ፈለግ ተከትለዋል። (ዘፍጥረት 6:5, 6, 11, 12) በአጭሩ፣ የሰው ዘር በአጠቃላይ ከአምላክ ምንም ዓይነት መመሪያ ሳይሻ ራሱን በራሱ ለመምራትና መኖሪያው የሆነችውን ምድር ለማስተዳደር መርጧል። ይሖዋ የሰዎችን የመምረጥ ነፃነት የሚያከብር አፍቃሪ አምላክ በመሆኑ የሰው ልጆች የሚጎዳቸውን ጎዳና ቢከተሉም እንኳ አካሄዳቸውን አስተካክለው ለእሱ እንዲገዙ አያስገድዳቸውም። *

ያም ሆኖ ይሖዋ ሰብዓዊውን ቤተሰብ አልተወውም። እስከ ዛሬ ድረስ “ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።” (ማቴዎስ 5:45) በተጨማሪም አምላክ ስለ ምድርና ስለ ዑደቶቿ ለመማር የሚያስችል ችሎታ ለሰው ልጆች የሰጣቸው ሲሆን ይህ እውቀት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሰዎች የአየር መዛባትንና እንደ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ያሉ ሌሎች አደጋዎችን አስቀድመው እንዲተነብዩ አስችሏቸዋል።

ከዚህም በላይ ሰዎች የትኞቹ የምድር ክፍሎች ለመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ለመጥፎ የአየር ጠባይ የተጋለጡ እንደሆኑ አውቀዋል። በአንዳንድ አገሮች እንዲህ ያለው እውቀት፣ ሰዎችን በማስተማር እንዲሁም የተሻሉ የሕንፃ አሠራር ዘዴዎችንና የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጫ መንገዶችን በመጠቀም ሕይወትን ለመታደግ ረድቷል። ያም ሆኖ በየዓመቱ የሚደርሱት የተፈጥሮ አደጋዎች ያለማቋረጥ እየጨመሩ መጥተዋል። ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሱት ነገሮች ብዙና የተወሳሰቡ ናቸው።

ለአደጋ በተጋለጡ አካባቢዎች መኖር

አንድን አደጋ ከባድ ነው የሚያሰኘው አደጋውን ያስከተለው የተፈጥሮ ክስተት ኃይለኛ መሆኑ ብቻ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ለአደጋው ክብደት ምክንያት የሚሆነው አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ነው። የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከ160 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ካለው ሕዝብ መካከል ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆነው የሚኖረው በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ሰዎች ሊሞቱ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ በሆነባቸው አካባቢዎች ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሊቅ የሆኑት ክላውስ ጄኮብ “ብዙ ሰዎች ለአደጋ በተጋለጡ አካባቢዎች እንዲኖሩ ካደረግህ፣ ቀደም ሲል ተፈጥሯዊ ክስተት የነበረው ነገር የተፈጥሮ አደጋ እንዲሆን ታደርጋለህ” በማለት ተናግረዋል።

አደጋ የሚያባብሱት ሌሎች ነገሮች ደግሞ ከተሞች ያለ ዕቅድና በፍጥነት መስፋፋታቸው እንዲሁም የደን መጨፍጨፍና ፍሳሾችን ሊመጥ ይችል የነበረው ሰፊ መሬት በሲሚንቶ መሸፈኑ ናቸው። በተለይም የደን መጨፍጨፍና መሬቱ በስፋት በሲሚንቶ መሸፈኑ የጭቃ ናዳ እንዲሁም የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊያስከትል ይችላል።

ከዚህም ሌላ የሰው ልጆች የሚሠሯቸው ነገሮችም የመሬት መናወጥ ከፍተኛ አደጋ እንዲያስከትል ሊያደርግ ይችላል፤ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚሞቱትና ጉዳት የሚደርስባቸው በመሬት መናወጡ ሳይሆን በሕንፃዎች መደርመስ የተነሳ ነው። ስለ መሬት መንቀጥቀጥ የሚያጠኑ ሰዎች “የመሬት መናወጥ ሰዎችን አይገድልም፤ ሰዎችን የሚገድሉት ሕንፃዎች ናቸው” የሚሉት በዚህ ምክንያት ነው።

