በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጫካ የሚለቀም ጣፋጭ ፍሬ

ከጫካ የሚለቀም ጣፋጭ ፍሬ

ከጫካ የሚለቀም ጣፋጭ ፍሬ

ፊንላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አውሮፓ ውስጥ በስካንዲኔቪያ አገሮች የሚገኙ በርካታ ቤተሰቦች ጫካ ሄደው የቤሪ ፍሬዎችን መልቀም ያስደስታቸዋል። ለምሳሌ ያህል በፊንላንድ፣ ጫካ ውስጥ መንሸራሸር የሚወዱ ሰዎች ጫካው የግል ይዞታ ቢሆንም እንኳ ሰዎቹ ምንም ጉዳት የማያደርሱና ወደ መኖሪያ ቤቶች የማይጠጉ እስከሆኑ ድረስ በነፃነት የመዘዋወር መብት ይሰጣቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ መብት በጽሑፍ የሰፈረ ሳይሆን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የስካንዲኔቪያ አገሮች ልማድ ነው። እንዲህ ያለው መብት ሰዎች አበባ፣ እንጉዳይና የተለያዩ የቤሪ ፍሬዎችን ከጫካ ውስጥ እንዲለቅሙ ያስችላቸዋል።

በፊንላንድ 50 ዓይነት በጫካ ውስጥ የሚበቅሉ የቤሪ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የሚበሉ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ በብዛት የሚገኙት ቢልቤሪ፣ ክላውድቤሪ እና ሊንጎንቤሪ ይባላሉ። *—ሣጥኖቹን ተመልከት።

የተለያዩ ቀለማትና ጣዕም ያላቸው ቤሪዎች እንደ አንድ የምግብ ዓይነት መቅረብ የሚችሉ ከመሆናቸውም በላይ ለጤናም ተስማሚ ናቸው። ሉኦኖንማሪያኦፓስ (የጫካ ቤሪዎች መመሪያ መጽሐፍ) የተባለው መጽሐፍ “በስካንዲኔቪያ አገሮች ቀኑ ረጅም በሆነባቸው [የበጋ ወራት] የሚበቅሉት ቤሪዎች ደማቅ ቀለምና ኃይለኛ ሽታ ያላቸው ሲሆን በማዕድንና በቫይታሚን ይዘታቸውም የበለጸጉ ናቸው” ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ቤሪዎች በደም ውስጥ ያለውን ስኳር ለመቆጣጠርና የኮሌስትሮል መጠንን ለመቀነስ የሚረዳ አሰር አላቸው። እንዲሁም የቤሪ ፍሬዎች ለጤና ጠቃሚ እንደሆኑ የሚታመንባቸውን ፍሌቨኖይድ የተባሉ ንጥረ ነገሮች ይዘዋል።

ጫካ ወርዶ የቤሪ ፍሬዎችን መልቀም አድካሚ የመሆኑን ያህል ጥቅም አለው? የቤሪ ፍሬዎችን መልቀም በጣም የሚወደው ዩካ “ገበያ ላይ ትንሽ ወደድ ስለሚል ከጫካ መልቀም ከወጪ ያድናል። ከጫካ የሚለቀመው ቤሪ ደግሞ ያልዋለ ያላደረ ነው” ብሏል። ባለቤቱ ኒና ደግሞ ሌላም ጥቅም እንዳለው ስትናገር “ቤሪ ለመልቀም ወደ ጫካ በምንሄድበት ጊዜ ከቤተሰባችን ጋር የምንዝናናበት አጋጣሚ እናገኛለን” ብላለች።

ኒና አክላም “ልጆች ይዛችሁ የምትሄዱ ከሆነ ለምግብነት የማይሆኑ ቤሪዎችን እንዳይበሉ እንዲሁም እንዳይጠፉ ልትከታተሏቸው ይገባል” በማለት ተናግራለች። አንዳንድ የቤሪ ዝርያዎች መርዛማ ስለሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

በስካንዲኔቪያ እንደሚኖሩት እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ ዩካ እና ኒና ጫካ ያስደስታቸዋል። ኒና “ደስ የሚል ጸጥታ የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ ጽዱና ንጹሕ አየር ያለበት ቦታ በመሆኑ ጫካ መሄድ እወዳለሁ። እዚያ ስሄድ መንፈሴ ይታደሳል። ልጆችም እዚያ ሲሄዱ ደስ ይላቸዋል” ብላለች። ዩካ እና ኒና በጫካ ውስጥ ያለው ጸጥታ ለማሰላሰል እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር ውይይት ለማድረግ አመቺ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

