ወደ ቫኑዋቱ መጥተው ዘና ይበሉ!
ወደ ቫኑዋቱ መጥተው ዘና ይበሉ!
ኒው ካሊዶንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ውጥረት ስላለብዎ ትንሽ ዘና ማለት ያስፈልጎታል? ከሆነ ሞቃታማ በሆነች አንዲት ደሴት ላይ ሲዝናኑ ይታይዎት። ሰማያዊ መልክ ባለው ውኃ ውስጥ ሲዋኙ፣ በሚያምር ጫካ ውስጥ ሲንሸራሸሩ ወይም ለየት ያለ ባሕልና አኗኗር ካላቸው የአገሬው ሰዎች ጋር ሲጨዋወቱ በዓይነ ሕሊናዎ ይታይዎት። እንዲህ ያለ ገነት አሁንም በምድር ላይ ይገኛል? እንዴታ! ራቅ ብለው የሚገኙት የቫኑዋቱ ደሴቶች ገነት ናቸው ማለት ይቻላል!
በአውስትራሊያና በፊጂ መካከል የምትገኘው ቫኑዋቱ የባላ ቅርጽ ያላት ሲሆን በፓስፊክ ውቅያኖስ በስተ ደቡብ ምዕራብ የሚገኙ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ 80 የሚያህሉ ትናንሽ ደሴቶችን ያቀፈች ናት። ጂኦሎጂስቶች እንደሚናገሩት በዚህ አካባቢ በላይኛው የምድር ንጣፍ ላይ የሚገኙት ግዙፍ ስፍሃን ቴክቶኒኮች (tectonic plates) በተጋጩበት ወቅት ትላልቅ ተራሮች ተፈጠሩ። የእነዚህ ተራሮች አብዛኛው ክፍል በውኃ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከውቅያኖሱ በላይ ብቅ ያለው የትላልቆቹ ተራሮች አናት ለቫኑዋቱ ደሴቶች መፈጠር ምክንያት ሆኗል። የላይኛው የምድር ንጣፍ በመገለባበጡ ምክንያት በዚህ አካባቢ በየጊዜው አነስተኛ መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች የሚከሰቱ ከመሆኑም በላይ ዘጠኝ ንቅ እሳት ገሞራዎች ተፈጥረዋል። ደፋር የሆኑ ጎብኚዎች የእሳተ ገሞራውን ቅልጥ ድንጋይ በቅርብ ርቀት መመልከት ይችላሉ።
በእነዚህ ደሴቶች ላይ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ይገኛሉ። በእነዚህ ደኖች ውስጥ ቅጠላቸው የተንዠረገጉ ግዙፍ የባንያን ዛፎች በብዛት ይታያሉ። ከ150 በላይ የሚሆኑ የኦርኪድ ዝርያዎችና 250 የሚያህሉ የተለያዩ የዕፅዋት ዓይነቶች ምድሩን አስጊጠውታል። ውብ የሆኑ የባሕር ዳርቻዎች ባሉትና በሾሉ ቋጥኞች በተከበበው ውቅያኖስ ውስጥ የተለያየ ቀለም ያላቸው ዓሣዎችና ኮራሎች በብዛት ይታያሉ። ቱሪስቶች ዱጎንግ ከተባለው ሰላማዊ የዓሣ ዝርያ ጋር ለመዋኘት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ኤፒ ደሴት ይመጣሉ። *
የሰው ሥጋ የሚበሉ ሰዎችና ሃይማኖታቸው
አውሮፓውያን አሳሾች ቫኑዋቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡት በ1606 ነበር። * በደሴቲቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች አስፈሪዎች ከመሆናቸውም ሌላ በአካባቢው የሰው ሥጋ መብላት በሰፊው የተለመደ ነበር። በወቅቱ በእስያ ከፍተኛ ተፈላጊነት የነበራቸውና ግሩም መዓዛ ያላቸው የሰንደል ዛፎች በብዛት ይገኙ ነበር። አውሮፓውያን ነጋዴዎች ከዛፎቹ ሊያገኙ የሚችሉትን ትርፍ በማሰብ በከፍተኛ ጥንቃቄ ወደ ደሴቲቱ በመምጣት ዛፎቹን ቆርጠው ይወስዱ ነበር። ከዚያ ደግሞ “ብላክበርድስ” ብለው የሚጠሯቸውን ሰዎች ማደን ጀመሩ።