መንግሥታት ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት አለመቻላቸውም ለሟቾቹ ቁጥር መብዛት ምክንያት ሊሆን ይችላል። የአንዲት የደቡብ አሜሪካ አገር ዋና ከተማ ባለፉት 400 ዓመታት ውስጥ በመሬት መናወጥ ሦስት ጊዜ ተደምስሳለች። በ1967 ከደረሰው ከመጨረሻው የመሬት መናወጥ ወዲህ የሕዝቡ ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ 5 ሚሊዮን ደርሷል። “ይሁን እንጂ ሕዝቡ የአደጋ ሰለባ እንዳይሆን ለማድረግ ሲባል የሕንፃ አሠራርን በተመለከተ የወጡ ሕጎች የሉም፤ ቢኖሩም ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ጥረት አይደረግም” በማለት ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ይናገራል።

መጽሔቱ የሰጠው ሐሳብ በዩናይትድ ስቴትስ በሉዊዚያና ግዛት በምትገኘው ኒው ኦርሊየንስ ከተማ ላይ ይሠራል፤ ከተማዋ የተገነባችው ለጎርፍ አደጋ በተጋለጠ ዝቅተኛ ቦታ ላይ ነው። ግድቦችና ዝቅተኛ ቦታ ላይ የሚጠራቀመውን ውኃ መምጠጫ ፓምፖች ቢኖሩም በ2005 ካትሪና በተባለችው አውሎ ነፋስ ከተማዋ በመመታቷ ብዙዎች ሲፈሩት የነበረው አደጋ ደረሰ። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ ዘገባ ሰዎች “ለዓመታት ሲነገሩ የቆዩ ማስጠንቀቂያዎችን” ችላ ብለዋቸዋል አሊያም “ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አላደረጓቸውም” ብሏል።

የምድር ሙቀት መጨመርን አስመልክቶ ከሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ የሆነ የቸልተኝነት ዝንባሌ ይታያል። በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት የምድር ሙቀት መጨመሩ ከአየር መዛባት ጋር የተያያዙ አደጋዎችን እንደሚያባብስና የባሕር ወለል ከፍታ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ያምናሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ከግምት መግባት አለባቸው እንጂ ለእነዚህ ችግሮች ተጠያቂው አምላክ አይደለም። የሰው ልጆች በሚሠሯቸው ነገሮች የተነሳ የሚፈጠሩት እነዚህ ችግሮች ሰው ‘አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል’ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያስታውሱናል። (ኤርምያስ 10:23) በተፈጥሮ አደጋዎች የተነሳ ለሚደርሰው ጉዳት አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ ሰዎች፣ ተፈጥሮም ሆነ መንግሥታት ለሚሰጧቸው ማስጠንቀቂያዎች ያላቸው አመለካከት ነው።

የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ማወቅ

በመጀመሪያ ደረጃ የተፈጥሮ አደጋዎች ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ሊከሰቱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። መክብብ 9:11 NW “ጊዜና አጋጣሚ” በሁላችንም ላይ ያላሰብነውን ነገር ሊያመጣብን እንደሚችል ይናገራል። ይሁንና ብዙውን ጊዜ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን የሚጠቁም አንድ ዓይነት የተፈጥሮ ክስተት ወይም ባለ ሥልጣናት የሚሰጡት ማስጠንቀቂያ ይኖራል። በመሆኑም ሰዎች ምልክቶቹን ካወቁ ከአደጋ ለመዳን የተሻለ አጋጣሚ ሊኖራቸው ይችላል።