የቤሪ ፍሬዎች በጣም የሚጣፍጡትና ከፍተኛ የምግብ ይዘት የሚኖራቸው ገና እንደተለቀሙ ነው። እነዚህ ፍሬዎች ሳይበላሹ ብዙ ጊዜ መቆየት አይችሉም። ስለዚህ በክረምት ወራት ለመጠቀም ሳይበላሹ እንዲቆዩ ለማድረግ ዘዴ መጠቀም ያስፈልጋል። በድሮ ጊዜ ሰዎች ፍሬዎቹ ሳይበላሹ እንዲቆዩ ለማድረግ ምድር ቤት ውስጥ በሚገኙ ቀዝቃዛ ክፍሎች ውስጥ ያስቀምጧቸው ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ማቀዝቀዣ ይጠቀማሉ። በርካታ የቤሪ ዝርያዎች ማርመላታና ጭማቂ ለመሥራት ያገለግላሉ።

አንድ ስዊድናዊ ጸሐፊ ስቬንስካ ቤርቦከን (የስዊድን የቤሪ መጽሐፍ) በተባለ መጽሐፋቸው ላይ “በጣም ቀዝቃዛ በሆነው የክረምት ወቅት በበጋ ወራት ከተቀመጡት ዕቃዎች ውስጥ የቤሪ ፍሬዎች አውጥቶ መመገብ ምንኛ የሚያስደስት ነው! እንዲህ ያለው ሁኔታ የበጋውን ትዝታ የሚቀሰቅስ ከመሆኑም በላይ መጪው የበጋ ወራት እንዲናፈቅ ያደርጋል” በማለት ጽፈዋል። በእርግጥም በዚህ ሐሳብ የማይስማማ አይኖርም። የቤሪ ፍሬዎች በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላሉ። ቁርስ ላይ ከእርጎ፣ ከግራኖላ ወይም ከኦትሚል ጋር ሊበሉ ይችላሉ። ከጫካ የሚለቀሙት እነዚህ ቤሪዎች ከዋና ምግብ በኋላ የሚቀርቡ ጣፋጭ ምግቦችንና ብስኩቶችን ለመሥራትም ያገለግላሉ። እንዲሁም ተፈጭተው ከተለያዩ ምግቦች ጋር ሲቀርቡ ለገበታው ውበት ይጨምራሉ።

ብዙ ሰዎች የቤሪ ፍሬዎችን ከገበያ ይገዛሉ። ይሁን እንጂ ብሩሕ በሆነ ቀን ንጹሕ አየር እየተነፈስክ ፍጹም ሰላም በሰፈነበት ጫካ ውስጥ ደማቅ ቀለም ያላቸውን ጣፋጭ የቤሪ ፍሬዎች ስትለቅም በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ገበታህን የሚያዳምቁ የሚጣፍጡ ፍሬዎችን በነፃ ብታገኝ ደስ አይልህም! ይህ ሁኔታ መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሰናል።—መዝሙር 104:24

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ “ቤሪ” የሚለውን ቃል የተጠቀምነው እንደ እንጆሪ ያሉ ትንንሽ ፍሬዎችን ለማመልከት ነው። በዕጽዋት ጥናት መሠረት “ቤሪ” የሚለው ቃል በአብዛኛው የሚያመለክተው በውስጣቸው በርካታ የዘር ፍሬዎችን የያዙ ትናንሽ ለስላሳ ፍሬዎችን ነው። በዚህ ፍቺ መሠረት ሙዝና ቲማቲምም ቤሪዎች ናቸው።

[በገጽ 24 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ቢልቤሪ (ቫክሲኒየም ሚርቲለስ)

ተወዳጅና ጣፋጭ የሆነው ይህ የቤሪ ዝርያ ሆርትልቤሪ ተብሎም ይጠራል። ብዙውን ጊዜ ከቢልቤሪ ፍሬዎች ስጎ፣ ፑዲንግ፣ ማርመላታ ወይም ጭማቂ ይሠራል። እንደ ቢልቤሪ ፓይ ያሉ ኬኮችን ለመሥራትም ያገለግላሉ። በተለይ ከወተት ጋር ሲበሉ በጣም ይጣፍጣሉ። ሆኖም ቢልቤሪዎች አፍህንም ሆነ ከንፈርህን ሰማያዊ ስለሚያደርጉ በድብቅ ለመብላት አትሞክር። እነዚህ ፍሬዎች አሳባቂው ቤሪ ተብለውም ይጠራሉ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ክላውድቤሪ (ሩበስ ቻሜሞረስ)

ይህ የቤሪ ዝርያ ረግረጋማ ቦታ በጣም ይስማማዋል። ይህ ዝርያ በፊንላንድ ሰሜናዊ ክፍል በብዛት ይገኛል። በቫይታሚን ኤ እና ሲ የበለጸገው ክላውድቤሪ ብዙ ፈሳሽ ያለው ከመሆኑም በላይ ገንቢ ነው። ከብርቱካን ከሦስት እስከ አራት ጊዜ የሚበልጥ ቫይታሚን ሲ አለው። ክላውድቤሪ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በረግረጋማ ሥፍራ የሚገኝ ወርቅ ተብሎ ይጠራል። እነዚህ ጣፋጭ ፍሬዎች ከምግብ በኋላ የሚቀርቡ የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦችንም ሆነ ምርጥ የአልኮል መጠጦችን ለመሥራት ያገለግላሉ።