ይህ ተግባር የአገሬውን ተወላጆች በሳሞአ፣ በፊጂ እንዲሁም በአውስትራሊያ በሚገኙ የሸንኮራ አገዳና የጥጥ እርሻዎች ውስጥ እንዲሠሩ መመልመልን ያካትት ነበር። ሰዎቹ በእርሻ ውስጥ ለሦስት ዓመታት በነፃ ለመሥራት እንደፈረሙ ተደርጎ ይነገር ነበር። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ብዙዎቹ ወደዚያ የተወሰዱት ታፍነው ነው። በ1800ዎቹ ዓመታት መገባደጃ አካባቢ ንግዱ ተጧጡፎ በነበረበት ወቅት በተወሰኑት የቫኑዋቱ ደሴቶች ላይ ከሚኖሩት ወንዶች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት ከአገራቸው ውጪ ይሠሩ ነበር። ብዙዎቹ ዳግም ወደ አገራቸው አልተመለሱም። በአውስትራሊያ ብቻ 10,000 የሚያህሉ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ሞተዋል፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የሞቱት በበሽታ ነው።
በአውሮፓ ተከስተው የነበሩ በሽታዎችም የቫኑዋቱ ነዋሪዎችን በጣም አጥቅተዋል። የደሴቲቱ ነዋሪዎች ኩፍኝ፣ ኮሌራ፣ ፈንጣጣና ሌሎች በሽታዎችን መቋቋም አልቻሉም ነበር። አንድ መጽሐፍ “ሌላው ቀርቶ ጉንፋን እንኳ ሕዝቡን ሊጨርሰው ነበር” ብሏል።
የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን በ1839 ቫኑዋቱ በደረሱ ጊዜ የአገሬው ሰዎች እራት ጋበዟቸው። ይሁን እንጂ እራት ሆነው የቀረቡት ራሳቸው ሚስዮናውያኑ እንደነበሩ ይነገራል! ከዚያ በኋላ ወደዚያ የተላኩት ሚስዮናውያንም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት በደሴቲቱ ላይ እየተጠናከሩ መጡ። በዛሬው ጊዜ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የቫኑዋቱ ሕዝብ ክርስቲያን እንደሆነ ይናገራል። የሆነ ሆኖ ፖል ራፋኤል የተባሉ ደራሲ “አብዛኛው ሕዝብ አሁንም ቢሆን፣ ጠጠር በመጣል መስተፋቅር ይሠራሉ እንዲሁም አሳማ እንዲደለብ ያደርጋሉ ወይም ጠላትን ይገድላሉ ተብሎ ለሚታመንባቸው የመንደር ጠንቋዮች አክብሮት አለው” በማለት ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቫኑዋቱ ካርጎ ካልት የሚባለው እምነት ሥር ከሰደደባቸው አገሮች መካከል አንዷ ናት። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ግማሽ ሚሊዮን የሚያክሉ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ወደሚገኝ የጦር ግንባር የሄዱት ቫኑዋቱን አቋርጠው ነበር። የደሴቲቱ ነዋሪዎች ወታደሮቹ ይዘውት በመጡት ከፍተኛ መጠን ያለው “ጭነት” በጣም ተገርመው ነበር። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የአሜሪካ ወታደሮች በሚሊዮን ዶላር የሚገመት መሣሪያና ንብረት ባሕር ውስጥ በመጣል ጥቂት ነገሮችን ብቻ ይዘው ተመለሱ። ካርጎ ካልትስ የሚባሉ የሃይማኖት ቡድኖች ወደቦችንና የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ካዘጋጁ በኋላ በውሸት የጦር መሣሪያ አማካኝነት ልምምድ አደረጉ። ይህንን ያደረጉት ወታደሮቹን ተመልሰው እንዲመጡ ለማጓጓት ነበር። በዛሬውም ጊዜ ቢሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የታና ደሴት ነዋሪዎች ጆን ፍረም ለተባለ መንፈስ እንደሆነ ለሚታሰብ “አሜሪካዊ መሲሕ” ይጸልያሉ። እነዚህ ሰዎች ይህ ሰው አንድ ቀን ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ጭኖ ይመጣል ብለው ይጠብቃሉ።
የተለያዩ ባሕሎች ያሉባት ደሴት