በ2004 ሲመሉዌ የተባለችው የኢንዶኔዢያ ደሴት በሱናሚ በተመታች ወቅት በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩት የደሴቷ ሕዝቦች መካከል የሞቱት ሰባት ነበሩ። አብዛኞቹ ሰዎች ውኃው ባልተለመደ ሁኔታ ወደ መሃል እንዲያፈገፍግ የሚያደርግ ማዕበል መታየቱ ሱናሚ እንደሚመጣ የሚጠቁም መሆኑን ያውቁ ስለነበር ይህን ሁኔታ ሲመለከቱ ከባሕሩ ዳርቻ ሸሹ። ሌሎች ሰዎችም ለማስጠንቀቂያዎች ትኩረት በመስጠታቸው ከኃይለኛ አውሎ ነፋሶችና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች ማምለጥ ችለዋል። በተለይ ደግሞ የምትኖረው ለአደጋ በተጋለጠ አካባቢ ከሆነ፣ አንዳንድ ጊዜ የተፈጥሮ ማስጠንቀቂያዎች ባለ ሥልጣናት ከሚሰጧቸው ማስጠንቀቂያዎች ስለሚቀድሙ ሁለቱንም ዓይነት ማስጠንቀቂያዎች ማወቅህ የጥበብ እርምጃ ነው።

የሚያሳዝነው ግን ስለ እሳተ ገሞራ የሚያጠኑ አንድ ሰው እንደተናገሩት “አደጋው በግልጽ የሚታይ ሆኖ ሳለ ሰዎች አደጋ መኖሩን ለመቀበል አሻፈረኝ የማለት ዝንባሌ” አላቸው። በተለይም ደግሞ የተሳሳቱ ማስጠንቀቂያዎች የተለመዱ ከሆኑ ወይም አደጋ ከደረሰ ረጅም ጊዜ አልፎ ከሆነ ሰዎች ስለ አደጋዎች የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ በቸልታ ይመለከቱታል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች አደጋ ተጋርጦባቸውም እንኳ ንብረቶቻቸውን ትተው መሄድ አይፈልጉም።

በብዙ አካባቢዎች ሰዎች በጣም ድሃ በመሆናቸው ከአደጋ ነፃ ወደሆነ ቦታ መዛወር አይችሉም። ለዚህም ቢሆን ግን ተጠያቂው ፈጣሪያችን ሳይሆን ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ መንግሥታት ብዙውን ጊዜ ለጦር መሣሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚያውሉ ቢሆንም ችግረኞችን ለመርዳት የሚያደርጉት ጥረት ግን በጣም ውስን ነው።

የሆነ ሆኖ ግን አብዛኞቹ ሰዎች ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን፣ መጠነኛ እርዳታ ማግኘት ይችላሉ። እንዴት? አምላክ፣ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በርካታ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሰጠን ሲሆን እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ሕይወታችንን ያተርፍልናል።

ሕይወት አድን የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች

አምላክን አትፈታተኑት። ዘዳግም 6:16 “አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት” ይላል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ ሕይወት ያላቸው አመለካከት በአጉል እምነት ላይ የተመሠረተ ስላልሆነ አምላክ ሁልጊዜ ከአካላዊ ጉዳት ይጠብቀናል ብለው አያስቡም። በመሆኑም አደጋ እያንዣበበ መሆኑን ሲያውቁ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ያደርጋሉ:- “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል።”—ምሳሌ 22:3

ከቁሳዊ ንብረቶች ይልቅ ለሕይወት ትልቅ ቦታ ስጡ። “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ” አይደለም። (ሉቃስ 12:15) ቁሳዊ ነገሮች ጥቅም እንዳላቸው ባይካድም ለሙታን ግን ምንም አይጠቅሙም። ስለዚህ ሕይወትን የሚወዱና አምላክን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች ንብረታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ሕይወታቸውን ሳያስፈልግ አደጋ ላይ አይጥሉም።—መዝሙር 115:17