[ምንጭ]

Reijo Juurinen/Kuvaliiteri

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ሊንጎንቤሪ (ቫክሲኒየም ቪቲስ አይዲያ)

ይህ የቤሪ ዝርያ ከክራንቤሪ ጋር ተቀራራቢነት ያለው ሲሆን በፊንላንድና በስዊድን በብዛት ይገኛል። የሊንጎንቤሪ ፍሬዎች ተፈጭተው ከተለያዩ ምግቦች ጋር ሲቀርቡ እራት ላይ ለገበታው ውበት ይጨምሩለታል። ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ቤሪ ስጎ፣ ፑዲንግ፣ ጭማቂና የተለያዩ ብስኩቶችን ለመሥራት ያገለግላል። ሊንጎንቤሪ በተፈጥሮው ምግብ እንዳይበላሽ የሚያደርግ አሲድ ስላለው ቶሎ አይበላሽም። እንዲያውም በውስጡ ከፍተኛ የአሲድ መጠን ስላለው መጀመሪያ ላይ ጣዕሙ ብዙም አይወደድም።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሁልጊዜ አስደሳች ነው ማለት አይደለም!

ብዙውን ጊዜ ወደ ጫካ ሄዶ ቤሪ መልቀም አስደሳችና አርኪ ነው። * ይህ ሲባል ግን ምንም ዓይነት ችግር አያጋጥምም ማለት አይደለም። በላፕላንድ የሚኖሩት ፓሲ እና ቱዊሬ የሚባሉ ባልና ሚስት ጫካ ሄደው ለራሳቸውም ሆነ ለሽያጭ የሚሆን ቤሪ ይለቅማሉ። አንዳንድ ጊዜ የወባ ትንኝና ዝንብ የመሳሰሉ ተናካሽ ነፍሳት ይወሯቸዋል። ቱዊሬ “ሁኔታው የሚያበሳጭ ነው፤ ሌላው ቀርቶ አፍና ዓይን ውስጥ ይገባሉ” በማለት ዝግንን እያላት ተናግራለች። የሚያስደስተው ግን ለሥራው አመቺ የሆነ ልብስ በመልበስና የተባይ ማባረሪያ መድኃኒቶችን በመጠቀም መከላከል ትችላለህ።

ሰው ዝር ብሎበት በማያውቅ ጫካ ውስጥ መጓዝ በተለይ አካባቢው ረግረጋማ ከሆነ በጣም አስቸጋሪ ነው። ደረቅ መስሎህ የምትረግጠው መሬት ማጥ ሊሆን ይችላል። ፓሲ እና ቱዊሬ እንደሚናገሩት ለቀማውም ቢሆን አድካሚ ሊሆን ይችላል። ለረጅም ሰዓት አጎንብሶና ቁጢጥ ብሎ መልቀም እግርና ወገብ ሊያሳምም ይችላል።

ቤሪ ፈልጎ ማግኘትም ቢሆን ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ፓሲ “በርካታ የቤሪ ፍሬዎች ያሉበትን ቦታ ማግኘት ብዙ ጥረት ይጠይቃል” በማለት ተናግሯል። ቱዊሬ “ብዙ ጊዜ ከመልቀሙ ይልቅ የሚያታክተው ፍለጋው ነው” ብላለች። ከለቀማው በኋላ ማጠቡም ቢሆን ትልቅ ሥራ ነው።

የቤሪ ፍሬዎችን መልቀም እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ችግሮች ስላሉት አንዳንዶች በጫካ ውስጥ ለሚኖሩ እንስሳት መተው ይሻላል ይላሉ። ይሁን እንጂ ቤሪ መልቀም የሚያስደስታቸው እንደ ፓሲ እና ቱዊሬ ያሉ ሰዎች በየዓመቱ ወደ ጫካና ረግረጋማ ወደሆኑ ሥፍራዎች ይሄዳሉ። ለእነሱ ቤሪዎችን በመልቀም የሚያገኙት ደስታ ከሚከፍሉት መሥዋዕትነት ጋር ሲወዳደር በእጅጉ የላቀ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.27 ሁሉም ዓይነት ቤሪዎች ለምግብነት የሚያገለግሉ አይደሉም። አንዳንዶቹ ዝርያዎች መርዛማ ናቸው። ስለዚህ ጫካ ሄደህ ቤሪዎችን ከመልቀምህ በፊት የሚበሉትን ለይተህ ማወቅ ይኖርብሃል።