ይህች ደሴት የበርካታ ቋንቋዎችና ባሕሎች ባለቤት ናት። አንድ መመሪያ መጽሐፍ ደሴቲቱ “ከሕዝቧ ብዛት አንጻር በዓለም ላይ ካለ ከየትኛውም አገር በበለጠ በርካታ ቋንቋዎች የሚነገሩባት አገር እንደሆነች ትናገራለች” ብሏል። በቫኑዋቱ ደሴቶች ላይ ቢያንስ ቢያንስ 105 ቋንቋዎችና በርካታ ቀበልኛዎች ይነገራሉ። የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ቢስላማ ሲሆን እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ደግሞ የሥራ ቋንቋዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ በደሴቶቹ ላይ የሚኖሩ ሰዎችን በሙሉ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም የእያንዳንዱ ሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በአምልኮ ሥርዓቶች የሚመራ መሆኑ ነው። ከጥንታዊው የመራባት አምልኮ ጋር በተያያዘ በፔንተኮስት ደሴት ላይ የሚከበረው በዓል ሰዎች እግራቸው ላይ ታስረው ከረጅም ቋጥኝ ላይ ቁልቁል የሚወረወሩበት ልማድ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። በዚህች ደሴት ላይ በየዓመቱ የስኳር ድንች ምርት በሚሰበሰብበት ጊዜ ወጣትና አዋቂ ወንዶች ከ20 እስከ 30 ሜትር ርዝመት ካለው የእንጨት ማማ ላይ ወደታች ይወረወራሉ። መሬት ላይ ተፈጥፍጠው እንዳይሞቱ የሚታደጋቸው እግራቸው ላይ የታሰረው ረጅም የወይን ሐረግ ነው። ከላይ ተወርውረው በጭንቅላታቸው መሬቱን ጨረፍ አድርገው ማለፋቸው የመሬቱን “ለምነት” ስለሚጨምረው በቀጣዩ ዓመት ጥሩ ምርት ይገኛል ብለው ያምናሉ።
የማሊኩላ ደሴት አንዳንድ መንደሮቿን ለጎብኚዎች ክፍት ያደረገችው በቅርቡ ነው። በዚህች ደሴት ላይ ቢግ ናምባስ እና ስሞል ናምባስ የሚባሉ ጎሳዎች ይገኛሉ። ሰው በሊታ የነበሩት እነዚህ አስፈሪ ጎሳዎች ለመጨረሻ ጊዜ ሰው የበሉት በ1974 ነው። በተመሳሳይ የአንድን ሕፃን ልጅ የራስ ቅል “ማራኪ” እና ትልቅ ለማድረግ በጨርቅ ጥብቅ አድርገው የመጠቅለል ልማዳቸውን ከተዉም ዓመታት አልፏቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን የናምባስ ጎሳ አባላት በጣም ተግባቢ ከመሆናቸውም በላይ ስለ ባሕላቸው ለሌሎች መናገር ያስደስታቸዋል።
በገነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች
አብዛኞቹ ጎብኚዎች ወደ ቫኑዋቱ የሚሄዱት የተወሰነ ጊዜ ዘና ብለው ለመመለስ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን ከ70 ዓመታት በፊት ወደ ደሴቲቱ የሄዱት ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ‘በምድር ዳርቻ’ ላይ በሚገኘው በዚህ አካባቢ ያደረጉት እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቷል። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) (“የካቫ ሱሰኛ የነበረ ሰው ክርስቲያን ሆነ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በ2006 በአገሪቱ የሚገኙት አምስት ጉባኤዎች ምድር ወደፊት ገነት እንደምትሆን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰዎች በመናገር ከ80,000 የሚበልጥ ሰዓት አሳልፈዋል። (ኢሳይያስ 65:17-25) ደስ የሚለው ነገር በመጪዋ ገነት ውስጥ የኑሮው ውጣ ውረድ ከሚያስከትለው ጫናና ውጥረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እፎይ እንላለን!—ራእይ 21:4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 ዱጎንግ በውኃ ውስጥ የሚኖር ሣር በል አጥቢ እንስሳ ሲሆን እስከ 3.4 ሜትር ርዝመትና 400 ኪሎ ግራም ክብደት ሊኖረው ይችላል።