በጃፓን የሚኖረው ታዳሺ በ2004 የመሬት መናወጥ ሲደርስ ባለ ሥልጣናቱ መመሪያ እስኪሰጡ ሳይጠብቅ በአፋጣኝ ቤቱን ለቆ ወጣ። ታዳሺ ከቤቱና ከንብረቶቹ የበለጠ ሕይወቱ ውድ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በዚሁ አካባቢ የሚኖረው አኪራ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የደረሰው ኪሣራ መጠን የሚለካው በወደመው ቁሳዊ ነገር ሳይሆን ከግለሰቡ አመለካከት አንጻር ነው። ይህ አደጋ ኑሮዬን ለማቅለል ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረልኝ ይሰማኛል።”

መንግሥት የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያዎች አዳምጡ። “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምት መገዛት ይገባዋል።” (ሮሜ 13:1) ባለ ሥልጣናት አካባቢያችንን ለቅቀን እንድንወጣ ወይም ከአደጋው ለመትረፍ የሚረዳ ሌላ እርምጃ እንድንወስድ ትእዛዝ በሚሰጡበት ጊዜ ማስጠንቀቂያውን ሰምቶ ተግባራዊ ማድረግ ጥበብ ነው። ታዳሺ፣ ነዋሪዎች አካባቢውን እንዲለቁ ባለ ሥልጣናት የሰጡትን ትእዛዝ በማክበር ከአደጋው ቀጣና ርቆ በመቆየቱ ከዚያ በኋላ በደረሱት አነስተኛ ነውጦች ከመጎዳት ወይም ከመሞት ድኗል።

ባለ ሥልጣናት አደጋ እያንዣበበ መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ካልሰጡ፣ ሰዎች ያገኟቸውን መረጃዎች በሙሉ ከግምት በማስገባት መቼ ወይም እንዴት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው በግላቸው መወሰን ይኖርባቸዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ከአደጋ ለመትረፍ የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያዎች ይሰጡ ይሆናል። በአካባቢያችሁ እንዲህ ዓይነት መረጃ ካለ መረጃውን በደንብ ታውቁታላችሁ? ከቤተሰባችሁ ጋርስ ተወያይታችሁበታል? (በገጽ 7 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) በብዙ የዓለም ክፍሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች፣ በአካባቢያቸው የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሰጠውን አመራር በመከተል አደጋ ቢያንዣብብ ወይም ቢከሰት ሊወስዷቸው የሚገቡ እርምጃዎችን አስቀድመው ያዘጋጁ ሲሆን እነዚህን መመሪያዎች መከተልም በጣም ጠቃሚ መሆኑ ታይቷል።

ክርስቲያናዊ ፍቅር አሳዩ። ኢየሱስ “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ . . . እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:34) እንደ ክርስቶስ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ሌሎችን የሚወዱ ሰዎች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት በሚደረገው ዝግጅትም ሆነ በአደጋው ጊዜ በሕይወት ለመትረፍ በሚደረገው ጥረት እርስ በርሳቸው ለመረዳዳት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች የጉባኤው አባሎች በሙሉ ከአደጋው መትረፋቸውን ወይም ከአደጋ ነፃ ወደሆነ ቦታ መዛወራቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ እነሱን ለማግኘት ተግተው ይሠራሉ። በተጨማሪም እያንዳንዱ የጉባኤ አባል እንደ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ ምግብ፣ ልብስና አስፈላጊ ሕክምና የመሳሰሉትን መሠረታዊ ነገሮች ማግኘቱን ያጣራሉ። ከአደጋው ቀጠና ውጪ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በአደጋው ምክንያት ቤታቸውን ለመልቀቅ የተገደዱ የእምነት አጋሮቻቸውን ተቀብለው በቤታቸው ያሳርፏቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በእርግጥም ‘በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስር’ ነው።—ቈላስይስ 3:14