^ አን.7 ቫኑዋቱ በ1980 ብሔራዊ ነፃነቷን ከማግኘቷ በፊት ኒው ኸብሪዲዝ ተብላ ትጠራ ነበር።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ደስተኛ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው ደሴቶች
በ2006 በፕላኔቷ ምድራችን ላይ ደስተኛ ሕዝቦች ያላቸውን አገሮች በተመለከተ በተደረገው ግምገማ ቫኑዋቱ የመጀመሪያውን ሥፍራ አግኝታለች። ግምገማውን ያካሄደው ብሪታንያ የሚገኘው ኒው ኢኮኖሚክስ ፋውንዴሽን የተባለ ተቋም ሲሆን ሕዝቦቻቸው ደስተኞችና ረጅም ዕድሜ የሚኖሩ መሆናቸውን እንዲሁም በተፈጥሮ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መሠረት በማድረግ ለ178 አገሮች ደረጃ ሰጥቷል። ቫኑዋቱ ዴይሊ ፖስት የተባለ አንድ ጋዜጣ “[ቫኑዋቱ] የመጀመሪያውን ደረጃ ያገኘችው ሕዝቦቿ ደስተኞችና ወደ 70 ዓመት የሚጠጋ ዕድሜ የሚኖሩ በመሆናቸው እንዲሁም በፕላኔቷ ምድር ላይ እምብዛም ጥፋት ባለማድረሳቸው ነው” ብሏል።
[ሥዕል]
ባሕላዊ ልብስ
[ምንጭ]
© Kirklandphotos.com
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የካቫ ሱሰኛ የነበረ ሰው ክርስቲያን ሆነ
በፔንተኮስት ደሴት ላይ የሚኖረው ዊሊ ገና ከወጣትነቱ አንስቶ ካቫ የተባለውን መጠጥ በብዛት ይጠጣ ነበር። ይህ ኃይለኛ መጠጥ የሚጠመቀው ከበርበሬ ተክል ቅጠል ነው። ሁልጊዜ ማታ ወደ ቤቱ የሚገባው ሰክሮ እየተንገዳገደ ነበር። በየጊዜው ከመበደሩ የተነሳ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቀ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ጊዜ ሚስቱን አይዳን ይቆጣትና ይደበድባት ነበር። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ የሥራ ባልደረባው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና አበረታታው። ዊሊም በሐሳቡ ተስማማ። አይዳ መጀመሪያ ላይ ማጥናቱን ተቃውማ ነበር። ሆኖም የባሏ ባሕርይ መሻሻሉን ስትመለከት ሐሳቧን ቀይራ እሷም ማጥናት ጀመረች። ሁለቱም ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ዊሊ የመጠጥ ሱሱን ማሸነፍ ቻለ። በ1999 ከባለቤቱ ጋር ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኒው ዚላንድ
አውስትራሊያ
ፓስፊክ ውቅያኖስ
ፊጂ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ከከፍታ ቦታ ላይ ቁልቁል የሚወረወሩት ምድር ለም እንድትሆን የሚያደርግ የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም ነው
[ምንጭ]
© Kirklandphotos.com
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Kirklandphotos.com
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Kirklandphotos.com
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Kirklandphotos.com