ታዲያ አንዳንዶች እንደሚተነብዩት የተፈጥሮ አደጋዎች እየተባባሱ ይሄዱ ይሆን? ምናልባት እየተባባሱ ይሄዱ ይሆናል፤ ሆኖም ይህ የሚሆነው ለአጭር ጊዜ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሰው ልጅ ከአምላክ አመራር ተነጥሎ የኖረበት አሳዛኝ ዘመን በቅርቡ ሊያበቃ ስለሆነ ነው። ከዚያ በኋላ መላዋ ምድርና ነዋሪዎቿ ሁሉ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ፍቅራዊ አገዛዝ የሚተዳደሩ ሲሆን ይህ ደግሞ ቀጥለን እንደምንመለከተው ግሩም ውጤት ይኖረዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከፍተኛ የአየር መዛባት፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታና የመሳሰሉት ነገሮች በራሳቸው አደጋዎች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ አደጋዎች የሚባሉት በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ሲያስከትሉ ብቻ ነው።

^ አን.6 አምላክ ለተወሰነ ጊዜ መከራና ክፋት እንዲቀጥል ስለፈቀደበት ምክንያት ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት “‘ለምን?’—ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት” የሚል ርዕስ ባለው የኅዳር 2006 ንቁ! ላይ የወጡትን ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶችና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 11ን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለመሸሽ ተዘጋጅተሃል?

የኒው ዮርክ ሲቲ የአደጋ ጊዜ እርዳታ ቢሮ፣ ቤተሰቦች ቤታቸውን ለቅቀው መሄድ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይዘውት የሚሄዱት በጣም አስፈላጊ የአስቸኳይ ጊዜ ቁሳቁሶችን የያዘ፣ ጠንካራና ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ አመቺ የሆነ ሻንጣ አዘጋጅተው ቅርብ ቦታ እንዲያስቀምጡ ሐሳብ አቅርቧል። በሻንጣው ውስጥ የሚከተሉት ቁሳቁሶች ሊካተቱ ይችላሉ:- *

ውኃ በማያስገባ መጠቅለያ የተጠቀለሉ ጠቃሚ የሆኑ ሰነዶች ቅጂዎች

የመኪና እና የቤት ቁልፎች

በዱቤ ለመግዛት የሚያስችሉ ካርዶች (ክሬዲት ካርዶች) እንዲሁም ጥሬ ገንዘብ

የታሸገ ውኃና የማይበላሹ ምግቦች

የእጅ ባትሪ፣ AM/FM ሬዲዮ፣ ሞባይል ስልክ (ካለህ) እና ትርፍ ባትሪዎች

ቢያንስ ለአንድ ሳምንት የሚያገለግል መድኃኒት፣ አወሳሰዱን የሚገልጽ ዝርዝር፣ ሐኪም መድኃኒቱን ያዘዘበት ወረቀት እንዲሁም የሐኪሞች ስምና ስልክ ቁጥር። (መድኃኒቶቹን የአገልግሎት ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት መቀየር አትርሳ)

የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ መሣሪያዎች

ጠንካራና ምቹ የሆኑ ጫማዎችና የዝናብ ልብስ

የቤተሰብህን አባላት ማግኘት የምትችልበትን አድራሻና የምትገናኙበትን ቦታ የሚገልጽ መረጃና የአካባቢው ካርታ

ልጆችን ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ ነገሮች

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.35 ከላይ የቀረበው ዝርዝር የባለ ሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ባዘጋጀው መመሪያ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም አንዳንድ ጥቃቅን ለውጦች ተደርገውበታል። በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተው እያንዳንዱ ነገር ለአንተ ሁኔታ ወይም ላለህበት አካባቢ ተስማሚ ላይሆን ይችላል፤ አንዳንድ ቁሳቁሶችን መጨመር ያስፈልግህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ለየራሳቸው የሚያስፈልጋቸው የተለየ ነገር ይኖራል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

USGS, David A. Johnston, Cascades Volcano Observatory ▸